በሕጻናት፣ በማህበረሰብ፣ በሴቶች አቅም ግንባታ ላይ ላለፉት 20 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ይታወቃሉ። የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር በማስጀመርም ግንባር ቀደም ናቸው – የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬአለም ሽባባው። ‹‹ልጆች ባሉበት ሁሉ ምግብ ይኑር›› በሚል መርህ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የሕጻናት የምግብ ተሟጋች በመሆን ሲንቀሳቀሱም ነበር፤ ዛሬም አልቦዘኑም።
ከትምህርት ቤት ምገባ ጋር ተያይዞ በሚሰሩ ሥራዎች በተለየ መልኩ የሚታወቁት ወ/ሮ ፍሬአለም በዚህ ደረጃ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እንዲንቀሳቀሱ ያደረጋቸው እርሳቸው በመሠረቱት ባህር ዳር አካዳሚ ትምህርት ቤት ያጋጠማቸው አንድ አሣዛኝ ታሪክ እንደነበር ይናገራሉ። የትምህርት ቤት ምገባን እንዲጀመሩ ከዓመታት በፊት የገጠማቸው ይኼን ክስተት ‹‹ላስብበት›› በተሰኘው መጽሃፋቸው እንደሚከተለው ያስታውሱታል።
በትምህርት ቤታችን አንድ ልምድ አለን። ይህ ልምድ ጥሩ ሲሰሩ የነበሩ ተማሪዎች በውጤት መቀነስ ሲጀምሩ ምክንያቱን በመረዳት መፍትሄዎችን የመፈለግ፤ መፍትሄውን ለመስጠት ደግሞ ምክንያቱን ለማወቅ የሚሰሩ ሥራዎች አሉ። የመጀመሪያው ሥራ የቀነሱበትን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ ማድረግ፣ ሁለተኛውና ዋናው ደግሞ መፍትሄ መስጠት ነው። ይኼንኑ ለማድረግ መምህራን ክትትል ያደርጋሉ።
ሁልጊዜ እንደሚደረገው በትምህርት ቤቱ የሚገኙ ጥሩ ውጤት የነበራቸው እና ውጤታቸው የቀነሱ ተማሪዎች በመለየት ምክንያቱን የመፈለግ ተግባሩ ቀጥሏል። ይህ አጋጣሚ በተፈጠረበት ዓመት ላይ መምህራን እንደተለመደው ክትትል ሲያደርጉ አንድ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ውጤት መቀነስ ጋር ተያይዞ ያገኘነው ምክንያት እጅግ አስደንጋጭ እንደነበር መጽሃፉ ያትታል።
በትምህርታቸው ጥሩ ከሚባሉት ተማሪዎች መካከል እና ውጤታቸው ከቀነሱት መካከል ይህ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ነበር። ስለዚህ በክፍል ኃላፊው በኩል የተማሪውን ውጤት እያሽቆለቆለ የመምጣቱ መነሻ ለማወቅ ክትትል ይደረጋል። መምህርቷ በተለያዩ ዘዴዎች ምክንያቱን ለማወቅ ጥረቷን ቀጠለች፤ ተማሪው በትምህርት ቤት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በአንክሮ መመልከትን እንደ አንድ አማራጭ ነበር የተጠቀመችው።
ሁሉም ሕጻናት ምሣ ሊበሉ ቁጭ ሲሉ እርሱ ቀደም ብሎ ወደ መጫወቻ ሜዳው ይሄዳል። ታዲያ መምህሯ “ለምንድነው ምሣህን የማትበላው?” በሚል ስትጠይቀው “ሣታይኝ ቀርተሽ ይሆናል እንጂ በልቻለሁ” ይላታል።
ያን ዕለት ግን ምንም ሣትለው በነጋታው ተማሪዎች ዕቃቸውን አስቀምጠው ለሠልፍ ሥነ ሥርዓት ሲወጡ መምህሯ ወደ ክፍል ገብታ የእርሱን የምሣ ዕቃ ስትከፍት ምግብ የነካው ዕቃ አልበረም። ከዚያ በኋላ ነበር ለቢሮ ሪፖርት ያደረገችው። “ልጁ ባዶ ምሣ ዕቃ ነው ወደ ትምህርት ቤት ይዞ የሚመጣው፤ ልጁ ምግብ እያገኘ አይደለም፤ ስለሚደክመው ይሆናል በትምህርቱ የቀነሰው“ ስትል።
ይኼን ዜና ከሰማሁ በኋላ ለሦስት ቀን ያህል በብዙ ዝምታ ውስጥ መሆንን እንደመረጠች ያመላከተችው ወ/ሮ ፍሬአለም፤ የተሰበረ ሥሜታቸውን በመሰብሰብ ቀጣዩን እይታቸውን በትምህርት ቤቱ የልጅ ተመሳሳይ ታሪክ ባለቤት የሆኑ ተማሪዎች መኖር አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ ጥናቶች ወደማድረግ እንደተሸጋገሩ ይነግሩናል።
“በትምህርት ቤቱ ተመሳሳይ ችግር አለመኖሩን ማረጋገጥ ቻልን። ነገር ግን በአካባቢው ወደሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በመሄድ ሲጠይቁ፤ በተመሳሳይ ችግር ሰለባ የሆኑ በርካታ ሕጻናት ተማሪዎች በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንደሚማሩ ለማየትም ለመስማትም ቻልን። ይኼን ዓይነቱን ልብ የሚያደማ ክስተት ከሰማሁ በኋላ በራሴ አቅም ሃሳቤን የሚደግፍ መንግሥታዊም ይሁን የግል ድርጅቶችን በማስተባበር ለመፍትሄው መሥራት ጀምርኩ” ሲሉ አጋጣሚውን በመጽሃፋቸው ያትታሉ።
‹‹ልጆች ባሉበት ሁሉ ምግብ ይኑር›› የሚል መሪ ቃልን አንግበው የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር እንዲስፋፋ ለዓመታት ሲሰሩ ነበር። እንደ እርሳቸው ሁሉ በርካታ ግለሰቦች እና ድርጅቶች አሻራቸውን ሲያሣርፉ ነበር፤ እያሣረፉም ይገኛል።
በኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር በመንግሥት ደረጃ በ1987 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም የምግብ ፕሮግራም የተጀመረ ቢሆንም፤ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ እንዳልነበር ተደጋግሞ ይነሣል።
ወ/ሮ ፍሬአለም እና መሠል ለሀገር በራሣቸው አቅም እና ተነሣሽነት የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩን ተግባራዊ እያደረጉ የሚገኙት ግለሰቦች፤ ሀገር በቀል የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ተጠናክሮ እንዲሰራ ግፊት ሲያደርጉ ነበር።
በመንግሥት በኩል ከባለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር። መንግሥት ከትኩረት ባሻገር በጉዳዩ ላይ ተደጋግሞ ሲነሳ የነበረውን ሃገር አቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ፖሊሲ መዘጋጀት አለበት የሚለውን ጥያቄ በመመለስ ያለውን ቁርጠኝነቱን በተግባር ያሳየ መሆኑ ተነግሯል።
ሃገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ምገባ ፖሊሲና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ተጠናቆ በይፋ መጽደቁን ተከትሎ ወ/ሮ ፍሬአለም ሃገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ምገባ ፖሊሲና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ መፅደቁ የዓመታት ልፋታቸው ፍሬያማ እንደሆነ የተሠማቸው መሆኑን ነው ያስታወቁት።
የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ብዙ ባለድርሻ አካላት መሣተፍ አለባቸው፤ ምክንያቱም በአንድ አካል ብቻ የሚሰራ እንዳልሆነ የገለጹት ወ/ሮ ፍሬአለም ሥራው አቅምን የሚጠይቅ በመሆኑ በፖሊሲ ደረጃ መውጣቱ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩ ሁሉንም ባሣተፈና ኃላፊነት በተሞላ መልኩ ማከናወን የሚያስችል መሆኑን ነው ያመላከቱት። የፖሊሲ ሠነድ ዝግጅቱ በተራዘመ ጊዜም ቢሆን ሁሉንም ባለድርሻ ሴክተር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን በማሣተፍ ሐሳቡ ዳብሮ ፖሊሲ ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ መቻሉ ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው በትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ መርሃ-ግብር ፖሊሲና ስትራቴጂ ትግበራ የሁሉንም ድጋፍና የተቀናጀ ትብብር እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት። በመሆኑም ለፀደቀው የተማሪዎች ምገባ ፖሊሲና ስትራቴጂ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ያመላከቱት ሚኒስትሩ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር የተማሪዎችን ለረሃብ ተጋላጭነት በማስቀረት የተሟላ ጤናና ሥርዓተ ምግብ እንዲሁም የተሻለ የትምህርት አቀባበልና ውጤት እንዲኖራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
ዶክተር ጌታሁን እንዳሉት፤ መርሃ-ግብሩ የትምህርት ተሣትፎና ውጤታማነት ከማሻሻል ጎን ለጎንም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል። በትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሠነዱ ዋና ዓላማም ለሁሉም የቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው በየእለቱ በማዕድን የበለፀገ ምግብ ማቅረብ ነው።
ይህ ፖሊሲና ስትራቴጂ መፅደቁ ሁሉንም የቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች በማዕድን የበለፀገ ምግብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል። በዚህም የተማሪዎችን የትምህርት ተሣትፎና ውጤታማነት በማሻሻል ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ሲሉ ነው ያስረዱት።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013