የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ከቀናት በፊት የ6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጤት ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ መንግስት ለመመስረት የሚያበቃ ወንበር ማግኘቱን አሳውቋል። ቦርዱ ውጤቱን ይፋ ካደረገ በኋላ የአሸናፊው ብልጽግና ፓርቲ መሪ ዶ/ር አቢይ አህመድ ዘለግ ያለ የምስጋና እና የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለደጋፊዎቻቸው አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ዳግመኛ እድል ሰጠን እንጂ አላሸነፍንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ስለሚሰሯቸው እቅዶችም አብራርተዋል።በጠቅላይ ሚኒስትሩ እቅድ መሰረት በቀጣይ አምስት የስልጣን አመታት የሚከናወኑ አራት አበይት እቅዶች አሉ። እነሱም የመሰረተ ልማት ግንባታ፤ የተቋማት ግንባታ ፤ የጋራ ትርክት ፈጠራ እና የሞራል ልዕልናን ማስጠበቅ የሚሉ ናቸው።እነዚህ ስልጣን የያዘው ፓርቲ እቅዶች ናቸውና እነሱን በመተንተን የአንባቢን ጊዜ አናባክንም።ነገር ግን ብዙ ኢትዮጵያውያን ሀሳብ የሚሆንባቸው እና በፍጥነት ቢስተካከል ብለው የሚያስቧቸውን ነገሮች በመጥቀስ መንግስትን ማስታወስ አስፈላጊ ነውና እነሱን እናነሳለን።
እንግዲህ ነገሩ መጀመሪያ መቀመጫዬን ነውና የምንጀምረው መጀመሪያ መቀመጫችንም መቆሚያችንም ከሆነችው ከሀገራችን ህልውና እንጀምራለን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎችም ሹማምንት የሀገሪቱ የህልውና አደጋ የነበረው ህወሓት ከዚህ በኋላ ያ አደጋነቱ እንደተቀለበሰ ገልጸዋል። በእርግጥም አሁን ያለውን ሁኔታ ስናይ ህወሓት ግዝፈቱ ጠፍቶ ሟሙቷል። እንዲያም ቢሆን ግን አሁን ባለበትም ቅርጽ ቢሆን ችግር ለመፍጠር አያንስም። ስለዚህም የዚህ ሀይል ጉዳይ በፍጥነት መቋጨት አለበት።በጦር ሜዳ የተገኘው ድል በፖለቲካ መድረክም መደገም አለበት። ህወሓት እየተፈራገጠ በቆየ ቁጥር ብዙ ችግር መፈጠሩ አይቀርም።ስለዚህ ጁንታውን በታላቅ ፖለቲካዊ ቀዶ ጥገና ከተጣበቀበት የትግራይ ህዝብ ጀርባ ላይ ማላቀቅ ስልጣን የሚይዘው አዲሱ መንግስት አስቸኳይ የቤት ስራ መሆን አለበት።
ከትግራዩ ጉዳይ በማስከተል ፈጣን መፍትሄ የሚፈልገው ሌላኛው ጉዳይ የኑሮ ውድነት ጉዳይ ነው። የኑሮ ውድነቱ ቀን በቀን እየተባባሰ ነው።የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሚያወጣው ወርሀዊ የዋጋ ግሽበት መጠን የሚሳየው ነገርም ቢሆን የኑሮ ውድነቱ ሽቅብ እየጋለበ እንደሆነ ነው።ኢኮኖሚው አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ጤናው እየተመለሰ ይመስላል።ብዙ ተቋማት አትራፊ እየሆኑ ነው።ለማሳያነት የኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ታሪካዊ ትርፍ መጥቀስ ይቻላል።በማእድን እና በቡና የውጭ ንግድ የተገኘው ከፍተኛ ምንዛሬም ለኢኮኖሚው ማገገም ምልክት ሊሆን ይችላል።ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በጎ ምልክቶች ወደ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ህይወት መመንዘር አለበት። በተለይ በምግብ ላይ ያለው የዋጋ ንረት ፈጣን መፍትሄ ይፈልጋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በመግለጫቸው በፍጥነት የምግብ ፍላጎታችንን በማሟላት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከውጭ የምግብ ድጎማ መላቀቅ አለብን ብለዋል። ህዝቡ በፍጥነት የሚለው ላይ እንዲያሰምሩበት ይፈልጋል።የትግራዩ ዘመቻ በፍጥነት መጠናቀቅ ደግሞ ኢኮኖሚው ከተጨማሪ ጣጣ እንዲላቀቅ ያደርገዋልና ሁለተኛው የአንደኛው ተዛማጅ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።
በመቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል እንደገቡት ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በሀገር አመራር ላይ ማሳተፍ አለባቸው። በዘንድሮው ምርጫ ፓርቲቸው 96 በመቶ ገደማ ወንበሮችን ቢያገኝም እንኳ ድምጻቸውን ለተፎካካሪ ፓርቲ የሰጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም ቀላል አይደለም። በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫው እሳቸውም ሆነ ተቃዋሚዎች የፈለጉትን ያህል ጉራማይሌ ምክር ቤት እንዳላስገኘላቸው ባለፈው ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው የምስጋና መርሀ ግብር ላይ ተናግረዋል። ሆኖም አሁን አንዴ ምርጫው ተካሂዶ የተገኘው ውጤት ተገኝቷል። ከዚሀ በኋላ ሁነኛው መፍትሄ የሁሉም ዜጎች ድምጽ እየተደመጠ እንዲቀጥል ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተባብሮ መስራት ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሺ በሚቆጠሩት ምርጫ ጣቢያዎች በእያንዳንዳቸው አሸናፊ ባያደርጓቸውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ድምጾች ሰብስበዋል። እነዚህ ድምጾች ሲደመሩ ብልጽግናን ያልመረጡ ኢትዮጵያውያን በሚሊየን የሚቆጠሩ እንዲሆን ያደርጋቸዋል። ከ37 ሚሊየን መራጭ መሀከል 1 ሚሊየኑ እንኳን ብልጽግናን አልመረጠም ብንል የዚህ አንድ ሚሊየን ህዝብ ድምጽ መደመጥ አለበት። ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በገቡት መሰረት ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የሀገር ግንባታ ስራቸው አካል ሊያደርጉ ይገባል። በእስካሁኑ ሂደት በገዢው ፓርቲ እና በተፎካካሪዎች መሀከል የታየው ሀገርን የማስቀደም ሂደት አሁን ደግሞ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ማየት ኢትዮጵያውያን ለነገ የማይሉት ምኞታቸው ነው።
በመቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግስታቸው ባለፉት ሶስት አመታት የዴሞክራሲ ተቋማትን በመታገስ በነጻነት እንዲሰሩ በማድረግ ረገድ ያሳዩትን ቁርጠኝነት መቀጠል አለባቸው።ኢትዮጵያ በታሪኳ ነጻ የሚባለውን የምርጫ ቦርድ ያየችው ባለፉት ሶስት አመታት ነው።ያን ለማየት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትእግስት ወሳኝ ነበር።ይህ ትእግስታቸውም በመጨረሻ ፍሬ አፍርቶ ተአማኒ በሚባል ምርጫ ስልጣናቸውን ማስቀጠል ችለዋል።ነገር ግን አሁንም ይህ ትእግስት መቀጠል አለበት። በምርጫ ቦርድ ፤ በሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና በአንዳንድ ተቋማት ዘንድ የታየው ተስፋ ሰጪ ነጻነት እና ገለልተኝነት አሁንም ለቀጣይ አምስት አመታት ቢቀጥል አሁን በሶስት አመት ጨቅላነታቸው ብዙ የሰሩት ተቋማት በቀጣይ ምርጫ የስምንት አመት ጠንካራ ልጅ ሆነው ለኢትዮጵያ ይደርሱላታል። ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቢችሉ ቃል እንደገቡት ተጨማሪ ድጋፍ አርገው የተቋማትን እድገት ቢያፋጥኑ ካልሆነም ተቋማቱ አሁን የጀመሩትን እድገት እንዲቀጥሉ ባለፉት ሶስት አመታት ያሳዩትን መታገስ ቢያስቀጥሉ ለኢትዮጵውያን ውለታ ይሆናል።
በህዳሴ ግድብ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግስታቸው ባለፉት ሶስት አመታት ያሳዩት ቁርጠኝነት እንዲጠናከርም የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ነው። ህዳሴን መጨረስ ኢኮኖሚያውም ፖለቲካውም ፋይዳው ብዙ ነው።ስለዚህም የመንግስት ብርታት በጣም አስፈላጊ ነው።በህዳሴ ግድብ ላይ እንደታየው ሁሉ በሌሎችም ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ትጋትም የሚጠበቅ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከአመት አመት ወዴትም እልፍ በማይሉ ፕሮጀክቶች ዜና ተሰላችቷል። ልክ እንደ አንድነት ፓርክ እና መስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ቶሎ ተጀምረው ቶሎ የሚያልቁ ፕሮጀክቶችን ማየት ይፈልጋል። ኢትዮጵያውያን መንግስት ፕሮጀክት የሚያስመርቀው ምርጫ ሲደርስ ብቻ እንዳልሆነ ማየት ይፈልጋሉና በ2014ም ብዙ ፕሮጀክቶች አልቀው ወደ ስራ ሲገቡ ለማየት ጓጉቷል።አለቁ ተመረቁ የሚባሉ ተቋማትም ምርታቸውን በፍጥነት እንዲያደርሱ ይፈልጋል።
እነዚህ አስቸኳይ ስራዎች እንዳሉ ሆነው ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እቅዶች ውስጥ ጊዜ የሚወስዱትን የሀገራዊ ትርክት ፈጠራ እና በስነ ምግባር እና በሞራል ከፍ ያለ ትውልድ በመፍጠር እንሰራለን። በጥቅሉ የዘንድሮው ምርጫ በብዙ መልኩ ድል ቢሆንም እንኳ ዋናው ድል ግን የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ እቅድ ተዘጋጅቶ እና ተተግብሮ ህዝብ የፈለገውን እና ለሀገር የሚበጀውን ተጨባጭ ስራ መከወን ሲቻል ብቻ ነው።
/አቤል ገ/ኪዳን/
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013