በህገመንግሥቱ አንቀጽ 54 ንኡስ አንቀጽ 6 ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገዢነታቸው ለህገመንግሥቱ፣ ለህዝብና ለህሊናቸው መሆኑን ይገልፃል። ይሁንና አባላቱ ተገዥነታቸውን በተግባር እንዳላረጋገጡ በተለያየ ጊዜ ይገለጻል። ለዚህም ልዩ ልዩ ምክንያቶች መኖራቸውን የፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ።
በፌዴራሊዝም ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሀይለየሱስ ታዬ፤ ምክንያቱን በሦስት ከፍለው ያስቀምጡታል። ህዝብ ከምክር ቤቶች ጋር ያለው ቅርበት፣ የፓርላሜንታሪ ሥርዓቱና አባላቱ የተመረጡበት ሁኔታ ናቸው። በዚህም አባላቱና የወከላቸው ህዝብ በእጅጉ በመራራቃቸው የህዝቡን ፍላጎት አውቆ በመሥራት መፍትሄ ሊያመጡ አልቻሉም። ፓርላሜንታሪ ሥርዓቱ ላይ ደግሞ በፓርቲ ተወክለው በመግባታቸው በፓርቲው ዲስፕሊን ስለሚቀጡ ለህዝብ ወገንተኛ አይሆኑም። በዚህም ለህሊናቸው፤ ለህዝቡና ለህገመንግሥቱ እንዳይገዙ ሆነዋል ይላሉ።
የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፤ ተመራጮቹ የፓርቲ ሥራ እንዲሠሩ በመመረጣቸው የማያምኑበትን ጉዳይ አይቃወሙም። ይህ ደግሞ የመረጣቸውን ህዝብ ሳይሆን ፓርቲውን ብቻ እንዲያገለግሉ ያደርጋቸዋል። ፓርቲው በራሱ ከምክር ቤት አባልነት ማንሳት እንደማይችል ስለማያውቁ ፓርቲው ይወድቃል፣ ተአማኒነትን ያጣል በሚል ስጋት ለወከሉት ፓርቲ ብቻ እንደሚቆሙ ይናገራሉ።
ተቃራኒ ሃሳብ ያለው አባል እንኳን ቢኖር በብዙኃኑ ስለሚዋጥ ሀሳቡ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደማይችል የሚናገሩት አቶ ግርማ፤ ለአብነት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ህዝቡ ምንም አይነት ችግር እንዳይደርስበት ቢያስቀምጥም በማረሚያ ቤቶች የሚታዩ ችግሮችን ገልጸው እያሳዩዋቸው እንኳን ችግሩ እንዳልተፈጠረ አድርገው ሲቀበሉት ቆይተዋል። ይህ ደግሞ የመጣው የፓርቲ ደጋፊ በመሆናቸው ብቻ ነው። ባሉበት ለመቆየትም ሲሉ ህገመንግሥቱ የሰጣቸውን መብት በሚገባ ለመጠቀም እንደሚፈሩ ያስረዳሉ።
አባላቱ ያላቸው የአቅም ውስንነት ሌለው ተገዥ ላለመሆናቸው ምክንያት መሆኑን የሚያነሱት አቶ ግርማ፤ አቅም በተለያየ መልኩ ይገለጻል፤ ለአብነት በገንዘብ አቅም የሌላቸው ከሆኑ ከአባልነታቸው ሲነሱ ቤተሰብ ለማስተዳደር ይቸገራሉ። በዚህም የተባሉትን ብቻ ለመቀበል ይገደዳሉ። በተመሳሳይ በሙያ አቅማቸው የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምዳቸው ያነሰ ከሆነ ያሉበትን ቦታ ሊተካ የሚችል ነገር አያገኙምና የተሳሳቱ ውሳኔዎችን አሜን ብለው ይቀበላሉ፤ ተገዥነታቸውን አሳልፈው እንደሚሰጡ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ግርማ ገለጻ፤ አንድ ግለሰብ በህዝብ ተወካይነት ሲመረጥ ህዝቡ ምን እንደሚፈልግ አውቆ ችግሮቹን ነቅሶ በማውጣት ለፓርላማው አቅርቦ መፍትሄ ማፈላለግ ላይ እንዲሠራ ነው። ይሁንና አሁን ባለው ሁኔታ ይህ ሲደረግ አይታይም። ለዚህም አዲስ አበባ ላይ ቆሼ አካባቢ የደረሰው አደጋ ትልቅ ማሳያ ነው። አደጋው ትልቅና አሰቃቂ ሆኖ ሳለ የአካባቢው ተመራጮች ግን መፍትሄ ሲሰጡ አልታየም። ይህ ደግሞ ተወካዩና ህዝቡ የተራራቁ እንደሆኑ ያመላክታል።
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አቶ ጋሻው አይፈራውም እንደሚናገሩት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ልዩ ግዴታቸው ተገዢ ለሆኑበት አካል መቆምና መታገል ነው። ይሁንና ይህንን እያደረጉ ነው ማለት ያስቸግራል። ህገመንግስቱ እንዲከበር፤ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ የእነርሱ ድርሻ ሆኖ ሳለ በሦስቱ አካላት ማለትም በህግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው መካከል የሥልጣን ክፍፍል ባለመኖሩ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ ይታያል። ይህ ደግሞ በነጻነት ለመሥራት እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው መረዳት ይቻላል።
በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በአንድ ፓርቲ የምትተዳደር በመሆኗ ፓርላማው የአንድ ፓርቲ አባላትን ብቻ ይዟል። ይህ ደግሞ በግለሰቦች ውሳኔ ህግ ሊጣስ፣ የህዝብ ጥቅም ሊጓደል፤ ህሊናም ዋጋ ሊያጣ የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጥራል። ምክንያቱም አስፈጻሚውም፣ ተርጓሚውም ህግ አውጪውም የፓርቲው አካላት ናቸው። በዚህም የፓርቲውን አቋም ብቻ ያንጸባርቃል እንጂ ማንም ማንንም መቆጣጠር አይችልም።
በህገመንግሥቱ አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 7«በሥራ አፈጻጸም ረገድ የሚታዩ መሰረታዊ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችና የሀገር ደህንነት የሚነኩ ጉዳዮች ሲከሰቱ ምክርቤቱ ያጣራል፤ አስፈላጊ ርምጃዎች እንዲወሰዱ ያደርጋል» ቢባልም የጎሉ ጉዳዮችን አውጥቶ ከማሳየት አኳያ ችግር አለ የሚሉት አቶ ጋሻው፤ በንዑሰ አንቀጽ 16 ላይም እንዲሁ «በክልሎች ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ መፍታት ሳይችል ሲቀር ያለ ክልሉ ፈቃድ በራሱ አነሳሽነት ተገቢ ርምጃ እንዲወሰድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ያቀርባል፤ በተወሰነው ውሳኔ መሰረትም ለክልል ምክር ቤቱ መመሪያ ይሰጣል» የሚለውን እያስፈጸሙ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ጋሻው ማብራሪያ፤ በአንቀጽ54 ንኡስ አንቀጽ 7 «ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል የመረጠው ህዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ በህጉ መሰረት ከምክር ቤት አባልነቱ ይወገዳል» ይላል። ነገር ግን ይህ ሲከወን አልታየም፤ የህዝብ ተወካዮቹ ሲመረጡ ምን ያህል አካባቢውንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ያውቃሉ የሚለው ስለማይታይና ህዝቡ ግንዛቤው ያለመዳበር በመሆኑ አባላቱ በማን ያነሳኛል ባይነት፣ ያለተጠያቂነት እንዲሰሩ እድል ሰጥቷል። ከአገር ጥቅም ይልቅ የራስን ፍላጎትና ጥቅም ማስቀደም ላይ እንዲሠሩ ፈቅዷል።
የመረጣቸውን ህዝብ በቅርብ የሚያወያዩበትና በየጊዜው ክትትል የሚያደርጉበትን መድረክ ማመቻቸት፤ እንዲሁም«እኛ ለኢትዮጵያ ህዝብ የምንሰጠው እውቀት አለን፣ ህዝቡን በሚገባ እናገለግላን» የሚል ሥርዓት ማበጀት ላይ ከተሠራ መፍትሄው ቀላል እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ግርማ፤ ነጻ ምርጫን ማከናወንና ውድድሩን ነጻ ማድረግ፤ ነጻ ሲባልም የሚያስከፈል ዋጋ መኖሩን አምኖ የሚቀበል፤ ብቃት ያለው አባል ማፍራት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። የተጀመረው በግልፅ የመቃወምና የአገልጋይነትና የተገዥነት ስሜትም መጠናከር ይኖርበታል ይላሉ።
ፓርቲዎች ጠንካራ አባላቱን ወደ ፓርላማ ማስገባት ላይ እስካልሠሩ ድረስ አሁንም ቢሆን ህገመንግሥቱንም ሆነ ህሊናውን የሚያገለግል የፓረላማ አባል በምክርቤት ሊፈጠር እንደማይችል የሚናገሩት ዶክተር ሀይለየሱስ ናቸው። ለዚህም ማሳያው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜ የነበረው ተቃውሞ መሆኑንና ይህ አይነት ክርክር ሁሌም መጎልበት እንዳለበት ያነሳሉ።ፓርቲዎች የውጪ ዴሞክራሲ ላይ ብቻ ሳይሆን ውስጠ ዴሞክራሲም ላይ መስራት እንዳለባቸው ያስረዳሉ።
አቶ ጋሻው በበኩላቸው፤ የቁጥጥር ስርዓቱ ላይ መጀመሪያ መሥራት አለበት። ምክንያቱም ህግ አውጭው፣ ተርጓሚውና አስፈጻሚው በአንድ አካል የሚመራ ከሆነ ችግሩ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። ስለሆነም የአገር ጥቅምን የሚያስቀድሙ አባላትን በፓርላማው ውስጥ ማብዛት፣ የሦስቱ አካላትን የሥራ ድርሻ ነጣጥሎ በትክክል የሚመራቸውን አካል ማስቀመጥ ያስፈልጋል።
በ1997 ዓ.ም ምርጫ ተቃዋሚና የግል ተወዳዳሪዎች ከ547 የፓርላማ መቀመጫ ውስጥ አንድ ሦስተኛ ወይም 31 በመቶውን ማግኘት ችለው ነበር። ከዚያም በ2002 ዓ.ም ደግሞ አንድ ብቻ ተቃዋሚ ነበር የፓርላማ ወንበር ያገኘው። በ2007ዓ.ም ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የኢህአዴግ ተወካዮች ቦታውን ያዙ። ይህም የሃሳብ ልዩነትን በመገደቡ ፓርላማውን ፍዝ አደረገው። ለህዝብ፣ ለህሊና እና ለህገመንግሥቱ ከመቆም ይልቅ የአንድ ፓርቲን አላማ ማመፈጸም እንዲበረታታ አድርጓል።
በፓርላን መቀመጫ የአንድ ፓርቲ አባላት ብቻ ከተቆጣጠሩት የአሀገራዊና የህዝቦች ፍላጎት ቀርቶ የፓርቲና የግለሰቦች ፍላጎት ይበራከታል። ፓርቲዎችም ወደ ፈላጭ ቆራጭነት እንዲያመሩ ያደርጋል። ሰብዓዊ መብት ይጣሳል፣ የህግ የበላይነት አይኖርም፣ በተወካዮቹ ላይ አመኔታ የሚጥል ማህበረሰብም ይጠፋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው