የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ለጃፓናዊያን ታሪካዊ ቢሆንም አለመካሄዱ ምርጫቸው እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች አሣይተዋል። ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ከትናንት በስቲያ የቶኪዮን የለሊት ግርማ ገፎ በብርሃን ተንቆጥቁጦ በይፋ ተከፍቷል፤ ብዙ ቢሊየን ዶላሮች የፈሰሱበት ስቴድየም ካለ ተመልካች ራቁቱን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱን አስተናግዷል።
የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ከሌሎች ኦሊምፒኮች አንጻር በኮቪድ ምክንያት ይደብዝዝ እንጂ፤ በህብረ ቀለማት ያሸበረቀ፣ በርችትና የተለያዩ መብራቶች የተንቆጠቆጠ፣ በጥበባዊ እንቅስቃሴዎች የተዋበና የጃፓንን ሠማይ ያፈካ ነበር።እንደ ለንደን እና ሪዮ ኦሊምፒኮች ሕዝባዊ ፌስቲቫል ባይታይም በስታዲየሙ አናት የነበሩት 1 ሺህ 824 ድሮኖች የኦሊምፒኩን ውበት ሙሉ በሙሉ እንዳይደበዝዝ ታድገውታል።
68 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ባለው ግዙፍና ዘመናዊ ስታዲየም ውስጥ በእንግድነት የታደሙት 950 ሰዎች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ መካከል የፈረንሣዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እንዲሁም የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን ተገኝተዋል።
ዓለም በጉጉት በሚጠብቀውና ትኩረቱን ሁሉ አሰባስቦ በሚመለከተው የመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይም 200 የሚሆኑ አትሌቶች የየሃገራቸውን ባንዶራ እና መለያ ይዘው በሜዳው ላይ ታይተዋል። የኦሊምፒክ ችቦውን በመለኮስ ውድድሩ በይፋ መጀመሩን ያበሠረችውም ጃፓናዊቷ የቴኒስ ተጫዋች ናኦሚ ኦሣካ ነበረች። የአራት ጊዜ የቴኒስ ቻምፒዮና አሸናፊዋና የጃፓን ብሔራዊ ጀግና የሆነችው ኮከቧ ተጫዋች፤ በጃፓናዊያን ዘንድ ‹‹ውዷ ሐብታችን›› በሚል የክብር ሥም ትጠራለች።
በርካታ ውጣ ውረዶችን ያሣለፈው ኦሊምፒክ ሲከፈትም የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባህ፤ ‹‹ይህ የተሥፋ ነፀብራቅ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም ‹‹ይህ ሁላችንም ከምናስበው በላይ የሆነ ነገር ነው። በመጨረሻም ሁላችንም እዚህ በመገኘታችን እንኳን ደስ አለን።ውድድሩ ሁላችንም የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችን አድርገን፣ የቫይረሱ ተጠቂ የሆኑ ውጤቶችን እየሰማንና ደጋፊዎችም በሌሉበት በተለየ መልክ ይቀጥላል።ነገር ግን አሁንም ቢሆን የምድራችን ታላቁ ትርዒት፣ ፈጣኑ፣ ከፍተኛውና ጠንካራው ኦሊምፒክ ነው›› በማለት ተስፋ ሰጪ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ቢቢሲ አስነብቧል።
ከመነሻው አወዛጋቢና አከራካሪ በነበረው በዚህ ኦሊምፒክ በርካታ አነጋጋሪና አስደናቂ ጉዳዮችም ተስተውለዋል።የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ወርቅ በቻይና የተመዘገበ ሲሆን፤ በ10 ሜትር አልሞ መተኮስ (air rifle) ያንግ ኪያን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።እርሷን ተከትለው ውድድራቸውን ያጠናቀቁት ሩሲያዊቷ አናስታዚያ ጋላሺና እንዲሁም ስዊዘርላንዳዊቷ ኒና ክርስቲን ደግሞ ለሃገራቸው የብርና የነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ቀዳሚዎቹ አትሌቶች ሆነዋል።
ኢትዮጵያም ትናንት ማለዳ በወርልድ ቴኳንዶ በተካሄደ ውድድር በሜዳሊያ ሠንጠረዡ ትካተታለች በሚል ተሥፋ ቢደረግም አልተሣካም።ብቸኛው እና በኢትዮጵያ ታሪክ በዚህ ስፖርት በቀዳሚነት ተሣታፊ የሆነው ሰለሞን ቱፋ፤ በመጀመሪያው ውድድር ጃፓናዊ አቻውን ቢረታም በሁለተኛው ዙር ግን በቱኒዝያው ተቀናቃኙ ተሸናፊ ሆኗል።
በዘመናዊው የኦሊምፒክ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ኦሊምፒኩን ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ያደረገው ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ 19 መሆኑ ይታወቃል። ከወራት በኋላም ጃፓን በወረርሽኙ እየታመሠችና ዜጎቿም ኦሊምፒኩ እንዳይካሄድ በተለያየ መንገድ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ከትናንት በስቲያ በይፋ ተጀምሯል።ይሁን እንጂ የየሃገራቱ ልዑካን ወደ ጃፓን ሲገቡ እንዲሁም በዚያ በሚኖራቸው ቆይታበሚደረጉላቸው ምርመራዎች ቫይረሱ ያለባቸው አትሌቶች ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል።ታዋቂ አትሌቶችም ጭምር በቫይረሱ ምክንያት በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ በመደረጋቸው ሃገራቸውን መወከል ሳይችሉ ቀርተዋል። ሲኤንኤን ትናንት ጠዋት ብቻ 17 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውን በድረ ገጹ አስነብቧል። ይህም እንደ አጠቃላይ ያለውን የተጠቂዎች ቁጥር ወደ 127 እንዲጨምር አድርጎታል፡፡
ኦሊምፒክ ከየትኛውም ፖለቲካዊ ጉዳይ የፀዳ ቢሆንም ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ኦሊምፒኮች ላይ መሠል እንቅስቃሴዎች ሣይታዩ እንዳልቀሩ ይታወቃል። የጃፓኑ ኦሊምፒክም ገና ከጅምሩ መሠል ሁኔታ የተስተናገደበት ሲሆን፤ አልጄሪያዊው የጁዶ ተወዳዳሪ ውድድሩን አቋርጦ በመውጣት ፖለቲካዊ አቋሙን አንፀበርቋል።ፈቲ ኖሪን የተባለው ይህ አትሌት ከእሥራኤላዊ አቻው ጋር ከመፎካከር ይልቅ ውድድሩን ያቋረጠበት ምክንያት፤ እሥራኤል በፍልስጤም ላይ እያደረገች ባለችው ሁኔታ መሆኑን እንዲሁም ይህን ማድረጉ ግዴታው እንደሆነም አስታውቋል።
የኦሊምፒክ ድምቀት ከሆኑ ሃገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን ከመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ጀምሮ ብዙዎችን ያሣዘነና ያስከፋ ትዕይንት ገጥሟታል።በስታዲየሙ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ሂደቱ ሁለት ሰዎች መታየታቸው እንዲሁም ባልተሟላ ትጥቅ መታየታቸው ያልተጠበቀና በርካታ ኢትዮጵያውያንን ያስቆጣ ሲሆን፤ የሚመለከታቸው አካላትም በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ‹‹ኢትዮ ራነርስ ፋን›› ለተባለው ድረ ገጽ በሰጠችው አስተያየት ከሆነም፤ አስቀድሞ ባንዲራውን ለመያዝ እርሷ አሊያም አትሌት ብርሃኔ አደሬ ቢመረጡም በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በኩል ተወዳዳሪዎች ብቻ መያዝ እንዳለባቸው በመወሰኑ ሊሣካ አልቻለም።
ስድስት የልዑካን ቡድኑ አባላት የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ለማንገብ ቢዘጋጁም በስታዲየሙ የታዩት ግን ሁለት ሰዎች ያውም በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ የማይታወቁ ብቻ ነበሩ። ለዚህም ቡድኑ ለመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ስቴድየም መገኘት ካለበት ሰዓት አርፍዶ መድረሱ በምክንያትነት ተነስቷል።ፕሬዚዳንቷ ግን ቡድኑ በተመደበለት ተሸከርካሪ አስቀድሞ የተገኘ ቢሆንም መግቢያው ላይ እንዳይገቡ በመደረጉና የይለፍ ወረቀቱም ዘግይቶ የደረሣቸው በመሆኑ ችግሩ እንደተፈጠረ አስረድታለች።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ ባንዲራውን አንጋፋዎቹ አትሌቶች እንዲይዙት ቢወሰንም በዓለም አቀፉ ኮሚቴ አቅጣጫ መሠረት በተወዳዳሪ አትሌት እንዲያዝ መደረጉን ተናግረዋል። የወርልድ ቴኳንዶ አትሌቱ ሰለሞን ቱፋ ውድድር ስለነበረበት እንዲሁም የብስክሌት ተወዳዳሪዋም ራቅ ባለ ሥፍራ የምትገኝ መሆኗንም አያይዘው ገልፀዋል።
ሃገሪቷ በምትተዋወቅበት መድረክ መገኘት የሚችሉት ስድስት ሰዎች ቢሆኑም፤ በተሸከርካሪ አጠቃቀም ስህተት ምክንያት አርፍደዋል ሲሉ ነው የገለጹት። በመጨረሻም ቡድኑ ሁለቱን ተወካዮች የተቀላቀለ ቢሆንም ካሜራው ግን ያላሣያቸው መሆኑን ለዚህም የፎቶ ማስረጃ መኖሩን ለድረ ገጹ ጠቁመዋል። በዋናነት ቡድኑ አንድ ላይ ስለመሆኑና ለሁኔታው መከሰት አንዱ መንስዔ በኮቪድ 19 ጥንቃቄ ምክንያት ቡድኑ በአንድ አካባቢ አለማረፉ ነው።
ጉዳዩን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በድረ ገጹ የስፖርት ቤተሠቡን ይቅርታ ጠይቋል። ‹‹ክስተቱ በቀጣይ በክፍተታችን ላይ መሥራት እንዳለብን አሣይቶናል፤ በተለይ በቡድን ስፖርቶች ሰርተን የምንሣተፍበትን የስፖርት ዓይነት ከፍ በማድረግ ስፖርተኞቻችንን ማብዛት የቤት ሥራችን ነው።›› ሲል አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ወደ ቶኪዮ ከተጓዘበት ቀን ጀምሮ ሀገር የማስተዋወቁን ሥራ እየሰራ ነው ያለው መግለጫው፣ አሁንም ዕቅዳችን ትኩረታችንን በሙሉ ወደ ውድድሩ በማድረግ ውጤት አስመዝግበን ሕዝባችንን ማስደሰት ነው ብሏል። የስፖርት ቤተሠቡም ከፊታችን ያለውን ውድድር ብቻ በማሰብ በድጋፍ ከጎናችን እንዲሆን እንጠይቃለን›› ሲልም መግለጫ አውጥቷል።
በዚህም ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ በተለይ ለአዲስ ዘመን ‹‹ይህ ነገር በአትሌቶች ውጤት ላይ ተጽዕኖ አይኖረውም ብዬ አላስብም፡፡›› ሲል ገልጿል። ‹‹ምንም ቢሆን የሞራል ጉዳይ ነው፤ ፌዴሬሽኑ አትሌቶቹን በተገቢው መንገድ አዘጋጅቶ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲፈጠር እንኳን አትሌቶች ሌላው ሕዝብ ላይም ተጽዕኖ አይፈጥርም ማለት አይቻልም።›› ሲል ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቁሟል፡፡
‹‹የአትሌቲክስ ቡድን መሪው ዶክተር በዛብህ ነበር፤ እሱም በመክፈቻው ስታዲየም መግባት አልቻለም። ደራርቱ እና ዶክተር በዛብህ ከቶኪዮ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ሆቴል እንዲያርፉ ተደርገዋል። ቡድን መሪ ውስጥ ገብቶ ነገሮችን ማመቻቸት ነበረበት፤ ችግሩ የተፈጠረው ከዚህ ጋር ተያይዞ ነው›› ሲል የሲድኒ ኦሊምፒክ የማራቶን ባለድሉ ገዛኸኝ ይናገራል።
የተፈጠረውን ችግር ለመሻርና ሕዝቡን ለመካስ የሚቻለውም አትሌቶች ባደረጉት ጠንካራ ዝግጅቶችና በግል ጥረታቸው በሚያስመዘግቡት ውጤት መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይጠቁማል።
ከዚህ በኋላ ወደ ቶኪዮ የሚጓዙ አትሌቶች ቢያንስ ሁለትና ሦስት ቀን ቀደም ብለው በመድረስ መዘጋጀት እንዳለባቸውም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስታውቋል።ይህ ካልሆነ ዝግጅት ቢደረግም አትሌቱ በተገቢው መንገድ የሚመራው ከሌለ ሌላ ችግር መፈጠሩ እንደማይቀርም ገዛኸኝ አስተያየቱን ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ልዑክ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት የገጠመው ችግር በርካቶችን እንደ ማስቆጣቱ በቀጣይ ውድድሮች ሕዝቡን የሚክስ ውጤት መመዝገብ እንደሚኖርበት ገዛኸኝ አበራን ጨምሮ በርካቶች አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013