የዛሬው የዘመን እንግዳችን በኢትዮጵያ የሴቶችና የሃይማኖት እኩልነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ከነበራቸው ሰዎች አንዱ ናቸው። የሰራተኛ መብት ያስከበረውን አዋጅ ቁጥር 64/68 ይባል የነበረውን ከሰሩ ታላላቅ ሰዎች መካከልም እርሳቸው አንዱ ናቸው። ከህብረት ባንክ መስራቾች መካከልም ይጠቀሳሉ። በፖለቲካው ጎራም በመሰለፍ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት- መኢአድን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል። ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ምስረታ ላይም ተሳትፈዋል።
የትውልድ መንደራቸው ኢሉባቦር ጎሬ ነው። ጎሬ በጣም ትንሽ ከተማ ብትሆንም እርሳቸውን ጨምሮ የደርግ መንግስት የትምህርት ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴንና ሌሎች በርካታ ግለሰቦችን ለቁም ነገር አብቅታለች። በአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች አብዛኞቹ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ስለነበሩ ሚሲዩኖች ልጆቻቸውን ዘመናዊ ትምህርት አስተምረው ለቁም ነገር እንዲበቁ በማገዝ ለበርካቶች በር መከፈት ምክንያት ሆነዋል።
ከእነዚህ መካከል ደግሞ ዶክተር በዛብህ ደምሴ ተጠቃሽ ናቸው። ከዚች ትንሽ መንደር እንደመገኘታቸው እንደዛሬው ዘመናዊ ትምህርት ባልተስፋፋበት ወቅት እርሳቸው ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል። ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉት በተወለዱበት መንደር ነው። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ግን አዲስ አበባ በሚገኘው ተግባረዕድ ነው የተከታተሉት። በመቀጠልም ወደ ሶቪየት ህብረት ተጉዘው ለሰባት ዓመታት ቆይተው በታሪክና በኢኮኖሚክስ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘው ተመልሰዋል። አገር ቤት እንደተመለሱም ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይባል በነበረው መስሪያ ቤት ተቀጥረው ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል።
በኢትዮጵያ የተቀጣጠለው አብዮት በ1966 ዓ.ም ለውጥ እንዲመጣ እና አዲስ መንግስት እንዲመሰረት ምክንያት ሆነ። በመንግስት ምስረታ ማግስት ማለትም በ1967 ዓ.ም አዲሱ መንግስት የመንግስት አማካሪ ያስፈልገው ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የነበረው ምክር ቤት ፈርሶ ስለነበር አዲስ አማካሪ ማቋቋም ስላስፈለገ ነበር። 50 አማካሪዎች ከየመስሪያ ቤቱ እና ከየክፍለ ሀገሩ ተመረጡ። ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞች ለመማክርት ሸንጎው እንዲወከሉ መርጠው ከላኳቸው ሰዎች አንዱ ዶክተር በዛብህ ነበሩ።
በእዚህ የአማካሪ ቡድን ውስጥ ታላላቅ ሰዎች ተካትተውበት ነበር። መማክርት ሸንጎው ውስጥ ከነበሩት ሰዎች መካከል ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አሜሪካን አገር በቅርብ ያረፉት ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ፣ ደራሲና ገጣሚ መንግስቱ ለማን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። የዛሬው እንግዳችንና አንድ ሌላ ሰው ብቻ ነበሩ ከተመራጮች መካከል በባለሙያ ደረጃ የገቡት። እንጂ ሌሎቹ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ፣ ሚኒስትሮችና የዳበረ ልምድ የነበራቸው ናቸው። ለሁለት አመታትም በመማክርት ሸንጎው ሰርተው ወደ ወከላቸው መስሪያ ቤት ተመልሰው ለአምስት አመታት ካገለገሉ በኋላ መስሪያ ቤቱ ዳግም የፒኤች ዲ የትምህርት ዕድል ስለሰጣቸው ወደ ሞስኮ ላካቸው።
የፒኤች ዲ ትምህርታቸውን ተከታትለው እንደተመለሱ የገቡት የውጭ ንግድ ሚኒስቴር ይባል በነበረው መስሪያ ቤት የያኔው ሚኒስትር ወሌ ቸኮል አማካሪ በመሆን ነው። በአማካሪነት ለአራት አመታት ገደማ ሰርተዋል። በገንዘብ ሚኒስቴር በአማካሪነት ተመድበውም ካገለገሉ በኋላ በጡረታ ተሸኝተዋል።
ሆኖም ጡረተኛ ሆነው አልገፉም። የግል ስራቸውን መስራት ቀጠሉ። እርሳቸው በጡረታ በተሰናበቱበት ሰሞን አንዳንድ የግል ባንኮች ማቆጥቆጥ የጀመሩበት ወቅት ነበር። ከእነዚህ ባንኮች መካከል ሕብረት ባንክ ተጠቃሽ ነው። ባንኩ ሲቋቋም ለባንኩ መስራቾችን ሲያሰባስብ እርሳቸውንና ባለቤታቸውን የምስረታው አካል እንዲሆኑ አግባቧቸው። ከአገር ውጪ በሚገኘው ልጃቸው ስም አክሲዮን በመግዛት ህብረት ባንክን ከመሰረቱት ሰዎች አንዱ ለመሆን በቁ። በመሰረቱት ህብረት ባንክ ለአራት አመታት፣ በአቢሲኒያ ባንክ ደግሞ ለሶስት አመታት ተኩል ሰርተዋል።
ተማሪ እያሉም በፖለቲካው ተሳትፎ ቢኖራቸውም፤ የ1983 ቱን ለውጥ ተከትሎ ነው ባግባቡ የፖለቲካውን ጎራ ለመቀላቀል የቻሉት። ኢትዮጵያን ዴሞክራቲክ አክሽን (ኢዳግ) ሲቋቋም መስራችና የስራ አስፈጻሚ አባል ሆነዋል። በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በርካታ ተግባራትን ባከናወነውና በርካታ የህዝብ ድጋፍ የነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሲቋቋም ከመስራቾች መካከልም ይጠቀሳሉ።
የዛሬው እንግዳችን ዶክተር በዛብህ ደምሴ ባለትዳርና የአምስት ወንድ ልጆች አባት ሲሆኑ፤ ዘንድሮ 75 ዓመት ዕድሜ ላይ ናቸው። ከእርሳቸው ጋር በነበረን ቆይታ ከውጭ ጣልቃ ገብነት ጋር በተያያዘ እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን:- እርሶ በአባልነት የተሳተፉበት የደርግ ሸንጎ በተለየ መልኩ አከናውኗል ብለው ሊጠቅሱልኝ የሚችሏቸው ተግባራት ይኖሩት ይሆን? ባለፉባቸው ሂደቶችም ሊታረሙ ይገባቸዋል የሚሏቸውን ቢነገሩኝ?
ዶክተር በዛብህ:- በሚገባ የሚጠቀሱ በርካታ ተግባራት አሉ። ሸንጎው የሴቶች እኩልነት፣ የሃይማኖትን እኩልነት፣ አዋጅ ቁጥር 64/68 ይባል የነበረው የሰራተኛ መብትና ሌሎች በርካታ ተግባራትን ካከናወናቸው መካከል መጥቀስ ይቻላል። አሁን ያለው አብዛኛው ተግባር መነሻው ሸንጎው የሰራቸው አዋጆች ናቸው።
ይህ የመማክርት ሸንጎው ከሰራው ትልቅ ስራ መካከል የመሬትን ስሪት በተመለከተ ጉዳዩን ባግባቡ ተመልክቶ ውሳኔ አሳልፏል። በእዛን ጊዜ በጥቂት ሰዎች እጅ ተይዞ የነበረውን መሬት በአዋጅ እንዲቀየር ከመከሩት ስድስት ሰዎች መካከል ነበርኩበት። ምክረ ሃሳቡን ለስድስት አዘጋጅተው ለጉባኤው ካቀረቡ በኋላ ጉባኤው ለመንግስት አቅርቦ ተግባራዊ እንዲደረግ አስችሏል።
የሃይማኖት እኩልነት ይህ ሸንጎ ካከናወነው ትልቁ ተግባር አንዱ ነው። ለምሳሌ ከ1966 ዓ.ም በፊት በእስልምና ሃይማኖት የሚያምኑ ሰዎች በዓላቸው አይከበርም ነበር። የኢድ አል-ፈጥር፣ ኢድ አል-አድሐ (አረፋ) እና መውሊድ በዓላት ተግባራዊ የሆነው በእዛ ሸንጎ በተሰራ ስራ ነው።
በአዋጁ ላይ መሬትን በተመለከተ መሬትን መሸጥ መለወጥ ይቻላል፤ የግል ነው የሚል ሃሳብ ነበረው። የነበረው መንግስት ደግሞ የበለጠ መድረስ ያስፈልጋል በሚል መሬትን የራሱ እንዲሆን አደረገው። በእኔ እምነት አሁንም ቢሆን መሬት ንብረት መሆን አለበት፣ መሸጥ መለወጥ የሚፈቀድ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። አሁን ምርጫ ተደርጓል አዲስ መማክርት ይሰየማሉ፣ ምክር ቤት ይቋቋማል፤ ምክር ቤቱ ይህንን የመሬትን ጉዳይ በተመለከተ፣ ሊመለከተው ይገባል።
ያለፈው መንግስት ያራምድ የነበረው በዘርና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ኢትዮጵያን አሁን ስቃይ እያሳያት ይገኛል። እነዚህ ይሻሻላሉ ብዬ እገምታለሁ። አዋጅ ወጥቷል፣ አዋጁ የተመሰረተው በኢህአዴግ አላማ ላይ ነው። አላማው ደግሞ ቋንቋንና ዘርን የተመለከተ ስለሆነ ለኢትዮጵያ ይህ አይጠቅማትም። አዲስ የሚመሰረተው ምክር ቤት ይህንን ቢያሻሽለው መልካም ነው።
አዲስ ዘመን:- የዘንድሮን ምርጫ እንዴት ይገመግሙታል?
ዶክተር በዛብህ:- ምርጫው ምንም እንኳ ጥቂት ክፍተቶች ቢኖርበትም አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ ችግሮችን ማባባስ አንፈልግም። ምክንያቱም ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የኢትዮጵያ መኖር ነው። መስራት ያለብን ኢትዮጵያ ቀጣይነት እንዲኖራት ማድረግ ነው። ምክንያቱም አገር ውስጥ ያሉ ጠላቶች፣ ውጭ አገር ያሉ ፈረንጆች ኢትዮጵያን ለመበታተን ይፈልጋሉ።
ዩጎዝላቪያ የምትባል አገር ነበረች። ዩጎዝላቪያ ማርሻል ቲቶ በሚባሉ መሪ ትመራ ነበር። እኚህ ሰው ከቀዳማዊ ሃይለስላሴ ጋር የቅርብ ወዳጅ ነበሩ። በቲቶ ጊዜ ይህች አገር ትልቅ አገር ነበረች። በኋላ ግን በሃይማኖትና በዘር ልክ እኛ አገር አሁን ለመፍጠር እንደተፈለገው ብትንትኗን አወጧት። ይህንን የሰራው ማን ነው ካልከኝ ኢምፔሪያሊስቶች ናቸው። እስላሞች ተገደሉ፣ ተገፉ በሚል ሰበብ ብዙ ነገር ፈጥረው በታተኗት። አሁን እንደ ክሮሺያ አይነት ትናንሽ አገር አደረጓት። እነዚህ አገራት ምነው አሁን ዩጎዝላቪያን መልሰን ጠንካራ በሆንን ብለው ሳያስቡና ሳይቆጩ አይቀርም።
የእኛን አገርም ስታይ በዘርና በፖለቲካ እየተጫወቱ ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚፈልጉ አሉ። ያንን ነው መታገል ያለብን። ይህንን ካለሸነፍን የትም አንደርስም። ኢትዮጵያ ብዙ ችግር አለባት። አሁን ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ስንመለከት ደግሞ ኢትዮጵያ ብለው የሚጮሁ መሪ ናቸው። የለውጥ ፍላጎት ያላቸው ይመስለኛል። የኢትዮጵያን አንድነት፣ ኢትዮጵዊነትን ማራመድ የሚፈልገውን ሰው በእኔ እምነት መደገፍ ያስፈልጋል።
በእድሜዬ አራት ስርዓት አይቻለሁ። የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴን፣ የደርግንና የኢህአዴግን አሁን ደግሞ ብልጽግና ሆኗል። እንደአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ የገባችበት ጊዜ አላየሁም። ስለዚህ ኢትዮጵያን ለማዳን መረባረብ ይኖርብናል። አገራችን ችግር ላይ ነች። ለምሳሌ ግብጽንና ሱዳንን እንውሰድ፤ በእዚህ ውሃ ምክንያት ከፍተኛ ተጽእኖ ለመፍጠር እየሞከሩ ይገኛሉ። እነርሱን ለመቋቋም ደግሞ አንድነት ያስፈልገናል። አባቶቻችን ያቆዩልንን ኢትዮጵያን ለማቆየት መታገል ይኖርብናል። አሁን የምናየው ችግር ከፍተኛ ቢሆንም መስዋዕት የተከፈለባትን አገር ማቆየት ይገባናል። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎች የአገርን ችግር በመረዳት አንድነታቸውን ሊያጠናክሩ፣ ለኢትዮጵያ ሊያስቡ ይገባል ይሄ ብቻ ነው የሚጠቅመው። ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግም ነገሮችን በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን:- በምርጫ ሂደት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለምን ውጤታማ አልሆኑም? አሁን መንግስት በምርጫው ተሳታፊ የነበሩ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በመንግስት መዋቅር ለማሳተፍ ጥሪ አቅርቧልና እንዴት ተመለከቱት ?
ዶክተር በዛብህ:- ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን የምንሸነፈው ዋናው ምክንያት አንድነት ስለሌለን ነው። አንድ ብንሆን ይሄንን መንግስት በዝረራ እናሸንፈው ነበር። ትግልን ለማጠናከር አንድነት ያስፈልገናል። ትንንሽ ልዩነቶች ነው ያሉን፣ ያንን በማጥበብ በጋራ መታገል ያስፈልገናል። ምክንያቱም መኢአድም ሆነ፣ ኢዜማ፣ ሌሎቹም ፓርቲዎች እየታገሉ ያሉት እኮ አልማዙም፣ ወርቁም፣ ብሩም፣ ወታደሩም፣ ምኑም እጁ ውስጥ ካለው መንግስት ጋር ነው። እነርሱ ግን 100 ሺህ ብር ባንክ ውስጥ የላቸውም። አንድ ቢሆኑ ግን ተጠናክረው ሊቋቋሙት ይችላሉ።
ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ይሄ ምርጫ ብዙ እክሎች ቢኖሩትም ቀዳሚ ማድረግ ያለብን የኢትዮጵያን የመኖር ህልውና ነው። እንጂ ስለፖርቲዎች መሆን የለበትም። በዛብህ ለምን ተሸነፈ፣ ለምን አልተመረጠም መባል የለበትም። አንተ ያነሳኸውና መንግስት አብሮ ለመስራት ያቀረበው ጥያቄ በጎ አመለካከት ነው።
ሆኖም ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ሆነን ብንወዳደር ኖሮ ጠንካራና የበለጠ ተአማኒ የመሆን ዕድል ይኖረን ነበር። ስለተበታተንን ነው እንደዚህ የሆንነው። ወደፊትም ምርጫ ይኖራል። አሁን ባለው መልኩ የሚቀጥል አይመስለኝም። አመለካከታቸው አንድ አይነት የሆኑ ፓርቲዎች ይቀላቀላሉ ብዬ አስባለሁ። አብዛኞቻችን ፓርቲዎች አመለካከታችን አንድ አይነት ነው፤ ልዩነት የለንም። አንድ ሆነን ነው መታገል ያለብን። አዲስ አበባን ብንወስድ አንድ የግል ተወዳዳሪ ብቻ ነው ያሸነፈው። እነዛ ሁሉ ፕሮፌሰሮች አልሆነላቸውም። ችግሩን ተመልክቶ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት መስራት ይኖርብናል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትንሽ የተሻለ ነገር እንዲሰራ ይፈልግ ይሆናል። ግን ብዙዎቻችን እንደምናውቀው በየቀበሌው ያሉ ካድሬዎች እንዳሉ ናቸው። ጥቅማቸውን ማጣት አይፈልጉም። የቀደመው ነገር አልጠራም። በቀዳሚነት የማጥራት ስራ ሊሰራ ይገባል፣ ያለው ችግር መሻሻል ይኖርበታል።
በ1983 ዓ.ም ፓርቲ ስናቋቁም ኢሰፓ አባላት አባል እንዳይሆኑ ተከልክሎ ነበር። ግን ኢሰፓ ሶሻሊዝምን የሚያራምድ ፓርቲ ነው። መከልከል አይገባውም ብለን ተሟገትን። ዋና የኢሰፓ አባል የነበሩትን እነ ዶ/ር ሃይሉ አርአያን አስገባን። አመለካከት ነው ማንም ያመነበትን ሊያምን ይችላል። በኋላ ምክትል ፕሬዚዳንት ነው የሆነው። ሰው በእውቀቱ ነው መገመት ያለበት። አሁንም የማጥራት ስራ መሰራት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን:- ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል? በተለይ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ህግ ማስከበር ጋር ተያይዞ የተከሰተው ቀውስ በምን ሁኔታ ይፈታል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር በዛብህ:- እኔ በጠብመንጃ አላምንም። ምክንያቱም እኔ አንተን ብገድል የአንተ ወገን ደግሞ እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ። ስለዚህ መገዳደሉ የትም አያደርስም። ስለዚህ የመግባባት ነገር መፍጠር አለብን። አሁን ላለው የኢትዮጵያ ችግር ዋናው መሰረት ወያኔ ነው። ትልቁ ችግር ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጭኖ የሄደው የዘር ልዩነት ነው። እኔ ጎሬ፣ አዲስ አበባም ሆነ ውጭ አገር ስማር ኢትዮጵያዊነትን ነው የማውቀው እንጂ፤ አማራ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ ብዬ አስቤ አላውቅም። የአሸባሪው ህወሓት መንግስት ትቶልን የሄደው ጦስ ነው አሁን ኢትዮጵያን እየበጠበጠ ያለው።
አዲስ የሚቋቋመው ፓርላማ በቀዳሚነት ማየት ያለበት ህገ መንግስቱን የሚሻሻልበትን ወይም የሚለወጥበትን መንገድ ነው። ምክንያቱም የወያኔ ህገ መንግስት አሁን እንዳለ ተቀምጧል። አሁን ኢትዮጵያን እያበጣበጠ ያለውም እርሱ ነው። ያንን ህገ መንግስት እስካልለወጥን ድረስ በእዛው የሚቀጥል ከሆነ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ምንም ነገር ይኖራል ብዬ አልገምትም።
እኔ አሁን ተቃዋሚ ብሆንም ሁሉንም ነገር እቃወማለሁ ማለት አይደለም። የትኛውም አካል መንግስት ሆኖ ሲሰራ ጥሩም መጥፎም ሊሰራ ይችላል። ግን የወያኔ መንግስት በዘር ላይ የተመሰረተ አካሄድ ያራምድ ስለነበር ያንን በዘር፣ በቋንቋ የተመሰረተውን ፖለቲካ መቀየር ይኖርበታል። እኔ ኦሮሞ ሆንኩ፣ አማራ ሆንኩ፣ ትግሬ ሆንኩ ምን ይጠቅማል? አይጠቅምም፤ በኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው ማመን ያለብን። የዚህ አላማ አገር መበታተን ነው። ይህንን የሚያደርጉትም ኢምፔሪያሊስቶች ናቸው።
ባለፉት በርካታ ዓመታት እንደሚታወሰው ኢትዮጵያዊነት የሚለው ነገር ጠፍቶ ነበር። እኛም ስንታገል የነበረው ይህ የዘር ፖለቲካ አያዋጣም የሚሻለው አንድነትና ኢትዮጵያዊነት በማለታችን ነው መሪዎቻችን፣ አባላቶቻችንና ደጋፊዎቻችን የታሰሩት፣ የተገረፉትና የተገደሉት። የተገፋነው ኢትዮጵያዊነትን ይዘን ስለምንታገል ነው። እነርሱ ደግሞ በዘር ላይ የተመሰረተ አካሄድ ነው የሚፈልጉት። ኢትዮጵያን ለመበታተን ነው ፍላጎታቸው።
አዲስ ዘመን:- ኢትዮጵያን ለምንድን ነው ለመበታተን የሚፈልጉት?
ዶክተር በዛብህ:- በሃይለ ስላሴ ጊዜ አሜሪካኖች የኢትዮጵያን የምጣኔ ሃብት በሙሉ አጥንተው ያውቃሉ። ቤንዚን የት እንዳለ፣ ጋዝ የት እንዳለ፣ ወርቅ የት እንደሚገኝ… ሁሉን ነገር የት እንዳለ አጥንተው ያውቃሉ። ስለዚህ ጠንካራ ኢትዮጵያ ከሆነች እንደልባቸው መበዝበዝ አይችሉም።
የተበታተነች ኢትዮጵያ ከሆነች ግን እንደልባቸው ለመዝረፍ ይችላሉ። ለዚህ ነው አሁን በዘር የሚከፋፍሉን። አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ ብለው የሚከፋፍሉን እንደልባቸው ለመጫወት እንዲችሉ ነው ይሄ ሁሉ ረብሻ የሚሆነው። እና አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ይጠቅመናል።
አዲስ ዘመን:- መአህድ / የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተመሰረተበትን ሃላፊነት ተወጥቷል ማለት ይቻላል?
ዶክተር በዛብህ:- መአህድን የመሰረቱት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እና ሌሎች ስለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት የነበራቸው ሰዎች ናቸው። ያኔ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ሳይሆን መአህድ ብለው ነበር የመሰረቱት። የመላው አማራ ብለው የመሰረቱት ዘረኛ ስለሆኑ አይደለም። በእዛን ጊዜ በአማራ ላይ ይደርስ የነበረው ችግር፣ በየቦታውም ይገደል ስለነበረ የአማራውን ችግር ለመቋቋም እንዲቻል ብለው ነበር። እንደ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ዘረኝነትን የሚጠላ የለም። ሰውየው በኢትዮጵያዊነት ነው የሚያምኑት። ያንን ድርጅት ካቋቋሙ በኋላ ብዙ ታግለው፣ ታስረውና ዋጋ ከፍለው አረፉ።
እርሳቸው ካረፉ በኋላ ይሄንን ድርጅት በሃላፊነት የያዙት ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ናቸው። ቀደም ብሎም ከፕሮፌሰር ጋር ከምስረታው ጀምሮ አብረው ነበሩ። ኢንጂነር ሃይሉ መሪ ሆነው ሳለ ነው ቅንጅት ያን ያህል አብቦ ትልቅ ፓርቲ ሊሆን የቻለው፤ አራት ፓርቲዎች ተዋህደው ነው የመሰረቱት። የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ ቀስተ ደመና እና ኢድሊ ነበሩ። ሲመሰረት ኢንጂነር ሃይሉ ሻወል ሊቀመንበር ሆኑ። እኔ በእዚህ ወቅት ኢዴፓ ውስጥ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነበርኩ። አራታችን አንድ ላይ ስንሆን የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ላዕላይ ምክር ቤት 60 አባላት ነበሩት፤ እኔም የእዚህ ኮሚቴ አባል ሆንኩኝ። በታሰሩብን ጓደኞቻችን ምክንያት ከሻለቃ አድማሱ ጋር ወደ አሜሪካ የተጓዝነውና ለአንድ አመት በውጭ አገር ስንሰራ የቆየነውም የዚህ የላዕላይ ምክር ቤት አባል ስለነበርን ነው።
መኢአድን እንደ ድርጅት ካየኸው ለኢትዮጵያዊነትና ለኢትዮጵያ ያለው ትግል በጣም ከፍተኛ ነው። ቅንጅትም ሊመሰረት የቻለው በመኢአድ ጠንካራ መሰረት ላይ ሆኖ ነው። ኢዴፓም ለምስረታው ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ሌሎቹ ገና መቋቋማቸው ነበር። ይህ ትግል እንግዲህ በጣም ጥሩ ስራ ሰርቷል ብዬ እገምታለሁ። ለምሳሌ 1997 ዓ.ም ያነሳህ እንደሆነ የዴሞክራሲ ጭላንጭል የታየበት ጊዜ ነው። ትንሽ ጭላንጭል ስለነበረ ነው ቅንጅት ገብቶ ያንን ሁሉ ድል ያደረገው።
ሚያዝያ 29 ቀን 1997 ኢህአዴግ በጠራው ድጋፍ ሰልፍ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ይህንን ሁሉ ህዝብ ይዘን ምርጫውን ማሸነፍ አያቅተንም ነበር ያሉት። በማግስቱ ቅንጅት የድጋፍ ሰልፍ ሲጠራ በጣም በርካታ ሕዝብ ነው ወጥቶ አዲስ አበባን ያጥለቀለቀው። ይህንን ተከትሎ በተካሄደው ምርጫ ነው እነ ኢንጂነር ሃይሉ ሻወል፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሊታሰሩ የበቁት። እስር ቤት ሆነው የቅንጅትን ሁኔታ ወደ አሜሪካ ተጉዘው የሚያስረዱ ሁለት ሰዎች ተመረጡ። ሻለቃ አድማሱ መላኩ (በህይወት ያሉ) እና ዶክተር እኔ ነበርን የተመረጥነው። አሜሪካ የሄድንበት ዋና ጉዳይ የትግል ጓዶቻችን በግፍ መታሰራቸው በየእስቴቱ በመዞር ለማስረዳት ነው። በየእስቴቱ በመዞር ለአንድ አመት ያህል አስረዳን።
እንደሚታወሰው ቅንጅት በአዲስ አበባ ባካሄደው ምርጫ ከ138 መቀመጫ 137 ነው ያሸነፈው። ጎሬ ላይ እኔ ነበር የተወዳደርኩት። በከፍተኛ ደረጃ ነበር በእዛን ጊዜ ያሸነፍኩት። ግን ሌቦች ስለነበሩ አጭበረበሩ። ጎሬ ከተማ አራት ቀበሌ ነበሩ። ከእነዚህ ሶስቱን በከፍተኛ ደረጃ አሸንፌያለሁ።
ከዛ በኋላ ወያኔ ነቃ። ነቅቶ እኮ በቅንጅት ግፊትና ትግል ብዙ ነገር ሰርቷል። ምክንያቱም ያኔ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዓላማና ሃሳብ ልማት ከገጠር ወደ ከተማ ነበር።
ከእዛ በኋላ ነው ከከተማ ወደ ገጠር እንዲሆን የቀየሩት፤ አየህ ከቅንጅት በኋላ ንቃት አገኙ ማለት ነው። አንዳንድ ነገሮችንም ለመስራት ሞክረዋል። መንገድ ተሰርቷል፣ አዲስ አበባም ተለውጣለች። ግን ይህ አልነበረም የሚፈለገው። መገንዘብ የሚገባን ነገር አለ፤ የኢኮኖሚ እድገት እንላለን ግን ባግባቡ አንገነዘበውም። የኢኮኖሚ እድገት መሰረቱ የሰው ልጆች መሰረታዊ ነገር የመሟላት ጉዳይ ነው። ስራ፣ መኖሪያ ቤት፣ ልብስ፣ ምግብ ሲሟላ ነው የኢኮኖሚ እድገት ልንል የምንችለው። እዚህ ግን የኢኮኖሚ እድገት ጥቂት ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ፎቅ ይሰራሉ፣ ገንዘብ ያገኛሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ችግር ላይ ነው። ይህ መለወጥ አለበት።
ቅድም እንዳነሳሁት ምክር ቤቱ ከመስከረም በኋላ ስራ ሲጀምር ማሰብ ያለበት ለራሱ አይደለም፤ መስራት ያለበት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ምክንያቱም ብዙ ሰው ነው በአሁኑ ጊዜ በችግርና በረሃብ ላይ ያለው። በየቀኑ የኑሮ ውድነት እየጨመረ ይገኛል። ምክር ቤቱ በእውነት እሰራለሁ ካለ ለድሃው ህዝብ ማሰብ ያስፈልጋል። ለጥቂት ሃብታሞችና ሚሊየነሮች ምቾት መሆን የለበትም። ለድሃው ማሰብ ያስፈልጋል። አዲስ የሚቋቋመው ምክር ቤት ጥሩ ነገር ይሰራል ብዬ እገምታለሁ። መስራትም አለበት። ሕዝብ መረጠኝ ካለ አንዴ በልቶ ጾሙን ለሚያድረው ደሃው ሕዝብ ማሰብ ይኖርበታል። ጥቂት ሃብታሞች ብቻ ሃብት እንዲያካብቱ የምናደርግ ከሆነ ለኢትዮጵያ ሰራን ማለት አይቻልም።
እኔ አሁን ያለሁት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ውስጥ ነው። ነገር ግን ወዳነሳኸው ጥያቄ ስመለስ መኢአድ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የበለጠ ብዙ ስራ ሰርቷል። ያ ማለት ግቡን መትቷል ማለት ግን አይደለም። ምክንያቱም እኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባጠቃላይ ማሰብ ያለብን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሕዝብም መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን:- በትግራይ ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያውጅም አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአዲስ መልክ ወደ ግጭት እየገባ ይገኛል፤ ይህ ወዴት ያስኬዳል ይላሉ?
ዶክተር በዛብህ:- ጥይቱ የትም አያደርሰንም። እነዚህ ሰዎች ለኢትዮጵያ ውድቀት የሚታትሩ ናቸው። ኢትዮጵያን ለማተራመስ እና ለመዝረፍ ቀን ከሌት የተጉ ናቸው። በከተማ ውስጥ እንኳን ስንት ፎቅና ሃብት ነበራቸው። ያ ሁሉ ጥቅም ቀረባቸው። ታዲያ ምን ያድርጉ። በተለያየ አካባቢ ትንኮሳ የሚያደርጉት ጥቅማቸው ስለተቋረጠባቸው ነው። አላማቸው እንደገና ወርረው መጥተው ዳግም መምራት እኮ ነው። ‹‹የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር›› ይባላል። ይሄ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሞቷል ማለት ነው እነርሱ አሁን እንደገና መጥተው የሚመሩ ከሆነ። ጎረቤቶቻችን ሱዳንና ግብጽ እያስታጠቋቸው ነው። መንግስት ኢትዮጵያን ለማዳን መዋጋት ይኖርበታል። እየተዋጋም የሰላሙን መንገድ ለመፍጠር መስራት ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን:- የተለያዩ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና እንዴት መቋቋም ይቻላል? በተለይ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ግፊት ሲያደርጉ ይታያልና ከእዚህ አንጻር ያለውን ሁኔታ ለመግታት ምን መደረግ አለበት?
ዶክተር በዛብህ:- እኛ ኢትዮጵያውያን ላይ ይሄ ሁሉ ሃይል ችግር የሚፈጥሩብን ደሃ በመሆናችን፣ በርዳታ ስለምንኖር ነው። አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት ያን ያህል የሚፎክሩብንና የሚዝቱብን ያችኑ እርዳታ ለመቁረጥ ነው። እነዚህ የትግራይ ተገንጣይ መሪዎች ብዙ የዲፕሎማሲ ስራ ይሰራሉ። ለምሳሌ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊው ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ብትወስድ ምላሹን ታገኛለህ። እርሱ ብቻ አይደለም አሜሪካን አገር በተለያዩ ስልጣኖች ያሉ በርካታ ሰዎች አሏቸው። እነርሱ ፈረንጆቹ ላይ ተጽእኖ በማሳደርም ተሰሚነት አላቸው። በተጨማሪም የአሜሪካን አገር ሴኔት ውስጥ ተመራጮች የሚያግባቡ (lobbies) የሚባሉ አሉ። እነዚህ ገንዘብ ይከፍሏቸዋል። እነዚህ ሰዎች ይህንን ቴክኒክ ከእኛ የበለጠ ያውቃሉ። በእዛም ነው አሁን ተጽእኖ እያደረጉ እያስቸገሩን ያሉት።
ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል፣ ኢትዮጵያ እንድትገለል የአውሮፓ ህብረት የሚያደርገው ሩጫ ሳይታሰብ የሚደረግ ነገር ነው። ያለውን መንግስት ዴሞክራቲክና ሊበራል ሆኖ ከመስራት ወደ ሶሻሊስት ቻይናና ወደ ራሺያ እየገፋፉት ነው። በፊት የተሻለ ነበር። ዋናው ጥላቻቸው ደግሞ ከቻይና ጋር የተደረገው ግንኙነት ነው። ቻይናዎች ፓርኮችን እየሰሩ ናቸው፣ የተለያዩ ልማቶች ላይም አሉ ይሄ ሁሉ በጣም ያበሳጫቸዋል። ወደ ሶሻሊዝም እየገፋቸው ነው ብለውም ያምናሉ። ስለዚህ ለሶሻሊዝም ለሚገነባ መንግስት ብራችንን ለምን እንስጥ መምታት አለብን የሚል ነገር ይኖራል። ኢትዮጵያ ከራሺያና ከቻይና ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመሰረተችውን የበለጠ እዛ ውስጥ እንድትዘፈቅ እያደረጓት ነው።
አዲስ ዘመን:- የአውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ መንግስት በሰላማዊ መንገድ ስለተጠናቀቀው ምርጫም ሆነ ስለኢትዮጵያ ሌሎች በጎ ተግባራት ምንም ማለት አይፈልጉም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ግጭት ነው ትኩረታቸው፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው?
ዶክተር በዛብህ:- የኢትዮጵያን በጎ ነገርም ሆነ ሌሎች በጎ ተግባራትን መናገር አይፈልጉም። አንድ ቀላል ነገር ላሳይህ። አሜሪካንን ውሰድ እኔ ዘጠኝ ጊዜ ተመላልሻለሁ፤ ለአንድ አመት ያህልም ኖሬያለሁ። አሜሪካ ዴሞክራሲ ይላሉ፣ ውሸት ነው። በቅርብ ጊዜ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለን ጥቁር አሜሪካዊ ሰረቀ፣ ሌባ ነው በሚል አንድ ፖሊስ አንገቱ ላይ ረግጦ ገድሎታል፡ ይሄ አንድ ትንሽ ምሳሌ ነው። የአሜሪካንን እስር ቤት በሙሉ ብታይ 80 በመቶው ጥቁር ነው። በጣም ዘረኞች ናቸው።
በእነርሱ አይን ጥቁር በየሄደበት ሁሉ ሌባ ነው። በየሄደበት ሁሉ ይገደላል። የጆርጅ ፍሎይድ አጋጣሚ ሆኖ ስለተቀረጸ ነው እንጂ አሜሪካን አገር ስንቱ ጥቁር ነው ሲገደል የሚውለው። አውሮፓንም ብትወስድ ዘረኞች ናቸው። ዴሞክራሲ ይላሉ ውሸት ነው ዴሞክራሲ የለም። ትግራይ ውስጥ በደል ደረሰ፣ የሰብአዊ መብት ተጣሰ ይላሉ የራሳቸውን የአገራቸውን የሰብአዊ መብት ግን አልጠበቁም። ለስም ብቻ፤ ለፕሮፖጋንዳ የሚያደርጉት ነገር ነው። ምክንያቱም የሰብአዊ መብት ተማጋቾች የሚኖሩት ገንዘብ ከሲአይኤና ከሌሎቹም የሚያገኙት ጥቁሮች ናቸው ብለው እየገፋፉ ነው እንጂ እዚ ከእነርሱ የሰብአዊ መብት ረገጣ አይብስም።
አዲስ ዘመን:- የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ባለፈው የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር እንዲታይ ወስኗል፤ ይህ ከኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስራ አንጻር እንዴት ይታያል?
ዶክተር በዛብህ:- ተኩሱንም እየያዝክ ሰላማዊ መንገዱንም መከተል ያስፈልጋል። ማግባባቱ ተገቢ ነው። ብልህ መሆን ያስፈልጋል። ዲፕሎማሲው በጣም መሻሻል ያስፈልገዋል፤ ብዙ መሰራት አለበት። ምክንያቱም እነርሱ በዲፕሎማሲ ስለበለጡን እኮ ነው የአውሮፓ ህብረትም፣ የአሜሪካ ኮንግረስም፣ ሌሎቹም የሚረባረቡብን ዋናው ይህ ነው። እነርሱ ጥሩ ሰዎች አይደሉም እየሄዱ ይነግሯቸዋል።
በሚኒልክ ቤተ መንግስት ጊቢ አንድነት ፓርክ ተሰርቷልና ይሄም ሆነ ሌሎቹ የተሰሩት በቻይናዎች ነው። ይሄ ሁሉ እኮ አውሮፓ ህብረትንም ሆነ አሜሪካኖችን ያደብናቸዋል። ለዚህ ነው ወደ ሶሻሊዝም እየሄዱ ስላሉ ለምን ብራችንን እንስጥ የሚል ነው። በጣም ያሳዝነናል። አሜሪካኖችም የአውሮፓ ህብረትም አሁን በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለው ነገር በጣም ባሰ፣ ከመጠን በላይ ሆነ።
አሸባሪው ህወሓት 27 አመት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሲያደርግ ለምን አሁን እያደረጉ ያሉትን አላደረጉም? በርካታ ኢትዮጵያውያን በየቦታው ሲገደሉ ነበር እኮ! ዝምታ ነበር ምላሻቸው። እያጭበረበረ ምርጫ ላይ ስንት ነገር ሲያደርግ ለምን ይህንን አላደረጉም? ያኔ እኮ ዝም ብለው ነበር። አሁን ምንድን ነው ጭንቀታቸው። ይሄ የተለየ ነው። በእነርሱ ዘመን ምንም የማያውቅ አማራ ሲገደል ምንም አላሉም። አየህ በዛን ጊዜ ምንም አልተነፈሱም። ትግራይ ላይ ምንድን ነው አዲስ ነገር የተፈጠረው? ምንድን ነው እንዲህ የሚደረገው ከበስተጀርባው አንድ ነገር አለ። ቅድም ነግሬህ ነበር እኮ የአገርን ሃብት ያውቃሉ ወርቁን፣ ምኑን…፤ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ እምቅ ሃብት ያውቁታል። ትግራይ ትበተናለች ትግራይ ትሆናለች፣ አማራ ክልል ይበተናል አማራ ይሆናል፣ ኦሮሞ ክልል ይበተናል ኦሮሞ ይሆናል…ሌሎቹም ይቀጥላሉ፤ ጠንካራ ኢትዮጵያ የለም። እነዚህ ደግሞ ትንንሽ መንግስት ይሆናሉ እነርሱ እንደልባቸው ይደንሳሉ! ሃብት ይበዘብዛሉ። ስለዚህ ጠንካራ ኢትዮጵያን አይፈልጉም። ያልወጣ በርካታ ሃብት መሬት ውስጥ አለ። በታትነው እንደልባቸው ሊዝቁ ነው ዋናው አላማቸው።
የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ ሰዎች የሚወጥኑት ነገር ይኖራል። ረብሻ ለመፍጠር ጥረት ያደርጋሉ።መንግስት የጸጥታና የደህንነት ክፍሉን ማጠናከር አለበት። ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ማክሸፍ ይኖርበታል። ሰው ከሞተ በኋላ ማልቀስ ዋጋ የለውም። ሰዎች ከሞቱ፣ ቤታቸው ከፈረሰና ከተቃጠለ፣ ከተሰደዱ በኋላ የሚደረገው ነገር ሁሉ ብላሽ ነው። መንግስት ቀድሞ መገኘት አለበት። ቀድሞ ከተገኘ የተወጠነውን ሁሉ ማክሸፍ ይችላል። በየቦታው መረጃ በማግኘት ቀድሞ ስራውን መስራት ይኖርበታል። የህዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ስራ በመንግስት ላይ የተጫነ ስለሆነ መንግስት ሰላምን ለመፍጠር የሚያደርገው ትግል ከፍተኛ መሆን አለበት። ስለዚህ መወያየት ያስፈልጋል፣ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት መደረገ አለበት። አሸባሪው ህወሓት ሰሞኑን አማራንና አፋር ክልልን ለመውጋት ሙከራ አድርጓል። ዝም ብሎ ጥቃት የሚያስተናግድ የለም ሁሉም ይከላከላል። የመከላከል ስራም በከፍተኛ ደረጃ መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን:- በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመግታት ምን አይነት እርምጃ መወሰድ አለበት?
ዶክተር በዛብህ:- አሁን አገር ውስጥ ከፍተኛ ግሽበት አለ። ግሽበቱ ሊፈጠር የቻለው አይ ኤም ኤፍ እና የአለም ባንክ ሁል ጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያን መንግስት ገንዘብ ቀንስ ብለው ይጎተጉታሉ። ገንዘብ የመቀነሱ ነገር ነው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር የፈጠረው። ግሽበቱንም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያደረሰው ይህ ነው። የኢትዮጵያን ብር የመግዛት አቅም በጣም ቀነሰው። ይሄ ችግር በተለይ የታየው ደመወዝተኛ ለሆኑና በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ የህብረትብ ክፍሎች ኑሮውን ሊቋቋሙት አልቻሉም። ምክንያቱም በየቀኑ የእቃ ዋጋ ይጨምራል። ያንን መቆጣጠር የሚቻለው መንግስት ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ ነው።
ለምሳሌ ነጻ ገበያ የሚባል አለ። ይህ ማለት ነጋዴውን እንደፈለግክ ዝረፍ አይደለም። ነጻ ገበያ ማለት በነጻነት እንዲነግድ፣ ማዕቀብ እንዳይደረግበት ነው። እንጂ ያለቁጥጥር ዝም ብሎ መዝረፍ አይችልም። ቁጥጥርም አይደረግ ማለት አይደለም። ስለዚህ ጉዳዮ የሚመለከታቸው ተቋማት የዋጋውን ግሽበት በተመለከተ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርባቸዋል። መንግስት ዋጋውን መቆጣጠር ይጠበቅበታል።
ከዚህ በተጨማሪም አይ ኤም ኤፍ እና የአለም ባንክ ገንዘብ እንዲቀነስ ሲጠየቅ ለምን ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል። መንግስት በእነርሱ ትእዛዝ ብቻ የገንዘብን ዋጋ መቀነስ የለበትም።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር በዛብህ፡– እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2013