አርባ ሁለተኛው የመካከለኛና ምስራቅ አፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ቻምፒዮና(ሴካፋ) ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከተጀመረ ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን ይዟል። ከሃያ ሦስት ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት ይህ ውድድር ባለፉት ቀናት የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ሲከናወኑበት የቆየ ሲሆን ዛሬ ከሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ውጤት በኋላ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚዎች የሚለዩ ይሆናል።
ዘጠኝ አገራት በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር በምድብ አንድ ከኤርትራና ከቡሩንዲ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት የምድቡን ሁለተኛና የመጨረሻ ጨዋታ ከቡሩንዲ ጋር ያካሄደ ሲሆን አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል። በጨዋታው በእንቅስቃሴ የበላይነት የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በቸርነት ጉግሳ ግብ አንድ ለዜሮ መምራት ቢችልም ስልሳ ስድስተኛው ደቂቃ ላይ የቡሩንዲው አራት ቁጥር ሃኪም ኢሳ የአቻነቷን ግብ ከመረብ አሳርፏል። የአቻነቷ ግብ ከተቆጠረች በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተጭኖ ቢጫወትም ቡሩንዲ በአንፃሩ ውጤቱን አስጠብቃ ለመውጣት በመከላከልና ሰዓት በመግደል ከጨዋታው የምትፈልገውን ውጤት ይዛ ወጥታለች። በዚህም ኬንያን ተከትላ በአራት ነጥብ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያለፈች ሁለተኛዋ አገር ሆናለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአንፃሩ በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ከኤርትራ ጋር ሦስት ለሦስት በሆነ አቻ ውጤት በመለያየቱ በሁለት ጨዋታ ሁለት ነጥብ ብቻ አሳክቶ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ እድሉን በእጅጉ አጥብቧል።
ኢትዮጵያ የውድድሩ አዘጋጅ አገር እንደመሆኗና ዋናው ብሔራዊ ቡድን ከስምንት ዓመት በኋላ ለ2021 የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ባረጋገጠ ማግስት በሴካፋ በመሳተፉ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ በወጣቶች የተሞላው ስብስብ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ተገምቶ ነበር። ይሁን እንጂ በውድድሩ ከምድቡ አልፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ በእጁ የነበረውን እድል ሳይጠቀም ቀርቷል። በዚህም ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ ዛሬ በሚከናወኑ ሁለት ጨዋታዎች ውጤት ላይ የሚመረኮዝ ይሆናል፡፡
በምድብ አንድ ተጋባዥ የሆነችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሁለት ጨዋታዎች አድርጋ አንድ ነጥብ ብቻ በመሰብሰብ በጊዜ ከውድድሩ መሰናበቷን ያረጋገጠች አገር ስትሆን፣ በተመሳሳይ በሁለተኛው ምድብ ኤርትራ በሁለት ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ በማሳካት ሌላኛዋ ተሰናባች አገር ሆናለች። በምድብ አንድ ታንዛኒያ በአንድ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት የቻለች አገር ስትሆን ዩጋንዳ በአንድ ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ ሰብስባ ዛሬ ታንዛኒያን የምትገጥም ይሆናል። በዚህ ጨዋታ ታንዛኒያ ዩጋንዳን ማሸነፍ ከቻለች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚነት እድል እየሰፋ ይሄዳል። ዩጋንዳ ከተሸነፈች በአንድ ነጥብ ተሰናባች ስትሆን ኢትዮጵያ በአንፃሩ ሁለት ነጥብ በመያዝ ምርጥ ሁለተኛ ሆና ግማሽ ፍፃሜ ለመግባት እድል ይኖራታል። የታንዛኒያና ዩጋንዳ ጨዋታ ውጤት ብቻ ግን የኢትዮጵያን የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚነት እድል አይወስንም።
በሦስተኛው ምድብ ሙሉ ስድስት ነጥብ ሰብስባ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፏን ካረጋገጠችው ኬንያ ጋር የተደለደሉት ጅቡቲና ደቡብ ሱዳን በአንድ ጨዋታ ምንም ነጥብ ሳይኖራቸው ዛሬ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ የዩጋንዳን በታንዛኒያ መሸነፍ ጨምሮ የጅቡቲና የደቡብ ሱዳን ጨዋታን በአቻ ውጤት መጠናቀቅ መጠበቅ ግድ ይለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2013