ኢትዮጵያ በሚፈለገው ልክ ባይሆንም የገጸ ምድር ውሃዎቿን ለመጠቀም እንቅስቃሴ እያደረገች ሲሆን የከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀም ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ጥናቶች ያሳያሉ ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የከርሰ ምድር ውሃን ለመጠጥ እና ለመስኖ የመጠቀም ጅምር ሥራዎች ቢኖሩን አገሪቱ ካላት የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት እና በአገሪቱ ካለው የውሃ እጥረት አንጻር እምቅ አቅሟን አሟጣ እየተጠቀመች አይደለም ፡፡ የከርሰ ምድር ውሃን መጠቀም ያልቻለችው ደግሞ ተገቢው ጥናት ባለመካሄዱ እና የከርሰ ምድር ውሃ ያለባቸው አካባቢዎች በውል ባለመታወቃቸው ነው፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ፣ በየትኞቹ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ እንዳለ ለማወቅ፣ ምን ያህል የውሃ መጠን መኖሩን፤ ለምን ያህል ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ማወቅ፤ እንዲሁም ለሌሎች አገልግሎቶች ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል የኢትዮጵያ መንግስት ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በመተባበር ጥናት ለማካሄድ ስምምነት ላይ ከደረሱ ሰነባብቷል፡፡
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋምና የውሃ አቅርቦት መርሃ ግብር አስተባባሪ አቶ የወንድወሰን አንተነህ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ የገጸ ምድር ውሃ በቀላሉ ሊበከል እና ሊጠፋ የሚችል ሲሆን የከርሰ ምድር ውሃ ሁለተኛ አማራጭ ነው ፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃ ያለባቸውን ቦታዎችን መለየት እና ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችሉ መረጃዎችን መለየት አስፈላጊ በመሆኑ ነው የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት መጠን ለማወቅ የሚያስችል ጥናት የተጀመረው ፡፡
ከዚህ ቀደም የከርሰ ምድር ውሃ ለመጠቀም ቢፈለግ እንኳ እየተቆፈረ ውሃ መኖር አለመኖሩ ይታወቅ እንደነበር የሚያነሱት አቶ ወንድወሰን፤ አንድ ቦታ ላይ የከርሰ ምድር ውሃ ፍለጋ ተቆፍሮ ውሃ ካለው ጥቅም ላይ ይውላል፤ ከሌለው ደግሞ ሌላ ቦታ ሲቆፈር እንደነበር ጠቁመዋል ፡፡ በሌላ በኩል መጠነኛ ጥናቶች የተካሄዱ ቢሆንም በተደራጀ መንገድ ተሰንዶ አለመቀመጡን ነው ያብራሩት፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ከእንግሊዝ መንግስት ጋር በመሆን ጥናቱን ለማካሄድ የተፈራረሙ ሲሆን፤ ጥናቱን ከመጀመሩ በፊት መዘጋጀት ያለባቸው ተቋማዊ ነገሮች ባለመጠናቀቃቸው ጥናቱ ሳይጀመር ቆይቶ እንደነበር ጠቁመዋል ፡፡ በውሉ መሰረት ስራውን በባለቤትነት የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ሲሆን የእንግሊዝ መንግስት ደግሞ የፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋል ፡፡ ለጥናቱ ወደ ሶስት ሚሊዮን ፓውንድ ፈንድ ማድረጉንም ጠቁመዋል ፡፡
እንደ አቶ ወንድወሰን ማብራሪያ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ የዛሬ ስድስት ወር ገደማ የጥናቱ ጨረታ የወጣ ሲሆን የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የጥናት ቡድኖች ጨረታውን አሸንፈዋል ፡፡ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ደግሞ ጨረታውን ያሸነፉት አካላት ጥናቱን ማካሄድ ጀምረዋል ፡፡ ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂዎች ተጠቅመው እያጠኑ ይገኛሉ ፡፡ በሚያዝያ 2014 ጥናቱን ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል ፡፡
ጥናቱ በዋናነት ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ፣ ቆላማ፣ እና ዝቅተኛ አካባቢዎች አማራጭ የውሃ አቅርቦት ለመፍጠር የሚካሄድ ሲሆን፤ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በሶማሌ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 53 ወረዳዎች ውስጥ ነው እየተካሄደ ያለው፡፡
በመረጃ አያያዝ ችግር ምክንያት ከዚህ ቀደም የተጠኑ ጥናቶችም የት እንዳሉ እንደማይታወቁ ያብራሩት አቶ ወንድወሰን፤ ጥናቱ ሲጠናቀቅ በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶችንም በአንድ የመረጃ ቋት ለመሰብሰብ እንደሚቻል አብራርተዋል ፡፡ ለዚህም ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ቋት ይኖራል ብለዋል ፡፡
ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የልማቱን ስራ ለሚመለከተው አካል እንደሚያስተላልፍ የጠቆሙት አቶ ወንደወሰን፤ ውሃው ያለባቸው ቦታዎች ከተለዩ በኋላ የልማቱ ስራ በሌላ ፕሮግራም ፈንድ ይደረጋል ፡፡ ፕሮግራሙ ማጥናትና መረጃውን ለመንግሥት አቅርቦ መንግስት ማልማት እንዲችል እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡
እንግሊዝ በኢትዮጵያ ውስጥ በውሃ ዘርፍ ሁለት ፕሮግራም ያለው ሲሆን፤ አንደኛው አሁን ለጥናቱ የሚሆን ፈንድ ያቀረበው ፕሮግራም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚያለማ ነው ፡፡
በቅርቡ ጥናቱ የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገም ወርክሾፕ ተካሂዶ ነበር ። በወቅቱም የምርምር ተቋማት፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ፡፡ በወርክሾፑ ላይ የተገኙት በተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ጥናት ዳይሬክተር ዶክተር ዘነበ ላቀው፤ ተገቢው ጥናት ባለመካሄዱ ኢትዮጵያ ያላትን የከርሰ ምድር ውሃ በአግባቡ መጠቀም አለመቻሏን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
እየተካሄደ ያለው ጥናት የአገሪቱን የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት መጠን ለማወቅ የሚያስችል መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ዘነበ፤ ጥናቱ የትኛው አካባቢዎች ቅድሚያ ይሰጣቸው የሚለውን መሰረት በማድረግ በድርቅ የተጎዱና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ያረፈባቸው በመለየት የሚካሄድ ነው።
በደረቃማ አካባቢዎች ጤና ኬላዎች ተቋቁመው ውሃ ለማግኘት የሚቸገሩበት ሁኔታ መኖሩን ያስታወሱት ዶክተር ዘነበ ጥናቱ ይህንን ችግር ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል ። መንግሥት የከርሰ ምድር ውሃን ለመስኖ ልማትና ውሃ አቅርቦት ለማዋል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ላለው ስራ እገዛ እንደሚኖረው ጨምረው ተናግረዋል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2013