ዓለም በቴክኖሎጂ እየዘመነ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያም በተለያዩ ዘርፎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመከተል ከዓለም አገራት ጋር እየተሳሰረች ትገኛለች ። ቴክኖሎጂ ለወለደው ዲጂታላይዜሽን ምስጋና ይግባውና ካለፉት ዓመታት በተሻለ ፍጥነት ዓለም በአንድ ማዕድ እንደሚቋደሱ ቤተሰቦች እየሆነች መጥታለች ።
በተለይም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዲጂታል ፖርታል በመታገዝ የአገሪቷ ከተሞች ከአንዱ ወደ ሌላው በተሻለ ደረጃና ፍጥነት እያደጉ ይገኛሉ ። ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለም በዚህ መልኩ መሸጋገር በመቻሏ ወደፊት የሚመጡና የሚያድጉ ከተሞች ቁጥርም ተበራክቷል። እነዚህ ከተሞች ታዲያ የከተሞች ዲጂታል ፖርታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በባህል፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ ራሳቸውን ለሌላው ዓለም ክፍት ማድረጋቸው አያጠያይቅም።
የከተማ ፖርታሎቹ ሳይቆራረጡ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡና በወቅታዊ መረጃዎች የተሞሉ እንዲሆኑ አስችሏል። የከተሞች ዲጂታል ፖርታልን ማልማት ኃላፊነት የተጣለበት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ታዲያ የሀገሪቱን ዋና መዲና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ዋና ዋና የሚባሉት የኢትዮጵያ ከተሞችን የዚሁ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል ።
በተለይም ካለፉት ሶስት የለውጥ ዓመታት ጀምሮ ዲጂታል ኢኮኖሚን አንዱ የስትራቴጂክ እቅድ አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በአገሪቱ ያሉ ከተሞች የራሳቸው ፖርታል እንዲኖራቸው የማድረጉ ሂደትም አንዱ የዚሁ የዲጂታላይዜሽን አካል ነው ። ለዚህም በቅርቡ በሀያት ሪጀንሲ በይፋ የተመረቀው የስድስት ከተሞች የፖርታል አገልግሎት ጥሩ ማሳያ ነው ። የዲጂታላይዜሽን ፖርታል አገልግሎት ተጠቃሚዎቹ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣ አዳማና አርባ ምንጭ ከተሞች መሆናቸውም በመድረኩ ሲገለፅ ተደምጧል ።
በዚሁ ጊዜም በኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ የለማው የዲጂታል ፖርታል ሥራ መጀመሩንም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ገልጸዋል ። ከተሞች የራሳቸው ፖርታል እንዲኖራቸው መደረጉ አገራችንን ለተቀረው ዓለም ክፍት የምናደርግበት አንዱ መንገድ ነው ። ሆኖም ከለውጡ በፊት እንደ አገር የነበረው ዕውነታ ሲቃኝ እንዲህ እንደ አሁኑ ባለው የዲጂታላይዜሽን እጦት ወይም አለመራቀቅና መሳለጥ አገራት ከአገራት፣ ከተሞች ከከተሞች፣ አገልግሎት ፈላጊው ከአገልግሎት ሰጪው ጋር ተራርቀው የቆዩበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል።
በዚህ ክፍተት መካከልም አሰራሮች ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ቅልጥፍና ጋር ሳይናበቡ ለመጓዝ ተገድደው ኖረዋል ። በዚህ ምክንያትም ብልሹ አሰራርና ሙስና በአገልግሎቱ ሂደት መንገሱም አይዘነጋም ። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች፣ የአገራት ብሎም የከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም የራሳቸው የከተሞች መሻሻልና ዕድገትም በዚሁ ችግር ተተብትበው መቆየታቸው ይጠቀሳል ። በኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት ለምቶ ወደ ሥራ የገባው የከተሞች ዲጂታል ፖርታል በከተሞች መካከል ያለውን መራራቅ በማስወገድ ከፍተኛ መቀራረብን በመፍጠር ችግሮችን ይቀርፋል ። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ያሳልጣል፣ ዛሬ ላይም የዕለት ከዕለት ተግባራትንና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን እያቃለለ ይገኛል ።
‹‹አንድ ፖርታል ለብዙ ከተሞች አገልግሎት መስጠት ይችላል›› የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው የዲጂታል ፖርታል ዋና ዓላማ በአገር ውስጥ የሚሰጥ የመንግስት አገልግሎትን መደገፍ ነው ። ይሄን ፈር በመከተል በ10 ዓመቱ ዕቅድ ማብቂያ ላይ 85 በመቶ የሚሆነውን የመንግስት አገልግሎት በኦንላይን አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ የታቀደበት ሁኔታ አለ ። ከዚሁ ጋር ተሳስሮ የመሄዱ ጉዳይ አስፈላጊና ግድ የሆነውን የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን 60 ሚሊዮን የማድረስ እቅድም ታሳቢ ሆኗል ።
አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ በአገር ደረጃ የመንግስት አገልግሎት የሚሰጡ 124 አገልግሎቶች በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካይነት ተገኝቷል። እስከ ሐምሌ አንድ ቀን 2013 ዓ.ም ከ85 ሺህ በላይ ተገልጋዮች ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ጎብኝተውታል። አገልግሎቶችን ወደ 400 የማድረስ ሥራም ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል ። በተለይ የከተሞች አመራሮች (በየደረጃው ያሉ ከንቲባዎች) እነዚህንና በየደረጃው ዘመኑ የፈጠራቸውንና የሚፈጥራቸውን ዲጂታል መገናኛ መንገዶች በመጠቀም ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያገናኙበት መንገድ የመፍጠር ኃላፊነት አለባቸው።
ከአገራችን ባለፈ የአገራችን ከተሞች ከሌሎች አገሮች ከተሞች ጋር የሚገናኙበትን መንገድ መፍጠርም ግድ ይላቸዋል ። ምክንያቱም የከተሞች ዲጂታል ፖርታል ቴክኖሎጂ ፈርጀ ብዙ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ነው። በተለይም በመረጃ ተደራሽነት ዙሪያ እያበረከተ የሚገኘው እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። ዜጎች ባሉበት ሆነው ቀልጣፋ የመረጃና ሌሎች ተፈላጊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላል። ዜጎች አገልግሎት ይጠይቁበታል፤ የጠየቁትን አገልግሎትም በቀላሉ ያገኙበታል ። የተሟላ መረጃ ለማግኘትም ዓይነተኛ መሣሪያ ነው።
የውጭ አገር ጎብኚዎች ስለ ከተሞቹ ብሎም ስለ ኢትዮጵያ በቂ ዕውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ በኩልም አበርክቶው ከፍተኛ ነው ። ይህ ብቻም ሳይሆን በአጠቃላይ የአገር ኢኮኖሚም አስተዋፅዖው የላቀ ነው ። ለአብነትም በአሁን ወቅት በተጨባጭ የበርካታ አገራት ኢንቨስተሮችንና ታላላቅ ድርጅቶች ባለቤቶችን እንዲሁም የዲያስፖራውን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ወደ አገር ቤት መሳብ ያስቻለበት ሁኔታ አለ ። ስለዚህ ዲጂታላይዜሽንን አጠናክረን ስንቀጥልና ለቴክኖሎጂ ቅርብ ስንሆን ደግሞ ከዚህ የበለጠ ትልልቅ አቅም ያላቸውን ድርጅቶችን በመሳብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን ማሳደግ እንደምንችልም አበክረው ያስገነዝባሉ።
ሚኒስቴር ዴኤታው ዶክተር አህመዲን እንዳሉት፤ ለከተሞች አመራሮች በተለይም በመድረኩ ለተገኙትና ወደ ዲጂታል አገልግሎቱ በይፋ ለተቀላቀሉት የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል ። ማሳሰቢያና መመሪያው ያጠነጠነው የከተማ ፖርታሎቹ ሳይቆራረጡ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል የሚጠበቅባቸው ስለመሆኑ ነው። በወቅታዊ መረጃዎች የተሞሉ እንዲሆኑም ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው የሚመክሩም እንደሆኑ ተመልክተናል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአይሲቲ ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር ጄነራል የሆኑት ዶክተር ኢንጂነር አብዮት ሲናሞ በበኩላቸው ለፖርታል አገልግሎቱ የከተሞቹ ከንቲባዎች ትኩረት እንዲሰጡ ከማሳሰብ አለመቆጠባቸውንም አስተውለዋል። ምክንያቱን እንደጠቀሱት የከተማ ፖርታል የአገር ውስጥ ከተሞች ከአገር ውስጥ እና ከሌሎች የውጭ አገራት ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ በር የሚከፍት በመሆኑ ትኩረት መስጠቱ እጅግ አስፈላጊ ነው ። ኢትዮጵያ የያዘቻቸውን ትላልቅ የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት ኢኮኖሚዋን ወደ ዲጅታል ኢኮኖሚ ማሸጋገር የሚጠበቅባት ከመሆኑም አንፃር ትኩረት መስጠቱ አማራጭ የለውም።
የዲጂታል ፖርታሉን አገልግሎት አስመልክተው በመድረኩ ለተሳታፊውና ለከተሞቹ ኃላፊዎች ገለፃ ያደረጉትና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዲጂታል አገልግሎት ልማት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ፈቀደ ጌታሁን እንደተናገሩት፤ የዲጂታል ፖርታሉ አገልግሎት አብዛኞቹን የአገራችንን ከተሞች በወረቀት ላይ ከተመሰረተ አገልግሎት የሚያላቅቅ በመሆኑ ትኩረት መስጠቱ አስፈላጊ ነው ። ያልዳበረ አገልግሎት አሰጣጥንም ያሻሽላል፤ ብሎም ያስቀራል። ዜጎች ከመንግስት የሚያገኙት አገልግሎት ላይ ዕምነት እንዲኖራቸው በማድረግም የጎላ ድርሻ አለው። ምክንያቱም ከመንግስት የሚመጣ አገልግሎት ጠያቂው ማነው የሚለውን ስለማያውቅ ግልፅነቱ ይጨምራል። አገልግሎቱን የሚሰጠው አካል ለማን እንደሚሰጥ ስለማያውቅ ተጠያቂነቱም እንዲሁ የሚጎለብትበትን ዕድል ይፈጥራል ። በአጠቃላይ የመንግሥት አገልግሎትን በቀን 24 ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀናትን ያሳልጣል።
ኃላፊው በዚሁ ቴክኖሎጂ አገልግሎት አጠቃቀም ዙሪያ የተባበሩት መንግስታት 88 ከተሞችን ማወዳደሩን አስታውሰው ኬንያ 32ኛ ስትወጣ ኢትዮጵያ 54ኛ መውጣቷንም ጠቅሰዋል ። እንዲሁም በቴክኖሎጂው ሌሎች የዓለም አገራት የደረሱበት ለመድረስ አገራችን ብዙ መስራት ይጠበቅባታል። አብዝታ በቴክኖሎጂው መጠቀም ደግሞ ከሥራዎቹ ቀዳሚ ሊሆን ይገባዋል። ቴክኖሎጂውን ተጠቅማ በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦን ላይ ምርጫ ያካሄደችው የኢስቶኒያ ልምድም ለኢትዮጵያ ጥሩ ተሞክሮ ይሆናል።
የአዳማ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ በዚሁ መድረክ በተካሄደው የቃል ኪዳን ሰነድ ፊርማ ሥነሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የኢስቶኒያን ተሞክሮ በመውሰድ ኢትዮጵያን የላቀ የዲጂታል ቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ለማድረግ በትጋት ይሰራል። በተለይ አዳማ ከተማን ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። አንዱና ዋነኛው ከተማዋ የከተሞች ዲጂታል ፖርታል ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ነው ። እነ ጅማ፣ ሻሸመኔና ሌሎች የኦሮሚያ ከተሞችን ወደ አገልግሎቱ ለማስገባትም እቅድ መኖሩን ይናገራሉ።
ሌላው የዚሁ መድረክ ተሳታፊና ከኦሮሚያ ክልል ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ ዶክተር ልጅ ዓለም አየለ እንደተናገሩት ፤ዲጂታል ፖርታሉ (የመረጃ ቋቱ) ከተሞች የሚዘምኑበት ዋነኛ መንገድ ነው። አዳማ ከተማን ከባህር ዳር፣ አዲስ አበባና ከሌሎች የአገር ውስጥና የዓለም ከተሞች ለማወዳደርም ያስችላታል ። የከተሞቹ ነዋሪዎችም አገልግሎቱን በመጠቀም የተሻለና የዘመነ ኑሮ እንዲኖሩ ያግዛል ። በተለይም የመንግሥትን አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ ያደርጋል ። ብቻም ሳይሆን አገልግሎቱ ፈጣን ባለመሆኑ ምክንያት የታዩ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ።
ሌላውና የመድረኩ ተሳታፊ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰብስቤ ቡናቤ እንዳሉት አርባ ምንጭ ከተማ በአገር ብሎም በዓለም ደረጃ ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ መሆኗ ይታወቃል ። ከኢኮኖሚ ጠቀሜታም አንፃር በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቷ ስሟ ጎልቶ ይጠቀሳል። ሙዝ፣ ማንጎና አፕል ከፍራፍሬዎቿ መጥቀስ ይቻላል። በአሳና በአዞ እርባታ በአጠቃላይም በውሃ ሀብቷም ገናና ስትሆን ከውሃ ሀብቷ የአባያና ጫሞ መገኛም ነች። ከዚህ አኳያ ዲጂታል ፖርታል አገልግሎቱ ለአርባ ምንጭ የሚሰጠው ጠቀሜታ የሚያጠያይቅ አይሆንም። በመሆኑም ለዚህ ተግተው ለመሥራት ቃል ገብተዋል። አስቻይ የሆኑ ሁኔታዎችም ቢሆኑ መመቻቸታቸውን አልሸሸጉም። ከተማ አስተዳደሮቹ መረጃ እንዲያከማቹ፣ አዳዲስ ማሻሻያዎችን እንዲጨምሩ፣ አጠቃቀሙን እንዲያውቁ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሚያስችላቸውን ስልጠና መውሰዳቸውን ነው የጠቀሱት ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2013