ከፖሊስ ጣቢያው በተጠርጣሪነት የቀረበው ተከሳሽ በመርማሪው ፖሊስ የሚጠየቀውን ይመልሳል ። ፖሊሱ ተፈጽሟል ያለውንና በማስረጃ የያዘውን የወንጀል ድርጊት እየጠቀሰ የሰውዬውን ቃል ይቀበላል ። ግለሰቡ ሆነ የተባለውን ድርጊት ከፖሊስ መዝገቡ እየተነበበለት አንድ በአንድ ያዳምጣል ።
ፖሊሱ ደጋግሞ ጥያቄ ያቀርባል ። ተጠያቂው የሚሰጠውን ምላሽ እንደዋዛ አያልፍም ። ከሚናገረው፣ ከሚመልሰው ተነስቶ በቂ ማብራሪያ ይጠይቃል ። ለእሱ ከግለሰቡ ሁኔታ ማንነቱን መገመት አያቅተውም፣ እስከዛሬ የተደበቀ ምስጢርን በምን ዘዴ እንዳውጣጣ አሳምሮ ያውቃል ።
ፖሊሱና ተጠርጣሪው ተፋጠዋል ። ግለሰቡ የተጠረጠረበትን ወንጀል እስካሁን አላመነም። እየማለ፣ እየተገዘተ በተባለው ድርጊት ያለመሳተፉን ይናገራል። ከዚህ ቀድሞ በምንም ክስ ጣቢያ ቀርቦ ያለማወቁን በማስረዳት የሚያስቀምጣቸው ምክንያቶች የፖሊሱን ልቦና አላሸነፈም።
በእሱ ዘንድ የማይጠቅም፣የማያስፈልግ መረጃ የለም። ግለሰቡ እንዲናገር፣ እንዳሻው እንዲያወራ ዕድል ሰጥቶታል ። አሁን ተጠርጣሪው የህይወት ታሪኩን መናገር ጀምሯል ።
1983 ዓ.ም በአንድ ዕለት አንድ ጨቅላ ይህቺን ዓለም በለቅሶ ተቀላቀለ እናት ጥቂት ቀናት በአራስ ቤት እንደቆዩ ሀሳብ ገባቸው ። ደጋግመው ህጻኑን እያዩ ተከዙ፣እየተከዙ ዳግም በሀሳብ ነጎዱ ። ሀሳባቸው ወንዝ እያሻገረ ይመልሳቸው ያዘ ። ጨቅላውን እያዩ ብዙ ወጠኑ። ውጥናቸው ከአንድ ጥግ ሲደርሰ ሊከውኑት ከራሳቸው ተስማሙ ።
ወይዘሮዋ አሁን የልጃቸው አባት ጎናቸው የለም ። አጠገባቸው ሆኖ ‹‹አለሁሽ ›› አለማለቱ እያስከፋቸው ነው። ጊዜው የመንግሥት ለውጥ የተደረገበት ዘመን ነበር። አጋጣሚው እንዳሻ ሮጦ የልብ ለማድረስ አያመችም ። አራሲቱ ጨነቃቸው ። ቢጨንቃቸውም ያሰቡትን ሊያደርጉ ቆርጠዋል።
እናት የጨቅላው አባት አዲስ አበባ መሆኑን ከሰሙ ጀምሮ ዕንቅልፍ የላቸውም ። ልጃቸው ያለአባት እንዳይቀር አባወራው አለበት ከተባለው ስፍራ መሄድ አለባቸው፤ለአራስ ቤት ቆይታቸው ጊዜ አልሰጡም ።አንድ ቀን ማለዳ ህጻኑን በጀርባ አዘሉ። ጥቂት ገንዘብ ገንዘብ ቋጠሩ ።፡ባላቸውን ፍለጋ ጎንደርን ጥለው ሲወጡ አዲስ አበባ መልስ እንደምትሰጣቸው አልጠረጠሩም ።
ኑሮ በአዲስ አበባ…
አሁን ነፍስ የማያውቀው ህፃንና እናቱ አዲስ አበባ ገብተዋል። ለወይዘሮዋ ከተማው፣ ግርግሩና የሰው ባህሪይ ከኖሩበት ዓለም የተለየ ነው ። ያም ሆኖ ከብዙዎች መግባባት አልተቸገሩም ። አዲሱ ሚካኤል አካባቢ ቤት ተከራዩ ። ልጃቸውን ይዘው ብቻቸውን መኖር ሲጀምሩ ስለጠፋው ባላቸው አንዳች አልሰሙም።
ተስፋ አልቆረጡም። ለቀረቧቸው ስምና ምልክት እየጠቀሱ ‹‹አፋልጉኝ ››አሉ ። ቀናት ወራት ተቆጠሩ። ‹‹አየን፣ሰማን›› የሚል አላገኙም ። ወይዘሮዋ ራሳቸውን እየረዱ ልጃቸውን ማሳደግ ያዙ፤ልጅን ያለአባት፣ ያለ አጋር ማሳደግ ይከብዳል ። እሳቸው ከብቸኝነት ሌላ ምርጫ የላቸውም ። ለህጻኑ ያሻውን እያሟሉ፣ የጠየቀውን እየሰጡ ተንከባከቡት። በዕድሜው ከፍ እንዳለ ስሙን አሰፋ ሲሉ ሰየሙት ።
አሰፋ ..
አሰፋ ዕድሜው ለትምህርት ደረሰ ። እናት ደብተርና መጻፊያ ገዝተው ፣ አዲስ አልብሰው ትምህርት ቤት ላኩት። ከጓደኞቹ ጋር እየዋለ ከቤት ሲገባ ትምህርቱን ወደደው። በአበበች ጎበና ከተሰየመው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተመላለሰ መማሩን ቀጠለ ።
እስከ ስድስተኛ ዘልቆ ሰባተኛ ክፍል ሲገባ የእናቱ ተስፋ በረታ ። ያለአባት ያሳደጉት ልጅ ነገ የሚደርስበትን እያለሙ በፈገግታ ተሞሉ። እንዳሰቡት ሆኖ ልጃቸው ስምንተኛን ተፈትኖ አለፈ። ዘጠነኛ ክፍል ሲደርስ ለመጪው ጊዜ መበርታት እንዳለበት አልጠፋውም ።
አሰፋ የአስረኛ ክፍልን መልቀቂያ ተፈትኖ ውጤቱን በጉጉት ጠበቀ ። በፈተናው ካሸነፈ የእሱንና የእናቱን ኑሮ ይለውጣል። ይህ ካልሆነ የህይወት መንገዱ ይቀየራል ። የውጤት መስሚያ ጊዜው ደርሶ ከትምህርት ቤት ተገኘ ። የታሰበው አልሆነም ። አሰፋ ከባልንጀሮቹ ያነሰ ውጤት እንዳገኘ አወቀ።
አሁን የትምህርቱ ጉዳይ እንደማይሆን ተረድቷል ። ህይወትን ለመምራት፣ ኑሮን ለመቀጠል አማራጭ ሊኖር ግድ ይላል ። ወጣቱ ቆም ብሎ አሰበ ። ያለው ዕድል ሮጦ ማደር እንደሆነ ገባው ። ተዟዙሮ ባለታክሲዎችን ጠየቀ ። በረዳትነት መስራት እንደሚችል ነገሩት ። ጊዜ አልፈጀም። ከጎጃም በረንዳ ድል በር ከሚመላለስ መኪና በቀን አርባ ብር እየተከፈለው ስራ ጀመረ ።
አሰፋ የሚያገኘው ገንዘብ አልበቃውም ። እሱ ግን ለቁምነገር አልተቸገረም ። ባለው ተጠቅሞ ሁለተኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ ያዘ ። ይህ አጋጣሚም ከረዳትነት ወደ ታክሲ ሾፌርነት አመጣው ። በሙያው ዓመታትን እንደሰራ በሌላ መኪና የመቀጠር ዕድል አገኘ ።
አሁን አሰፋ ከትናንት ህይወቱ ተሻሽሏል ። ትዳር ይዞ የአንድ ልጅ አባት ሆኗል ። ወደቋሚ ሾፌር መቀየሩ ከብዙዎች አስተዋውቆ እርምጃውን ቀይሮታል።
አሰፋ የሚይዘው መኪና የባለቤቱ አጎት የሆነን ንብረት ነው ። ሰውዬው አመኔታ ስላላቸው መኪናው እሱ ዘንድ ውሎ ያድራል ። መኪናውን ከመሸጥ መለወጥ ውጭ የሚገባውን ሁሉ እንዲያደርግ ህጋዊ ውክልና ተሰጥቶታል ።
አሰፋ በየቀኑ ከመኪናው የሚጠበቅበትን አምስት መቶ ብር ያስገባል ። ገንዘቡን እንዲሰጥ ለታዘዘው ዘመድም ያስረክባል ። ዘመድዬው የተቀበለውን ገንዘብ በመኪናው ባለቤት የባንክ ደብተር እያስገባ ቀሪ ቀናትን ይጠብቃል ።
ሾፌሩ በአደራና በውክልና በተሰጠው መኪና ሲሰራ ውሎ አመሻሹን ወደ ሱሉልታ ይመለሳል ። ለኑሮ በመረጠውና ተከራይቶ በሚኖርበት የሱሉልታ ከተማ ሚስትና ልጆቹን ያስተዳድራል ። አንዳንዴ ከባልንጀሮቹ ዘንድ እያመሸና እየተዝናና ይገባል ። አሰፋ የመኪናው በእጁ መሆን ኮንትራት ባገኘ ጊዜ እንዲጠቀም አድርጎታል። ይህ አጋጣሚ ዳጎስ ባለ ገቢ ኪስ ያወፍራል፣ ከታሰበው ልቆ ፍላጎት ይሞላል ። አንዳንዴ የአሰፋ ኮንትራት በምሽት ሊሆን ይችላል ። እንዲህ ባልገጠመው ቀን ከባልንጀሮቹ አይርቅም ። በሚሉት እየተስማማ የፍላጎታቸውን ይፈጽማል።
ሚያዚያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም…
በዚህ ቀን አሰፋ እንደልማዱ አዲስ አበባ ውሏል ። ማምሻውን ሱሉልታ እስኪገባ ጥቂት መስራት እያሰበ ነው ። ከጋቢና ተቀምጦ ዙሪያ ገባውን የሚቃኘው የሾላ አካባቢ ዛሬም ግርግር ይዞታል ። አሰፋ በድንገት ሀሳቡን ቀየረ ። ተቀምጦ ስራ ከሚጠብቅ ርቆ ቢሰራ እንደሚበጅ ወስኖ ጎንደርና ባህርዳር ለመጓዝ አቀደ።
በዚህ ሰአት ምሽቱን የሚጓዙ መንገደኞች እንደ አሰፋ ያሉ ሾፌሮችን ይፈልጋሉ ። ካሰቡት ለመድረስ የሌሊት መንገድ ምርጫቸው የሆነ ከመደበኛው ክፍያ በእጥፍ ተነጋግረው ሌሊቱን መጓዝ ይፈልጋሉ ።
አሰፋ በእንዲህ አይነቱ ጉዞ ደጋግሞ ተመላልሷል። የመንገዱን ስጋትና ፍራቻ አያጣውም ። እሱ ግን ለመቅረትና ለመተው ወስኖ አያውቅም ። ሁሌም በደላሎች ገበያ ባገኘ ቁጥር ዋጋ እየተነጋገረ ሌሊቱን ይጓዛል ። በየቀኑ የሚሰማቸው የአደጋ ዜናዎች ሁሌም ያስደነግጡታል ። ለጊዜው አዝኖ መልሶ ይረሳል። ካሰበው ደርሶ ሲመለስም ስለ ነገው ያስባል ።
የመኪናውን መስታወት ከፍቶ ባሻገር የሚቃኘው ሾፌር ድንገት ሀሳቡ በሌላ ትኩረት ተወሰደ ። በቅርብ ርቀት እያየው ያለውን ሰው በመጠኑ ያውቀዋል ። አመጣጡ ወደ እሱ እንደሆነ በገባው ጊዜ መስታወቱን ዝቅ አድርጎ አንገቱን አስጠጋለት ። ከሰላምታ በኋላ ሰውዬው ያሰበውን ነገረው ። ከሁኔታው ጊዜ ያለው አይመስልም ።
አሰፋ ሰውዬው በአጭሩ የነገረውን ጉዳይ መናቅ አልፈለገም ። እሱን በወጉ አለማወቁ ግን ከጥርጣሬ ጥሎታል ። ወጣቱ ከአንድ ስፍራ የኮንትራት ስራ እንዳለ እየነገረው ነው ። በዚህ ሥራ እምብዛም ያለመነው አሰፋ መሄድ እንዳይማፈልግ ነግሮት የምሽት መንገዱን ሊጠብቅ ወሰነ ።
ሰዓቱ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት እያለ ነው ። እስካሁን በእሱ መኪና ለመሄድ የመጣ መንገደኛ የለም፤ አሰፋ ይህን ሲያውቅ ልቡ አመነታ፡፤የሩቅ መንገዱን ትቶ ከተባለበት ስፍራ ሊሄድ አሰበ ። ሀሳቡ ከሁለት ቢከፈልም በቶሎ አልወሰነም ።ጊዜው ከምሽቱ ሁለት ሰአት ላይ እያመለከተ ነው።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አሰፋና ሰውዬው ዳግም ተገናኙ ። የተባለው ስራ በአልጋ ላይ የዋለን ግለሰብ ከአዲስ አበባ ጎንደር ማድረስ እንደሆነ አወቀ ። አሰፋ ትንሽ አመንትቶ ስለ ክፍያው ጠየቀ ። ለአንድ ጉዞ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ብር እንደሚከፍለው ነገረው። ሲመለስ ተሳፋሪ እንደማያጣ ገመተና በክፍያው ተስማማ።
ከምሽቱ አራት ሰአት እንደሆነ የተባለውን በሽተኛ ለማምጣት ወደቦሌ መድኃኒያለም አቅጣጫ ተጓዙ። ከሾላ ዳንኤል የተባለውን ተሳፋሪ ይዘዋል ። መንገድ ላይ የሚቀላቀላቸውን ሌላ ሰው ማግኘት ነበረባቸው፤ ካሌብ ይባላል። ይህ ሰው ይመጣል በተባለበት ሰዓት አልደረሰም ።ጊዜ ወስደው በትዕግስት ጠበቁና አሳፈሩት ።
ካሌብ በእስር ህይወት ተመላልሷል ። ጊዜያትን እያሳለፈ በሚወጣበት ማረሚያ ብዘዎች ያውቁታል። በሌብነትና ከባድ ውንብድና ወንጀሎች የተከፈቱ መዝገቦቹ እስር ሲያስከፍሉት ቆይተዋል። ዛሬም ግን የተማረ አይመስልም፤የሚሻውን ለማድረግ አጋጣሚዎችን ይጠብቃል።
ካሌብ በለስ በቀናው ቀን በጩቤና ሽጉጥ እያስፈራራ ያማረውን ይወስዳል ። ሁሌም ማምለጫ መንገድ አይጠፋውም ። ወንጀል ሲፈጽም ዙሪያ ገባውን በትኩረት ይቃኛል፡፤ከእጁ የገባውን ይዞ ለመሰወር ችሎታው ልዩ ፍጥነቱ ተአምር ነው።
መንገዳቸውን ከመቀጠላቸው በፊት አሰፋ ከካሌብ ጀርባ ሽጉጥ መኖሩን ተመለከተ ። ደጋግሞ እጁን ወደኋላ እየላከ ይነካካዋል ። ሶስቱም ቦታቸውን እንደያዙ ወደተነገረው በሽተኛ ቤት እንዲነዳ አዘዙት ። መንገዱ እንደተጀመረ የተባለው አልሆነም ። በድንገት የጉዞ አቅጣጫው ተቀየረ ። ሁሉም ባነሱት ሀሳብ አሰፋ አልተቃወመም ። በነገሩትና ሊደረግ በታሰበው ጉዳይ ተስማምቶ ወደ ቦሌ ሚካኤል መንገድ መሪውን ጠመዘዘ።
ሌሊት 7፡ ሰአት ከ30 …
የደረሱበት ስፍራ የንግድ ቦታ ነው ። እኩለ ሌሊቱን ያጋመሰው ውድቅት ጭርታ አልያዘውም ። አሁንም በቦሌ ሚካኤልና አካባቢው ሱቆች በስራ ላይ ናቸው ። ሻጭና ገዢ እንደቀን ውሏቸው ይገበያያሉ ። እግረኞች መንገዳቸውን ይዘው ይጓዛሉ ። ከአሰፋ ጋር የነበሩት ሶስት ሰዎች ፈጥነው መውረድ አልፈለጉም ። መኪናውን ጥግ ሳያይዝ እንዲቆም የተነገረው አሰፋ ሞተር አጥፍቶ የተባለውን አድርጓል።
ሁለቱ ሰዎች…
መኪናው ያለአንዳች ምክንያት በቦታው መቆሙን ያስተዋሉት ሁለት ሰዎች ቡቲኮቹን ተከልሎ ከቆመው ሚኒባስ ዓይናቸውን አልነቀሉም ። የተለየ ጥርጣሬ ገብቷቸው ይንሾካሾካሉ ። ከሁለቱ አንደኛው መብራት አጥፍቶ ከቆመው መኪና የተወሰኑ የታርጋ ቁጥሮችን ለማንበብ ሞከረ ። የመጨረሻዎቹ ቁጥሮች ሆን ብለው በጭቃ ተቀብተዋል ። ወጣቱ ኮዱንና የታዩትን ቁጥሮች በልቡ እንደምንም ያዛቸው ። ወዲያው ለሽንት ወደ አንድ ጥግ ዞር ብሎ ቆመ ።
አቶ መሐመድ ሱቃቸውን ከፍተው የሌሊት ደንበኞችን ያስተናግዳሉ ። አካባቢው ጨለማ አይመስልም። ቦግ ብሎ ያለው መብራት በሱቁ ያለውን ሸቀጥ አንድ በአንድ ያሳያል ። ለሽንት ዞር ያለው ወጣት መለስ ከማለቱ ‹‹እንዳትንቀሳቀስ›› የሚል ድምጽ ደጋግሞ ተሰማው።በድንጋጤ ወደ መሐመድ ሱቅ አስተዋለ ።
ከመኪናው አንድ ግዙፍ ባለኮፍያ ወርዶ መሐመድ ሱቅ ላይ ተገትሯል ። የእጁ ሽጉጥ በግልጽ ይታያል ። ብዛት ያለው የጆንያ ሩዝ፣ተሸክሞ ውስጥ ላሉት እያቀበለ ነው ። ሾፌሩና ሁለቱ ከሱቁ የሚመጡ ሌሎች ዕቃዎችን ወደመኪናው በችኮላ ያስገባሉ።
የሰፈሩ ወጣት ዓይኑን ማመን አልቻለም፤ወደሱቁ ተጠግቶ የሆነውን ጠየቀ።አቶ መሐመድ ራሳቸውን ይዘዋል፡፤ ሰዎቹ በሽጉጥ አስፈራርተው እንደዘረፏቸው ነገሩት፤ወጣቱ ጊዜ አላጠፋም። ጎንበስ ብሎ ድንጋዮች አነሳ አከታትሎም ወረወረ።
ድንጋዮቹ የመኪናውን አካል እየመቱ ከመሬት አረፉ። ወጣቱ በዋዛ አላቆመም ወደ ሾፌሩ፣ወደዘራፊዎቹ፣ ሳያቋርጥ ወረወረ ። ድንጋዮቹ ዒላማቸውን አልሳቱም። አሰፋ መኪናውን በፍጥነት ማስነሳት ጀመረ። ወጣቱ በአካባቢው የቆመ መኪና ለምኖ ዘራፊዎችን ተከተለ ። ፊትና ኋላ ተሯሯጡ ። የአሰፋ ፍጥነት አልተቻለም ። በአንድ አፍታ ከዓይን ተሰወረ።
የፖሊስ ምርመራ…
ሌሊቱን የክስ ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ ተበዳይንና ምስክሮችን አቅርቦ መረጃ ሰበሰበ ። ዝርፊያው በጦር መሳሪያ የታገዘ ከባድ ውንብድና ነው ። መርማሪው ዋና ሳጂን ኤፍሬም አስራት ባለሱቁን ጠየቀ ። አቶ መሐመድ ዘራፊዎቹ ጥሬ ሰላሳ ሺህ ብር፣ግምታቸው ሃያ ሺህ ብር የሆነ ባለመቶብር ካርዶችና አምስት የከረጢት ሩዝ በሽጉጥ አስፈራርተው መውሰዳቸውን ተናገሩ ።
መርማሪው ቃላቸውን በዶሴ አስፍሮ ተፈላጊዎችን አሰሰ ። ከቀናት በኋላ አሰፋ ከፖሊስ እጅ ገባ። ስለድርጊቱ ተጠየቀ ። አላደረኩትም ሲል ካደ ። ፖሊስ ድርጊቱን በማስረጃ አረጋግጦ ለዓቃቤ ህግ ክስ አሳለፈው።
ውሳኔ …
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም የተሰየመው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ካልተያዙ ግብረአበሮቹ ጋር በጦር መሳሪያ ታግዞ ዝርፊያ የፈጸመው ሾፌር ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል። ድርጊቱ ከባድ የውንብድና ወንጀል በመሆኑም እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአምስት አመት ጽኑ እስራት ይቀጣ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2013