ከወንጀል ምዝገባ እስከ ውሳኔ ያለውን ሂደት ግልጽ የሚያደርግ አሠራር ሊዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፡- ፍትህ ሚኒስቴር ከወንጀል ምዝገባ እስከ ውሳኔ ያለውን ሂደት በግልጽ ማወቅ የሚቻልበት የተቀናጀ የወንጀል የመረጃ ሥርዓት ሊዘረጋ መሆኑን አሳወቀ።

የፍትሕ ሚኒስቴርና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የተቀናጀ የወንጀል የመረጃ ሥርዓትን ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ትናንትና ተፈራርመዋል። የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ናቸው።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር)፤ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 የመንግሥት አሠራር ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት እንደሚደነግግ እንዲሁም፤ መንግሥት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ፍትህ ሚኒስቴርም የተሰጡትን ሃላፊነቶች ለመወጣት የወንጀል ምርመራ፣ ክርክር፣ ክስና ማስቀጣትን በተመለከተ ሰፋፊ ሃላፊነቶች እንዳሉበት አንስተዋል።

በተግባሮቹ ውስጥ ፌዴራል ፖሊስ፣ ፍትህ ሚኒስቴር ተቀናጅተው ከሚሠሯቸው ሥራዎች መካከል ዋነኛው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር መሆኑን ጠቁመዋል።

የወንጀል መዝገብ መረጃ ሥርዓት ወቅቱን የዋጀ፣ ዘመናዊ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂነትን ያሰፈነ፣ ቀልጣፋ ደህንነቱ የተረጋገጠ ሥርዓት ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ከኢንስቲትዩቱ ጋር ለአንድ ዓመት ያህል ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በተደረገው ስምምነት መሠረት ማስረጃን መሠረት በማድረግ በተለየ መልኩ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን) በመጠቀም እያንዳንዱን አገልግሎት ግልጽ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆን የሚያስችል ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል።

ከወንጀል ምዝገባ እስከ ውሳኔ ያለውን ሂደት በግልጽ ማወቅ የሚቻልበት ሥርዓት በመዘርጋት በፍትህ ሥርዓቱ ጉልህ ሚና የሚጫወት ተግባር ሊሆን የሚችል መሠረት መጣሉን ጠቁመዋል።

ስምምነቱ በተለይም የባለሙያ እንግልትን ከመቀነስ፣ የዐቃቤ ሕግና የፖሊስ የወንጀል ውስጥ ያለውን ሂደት በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ የሚያስችል መሆኑ ተናግረዋል።ስምምነቱ የወንጀል የመረጃ ሥርዓትን በማዘመን ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።

የአርተፊሽያል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሥርዓቱ ህብረተሰቡ ቤቱ ሆኖ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚረዳውና ከፍትህ አካላት ጋር በመገናኘት የፍትህ ሥርዓቱን ግልጽነት ለማስፈን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የሚከታተላቸው ጉዳዮች የት እንደደረደሱ የሚከታተልበት በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተደገፈ መሆኑንም አመላክተዋል።ደንበኞች በተለያዩ ቋንቋዎች በመጠቀም የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችላቸው መሆኑንም አመልክተዋል።

አሠራሩ ሲተገበር ሕዝቡ በፍርድ ቤት ላይ እምነት እንዲያሳድር በማድረግም የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።ከፌዴራል ፖሊስ እና ክክልል የፍትህ አካት ጋር የሰመረ ግንኙነት በመፍጠር መረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ቢሆንም ከተያዘው ጊዜ ባነሰና በተገባው የጥራት ውል መሠረት አጠናቅቆ ለማስረከብ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ 84 ሚሊዮ ብር የተያዘለት ሲሆን፤ ሥራውን አጠናቅቆ ለማስረከብ አንድ ዓመት እንደሚፈጅ ተጠቁሟል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም

Recommended For You