“ጥርስ የገባች አገር”፤
ኢትዮጵያ ከተገለጸችባቸው በርካታ አባባሎች መካከል ከላይ በንዑስ ርዕስ የተመለከተው “ብዙ ጥርሶች ውስጥ” እየገባች መውጣቷን የሚያመለክተው አባባል በግሌ ልዩ ትርጉም ስለሚሰጠኝ ቀልቤን ይስበዋል ። አገሬ የተወከለችበት ይህ ቅጽል የመጽሐፍ ርዕስ ነው ። መጽሐፉን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ የመለሱት የሕግ ባለሙያው ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እና መዝገቡ ምትኬ ቢልልኝ የተባሉ ሁለት የአገሪቱ ምሁራን ነበሩ ። ብዙ ሰዎች የመጀመሪያውን ስም ከደርጉ መራሔ መንግሥት ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር የሚያሳስቱት የሁለቱም ስም ከነአባት እና ማዕረጋቸው ጭምር ሞክሼ ስለሆነ እንጂ ከዚህ ያለፈ ቀረቤታ የላቸውም ።
ወደ ቋንቋችን በትርጉም የተመለሰው መጽሐፍ ርዕስ “Ethiopia at Bay” የሚል ሲሆን ደራሲው ደግሞ አሜሪካዊው ዶ/ር ጆን ስፔንሰር (John Hathaway Spenser) ናቸው ። እኒህ ደራሲ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረበት ዓመት በ1928 ዓ.ም ሲሆን አዲስ አበባ በጠላት እጅ ስትወድቅም የፋሽስቶችን አሰቃቂ ግፍ የተመለከቱ የዓይን ምስክር ነበሩ ።
እኒሁ ስመ ገናና አሜሪካዊ ደራሲ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (እ.ኤ.አ ከ1943 – 1974) ለረጅም ዓመታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤትን በአማካሪነት አገልግለዋል ። የሰውዬውን ፖለቲካዊ አቋም በተመለከተ አንዳንዶች የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰጡ ስማቸውን በክፉም ይሁን በደግ ደጋግመው ቢያነሱም እርሳቸው ግን “በኢትዮጵያ ፍቅር ወድቀው” አገሪቱን እንደ ቤታቸው እያገለገሉ መኖራቸውን ሲናገሩ የኖሩት በኩራት ነበር ። በአጸደ ሥጋ እስከተለዩበት ኦገስት 25 ቀን 2005 ድረስ በአገራችን ዙሪያ ገብ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በርካታ የታተሙና ያልታተሙ ጽሑፎችን አስነብበዋል ። የዚህ ጽሑፍ ዋና ትኩረት በመጽሐፉ ላይ ሂሳዊ ዳሰሳ ለማድረግ ሳይሆን “ጥርስ የገባች ሀገር” ስለሚለው የውሰት ርዕስ ዝርዝር ምንጩንና አመንጭዎችን ለማስተዋወቅ ስለሆነ በይዘቱ ላይ ጠልቄ ሳልገባ ወደ መነሻ ጉዳዬ አቀናለሁ ።
የተለያዩ ኃይላት በዘመናት ውስጥ ኢትዮጵያን “በመንጋጋ ጥርሳቸው ሊያላምጧት” ለምን ሲያደቡ እንደኖሩ የምናረጋግጠው ወደ ኋላ መለስ ብለን የታሪካችንን ዱካ ስንፈትሽ ነው ። ብዙ ወራሪዎች ዓይናቸው ደም ለብሶና ጠብመንጃቸው ባሩድ ጎርሶ አገራችንን ሊውጡ ሲያሰፈስፉ የኖሩትና ሙከራቸውም ሲከሽፍ የኖረው ጂኦ ፖለቲካዊ የስበት ማዕከል በመሆናችንና በተፈጥሮ የታደልናቸው ፀጋዎቻችን ስለሚያስጎመጃቸው ነበር/ነውም።
ባህር ተሻግረውና ውቅያኖስ አቋርጠው የደፈሩንም ሆነ “ክፉ ጎረቤት እንቅልፍ አያስተኛ” እንዲሉ የቅርብ የድንበር ተጋሪዎቻችን የሚጎነታትሉን ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ምክንያቶች እንጂ ሌላ ማመካኛ እንደሌላቸው ማረጋገጥ አይከብድም ። እንጂማ ኢትዮጵያ የትኛውን አገር ወራ በማንስ ላይ ፎክራ ታውቃለች ? ለሰላም ማስከበር ዘመቻ ካልሆነ በስተቀር ለወራሪነት የትኛውን ድንበር ተሻግራ የማንን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ሙከራ አድርጋለች ? ስለ ኢትዮጵያ ዘመን አይሽሬ ሰላማዊ ባህርያት የሃይማኖት ድርሳናትም ሆኑ የዓለም ታሪኮች ቢመሳከሩ እውነቱን ለመመስከር “ዓይን አፋር” አይሆኑም።
አገሬን በጥርሳቸው ሊያመነዥጉ ኃይላቸውን አሰልፈው፣ ትጥቅና ስንቃቸውን ሸክፈው የተዳፈሩን የውጭ ጠላቶቻችን የጀግኖቻችንን ጡጫ በማያዳግም ምት ቀምሰው በውርደት ሲመለሱ የኖሩት በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በጥቂት ዓመታት ውስጥ ምሳቸውን እያገኙ ከተደቆሱ በኋላ ነበር ። በአገራችን የቅርብ ዘመናት ታሪክ የፋሽስት ወራሪ ኃይል ከተሸነፈም በኋላ ቢሆን ለአምስት ዓመታት ያህል ጥላው እያስበረገገውና በአርበኞቻችን ብርቱ ክንድ ቁም ስቅሉን እያየ የሰነበተው አሸናፊ ስለሆነ ሳይሆን እየተደናበረ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት በመንፈራገጥ ነበር ። እንጂማ እስከ አድዋ ጦርነት ድረስ የአገራችን የጦር ሜዳ ውሎዎች የተጠናቀቁት ለሰዓታትና ለቀናት ያህል ብቻ አልነበር ።
ዛሬም የእናት ሀገር ጥሪ፤
ለአገራችን የብብት ውስጥ እባጭ ሆነው እረፍት ሲነሱን የኖሩት ከውጭ ጠላቶቻችን ይልቅ በእኛው መካከል የበቀሉት የእንግዴ ልጆች ናቸው ። በአድዋ ጦርነት ወቅት ለጠላት በመሰለል፣ ከአርባ ዓመታት በኋላም ለበቀል አሰፍስፎ ቅሌቱን ለማካካስ ዳግም ለተዳፈረን የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት በባንዳነት፣ በሱማሊያ ጦርነት ወቅትም ከጀርባ ሆኖ በአይዞህ ባይነትና በመረጃ አቅራቢነት ለጠላት አድረው አብረው ሲወጉን የኖሩት “የእኛ” የሚባሉት ጉዶች ናቸው ።
የሱማሊያ ወራሪ ኃይል በ1969 ዓ.ም ሙሉ አቅሙን አሟጦ በተዳፈረን ወቅት እና በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል “ገንጣይና አስገንጣይ” ይባሉ የነበሩት እኩይ ኃይላት አገሪቱን የውጥር ይዘው በቀሰፏት ወቅት ብብታችን ሥር ተወሽቀው እሳቱን ከውስጥ በማራገብና ለጠላት ወዶ ገብ በመሆን ሲፋለሙን የነበሩት ይህቺው እናት አገር ያበቀለቻቸውና ከእኛው ከራሳችን “አደይና አቦይ” የተወለዱት ህሊና ቢስ የአንድ ቡድን ጥርቅሞች ነበሩ ። አንዳንዶች በፖለቲካ ነፃ አውጭነት፣ አንዳንዶችም በበረሃ ሽፍትነት፣ የተቀሩት በከተማ ሸማቂነት ተሰልፈው እንደምን አገር ሲያምሱ እንደኖሩ ያልመሸበት አዳፋ ታሪካቸው ምስክር ነው ።
የውጭ ጠላቶችም ሆኑ የውስጥ ቅጥረኛ ሆድ አደሮች በአገሪቱ ህልውናና ሉዓላዊነት ላይ በዘመቱበት ወቅት ሁሉ የጀግናው ሠራዊታችን አጋርና ደጀን በመሆን ለክንዱ ብርታት ደጋፊ እየሆነ ከጎኑ በመሰለፍ ሲያበረታታው የኖረው “ለእናት ሀገሩ ጥሪ” ፈጣን ምላሽ በመስጠት ታሪኩ የደመቀው መላው ሕዝባችን ነው ። ይህ ታላቅ ሕዝብ ከውጭ ወራሪዎችም ጋር ሆነ ከውስጥ ከሃዲያን ጋር ሲፋለም የኖረው ልጆቹን መርቆ ግንባር ድረስ በመላክ ብቻም ሳይሆን የትጥቁም ሆነ የስንቁ ዋና ምንጭ በመሆን ጭምር ነበር ። የቀዳሚ ነገሥታቱም ጥሪ ቢሆን “ባለህ ትጥቅና ስንቅ ዝመት” የሚል አዋጅ እንጂ “ወኔህን አኮስትረህ ብቻ ተሰባሰብ” በሚል የግዳጅ ቅስቀሳ ጥሪ አልነበረም ።
የሩቆቹን ታሪኮቻችንን ለጊዜው አቆይተን የቅርብ ዘመኑን አንድ ታሪክ ብቻ መዘን ከዛሬው እውነታ ጋር እንመዝነው ። የዚያድ ባሬ ወራሪ ጦር የምሥራቁን የአገራችን ክፍል በእብሪት በወረረበት ወቅት በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠረው መደበኛና የሚሊሽያ ሠራዊት ስንቁ እንዳይጎድልበት ኃላፊነቱን ወስዶ ሲያገለግለው የነበረው በየቀበሌው የተደራጀው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደነበር ደማቅ ታሪኩ ምስክር ነው ። የምሥራቁ ግንባር በድል ተደምድሞ ሠራዊታችን ፊቱን ወደ ሰሜን በማዞር ከያኔው “የእናት ጡር ነካሽ” ከዛሬው “አገር ለማፍረስ” ካበደው የህወሓት በድን ጋር የሞት ሽረት ተጋድሎ ሲደረግም ደጀን በመሆን ያለምንም መሰልቸት የስንቅ አቅራቢነቱን ድርሻ ሲወጡ የነበሩት “የእናት ሀገር መደፈር” ያንገበገባቸው እናቶች፣ እህቶች፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶችና አረጋውያን ሳይቀሩ በነቂስ እየወጡ ተሳትፎ በማድረግ ነበር ።
ወራሪው የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ከአድዋ ሽንፈቱ በኋላ በአርባኛ ዓመቱ ነፍጡን ዳግም ወልውሎ በፋሽስታዊ ተልዕኮ አገሪቱን ለማፈራረስ ተደራጅቶ እንደመጣው ሁሉ “ያዳቆነ ሰይጣን…” እንዲሉ የህወሓት ቡድንም መሰል ፋሽታዊ ተግባር ለመፈጸም በአርባ ዓመት ዝግጅት ተደራጅቶ እነሆ በአገር ላይ ዘምቶ “ኢትዮጵያን ካልበታተንኩ” እያለ በማቅራራት ላይ ይገኛል ። ይህ ቡድን በምን ዓይነት ሥነ ልቦናና ስሪት እንደተፈጠረ ለጊዜው ግር ቢያሰኝም ዘመኑን በሙሉ ለአራት ዐሠርተ ዓመታት ያህል ለአገርና ለወጣበት ሕዝብ ሳይቀር ጠላት እንደሆነ የመኖሩ ምሥጢር ቀስ በቀስ ገሃድ እየወጣ ድብቅ ባህርይው ይፋ ከሆነ ውሎ አድሯል ።
ይሄው የጥፋት ቡድን አገርን በሚመራበት ወቅትም ሳይቀር የሕዝብ ጠላት ሆኖ ዛሬም ወደተፈጠረበት ሽፍትነት ተመልሶ በንጹሐን ደም እየተጨማለቀ ስለመኖሩ ሌላ መሰል የዓለም ታሪክ ለተነጻጻሪነት ይፈለግ ቢባል ተመሳሳይ ብጤ ለማግኘት ያዳግት ይመስለኛል ። በአርባ ዓመታት ውስጥ ሲሸርብና ሲያውጠነጥን የኖረውን “ሀገርን የማፈራረስ” ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲተጋ የነበረው ገና ከዘፍጥረቱ ጊዜ ጀምሮ እንደነበር በሚገባ ይታወቅ ነበር ። ለዚህም ነው ከፋሽስት ኢጣሊያ የአርባ ዓመት ዝግጅት ጋር ለማመሳሰል የተሞከረው ። በተልእኮውና በፋሽስታዊ ድርጊቱስ ቢሆን ምን ልዩነት አለው ።
ለአገር ሉዓላዊነት የክብር ዘብ የቆመን ሠራዊት ማዋረድ፣ ሰላማዊ ሕዝብን ያለርህራሄ መጨፍጨፍ፣ የመሠረተ ልማቶችን ማውደም፣ በሰላማዊ የጎረቤት አገራት ላይ “በጠብ ያለሽ በዳቦ” ምክንያት አልባ ሰበብ ትንኮሳ ማካሄድ፣ በራስ ሕዝብ ላይ ወረራ መፈጸም ሳያንስ የተፈጠሩበት ማሕበረሰብ የምግብ እርዳታ እንኳን እንዳይደርሰው ለረሃብ እየዳረጉ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ መጠቀም፣ በደምና በአጥንት መሠረቱ የጸናን ሉዓላዊ አገር “በአንድ ጀንበር አፈራርሳለሁ” እያሉ መቃዠት ከፋሽስቶችና ከናዚዎች ታሪክ በምን ይለያል ። ይብስ ካልሆነ በስተቀር ልዩነት የለውም ።
የዚህ እኩይ ቡድን ትርፍራፊ ኃይል በጎረቤት ክልሎች ላይ የከፈተውን ወረራና ትንኮሳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማምከን ዳግም ከአርባ ዓመት በኋላ የእናት አገር ጥሪ የደረሰው ሕዝባችን ያለ ማንም ቅስቀሳ ደማቅ ታሪኩን እየደገመ ያለው ለወረት ሳይሆን ባህሉ ስለሆነ ነው ። ህወሓት የውስጥ ጠላትነቱን እያጠናከረ ያለው ከውጭ ኃይላት ጋር በማበር ጭምር እንደሆነ የጥፋት ተግባሩ እየተገለጠ ነው ። ከላይ በራሱ መንጋጋ፣ ከሥር “አለሁልህ” እያሉ ለአመጽ ድርጊቱ ድጋፍ በሚሰጡት መልከ ብዙ ያገጠጡ ጥርሶች ውስጥ አገሪቱን አስገብቶ ለማኘክና ለማሳኘክ መሞከሩ የጅልነት እብደት ካልሆነ በስተቀር ሙከራው ዞሮ የሚያከስመው ራሱንና “ቅጥረኛ” ደጋፊዎቹን ብቻ ነው ።
ለእናት አገሩ ጥሪ ጆሮውንም ነፍሱንም ለመስጠት የማይሳሳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም እንደ ትናንቱ ልጆቹን ለፍልሚያ ሆ እያሰኘ መሸኘት ብቻ ሳይሆን ስንቁን አዘጋጅቶለትና በግዳጅ ቀጣናው ድረስ እያደረሰ “የእኔ ጀግና እነሆ ከጎንህ ነኝ!” የሚለው የወረት ቅስቀሳ ወኔውን አሙቆት፣ በፕሮፖጋንዳ ዘመቻም ጊዜያዊ ቀልቡ ተሰልቦ ሳይሆን የፀና ኢትዮጵያዊ ባህሉና ታሪኩ ስለሆነ ነው ። እናቶችና እህቶች እንደለመዱት በነቂስ ወጥተው ስንቁን ለመሰነቅ የሚሽቀዳደሙት፣ ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የሚሊሽያ የልዩ ኃይላት በየአካባቢው ሲደርሱ ሕዝቡ በሆታና በዕልልታ እየተቀበለ የሚያስተናግዳቸው ባህሉና ታሪኩ ስለሆነና የማታ ማታ ድሉ የጀግኖች ልጆቹ እንደሚሆን ሙሉ እምነት ስላለው ነው ። በአንጻሩ ይህ ጨካኝ አረመኔ ቡድን እንኳን ሕዝቡን ሊታደግ ቀርቶ ከዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ የተላከው የነፍስ አድን እህል እንዳይደርስ መንገድ መዝጋቱና ጭነቶቹን በአረር ማጋየቱ የጭካኔው ጫፍና መገለጫ ነው።
ይህ አሸባሪ የትህነግ ትርፍራፊ እየተላተመ ያለው ከመቶ ሚሊዮን ከሚልቅ “አትንኩኝ ባይ” ሕዝብ ጋር መሆኑን ምነው የሚመክረው አጣ? መከላከያ ሠራዊታችንም ለእናት አገሩ ጥሪ ቀርቶ የተጠቁ ወዳጅ አገራትን ሰላም ለማስጠበቅ እንኳን ወደኋላ የማያፈገፍግ ጀግና መሆኑስ ልባቸው የደነደነው ከሃዲያን እንዴት ሊገነዘቡ አልቻሉም? ዛሬም በዳግም የእናት አገር ጥሪ ምላሽ እየሰጠ ያለው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተላልፈው መልእክት ለአሸባሪው ቡድን በግልጽ እየደረሰው ቢሆንም በረሃብና በጦርነት እየተቀጣ ያለው የትግራይ ሕዝብ በራሱ አንደበት በቃችሁ ብሎ ሊተፋቸው ግድ ነው ። ይሄው ነው ። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2013