የኢትዮጵያ መለያ የሆነውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ለብሰው በቅጡ ጨለማው ተገፎ ከተማው ላይ በሰፊው ብርሃን ከመፈንጠቁ በፊት ለመከላከያ ሠራዊት የድጋፍ ሰልፍ ከየቤታቸው የወጡት አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን መስቀል አደባባይ የደረሱት በእጃቸው መፈክር ይዘው በሆታ ድምፃቸውን በማሰማት ነበር ።
ያለምንም ቀስቃሽ ኢትዮጵያዊነት አሸንፎት የወጣው ሕዝብ ዋነኞቹ ዓላማዎቹ ሶስት ነበሩ ። የመጀመሪያዊ አሸባሪው ህወሓት ህጻናትንና አረጋውያን እያስገደደ ለጦርነት ማሰለፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዲቆጡና በመስቀል አደባባይም ተገኝተው ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ አስገድዷቸዋል ። ሁለተኛው የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነትም ኢትዮጵያውያንን አንገብግቧቸዋል። ሶስተኛው ደግሞ የአገርና የወገን መከታ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊትን መደገፍና አለኝታነትን መግለጽ የድጋፍ ሰልፈኞቹ ትኩረት ያደረጉበት ጉዳይ ነው ።
ድጋፋቸውን የገለፁት ወጣት ሴቶች እና ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ አቅመ ደካማ እናቶች እና አባቶችም ለመከላከያ አጋር መሆናቸውን ለማሳየት እልህ እያንገበገባቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ ተደምጠዋል ። ወጣቶች ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፈው የሕይወት መስዋዕትነት እስከ መክፈል የሚደርስ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ሲገልፁ፤ እናቶች እና አባቶች ደግሞ የስንቅና ትጥቅ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በጸሎት ለማገዝ እና የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ሲናገሩ በፍጹም ኢትዮጵያዊነት ስሜት ነው ።
ሁለት እጃቸውን ከፍ አድርገው ከስር የመከላከያ ሠራዊትን ፎቶን የሚያሳይ ከላይ ‹‹ኢትዮጵያ በጀግኖቿ አፍራ አታውቅም፤›› የሚል መፈክርን የያዙት አዛውንት፤ እንኳን በቅጡ መሳሪያ ለሌለው በኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያን እየወጋ ላለው የህወሓት አጥፊ ቡድን ቀርቶ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ እና ጀግኖች ኢትዮጵያውያን እስከ አፍንጫው ለታጠቀም የውጪ ወራሪ ኃይል እንደማይንበረከኩ የሚያመላክት ነው። አዎ! በእርግጥም ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ተንበርክከው አያውቁም። ይህንን በጣሊያን ጦርነት ብቻ ሳይሆን ጥንት ተካሂደዋል በተባሉ ከግብፆችም ሆነ ከጣሊያን ጋር በተካሄዱ ጦርነቶች ኢትዮጵያ በጀግኖቿ አፍራ እና ተሸንፋ አታውቅም ።
ሶስት ወጣቶች ከፊት ለፊት ‹‹ ትናንትናም ዛሬም ኢትዮጵያውያንን ማንበርከክ አልተቻለም፤ አይቻልም።›› የሚል ትልቅ መፈክር በቀኝ እጆቻቸው በመያዝ፤ ግራ እጆቻቸውን ጨብጠው ድጋፋቸውን በመጮህ ሲገልፁ ነበር ። በእርግጥም በውጪ ጠላቶች ለዘመናት ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ተሰርቷል ። ከግልፅ ጦርነት ባሻገር በሴራም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ተሞክሯል ። ነገር ግን አልሆነም። ኢትዮጵያውያንን ማንበርከክ አልተቻለም አሁንም አይቻልም።
ኢትዮጵያውያንን ማንበርከክ የማይቻልበትን ምክንያት ደግሞ በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙ አንድ አዛውንት በሁለት እጃቸው ‹‹ ኢትዮጵያውያን መተባበራችን፤ የአሸናፊነታችን ሚስጥር ነው ።›› በማለት ከፍ አድርገው አሳይተዋል ። በተጨማሪ ‹‹ የአሸናፊነታችን ምስጢር እውነት እና ፍትሕ ነው።›› የሚል መፈክርን የያዙ ጎልማሶችም፤ አሸናፊነት ከእውነት እና ከፍትሕ ጋር እንጂ ከሐሰት እና ከበዳይነት ጋር እንደማይሆን በማመላከት በመስቀል አደባባይ መፈክሩን ከማሳየት ባሻገር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ ቆይተዋል ።
እውነት እና ፍትሕ ይዞ የቆመ ኃይል በእርግጥም አሸናፊነቱ አያጠያይቅም ። የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ምስጢር በእርግጥም እውነትና ፍትሕ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፤ አሸናፊነቱ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ እና በዓለም ምሳሌ ሆኖ ሊቀጥል የሚችል ነው።
‹‹በትብብራችን ፊት የሚቆም ኃይል የለም›› የሚል ትልቅ መፈክር ይዘው በጋራ ሲጓዙ የነበሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ደጋፊዎችም ኢትዮጵያዊነት መለያችን ትብብራችን መሆኑ የገለፁበት ሲሆን፤ ይህ ትብብር እስከመቼም እንደሚኖር ያመለከቱት ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያውያንን መነጣጠል አይቻልም›› በማለት መፈክሩን አጉልተው ሲያሳዩ የነበሩት እናት ናቸው ። በሴራ ብዙ አገራት ተበታትነዋል፤ ፈራርሰዋል። እንዳልነበር ሆነው መንግሥት እና አገር አልባ ሆነው ታይተዋል ። ኢትዮጵያውያን ግን ተባባሪዎች ከመሆናቸው ባሻገር ሊነጣጠሉ የማይችሉ እንደሰርገኛ ጤፍ የተደባለቁ ናቸው እና ማንም ሊለያቸው እና ሊበታትናቸው እንደማይችል ከመግለፅ ባሻገር፤ ያሉበትንም ችግር በመተባበር ማለፍ እንደሚችሉ የሚያሳዩም በርካታ መልዕክቶች በጉልህ ታይተዋል ።
ወታደር የቆመው ለመላው ኢትዮጵያውያን ነው። ከስር የኢትዮጵያን ባንዲራ የያዙ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ፎቶ የሚያሳይ ከላይ ‹‹መከላከያ ለሕዝቦች ደህንነት የቆመ ታማኝ ሰራዊት ነው›› በማለት መከላከያ ዓላማው ኢትዮጵያን ማዳን ብቻ መሆኑን ያመላከቱ ቀልብ ሳቢ መልዕክቶች ታይተዋል ።‹‹ የምንዋጋው ጦርነት የህልውና እና አገር የማዳን ዘመቻ ነው›› የሚል እንዲሁም ‹‹በኢትዮጵያ ልጆች ትግል አሸባሪው ከምድረ ገፅ ይጠፋል›› የሚሉ መፈክሮችም የብዙዎችን ቀልብ ስበዋል ። እነዚህ መፈክሮች መልዕክታቸው ግጭቱ በመንግሥት በኩል ተፈልጎ የተገባበት ሳይሆን በአስገዳጅ ምክንያት የተካሄደ መሆኑን በመጨረሻም አሸባሪው ከምድረ ገፅ መጥፋት እንዳለበት የሚያመላክቱ ናቸው ።
አሸባሪው ቡድን ብቻውን አለመሆኑን ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተባብሮ እየሰራ እንደሚገኝ ለማመልከት ‹‹እርዳታ እየለመነ ኢትዮጵያን የሚወጋ ጠላት ወያኔ ብቻ ነው›› የሚል መፈክርም የሰልፉ ተሳታፊ ወጣቶች ይዘው ታይተዋል ። ‹‹ጁንታው የኢትዮጵያ ነቀርሳ ነው።››፤ ‹‹በአሸባሪው ጁንታ ስንደማ አንኖርም››፤ ‹‹ህወሓት የኢትዮጵያ ካንሰር ነው›› ፤ ‹‹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ መመኘት እንጂ መተግበር አይሞከርም›› የሚሉ እና ‹‹ የአሸባሪው ቀቢፀ ተስፋ ቅዠት በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ይመክናል›› የሚሉ መፈክሮችም በድጋፍ ሰልፉ ላይ ተስተውለዋል ። እነዚህ መፈክሮች መነሻቸው የህወሓት አጥፊ ቡድን ዓላማ ኢትዮጵያን ማፈራረስ መሆኑን፤ በሽታ በመሆኑ ተነቅሎ ካልተጣለ አደገኛነቱን የሚያመላክቱ ናቸው ።
የኢትዮጵያን ካርታ እና የሰላም እርግብ ላይ ሰንደቅ ዓላማ በማከል ‹‹ኢትዮጵያ አሸንፋለች ሰላሟን ትጠብቃለች›› በማለት የኢትዮጵያ አሸናፊነት እየተረጋገጠ መሆኑን ለማመልከት ከተያዘው መፈክር በተጨማሪ ፤ ‹‹የብልፅግና ጉዟችንን ለማረጋገጥ ሰላማችንን እናስጠብቃለን›› በማለት የኢትዮጵያ ቀጣይ ጉዞ ዕድገት እና ብልፅግና እንጂ ጦርነት፣ ዕልቂት እና ስደት እንደማይሆንም በመፈክሮች በተለያየ መልኩ ተንጸባርቀዋል ። ያለፉት ጊዜያት ለኢትዮጵያ ፈታኝ ወቅቶች እንደነበሩ ቢታወሱም፤ በዚህ ሁሉ ፈታኝ ጊዜ ውስጥ ምርጫ ተከናውኗል፤ ግድቡም ተሞልቷል፤ ችግኙም ተተክሏል በማለት፤ ‹‹ መርጠናል፤ ተክለናል፤ ሞልተናል›› የሚሉ መፈክሮች መስቀል አደባባይ አድምቀውት ውለዋል።
በእርግጥም ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስቸጋሪ ወቅት ላይ ብትሆንም በብዙ መልኩ አሸንፋለች ። እውነት ነው ኢትዮጵያ መርጣለች ። እውነት ነው ግድቡን ሞልታለች ፤ እውነት ነው ችግኝም ተክላለች። በተመሳሳይ መልኩ ጊዜዋን ጠብቃ እነዚሁኑ ሁነቶች ደጋግማ ትፈፅማለች ። በሰሜኑ ያለው ግጭትም ለሕዝብ በቆመው የመከላከያ ሠራዊት አሸናፊነት አሸባሪውን ከምድረ ገፅ በማጥፋት ይጠናቀቃል ። የኢትዮጵያ ትንሳኤ ተረጋግጦ ለአፍሪካውያን ለቅኝ ተገዢዎች የነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ በዕድገት እና በብልፅግናዋ፤ በሰላም እና በዴሞክራሲዋ በተዘዋዋሪም ቢሆን በኢኮኖሚ በቅኝ የማትገዛ በመሆኗ እንደምሳሌ የምትጠቀስበት ጊዜ ብዙ ሩቅ አይሆንም ። እነዚህ ሁሉ እውነቶችና ተስፋዎች ሰሞኑን በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ መስቀል አደባባይን ያደመቁ መልዕክቶች ነበሩ።
የፌኔት እናት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2013