ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ዓመት በፊት የባንኮችና ኢንሹራንሶች ባለቤትነት መቶ በመቶ በኢትዮጵያውያን መያዝ እንዳለበት የሚገልጽውን አዋጅ በመጥቀስ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ዜግነት በነበራቸው ጊዜ አክሲዮን የገዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለአክሲዮኖች ላይ አክሲዮኖቻቸው እንዳይንቀሳቀሱና በአክሲዮኖቻቸው ያገኙት ትርፍ እንዳይሸጥ ክልከላ ወጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ባንኩ ትላንት በዋና መስሪያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንሱ ዘርፍ እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥናቶች ማጥናቱንና በሚመለከታቸው አካላት ውይይት ተደርጎበት ሲጸድቅ ስራ ላይ እንደሚውል አስታውቋል፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በፋይናንሱ ዘርፍ የሚያደርጉት ተሳትፎ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ስለሚኖረው አንደምታ የምጣኔ ሀብት ምሁራንን አናግሮ ተከታዩን አጥናክሯል፡፡
ዶክተር ደመላሽ ሀብቴ በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ከፍተኛ ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በፋይናንሱ ዘርፍ መሳተፋቸው በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ስለሚፈጥረው ተጽዕኖ ሲያብራሩ “በሀገራችን ለልማት የሚውል ገንዘብ የሚገኘው ከ60 በመቶ በላይ ከግብር ነው፡፡ የተቀረው ደግሞ ከብድር ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግሉ ዘርፍ በማዘዋወር ፣ ከውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፣ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚላክ ገንዘብ (ረሚታንስ) ፣ ከእርዳታ እና ከፖርትፎሊዮ ኢንቨስትመንት ነው፡፡
የፖርትፎሊዮ ኢንቨስትመንት ማለት ቀደም ብለው በተቋቋሙ ድርጅቶች ውስጥ አክስዮን በመግዛት ከፊል ባለቤት መሆን አሊያም መንግስትም ይሁን የግል ሴክተሩ ቦንድ በማውጣት ለሽያጭ ሲያቀርብ በመግዛት የሚደረግ የኢንቨስትመንት አይነት ነው፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንሱ ዘርፍ የሚያደርጉት ተሳትፎ የፖርትፎሊዮ አንቨስትመንት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የፋይናንስ ሴክተሩ ያዋጣናል ብንከስርም እንክሰር ካተረፍንም ጥሩ እናትርፍ ብለው ከመጡ መግታት አያስፈልግም፡፡ ከሃያ ዓመታት በኋላ እንዲቋረጥ መደረጉም ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሆን ተብሎ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎውን እንዳያሳድግ የተወሰደ እርምጃ ነው፡፡ በአሁኑ ዘመን ወደፊት ከቀደሙት ጋር ለመስተካከል በጣም መስራት ይገባል፡፡
እነዚህ ሰዎች ገንዘብ ከውጪ አምጥተው አክስዮን በመግዛት ቀደም ብለው በተቋቋሙ ድርጅቶች ውስጥ ባለቤት ሲሆኑ ትርፍ ለማግኘት ኃላፊነቱን ራሳቸው ወስደው ነው፡፡ ይሄ በጣም ጥሩ መንገድ ነው፡፡ አንደኛ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ስለሚያመጣ መንግስትን ብድር ውስጥ ከመግባትና ዕዳ ከመክፈል ያድነዋል፡፡ ድርጅቱ የሚያተርፍ ከሆነ ገንዘብ ይሰበስባል፤ ድርጅቱ እየሰፋ ሲሄድ ተጨማሪ የሰው ኃይል ይቀጥራል፡፡
አፍሪካ ውስጥ እአአ በ 2017/18 በጣም ዝቅተኛ ሆኖ የታየው ይህ ሼርና ቦንድ የመግዛት የፖርትፎሊዮ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በጣም አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ነው የቀነሰው ፡፡ ምክንያቱም ግለሰቦች ስለሆኑ አብዛኞቹ ኃላፊነት መውሰድ አይፈልጉም፡፡ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ወጥ በሆነ መልኩ ባልተረጋጉበት እና የተተበተበው ቢሮክራሲ ባለበት ገብቶ ለመስራት አይደፋፈሩም፡፡ አንደኛው ለልማት የሚውል ገንዘብ ምንጭ ይህ የፖርቶፎሊዮ ኢንቨስትመንት ስለሆነ በዘርፉ ለመግባት ፍላጎቶች ካሉ መንግስት ማበረታታት አለበት ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ደመላሽ ገለፃ የፋይናንስ ዘርፉ በሚፈለገው መጠን ለሀገሪቱ እድገት አስተዋጽኦ እያደረገ አይደለም፡፡ በ2018 የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት እድገት ስንመለከት 10 ነጥብ 9 በመቶ ነው፡፡ ከዚህ 10 ነጥብ 9 በመቶ እድገት 4 ነጥብ 4ቱ የኢንዱስትሪያል ሴክተሩ አስተዋጽኦ ነው፡፡ በዋነኝነት ይህ ውጤት የተመዘገበው በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሳይሆን በግንባታ ኢንዱስትሪው ነው ፡፡ ተከታዩ እንደ ትራንስፖርት ፣ ንግድ እና ባንክ ያሉትን ያቀፈው የአገልግሎት ዘርፉ ሲሆን 4 በመቶ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ 2 ነጥብ አምስት በመቶ አስተዋጽኦ በማድረግ በሶስተኛ ደረጃ የሚገኘው ግብርና ነው፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ሴክተሩ አሁንም ቢሆን በጣም ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ በጣም ከፍተኛ ትርፍ እያስገኘ ያለው የአገልግሎት ዘርፉ አይደለም፡፡
በፋይናንስ ሴክተሩ ላይ ተጥሎ የነበረውን ይህን እገዳ ለማንሳት መታሰቡ ወደሰፊው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመቅረብ አንድ እርምጃ ነው፡፡ እርምጃው ትክክለኛ ነው፡፡ የሀገሪቱን የቁጠባ ደካማ አቅም ከፍ እንዲልና ለኢንቨስትመንት የሚውል ተጨማሪ ገንዘብ እንዲመጣ ያደርጋል፡፡ ይህ ለኢንቨስትመንት ሊውል የሚችል ገንዘብ በመምጣቱ የሚደርስ ምንም አይነት ችግር የለም፡፡
ጉዳት የሚኖረው ተጨማሪ ገንዘቡ ለማግኘት ሼር የሚሰጠው ድርጅት ይህን ገንዘብ ተጠቅሞ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ካልሰራ ነው፡፡ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የማጭበርበር የመኒ ላውንደሪ ያሉ ስጋቶችን ለመቅረፍ የመንግስት ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡ አሜሪካን የገጠማት ችግር እኛም ሀገር እንዳይከሰት መንግስት አይኑን ከፋይናንስ ሴክተሩ ላይ ማንሳት የለበትም፡፡ ህንድና ቻይና እንዲ ያለውን ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ በእነዚህ ሀገራት አልተከሰተም፡፡
የፋይናንስ ዘርፉ ኢትዮጵያ ለምታስመዘግበው ዕድገት አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ አልዳበረም፡፡ ስለዚህ ይህንን ሴክተር ማነቃቃት ነው የሚያስፈልገን፡፡ ከዛ ውጭ ትርፉን ወደሌላ የመውሰድ እና ለሌላ የመሸጥ ጉዳይ ከንብረት ጋር የተያያዙ መብቶች ናቸው፡፡ ይህን መብት መንግስታት ማክበር እንጂ መጣስ የለባቸውም፡፡ ኢንቨስትመንት ሁልጊዜም የሚመጣው ለጽድቅ ሳይሆን ትርፍ ለማግኘት ነው፡፡
የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ እየጨመረ ሲሄድ የውጭ ምንዛሬ ክምችታችንም ስለሚያድግ ትርፋቸውን በውጭ ምንዛሬ ለመስጠት አንቸገርም፡፡ ሌላው ዓለም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው እነዚህን መብቶች በማክበር ነው፡፡ በራችንን ይበልጥ ክፍት እያደረግን መሄድ ነው የሚገባን፡፡ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ እርምጃ መውሰድ ሳይሆን ቀስ በቀስ ወደ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚው መሄድና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ለሌሎች የውጭ ሀገር ዜጎች በሩ ክፍት መሆን አለበት፡፡
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምርምር ኢንስቲትዩት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተመራማሪና የንግድና ኢንዱስትሪ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ አሚን አብደላ በበኩላቸው እገዳው ሲጣል ወደኋላ ተመልሶ እንዲሰራ መደረግ አልነበረበትም ነበር፡፡ አስፈላጊ ነው ተብሎ ቢታመን እንኳን ከዚህ በኋላ በሚል ነበር መውጣት የነበረበት፡፡ ‹‹ትውልደ ኢትዮጵያዊ ማለት የውጭ ሀገር ዜጋ ነው፡፡ አሁን ባለው ሕግ መሰረት ደግሞ የውጭ ሀገር ዜጋ ባንክ ማቋቋም አይችልም፡፡ ነገር ግን አዲስ የውጭ ሀገር ባንክ ማቋቋምና የነበረ ባንክ ሼር መግዛት የተለያዩ ነገሮች ናቸው” ይላሉ፡፡
እንደ ኢኮኖሚ ተመራማሪው ገለጻ ሙሉ ለሙሉ ከሚታገድ እገዳዎችን በተለያየ መንገድ መጣል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ያደረገ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ትርፉን መውሰድ ሲፈልግ ከዚህን ያህል መቶኛ በላይ በብር እንዲወስድ የሚል ህግ ማኖር ይቻላል፡፡ በዶላር የሚጠይቅ ከሆነ የተወሰነ መጠን ዶላር መጣ እንጂ መልሶ ዶላር እየወጣ ነው ማለት ነው፡፡ በእያንዳንዱ ባንክ ደግሞ የትውልደ ኢትዮጵያዊ ሼር ከሆነ 10 ፐርሰንት በላይ እንዳያልፍ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህም ባንኮቹ በውጭ ሀገር ዜጎች ተጽዕኖ ስር እንዳይወድቁ ማድረግ ይቻላል፡፡
አቶ አሚን “ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በፋይናንሱ ዘርፍ የሚያደርጉት ተሳትፎ ጠቀሜታ አለው ጉዳትም ሊኖረው ይችላል፡፡ የውጭ ሀገር ዜጎች በመሆናቸው ዜግነት ያገኙበት ሀገር እነርሱ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ ለእነሱ ዜግነት የሰጠቻቸው ሀገር ከኢትዮጵያ ጋር ችግር ውስጥ ብትገባ ሊመጣ የሚችል ነገር ይኖራል፡፡ ይህ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊከሰት የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ኢንቨስት ያደረጉትን መልሰው በዶላር ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ ፋይናንስ የተለየ ትኩረት ስለሚደረግበት እንጂ በሌለው ሴክተር ላይም ብንመለከት ተመሳሳይ ነው፡፡
ለምሳሌ ሲሚንቶ የሚያመርት የውጭ ሀገር ፋብሪካ ምርቱን ወደ ውጭ ሀገር ሳይልክ ሀገር ውስጥ በኢትዮጵያ ብር ነግዶ ያተረፈውን ትርፍ ብሄራዊ ባንክ ወደ ዶላር ቀይሮ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ድርጅቱ ሲቆም ደግሞ እንዳለ ድርጅቱን ሽጦ ያገኘውን ብር ለብሔራዊ ባንክ አቅርቦ በዶላር ይቀየርለታል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ዶላርን አምጣ ነው የምታገኘው፡፡
ስለዚህ እንደዚህ አይነት ድርጅቶች ቢበዙና ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ አምስቱ በሶስት ዓመት ውስጥ ከኢትዮጵያ መውጣት ቢፈልጉ ዶላር ከየት መጥቶ ይከፈላቸዋል? ይህ ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የሚከትና ታማኝ እንዳትሆን የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ይህ በፋይናንስ ዘርፉ ላይም ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው፡፡ ጥቅምና ጉዳቱ ምንድን ነው የትኛው ያመዝናል በአጭር ጊዜ ምን ሊያመጣ ይችላል ስለዚህ ምን ማድረግ አለብን ፡፡ ለረጅም ጊዜ በራችንን መክፈታችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎን ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ስንከፍት በጥናትና በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ የተመሰረተና በኋላ ችግር ውስጥ የማይከተን መሆን አለበት፡፡
የገባው ዶላር የትና ምን ላይ ነው የሚውለው የሚል ነው መሰረታዊው ጥያቄ በሀገር ውስጥ ብቻ የሚገደብ ቦታ ላይ ውሎ ከሆነ ዶላር ማምጣት የማይችል ዶላር ስለሆነ ከየት መጥቶ ነው የሚከፈለው ተብሎ መታሰብ መቻል አለበት፡፡ ዝም ብለን መዝጋት ሳይሆን እያየን እያጠናን በአጭር ጊዜ ይሄ ሊኖር ይችላል፤ በመካከለኛ ጊዜ ይሄን ያህል አወንታዊና አሉታዊ ነገር ይኖረዋል በአጠቃላይ አወንታዊው ነገር ያመዝናል፤ ስለዚህ ‹‹ይህን እንፍቀድ ያንን ደግሞ እናቆይ›› እየተባለ እየተጠና ነው እንጂ ለመጣው ሁሉ ፍቃድ እየሰጡ ግባ ማለት ውሎ አድሮ ችግር ያስከትላል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
የትናየት ፈሩ