ከአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥራዎች መካከል የተቀናጁ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማልማት፣ ማስተዳደርና ለአልሚ ባለሃብቶች ማስተላለፍ ነው:: የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ በዋናነት በእሴት ጭመራ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሲሆን፤ ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና የግብርና ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ ማስቻል፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ የሚያግዝ ነው::
በአገሪቱ ከሚገኙ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ወደ ሥራ የገባው ዲላ መካከለኛ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ ሲሆን፤ ፓርኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመረተውን ድፍድፍ የአቮካዶ ዘይት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችሏል:: የደቡብ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ በተለይ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ የዲላ መካከለኛ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ድፍድፍ የአቮካዶ ዘይት ኤክስፖርት ማድረግ መቻሉን ይፋ አድርገዋል::
ፓርኩ በቅርቡ 22 ቶን የሚጠጋ ድፍድፍ የአቮካዶ ዘይት ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን የገለጹት አቶ ጥላሁን፤ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የአቦካዶ ድፍድፍ ዘይት እያመረተ ያለውም ‹‹ሲይዝ አግሮ ኢንዱስትሪ›› የተባለ አገር በቀል ድርጅት እንደሆነ ተናግረዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ ‹‹ሲይዝ አግሮ ኢንዱስትሪ ማህበር በአንድ ፈረቃ 22 ቶን የሚጠጋ ድፍድፍ የአቦካዶ ዘይት አምርቶ ወደ ጣሊያን አገር በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ጀምሯል:: ድፍድፍ የአቮካዶ ዘይቱ ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ሲሆን፤ አሁን ወደ ጣሊያን የተላከው ለኮስሞቲክስ ግብዓት የሚውል ነው::
የአቮካዶ ድፍድፍ ዘይቱ ተጣርቶ ለተለያዩ የኮስሞቲክስ አገልግሎቶችና ለሌሎች ምርቶችም በግብዓትነት እንዲያገለግል ይደረጋል:: በዲላ አካባቢ አቮካዶ በስፋት የሚመረት እንደመሆኑ ይህን መሰረት በማድረግ ወደ ምርት የገባው ኢትዮጵያዊው ባለሃብት፣ ወደ ማምረቱ የገባውም ባለፈው ዓመት ነው:: በጌዲዮ ዞን ዲላ አካባቢ በዓመት ሁለት ጊዜ የአቮካዶ ምርት የሚሰበስብ በመሆኑ ድርጅቱ የደረሰውን የአቮካዶ ምርት በመጠቀም በአሁኑ ወቅት 22 ቶን ድፍድፍ የአቮካዶ ዘይት አምርቶ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምሯል:: ድርጅቱ በሶስት ፈረቃ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ አሁን በአንድ ፈረቃ ብቻ በማምረት ምርቱን ወደ ጣሊያን ልኳል::
ምርቱን ወደ ሌሎች አገራት ለመላክ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወደ አሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች ገበያ ለመግባትም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል:: ምርቱ ኦርጋኒክ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ከኮስሞቲክስ አገልግሎት ባለፈ ለምግብነት እንዲውል የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል:: አገልግሎቱን የገበያ መዳረሻውን ለማስፋት የክልሉ መንግሥት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል:: አሁን የአቮካዶ ድፍድፍ ዘይቱን በአንድ ፈረቃ ብቻ እያመረተ ያለው ይህ ድርጅት 60 ለሚደርሱ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ጠቅሰዋል::
በቀጣይ በሶስት ፈረቃ ማምረት ሲጀምር ደግሞ 160 ለሚደርሱ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል ሲሉም አስታውቀው፣ ድርጅቱ በቀጥታ ከፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ ሶስት ሺ ከሚደርሱ አቮካዶ አምራች የአካባቢው አርሶ አደሮች ትስስር በመፍጠር የአቦካዶ ምርት በወቅቱ እየተረከባቸው መሆኑን ገልጸዋል:: ከ17 እስከ 20 የሚደርሱ የሕብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖችም ከድርጅቱ ጋር የገበያ ትስስር መፍጠራቸውን ተናግረዋል:: በዚህም በጌዲኦ ዞንና እና በሲዳማ ክልል የሚገኙ አቡካዶ አምራች ዩኒየኖች በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር መሰረት የአቮካዶ ምርት ለኢንዱስትሪው እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል:: በዚህም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሰፊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውቀዋል:: አቶ ጥላሁን እንዳብራሩት፤ በጌዲኦ ዞን የአቮካዶ ምርት በበቂ ሁኔታ አለ:: በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ወላይታ ዞን ላይም አቮካዶ በስፋት ይመረታል::
አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከሚገኝበት ዲላ ከተማ ከ100 እስከ 150 ኪሎ ሜትር ባለ ርቀት የሚገኝ ሲሆን፣ የአቮካዶ ምርቱን የትራንስፖርት ችግር የሌለ በመሆኑ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል:: በአሁኑ ወቅት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዲዮ ዞን አካባቢ እንዲሁም ሲዳማ ክልል ላይ የተወሰነ የአቮካዶ ምርት እየገባ ይገኛል:: በቀጣይም ድርጅቱ የማምረት አቅሙን እያሳደገ ሲሄድ በደቡብ ኢትዮጵያ ወላይታና አቮካዶ በከፍተኛ መጠን በሚመረትበት ጌዲዮ ዞን ያለውን ሰፊ የአቮካዶ ምርት በመቀበል የአቮካዶ ድፍድፍ ዘይት በከፍተኛ መጠን ማምረት ይቻላል:: በዚህም ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጠራል፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ይደረጋል፤ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለአገሪቷ በማስገኘት በኩልም ትልቅ አበርክቶ ያደርጋል:: በተለይም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና አቦካዶን በተለየ መንገድ ለማልማት ያግዛል::
ጥሩ የዘይት አቅም ያላቸውን የአቮካዶ ዝርያዎችን ችግኝ በማፍላት ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ትልቅ ሥራ እየተሰራ ሲሆን፤ አርሶ አደሩን ጨምሮ የአካባቢው ሕብረት ሥራ ማህበራት የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ነው:: በተለይም ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዲቻልና ተጨማሪ የዝርያ ማሻሻያ ማድረግ እንዲቻል የልማት አጋር ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግሥታትና የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት በስልጠናና በተለያየ መንገድ ድጋፍ እያደረጉ ነው:: ፓርኩ በተለይም ጂ አይ ዜድ ከተባለ አጋር የልማት ድርጅት ጋር በተለይም አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂውን በሰፊው መጠቀም እንዲችል፣ ዝርያውን አሻሽሎ የተሻለ ምርት እንዲያመርትና እንዲያሳድግ በዚህም ተጠቃሚ መሆን እንዲችል በጋራ እየሰራ ይገኛል:: ፓርኩ በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶች እንዳሉትም ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ፍላጎት ያሳዩ አስር የሚደርሱ የአገር ውስጥና የውጭ ባላሃብቶች እንዳሉ ጠቁመዋል::
አሁን የአቮካዶ ድፍድፍ ዘይት ማምረት የጀመረው ‹‹ሲይዝ አግሮ ኢንዱስትሪ›› ማህበር በቡና ልማት ጭምር የተሰማራ ባለሃብት በመሆኑ በቀጣይ ቡና ላይ እሴት በመጨመር ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሽጎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል:: ሌሎች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ለመሥራት ፍላጎት ያሳዩ ባለሃብቶች እንዳሉ አመላክተዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ በኢንዱስትሪ ፓርኩ መሰማራት በሚያስችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ሰፋፊ ጥናቶች ተደርገዋል:: አሁን መካከለኛ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ እየተሰራ ሲሆን፣ የዲላው የኢንዱስትሪ ፓርክ በአስር ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ነው::
ግንባታውም ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል:: የግንባታው 95 በመቶ የተጠናቀቀው የይርጋጨፌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በክልሉ ሁለተኛው መካከለኛ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ከስድስት ወራት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም ጠቁመዋል:: በቡና ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች በይርጋጨፌው አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው ቡና ላይ እሴት ጨምረው ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል:: ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳብራሩት፤ የይርጋጨፌ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እስከ አስር የሚደርሱ ባለሃብቶችን የመቀበል አቅም አለው::
በመሆኑ ከቡና በተጨማሪም ወተት፣ ማርና ሌሎች ፍራፍሬዎች ማቀነባበር ላይ የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የአገር ውስጥ አልሚ ባለሃብቶች ማልማት የሚችሉበት ሁኔታም ተመቻችቷል:: በአካባቢው በሚገኙ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ከአርሶ አደሩ ማሳ እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ትስስር ማጠናከር ያስፈልጋል:: በግብርናው ከሚያመጣው የሥራ ዕድል ባሻገር አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሰፊ የሆነ የሥራ ዕድል እንዲፈጠሩ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲሰፋና የገበያ ትስሰሩ እንዲጎለበት የማድረግ አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሊሰራበት ይገባል::
ከፍተኛ የገበያ ትስስር ሲፈጠር አርሶ አደሩ በምርቱ ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናል ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በአካባቢው የሚመረቱ አቮካዶን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችም እሴት ካልተጨመረባቸው ለብክነት ተጋላጭ የሚሆኑበት ሁኔታ ሰፊ እንደሆነም አመልክተዋል:: በመሆኑም ምርቶቹን በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮሰስ ማድረግ አዋጭ መሆኑን አስታውቀዋል:: በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአራትና ከዛ በላይ በሆኑ ክልሎች አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ እየሰራች መሆኗንም ተናግረው፣ ከእነዚህ መካከልም አንዱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሆኑንና በቀጣይም ይሄው እየሰፋ እንደሚሄድ ገልጸዋል::
አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢትዮጵያ አዲስ መሆናቸውን አቶ ጥላሁን ጠቅሰው፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር ጥብቅ ትስስርና ቅንጅት ማድረግን እንደሚፈልግ ይገልጻሉ:: በተለይም ከጥናትና ምርምር ጋር ተያይዞ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ቢሮና ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተቀናጅቶ መስራትን እንደሚጠይቅ አመልክተው፣ ሁሉም አካላት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል::
አሁን በቅንጅት ከመስራት አንጻር ያለውን ክፍተት ለመሙላትም በጋራ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል:: ከኃይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ ክፍተት እንዳለም ጠቁመው፣ የመብራት መቆራረጥ ለስራው እንቅፋት እንደሆነም አስታውቀዋል:: ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሆነም ይገልጻሉ:: አሁን በአንድ ፈረቃ እየተመረተ ያለው የአቮካዶ ድፍድፍ ዘይት በቀጣይ በሶስት ፈረቃ ያመርታል ሲባል ያለምንም የኃይል መቆራረጥ ነው ሲሉ አብነት ጠቅሰው ያመለከቱት አቶ ጥላሁን፣ ይህን የአሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መሰል ችግሮችን ከወዲሁ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል:: ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳስታወቁት፤ የአቮካዶ ድፍድፍ ዘይት እያመረተ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመረው ‹‹ሲይዝ አግሮ ኢንዱስትሪ›› ማህበር በቀጣይ በሶስት ፈረቃ ወደማምረቱ ይገባል::
በዚህ ጊዜም አሁን እያመረተ ካመረተው 22 ቶን በላይ በዓመት እስከ 130 ቶን የማምረት አቅምም አለው:: የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪም እንዲሁ ከፍ የሚል ሲሆን፣ አሁን ላይ አንድ ሊትር ድፍድፍ የአቮካዶ ዘይት በአማካይ እስከ 30 ዶላር ገቢ እያስገኘ ነው:: ከጣሊያን ውጭ ያሉ እንደ አሜሪካ፣ ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮችና ሌሎች አገራትም ድፍድፍ የአቮካዶ ዘይት የመግዛት ፍላጎት ያሳዩ በመሆናቸው ምርቱን በስፋት ማምረት ይገባል:: ከአቮካዶ በተጨማሪም ሌሎች ሰፊ የገበያ ፍላጎት ያላቸው ምርቶች ስለመኖራቸውና እዛም ላይ መሥራት ያስፈልጋል:: የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም አስመልክቶ ሲያብራሩም አሁን አቮካዶ እየለማ ያለው ሰፊ በሆነ ማሳ ሳይሆን፤ አርሶ አደሩ ባለው የአቮካዶ ዛፍ መጠን ነው ሲሉም ገልጸዋል::
እያንዳንዱ አርሶ አደር አምስትና አስር የአቮካዶ ዛፍ እንዳለው ጠቅሰው፣ እነዚህ አርሶ አደሮች በጋራ ሕብረት ሥራ ማህበር መስርተው ከአልሚ ባለሃብቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የአቮካዶ ምርታቸውን እያቀረቡ እንደሚገኙና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል:: በእያንዳንዱ አርሶ አደር ማሳ ውስጥ የአቮካዶ ዛፍ እንዳለም አመልክተው፣ ከአቮካዶ ምርት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ስልጠናዎች ለአርሶ አደሩ እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል::
በዚህም የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ እንደሆነና የአቦካዶ ድፍድፍ ዘይት ወደ ውጭ ገበያ እየተላከ መሆኑን አስታውቀው፣ ቡና፣ ወተት፣ ማርና በሌሎች ምርቶችም እየተሰራ ያለው ሥራ አበረታችና ውጤታማ መሆኑንም ተናግረዋል:: ምርቶቹ በስፋት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበት ሂደት ስለመኖሩ ገልጸዋል:: የአካባቢው ከፍተኛ መጠን ያለው የአቮካዶ ምርት እንዳይባክን ፋብሪካ መገንባት ማስፈለጉን አቶ ጥላሁን ተናግረው፣ በአሁኑ ወቅትም የዲላው የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቴክኖሎጂ በማሸጋገርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ካለው አስተዋጽኦ ባለፈ የአቮካዶ ዘይት ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩ ክልሉ በእድገትና ሽግግር ምዕራፍ ላይ እንዲሚገኝ የሚያሳይ ነው ብለዋል። በቀጣይ በፍራፍሬም ሆነ በሌሎች ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ስራ መሰማራት ለሚፈልጉ አልሚ ባለሃብቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እንዲመጡ ዋና ስራ አስፈጻሚው ጥሪ አቅርበዋል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም