በዓለም ላይ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች ይልሱት ይቀምሱት ያጡ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል። ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ ችግሮች ለርሃብ መከሰት መነሾ የሚሆኑ ጉዳዮች የሚተነበዩ ቢሆንም፤ ሳይታሰብ ተከስተው ብዙዎችን ለችጋር የሚያጋልጡ አጋጣሚዎች መኖራቸውም ይታወቃል። መነሻ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ረሀብ ጊዜ አይሰጥምና እነሱን መታደግ ይዋል ይደር የሚያሰኝ ስራ አይሆንም።
ለረሃብ የሚዳረጉ ሰዎች ትናንት በሞቀ በደራ ቤታቸው አብስለው ይበሉ፤ ቀድተው ይጠጡ የነበሩ ናቸው። ረሀብ የእነሱን ደጃፍ የማይነካ ይመስላቸው የነበሩም ብዙዎች ናቸው። በተለይም ከተፈጥሮ ችግሮች እንደ ጎርፍና መሬት መንሸራተት፤ ከሰው ሰራሽ ችግሮች እንደ ጦርነትና ግጭቶች ያሉት ሲከሰቱ ያበሰሉትን እስኪበሉ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን በተደጋጋሚ አይተናል።
ይህም ሆኖ በቅድመ ትንበያ ረሀብ ሊከሰት እንደሚችል ቢታወቅ እንኳን ለመከላከልም ሆነ ለችግር ታጋላጮችን ለመታደግ የሚሰሩ ሥራዎች የሚደርሰውን ጉዳት መቶ በመቶ ለማስቀረት የሚችሉበት እድል በጣም ጠባብ ነው። የሰው ልጅ ለርሃብ የሚጋለጥበትን እድል ሙሉ ለሙሉ የማስቀረቱ ጉዳይ ህልም ቢሆንም ለርሃብ የተጋለጡ ሰዎችን ለሞትና ለከፋ ጉዳት ሳይዳረጉ የመታደጉ አቅም ግን በራሱ በሰው እጅ ያለ እድል ነው።
ለዚህ ደግሞ ከቀዳሚዎቹ መፍትሄዎች መካከል በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፤ በድህረ ምርት ወቅት የሚከሰቱ የምርት ብክነቶችን መቀነስ እና በዘመናዊ መንገድ በመታገዝ ለረዥም ጊዜ ሳይበላሹ የሚቀመጡ ምርቶችን ማዘጋጅትና የመጠባበቂያ ክምችትን ማሳደግ ይጠቀሳሉ። በቅርቡ በተካሄደው «ከረሀብ ነጻ ዓለም» ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ እየተነሱ ያሉ ሃሳቦችም በግልጽ የሚያመላክቱት ይህንኑ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያን ብቻ እንደ ምሳሌ ብንወስድ ከላይ ያነሳናቸውን ሃሳቦች የሚያጠናክርልን መረጃ ማግኘት እንችላለን።
«ከረሀብ ነጻ ዓለም» በተሰኘው መድረክ የተገለጹ መረጃዎች እንዳመላከቱት፤ በኢትዮጵያ በየዓመቱ አርባ ስድስት ሚሊዮን ሰው መመገብ የሚችል ምርት በድህረ ሰብል ወቅት በአግባቡ ባለመሰብሰቡ ይባክናል። ይህ አሀዝ በሀገሪቱ በየዓመቱ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ (የእለት ጉርስ) ከሚያስፈልጋቸው ተረጂዎች ቁጥር አንጻር ሲታይ በእጅጉ የበዛ ነው። ባጭሩ ድህረ ምርት ብክነትን ብቻ መከላከል የምንችልበትን እድል ብንጠቀም በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች ለረሀብ የሚጋለጡ ዜጎቻችንን ለመታደግ ሌሎችን ደጅ መጥናት አይጠበቅብንም ማለት ነው።
በነገራችን ላይ ከላይ የተጠቀሰውን አሀዝ መነሻ በማድረግ ያለማጋነን ቢያንስ የሶስት የጎረቤት ሀገራት ዜጎችን ለመቀለብ የሚያስችል ምርት በየዓመቱ እያባከንን መሆኑን መገመት አይከብድም። ጉዳዩ በዚህ ደረጃ ትኩረት ማግኘትና የሁሉንም ተሳትፎ ባካተተ መልኩ ሊሰራበት የሚገባ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የድህረ ምርት ብክነትን በመከላከል ይህን ያህል አቅም መፍጠር የምንችል ከሆነ ሌሎች ግብርናውን የሚያሳድጉ መንገዶችን አሟጠን መጠቀም ብንችል ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰቡ ቀላል ነው።
ለምሳሌ በየአካባቢው ጦም የሚያድሩ መሬቶችን በሰብል መሸፈን ቢቻል፤ አቅም በፈቀደ አጠቃላይ የግብርና ስራው በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ማከናወን ቢቻል፤ ኩታ ገጠም እርሻ ማስፋፋት ቢቻል፤ የግብርና ምርቶችን በኢንዱስትሪ በመደገፍ እሴት ጨምሮ ለሀገር ውስጥ ሆነ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ቢሰራ ውጤቱ የሚያስጎመዥ ነው። እዚህ ላይ ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ የግብርና ዘርፉን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ማሳደግ ከላይ ከተዘረዘሩት በላይ ሰፊ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ነው።
ለምሳሌ «ከረሀብ ነጻ ዓለም» ዓለም መፍጠር ማለት ለእለት ጉርስ ሆድን መሙላት ብቻ ተደርጎ መወሰድ ያለበት አይመስለኝም። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የጤና መጓደል ጉዳይ ሲነሳ እንደ ማህበረሰብ ቀዳሚ ምክንያት ተደርገው ከሚወሰዱት ምክንያቶች መካከል በቂ ምግብ አለማግኘት መሆኑ ይታወቃል። በተለይም በህጻናት እድገት ላይ ከመቀንጨር ጀምሮ ህይወታቸውን ሙሉ ለሚከተሉ ችግሮች እየተዳረጉ ያሉት በለጋ እድሜያቸው በቂና የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ነው።
ይህንን ተከትሎ ቤተሰብ ለውጣ ውረድ እና ለገንዘብ ወጪ ከመዳረጉ ባለፈ መንግሥት በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የህክምና ቁሳቀስና መድኃኒት እንዲያስገባ የሚገደድ መሆኑ የችግሩን ተሻጋሪነት አመላካች ነው። በሌላ በኩል አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የግብርናው ዘርፍ አብዛኛውን ሰው የሚያሳትፍ መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን መስኩ በዘመናዊ መንገድ የሚመራ ባለመሆኑ ከአድካሚነቱ እና ከልፋቱ አንጻር በቂ ትርፍ እየተገኘበት አይደለም።
በዚህም የተነሳ አብዛኛው የአርሶ አደር ልጅ በእርሻ ሥራ ላይ የሚቆየው በከተማ ለመኖር የሚያስችለውን አማራጭ እስኪያገኝ ድረስ ብቻ ነው። ምን አልባትም ብዙሀኑ የአርሶ አደር ልጅ በየተገኘው አጋጣሚ በአካባቢው ወዳሉ ከተሞች ወይንም ወደ አዲስ አበባ በማቅናት በግለሰብ ቤትና በቀን ሰራተኝነት ህይወቱን ለመግፋት ይገደዳል። ቀሪው ደግሞ በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ በአየርም በባህርም ወደ ሌሎች ሀገራት በመሰደድ ለአስከፊ ህይወት ይዳረጋል።
የዚህ ሁሉ ጉዞ መዳረሻ ራስን ብሎም ቤተሰብን ከረሀብ ለመታደግና የተሻለ ኑሮ ለመኖር ነው። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለግብርና ትኩረት መስጠትና ግብርናውን ማዘመን በተዘዋዋሪ ከላይ ለተነሱት ጉዳዮች ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። እዚህ ላይ በጽሁፌ ውስጥ ለግብርናው ትኩረት መስጠት… ግብርናውን ማዘመን እያልኩ ያስቀመጥኳቸው ቃላትና ሀረጋት ድንች እንደመላጥ ቀላል አለመሆናቸውን አምናለሁ።
በትንሹ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን ዞር ብለን ብንከልሰው የዛሬ ሃምሳ ዓመት ግድም የንጉሱን ሥርዓት በማስቆም ለውጥ ለማምጣት ሲሯሯጡ የነበሩት አካላት በርካታ ጥያቄዎችን ያነገቡ ነበሩ። ከእነዚህም ለውጥ የሚፈልጉ ሀገራዊ ጉዳዮች መካከል የአርሶ አደሩ ልፋትና ተጠቃሚነት ተመጣጣኝ አይደለም የሚለው ቀዳሚው ነበር። ለውጥ ፈላጊዎቹን የተኩትም ቢሆኑ እንደ ሀገር ትኩረት ከሚሹ ቀዳሚ አጀንዳዎች ተርታ ግብርናን በማዘመን አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግና ሀገርን ከልመና ማላቀቅ ቀዳሚ እቅዳቸው ነበር።
በቅርቡም የተጀመረው አዲሱ የለውጥ እንቅስቃሴ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአርሶ አደሩ ብሎም አጠቃላይ ለአረንጓዴ ልማት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን እያየን ነው። ዛሬም የብዙኃኑ አርሶና አርብቶ አደር እጣ ፈንታ በየእርሻ ማሳው በሬና ፈረስ ከመጎተት የተላቀቀ ባይሆንም፤ ግብርናውን ከጓሮ አትክልት ልማት አንስቶ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እና አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ አማራጭ የሌለው መዳረሻችን በመሆኑ ሁላንችም ትኩረት ልንሰጣው ይገባል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም