የቱርኩ ፕሬዚዳንት ታይፕ ኢርዶጋን በድጋሚ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል ጦርነት እንድታቆም ይነግሯታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው በትናንትናው ዕለት ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማቆም ጥሩ ጅምር ሊሆን እንደሚችልም አስተያየት መስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
“ትርምፕ ግጭቶችን ለማቆም ቃል ገብተዋል… ያ ቃል እንዲፈጸም እና እስራኤል ጦርነት እንድታቆም እንዲነገራት እንፈልጋለን” ብለዋል ኢርዶጋን።
ኢርዶጋን አክለው እንደተናገሩት፤ እስራኤል በፍልስጤም እና ሊባኖስ የምታደርገውን ወረራ እንድታቆም ትራምፕ አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ካስቆመ ጥሩ ድምር ይሆናል።
ቱርክ እስራኤል በፍልስጤም እና በሊባኖስ ግዛቶች የምታካሂደውን ወረራ አጥብቃ የምታቀወም ሲሆን ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት አቋርጣለች። ቱርክ በእስራኤል ላይ በዓለም አቀፉ የወንጀሎች ፍርድ ቤት የቀረበውን የዘር ማጥፋት ክስ ደግፋ ለመከራከርም ያመለከተች ሀገር ነች።
የትራምፕ ፕሬዚዳንት መሆን በመካከለኛው ምስራቅ ባለው የኃይል ሚዛን ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል ያሉት ኢርዶጋን፤ አሁን ያለውን የአሜሪካ ፖሊሲ መከተል በቀጣናው ያለውን ቀውስ እንደሚያባብሰው ገልጸዋል።
ቱርክ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት በአዲስ መልክ እንዲስተካከል የሚፈልጉት ኢርዶጋን፤ ከትራምፕ ጋር በስልክ ማውራታቸውን እና ቱርክን እንዲጎበኙ ግብዣ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። ኢርዶጋን አክለውም ትራምፕ ግብዣውን እንደሚቀበሉት ተስፋ አለኝ ብለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም