ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን ሀብት ክምችት ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ማዕድናት መካከል አንዱ ወርቅ ሲሆን አገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ክምችት እንዳላት በጥናት ተረጋግጧል፡፡ እስካሁን በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከ517 ቶን በላይ የወርቅ ክምችት መገኘቱን ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ወርቅ ሲባል ሁለት አይነት ነው፡፡ ጽንሰ ወርቅ እና ደለል ወርቅ ተብሎም ይጠራል፡፡ ደለል ወርቅ ከላይ ያለው ድንጋይ በተለያዩ ምክንያቶች ሲበሰብስና ሲፈረካከስ ከዚያ ውስጥ ሊወጣ የሚችል የወርቅ አይነት ነው፡፡ ይህንን አይነቱ ወርቅ አብዛኛውን ጊዜ ከተራራ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ በውሃ ወይም በንፋስ ዝቅ ወዳለ ቦታ እየሄደ ላይ መጥቶ ይከማቻል፡፡ ይህም በአነስተኛ ቴክኖሎጂና በትንሽ ወጪ ሊመረት ይችላል፡፡ የደለል ወርቅ ጊዜያዊ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ሊያልቅ ይችላል፡፡
ጽንሰ ወርቅ መሬት ውስጥ በጣም ወደታች ተገብቶ የሚወጣና ተፈጭቶ በትልቅ ቴክኖሎጂ የሚመረት ነው። ትልቅ የሚባለውም ጽንሰ ወርቅ ነው፡፡ አሁን ላይ ያለው መረጃ እንደሚያሳየው የደለል ወርቅ በዚህ ደረጃ አለ ማለት ትልቅ ክምችት ያለው ጽንሰ ወርቅ እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ጽንሰ ወርቅ በጥልቀት በትልቅ ቴክኖሎጂ እና ረጅም ጊዜ (ከ30 እስከ 50 ዓመታት) የሚፈልግ ነውና ያለው ክምችት ቀላል የሚባል እንዳልሆነ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
ጽንሰ ወርቅ ከፍተኛ ሀብትና ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ እንደመሆኑ ከፍተኛ አቅም ባላቸው ትላልቅ ኩባንያዎች የሚሰራ ነው፡፡ የወርቅ ማዕድን ሀብት በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ክልል፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በሌሎችም ክልሎች በስፋት ይገኛል፡፡ በሀገራችን ጥቂት ኩባንያዎች ናቸው በዚህ ልማት የተሰማሩት፡፡ በአብዛኛው በደለል ወርቅ ልማት ላይ በባህላዊ መንገድ የማልማት ስራ ነው እየተከናወነ ያለው፡፡
መንግሥት የማዕድን ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦና ለዜጎች ከሚፈጥረው የሥራ እድል አንጻር በመመልከት በሰጠው ትኩረት ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ እንዲሆን መደረጉ ይታወቃል፡፡ ይህን ተከትሎም የማዕድን ሀብትን ጥቅም ላይ በማዋል የኢኮኖሚ ምንጭ ሆኖ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት እንዲችል በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡
ለአገሪቷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ይታወቅ የነበረው ወርቅ ባለፉት ዓመታት ከሕገወጥ ወርቅ ማምረትና ግብይት ጋር በተያያዘ ለብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን መቀነሱ ይታወቃል፡፡ የወርቅ ምርቱ በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሀገሮች ይወሰድም ነበር፡፡ መንግስት ይህን ሕገወጥ ድርጊት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም በርካታ ሕገወጦች በቁጥጥር ስር ውለውም እንደነበር ይታወሳል፡፡ በድርጊቱ የተጠረጠሩ የውጭ ዜጎች ላይም ጭምር እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ይታወቃል፡፡
የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመላክተው፤ የወርቅ ምርት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ የኤክስፖርት ምርቶች መካከል አንዱ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ለውጭ ገበያ ከሚላክ ወርቅ ብቻ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይገኝ ነበር፤ በ2014 ዓ.ም ከወርቅ ብቻ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 672 ሚሊዮን ዶላር ደርሶም ነበር፡፡
ይህ ወርቅ የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሬ እየቀነሰ መጥቶ አነጋጋሪ እስከ መሆን ደርሷል፡፡ የወርቅ ክምችቱ ሳይኖር ወይም ሳይመረት ቀርቶ ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች የወርቅ ሀብቱ ለብሔራዊ ባንክ እንዳይደርስ በመደረጉ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይም ወርቅ ለኮንትሮባንድ ንግድና በሕገወጥ ግብይትና ዝውውር የተጋለጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እምብዛም ውጤት ሳያስገኝ ዓመታት አልፈዋል፡፡
ለእዚህ ምክንያት ከተባሉት መካከል ብሔራዊ ባንክ ለወርቅ አቅራቢዎች የሚሰጠው ክፍያ አማላይ አለመሆኑና የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ሁኔታም ብሔራዊ ባንክ ለአቅራቢዎቹ የሚሰጠውን ዋጋ በየጊዜው እያሻሻለ እንዲሄድ አርጎት ቆይቷል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የሚመረተው ወርቅ ሕገወጦች እጅ በመውደቁ ለባንኩ የሚገባው ወርቅ መጠን ሲያሽቆለቁል ቆይቷል፡፡
በተለይ ወርቅ አምራች በሆኑት ክልሎች በቤኒሻንጉል፣ በጋምቤላ እና በትግራይ ክልል ሕገወጥነት ተንስራፍቶ ወርቅ አግባብ ባልሆነ መልኩ ግብይት ሲካሄድበት ከመቆየቱም ባሻገር በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት ሀገሮች ይወጣም ነበር፡፡
በመንግሥት በኩል ኮንትሮባንድ ንግድና ሕገወጥ ዝውውር ለመከላከል የጸጥታ አካላት ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራዎች ሲሰሩና ክትትል ሲደረግ ቢቆይም፣ በክልሎች እየጨመረ የመጣው የወርቅና የማዕድናት ኮንትሮባንድ ንግድን ማስቆም ሳይቻል ቀርቷል፡፡
ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት በማዕድን ዘርፍ በተለይ በወርቅ ልማትና ግብይት ላይ የገጠመውን ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ማዕድን አምራቾችና አዘዋዋሪዎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በሕገወጦች ላይ እርምጃ በመውሰድና የተለያዩ ማሻሻያዎች በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ከወራት በፊት ደግሞ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የታመነበት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሙሉ ትግበራ መግባቱ ይታወሳል፡፡ ይህ ለወጪ ንግዱ፣ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር፣ ወዘተ ከፍተኛ ፋይዳለው ይታወቃል፡፡ ማሻሻያውን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ አድርጓል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሬ ግብይቱ ከብሔራዊ ባንክ ውጪ እንዲከናወን ወይም በገበያ እንዲመራ የሚያስችል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ ያደረገው ማሻሻያ ለወርቅ አቅራቢዎች ዘላቂ ማበረታቻ እንደሚፈጥር በመታመኑ እና የወርቅ አቅርቦትን በዘላቂነት ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የተሻሻለ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ባንኩ የወርቅ ዋጋን አስመልክቶ ከሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ በዋለው አሰራር መሰረት የወርቅ መግዣ ዋጋ ባንኩ ድረ-ገፅ ላይ በየዕለቱ በሚገለጸው የውጭ ምንዛሪ መሸጫ ተመን ላይ ተመስርቶ የሚወሰን እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል፡፡
መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉት እነዚህን መሰል ማሻሻያዎች ደግሞ ወደ ባንኩ በሚገባው የወርቅ መጠን ላይ ለውጦች እንዲታዩ እያደረጉ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው 100 ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በተገመገመበት ወቅት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በተያዘው በጀት ዓመት የስምንት ነጥብ አራት በመቶ እድገት የማስመዝገብ ውጥን ተይዟል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው 100 ቀናት ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም በወጪ ንግድ፣ በመንግሥት ገቢ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በውጭ ምንዛሪ ግኝት የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል። ከወጪ ንግድ አንጻር በተለይ በወርቅ ወጪ ንግድ እጅግ ስኬታማ ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል።
ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት ዓመቱን ሙሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን አራት ቶን ብቻ እንደነበር የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ብቻ ሰባት ቶን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን ተናግረዋል። ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣቱን አመላካች ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደ ሚያመላክተው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በራሱ ለውጥ ማምጣት ችሏል፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲያስ እንዳሉት፤ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገው የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የማዕድናት ምርታማነትን በተለይ የወርቅ ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአነስተኛ ደረጃ ይመረት የነበረው የማዕድን ምርት በከፍተኛ መጠን እያሳደገው ነው፡፡
የማእድን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እንዳሉትም፤ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ነጥብ ስድስት ቶን ወርቅ ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት /ባለፉት ሶስት ወራት/ ብቻ የእቅዱን 70 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል፤ ማሻሻያው የማዕድናት አምራቾችን ተጠቃሚ እያደረጋቸው በመሆኑ የተሻሉ ማሽነሪዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ገዝተው ወደ ምርት ሂደቱ እየገቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የባሕላዊ አምራቾች ካፒታላቸውን በማጠራቀም ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ፤ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ፤ ገቢያቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ ምርትን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተያዘው በጀት ዓመትም ለማምረት ከታቀደው ስምንት ነጥብ ስድስት ቶን ወርቅ ሶስት ሺህ 600 ኪሎ ግራም ያህል ወርቅ በባሕላዊ መንገድ የሚመረተው ሲሆን፤ የባሕላዊ የማዕድን ቁፋሮ ወደ አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ እንዲያድግ እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ባሕላዊ የማዕድን አመራረት ዘዴ ከፍተኛ የሆነ የምርትና የጉልበት ብክነት እንዳለው ጠቅሰው፤ የምርትና የጉልበት ብክነትን ለመቀነስ አመራረቱን የማዘመን ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ አስታወቀዋል፡፡
በክልል ደረጃም ወርቅ ለማምረት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ጥረቶች እየተደረጉ ለውጦችም እየታዩ ስለመሆናቸው ይገልጸል፡፡ ለአብነትም የትግራይ ክልል ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ሕገወጥነት በተስፋፋበት የወርቅ ምርት ላይ በተደረገው ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ብሔራዊ ባንክ ባደረገው የወርቅ መግዣ ተመን የተነሳ በዓመቱ መጨረሻ ወራት ጀምሮ አበረታች ለውጦች እየታየ መሆኑን የክልሉ መሬት አጠቃቀም አስተዳደርና ማዕድን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
ክልሉ በ2016 በጀት ዓመት ወርቅ በማምረት 50 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማስገባት አቅዶ፤ በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ባሉ ሦስት ወራት እቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ችሏል፡፡ ይህ የሆነበት ዋንኛ ምክንያት በተሰራው ጠንካራ የክትትልና የግምገማ ሥራ በተለይ ወርቅ ላይ ትኩረት መሰጠቱ በዓመቱ መጨረሻም የተያዘውን እቅድ ማሳካት ተችሏል፡፡ በባለፈው ዓመት ማገባደጃ ሦስት ወራት የወርቅ ምርት በሕጋዊ መንገድ ወደ ብሔራዊ ባንክ የመግባት ሁኔታ በመነሻነት የተያዘና ይህንን እቅድ ሊያሳካ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በክልሉ በተያዘው 2017 በጀት ዓመት 800 ኪሎ ግራም ወርቅ ገቢ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡ ይህም 700 ኪሎ ግራም ወርቅ በኢዛና ድርጅት (ኢዛና ሕጋዊ የሆነ ወርቅን ከአምራቾች ተረክቦ ለብሔራዊ ባንክ የሚያስገባ ነው) አማካኝነት የሚገባ ሲሆን፤ 100 ኪሎ ግራም ከባሕላዊ አምራቾች ገቢ እንዲደረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ አሁን ላይ በወርቅ ምርት ላይ ለውጦች እየተመዘገቡ ስለመሆናቸው ወደ ብሔራዊ ባንክ እየገባ ያለው የወርቅ መጠንና ለውጪ ገበያ ቀርቦ ያስገኘው ከ500 ሚሊየን ዶላር በላይ ያመለክታል፡፡ በተለይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው፡፡ በዚህ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን ባለፈው ዓመት ዓመቱን በሙሉ ከተገኘው ውጤት ሁለት እጥፍ ሊሆን ትንሽ የቀረው መሆኑም ይህንኑ ያመለክታል፡፡
እንደ ሀገር በወርቅ ግብይት ላይ እየታየ ያለው ለውጥ ሀገሪቱ ከወራት በፊት ተግባራዊ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና እሱን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ታምኖበታል፡፡
ሀገሪቱ ካላት እምቅ የወርቅ ማእድንና በባሕላዊና በዘመናዊ መንገድ እየለማ ካለው የወርቅ ሀብት ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ የማሻሻያው ትግበራ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፤ ማሻሻያው ገና ወደ ትግበራ እንደገባ ትልቅ ውጤት ማየት ተችሏል፡፡ ይህ ውጤት በቀጣይም ሰፊ ለውጥ መመዝገብ እንደሚችልም ያመላክታል፡፡
ይህን ውጤት ዘላቂ ለማድረግ በማሻሻያው ትግበራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህም ወርቅን ሲፈጸምበት ከቆው ሕገወጥ ተግባር ለመታደግ የተጀመረውን ጥረት ውጤታማ ማድረግም ይቻላል፡፡ ወርቅ በዚህ ልክ ዋጋ እያወጣ ከመጣ አምራቾች ለሕገወጦች ከማቅረብ ይልቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ይነሳሳሉ፤ በዚህም ሀገር ከወርቅ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ ይመጣል፡፡
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም