አቶ ተፈራ በዬራ በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የከተማና መሠረተ ልማት ተመራማሪ
ኢትዮጵያ ከተሜነት በፍጥነት እየተስፋፋባቸው ከሚገኙ ሀገሮች አንዷ ናት። መረጃዎች የሚያመለክቱትም ይህንኑ ነው፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ የከተሞች ምጣኔ 25 በመቶ አካባቢ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። የከተሜነት መስፋፋት ፍጥነቱም አምስት ነጥብ አራት በመቶ ነው። ይህም የኢትዮጵያ ከተሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የከተሞች እድገት ከሚታይባቸው ሀገራት መካካል መሆናቸውን ያመለክታል።
ከተሞች በእቅድ እና በፕላን እንዲመሩ በማድረግ በኩል ግን ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ክፍተቶቹን ለመሙላት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ከችግሩ ስፋት ጋር በተያያዘ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ሳይቻል ቆይቷል።
በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች የኮሪደር ልማት ማካሄድ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያትም ይሄው እንደሆነ ይገለጻል። በኮሪደር ልማቱ መሰረተ ልማቶችን ከተሞችን በሚመጥን መልኩ መዘርጋት፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን ማልማት፣ ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር ስራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የከተማና መሠረተ ልማት ተመራማሪ አቶ ተፈራ በዬራ ከተማ በ21ኛው ክፍለዘመን ትልቁ የኢኮኖሚ መሰረት ተብሎ እንደሚወሰድ ይናገራሉ። ከተሞች ይሄንን ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ደግሞ በፕላን መመራት ይኖርባቸዋል ሲሉ ያስገነዝባሉ። የሚጠበቅባቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ እንዲሆን በፕላን የግድ መመራት ይኖርባቸዋል። ከተሞች ሲስፋፉ የሚቀጥለው ትውልድ ጭምር ታሳቢ መደረግ ይኖርበታል። ትክክለኛ የከተማነት ሚናቸውን እንዲወጡ በእቅድ መመራት አለባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ከተሞች አምስት ነጥብ አራት አካባቢ የሆነ ፈጣን የከተሜነት እድገት የሚታይባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህ ከተሞች በፕላን ካልተመሩ ያለውን ህዝብ ለማስተናገድም ችግሮች የሚፈጥሩ ይሆናሉ ይላሉ። ከተሞቹ አስተዋፅኦ ማበርከት ሲጠበቅባቸው በተለያዩ ችግሮች የተወሳሰቡ ይሆኑና ችግር ፈጣሪ ይሆናሉ ሲሉ ያመለክታሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን በከተሞቻችን ከሚታዩ መሰረታዊ ችግሮች መካከል የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ በእቅድ አለመመራት፣ የከተሞች ያለ ቁጥጥር ወደጎን ማደግ፣ የትራፊክ መጨናነቅ፣ የስራ አጥነት መብዛት እንዲሁም ደካማ የአካባቢ ንፅህና እና የቆሻሻ አወጋገድ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ችግሮች ተደማምረው በከተሞቻችን ለሀገራችን የኢኮኖሚ እድገት የሚፈለግባቸውን ሚና እንዳይወጡ እያደረጋቸው ይገኛል።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት አሁን እንደ ፕላን ስትራቴጂ እየተጠቀመ የሚገኘው ኮሪደር ልማት ስራዎችን ማከናወን መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀደም ሲልም የስማርት ከተማ እቅድ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ጠቁመዋል። ከልማቱ ጠቀሜታዎች መካከል ከተማ ውስጥ ተሽከርካሪ ያለምንም ትራፊክ መጨናነቅ መንቀሳቀስ የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር አንዱ እንደሆነ ገልጸው፣ የስማርት ከተማ ስራውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የኮሪደር ልማት እገዛ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።
አቶ ተፈራ እንዳብራሩት ፤ የኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ ትላልቅ ከተሞች ጭምር የተመሰረቱበት በፕላን ባልተመራ ሁኔታ ነው። መንገዶች በጣም ጠባብና የተጨናነቁ መሆናቸውም ይህንን ያመለክታል። ለብስክሌት የሚሆን መንገድ በአግባቡ አልተገነባም፤ ሰፊ የእግረኛ መንገድ እንዲሁም በቂ የመናፈሻ አረንጋዴ ስፍራዎች የሉም።
የኮሪደር ልማቱ መተግበር እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ብትሆንም በቂ የህዝብ መፀዳጃዎች የሏትም። የህዝብ መጸዳጃ በበቂ ሁኔታ ባለመሟላቱና መጸዳጃ ቤት በተወሰነ ርቀት ባለመኖሩ ተፈጥሮኣዊ ለሆነው ጉዳይ በትክክል ምላሽ እየተሰጠ አልነበረም።
የከተማዋ እድገት ይህንንም የሰው ልጅ ተፈጥሮኣዊ ባህሪ ከግምት ባስገባ መልኩ በአግባቡ ማስተናገድ እንዳልተቻለ አስታወሰው፤ ይህንን ጨምሮ በከተማዋ ያሉ የመሰረተ ልማት ችግሮችን በአግባቡ በመፍታት ከተማዋን ለማስተዳደር አሁን እየተከናወኑ የሚገኙት የኮሪደር ልማት ስራዎች እነዚህን ያካተቱ መፍትሔዎች ይዞ የመጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገድ ችግር መፍታት፣ ለብስክሌት መሄጃ የሚሆን መንገድ መገንባት፣ ሰፊ የእግረኛ መንገድና መናፈሻ ስፍራዎችን ማዘጋጀት፣ ታክሲዎችና አውቶቡሶች የሚጭኑና የሚያወርዱባቸውን ተርሚናሎች ማሟላት፣ አጠቃላይ የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን የመገንባት የጎላ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።
በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች የመብራት ኃይል መሰረተ ልማት እንዲሁም የቴሌኮም ኬብሎች በአግባቡ አለመዘርጋታቸውን ጠቅሰው፣ በኮሪደር ልማቱ እነዚህ ችግሮች በአግባቡ እየተቀረፉ መሆናቸውንም ይጠቁማሉ። እነዚህም ድምር ስራዎች የከተማ ነዋሪ ህይወት ለማሻሻል ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከተሞች ሲመሰረቱ የወደፊቱን ትውልድ ታሳቢ አድርገው እና በአግባቡ ታቅደው መሆን እንዳለበት አመልክተው፣ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ መሰረተ ልማት እየተሟላላቸው ማደግ እንደሚገባቸው አስታውቀዋል።
ከተሞች ተገቢ የመሰረተ ልማት እየተሟሉላቸው የማያድጉ ከሆነ አሁን የሚታዩት አይነት ችግሮች መከሰታቸው እንዳማይቀር አስገንዝበው፣ በተለይ የመንገድ መሰረተ ልማት ዋነኛው መከናወን ያለበት መሆኑን ይገልጻሉ። የኤሌክትሪክ፣ የፍሳሽ እና የመሳሰሉት መሰረተ ልማቶችም መንገድን ተከትለው የሚሄዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አንድን ከተማ ከተማ የሚያሰኘው መንገድ በሚፈለገው ደረጃ ሲገነባ ነው ይላሉ።
አሁን መንግሥት ይሄንን ለማስተካከል ሲመጣ የከተማ ልማት የህዝብ መሆኑንና ለሚቀጥለው ትውልድ የሚሰራ ስራ መሆኑን ማወያየት፣ ህዝቡም ተሳትፎ በማድረግ እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉም አስገንዝበዋል። ከዚህ አኳያ ግንዛቤ መፍጠር ላይ በስፋት መሰራት አለበት ሲሉም ተናግረው፣ ህዝቡ ስራው የኔ ነው ብሎ ከተቀበለ መሰረተ ልማቱ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አመላክተዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ተመራማሪው እንዳስታወቁት፤ በኮሪደር ልማቱ እንደ አዲስ እየተሰራች ያለችው አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የከተሞች ልማት ስራዎች በሀገሪቱ የከተማን ደረጃ የሚያሳድጉ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ማሳያ ይሆናሉ። ይህም ለከተሞቹ ነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ፣ የስራና የመሳሰሉትን አካባቢዎችን መፍጠር ያስችላል።
ስማርት ከተማ ሲገነባ ቱሩፋቶችን ይዞ እንደሚመጣ ገልጸው፤ ለአብነትም በከተሞች የሚሰሩ አረንጓዴ የውበት ስራዎችን ጠቅሰዋል። ይህ ልማት በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፣ መንፈስን ያድሳል፤ በእግር ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤ የትራፊክ መጨናነቅን ይቀንሳል፤ በእግር መሄድ ለጤና ያለውን ሚና ያሳድጋል ሲሉ አብራርተዋል።
አቶ ተፈሪ እንዳሉት፤ የኮሪደር ልማቱ መከናወን ወይም በአካባቢው አስፈላጊው የመሰረተ ልማት መዘርጋቱ ቱሩፋቱ ብዙ ነው። ከቱሩፋቶቹ መካከል የአካባቢው የመሬት ዋጋ በዚያው ልክ የሚያድግ መሆኑ ይጠቀሳል፤ የአካባቢው ውበት ይጨምራል። የውበቱ መጨመር ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
የኮሪደር ልማቱ ዋነኛ ዓላማ የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ነው። ሰው የተሻለ ተስፋ ማድረግ እንዲችል፣ በሀገሩ በዚህ መልኩ ማደግ እንደሚችል እንዲረዳ፣ መጪው ትውልድ የተሻለ አካባቢ እያየ ራእይ እንዲኖረው ያደርጋል። የኮሪደር ልማት በተሰራባቸው አካባቢዎች የሚታየው የሰዎች እንቅስቃሴ እና የመዝናናት ሁኔታም ለቱሪዝም ዘርፉ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የውጭ ቱሪስቱ ለጉብኝት እንዲመጣ በመስህብነት ያገለግላል። የአካባቢንና የከተማን ደረጃ ለመቀየር የጎላ አበርክቶ አለው።
ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ የተገነባው የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ሲታይ በተያዘው ሳምንት ጭምር ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እየተካሄደበት መሆኑን አንስተው፣ የሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ስብሰባ የማስተናገድ አቅም ላይ የራሱን ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የማስተናገድ አቅም መጨመሩ ሌሎች በከተማዋ እና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የመናፈሻ ፓርኮችንም ለማስጎብኘት እድል ይፈጥራል ሲሉ አብራርተዋል።
በምሽት ላይ የሚታየው የከተማዋ ውበት ከቀደመው አኳያ ሲታይ የተለየ ስሜትን እንደሚያጭርም ተናግረው፤ የኮሪደር ልማቱ ለሀገሪቱና ለነዋሪው ምቹ ማድረግ እንደሚቻል ማሳያዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል። የኮሪደር ልማቱ የሀገር ውስጥ ሀብትን በማንቀሳቀስ መንግስትና ባለሀብቱን በማስተባበር ሀገርን መለወጥ እንደሚቻል ያመላከተ የልማት ስትራቴጂ መሆኑን ያስረዳሉ።
በቀጣይ አይቀሬ በሆነው የከተሜነት መስፋፋት እያደገ የሚመጣውን የህዝብ ቁጥር ማስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ አስቀድሞ መፍጠር ይገባል ያሉት አቶ ተፈሪ፣ ከተሞች አስፈላጊውን መሰረተ ልማት አሟልተው እንዲገነቡ ለማድረግ በእቅድ መመራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ከወዲሁ በመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ላይ መሰራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
‹‹ዋነኛው የሀገራችን ከተሞች ችግር ከተማ እየቀደመ እኛ እየተከተልን መሆኑ ነው›› የሚሉት አቶ ተፈሪ፤ ቀድሞ አስቦ ከተማን መምራት እንደሚገባ አመልክተዋል። ከዚህ በፊት የነበረውን ምላሽ የመስጠት አካሄድ እንደነበር ጠቅሰው፣ ከተማ ከሄደ በኋላ በህገወጥነት ወደጎንዮሽ እየተስፋፋ ሲሄድ እየተከተልን ከተማ ስንል ቆይተናል ብለዋል።
አሁን ግን በከተማና ገጠር ትስስር እንዲሁም በመሬት አጠቃቀም ላይ በመስራት የትኛው አካባቢ ለየትኛው መዋል እንደሚገባው በመለየት ቀድሞ በማቀድ ከተማ መመራት እንዳለበት ተናግረዋል። ከተማ በእዚህ መልኩ የሚመራ ከሆነ ከተሞችን በሚፈለገው መልኩ ማሳደግ ይቻላል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ከተማ ዞሮ ዞሮ ወደ ገጠር የሚስፋፋ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀድመን ገጠርን የምንሰራ ከሆነ ፤ ሰዎች መንገድ ዳር መጥተው እንዳይሰፍሩ ማድረግ እንችላለን ብለዋል። ገጠሩን በእቅድ የምንመራው ከሆነ እና በገጠር እና በከተማ ያለው ትስስር በተቀናጀ መልኩ ከተመራ፣ ከተሞቻችን እንዲመሩን ሳይሆን እኛ ወደ ምንፈልገው ደረጃ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ከተሞቻችንን መምራትና ማሳደግ እንችላለን›› ሲሉ አቶ ተፈራ ተናግረዋል።
አሁን በኮሪደር ልማቱ የሚታዩ ማስተካከያዎች እና ከተማን እንደገና የማደስ ስራዎች አቅዶ ባለመስራት የተፈጠሩ ችግሮች የሚፈቱበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከተሞቻችን በእቅድ እና በእቅድ ብቻ እንዲመሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ቀድሞ ማቀድን መከተል ከተቻለ በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ የመሰረተ ልማት ችግሮችንም አስቀድሞ መፍታት እንደሚቻል አቶ ተፈሪ አስገንዝበዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በሀገሪቱ እንደ ችግር የሚታየው የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖሩ ነው። የትኛው አካባቢ ለየትኛው መዋል እንዳለበት የሚያሳይ ለቤት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኮመርሻል፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለአረንጓዴ ስፍራዎች የሚለውን ቀድሞ ማቀድ እና ማስተዳደር ያስፈልጋል። አረንጓዴ ስፍራዎች የከተማ ሳምባ በመሆናቸው በእቅድ መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ሁሉም አካባቢ በፎቅ የሚሞላ ከሆነ፤ ከተማ ሳምባ ያጣል፤ በመሆኑም አረንጓዴ ስፍራዎችንም ጭምር ማቀድ ይገባል።
ለአሁኑ ለሀገሪቱ የሚያስፈልገውን የከተማ ደረጃ ለማምጣት የኮሪደር ልማት ተጀምሯል። የህዝብ ቁጥሩ እየሰፋና እያደገ በመሆኑ አሁን ባለንበት የከተማ ደረጃ መቀጠል ስለማይቻል የኮሪደር ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ይገባል ሲሉም አስገንዘበዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከገጠር ወደ ከተማ ከፍተኛ ፍልሰት ይታያል። ይህንንም ችግር ለመቀነስ በእያንዳንዱ ከተማ ላይ መስራት ያስፈልጋል። ለምሳሌ በመዲናዋ የሚታየው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር በእያንዳንዱ ከተማ አስፈላጊ መሰረተ ልማት በመገንባት ለኢኮኖሚያዊ ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር ፍልሰቱ ሚዛናዊ እየሆነ ይሄዳል። የተመጣጠነ የከተማ እድገት ማምጣት ያሻል።
የገጠር እና የከተማ ትስስርን ማጠናከርም ያስፈልጋል ያሉት አቶ ተፈራ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ቀድመው ባደጉ ከተሞች የኮሪደር ልማት ማካሄዱ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ለዚህም ቀጣይነት ያለው ውይይት ማድረግ ላይ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቅሰው፤፡ የህብረተሰቡን ድጋፍ ለማስቀጠል በልማቱ የተገኙ ውጤቶችን ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ተገቢው የመሰረተ ልማት ሥራ በከተሞች ብቻ ሳይሆን በገጠር አካባቢዎችም ጭምር መካሄድ አለበት። መሰረተ ልማቱ አርሶ አደሩንም ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ በገጠር አካባቢ መንገድ ዳር የሚሰፍረው አርሶ አደር ምርቱን ለገበያ ማቅረብ የሚችልበት ምቹ መሰረተ ልማት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም