አሸባሪውን ህወሓት ከገባበት ቅርቃር ለማውጣት የሚደረገው ሩጫ ተጣጡፏል፡፡ የጁንታው ደጀን የሆነው ሀይል ዋነኛ ተላላኪያቸው ከጨዋታው እንዳይወጣባቸው በዲፕሎማሲውም፣ በፕሮፓጋንዳውም ፣ በቀለብ ሰፈራውም ሲመች ደግሞ መሳሪያ በማስታጠቁም እየተባበሩ ነው፡፡ መጨረሻው ውጤት አልባ እንደሚሆን ቢታወቅም ቅሉ የጁንታው ደጋፊ የሆኑት ሀይሎች የሚያደርጉት ርብርብ እና ትጋት ግን አስገራሚም አሳፋሪም ነው፡፡ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ም/ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ አንዳንድ የምእራባውያን ሀገራት ግለሰቦች ጭምር ጉዳዩ የሀገራት የዲፕሎማሲ ጉዳይ ሳይሆን ግላዊ ጉዳያቸው እስኪመስል ድረስ ቀን ከሌት እየተረባረቡ ነው፡፡ በእርግጥ የጁንታው የህልውና ጉዳይ ግላዊ ጉዳያቸውም ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ እነዚህን የጁንታውን የምእራብ ደጀኖች ማወቅ እና በስማቸው መጥራት አስፈላጊ ነው፡፡ ዛሬ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡
የዋሽንግተኑ ቡድን
በዚህ ቡድን ውስጥ ብዙ በግለሰብ ደረጃ ለህወሓት ስስ ልብ ያላቸው ሹማምንት አሉ፡፡በአብዛኛው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን በስልጣን ላይ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ በዘመነ ኦባማ አሁን ደግሞ በዘመነ ጆ ባይደንም ዋይት ሀውስ መግባት የቻሉት ግለሰቦች ሲሆኑ በተንሸዋረረ የውጭ ፖሊሲ እይታቸው የሚታወቁ ናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በዘመነ ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ አጥታዋለች የሚባለውን የአለም መሪነት ለመመለስ የሚሰሩ ሲሆን በተለይም ከቻይና ጋር ላለባቸው ፉክክር አፍሪካ ላይ አይናቸውን ጥለው የሚረባረቡ ናቸው፡፡ አሜሪካን ወደ መሪነት የመመለስ ጉዳይ በእርግጥ የራሳቸው የአሜሪካውያን ጉዳይ ነው። ነገር ግን ይህን ተልእኮ እንዲፈጽም ስልጣን የተሰጠው የፕሬዚዳንት ባይደን የውጭ ጉዳይ ቡድን ተልእኮውን ለማሳካት የሚሄድበት መንገድ መስመር የሳተ ይመስላል፡፡ ይህ መስመር መሳትም ቡድኑ ኢትዮጵያ የክልል ወሰኖቿን የቱጋ ማስመር እንዳለባት እና የጸጥታ ሀይሏን የቱጋ ማስፈር እንደሚገባት መመሪያ ለመስጠት ሲሞክር ታይቷል፡፡
የፕሬዚዳንት ባይደን የውጭ ጉዳይ ቡድን ከዚህ ቀደም ያለው ሪከርድ ሲታይ አሳሳቢ ነገሮች አሉት። ይህ ቡድን በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ስር በስልጣን በነበረበት ከ2008 – 2016 እ.ኤ.አ እስከዛሬ ድረስ ያላለቁ ሶስት ጦርነቶችን በሶስት ሀገራት አስጀምሮ የወጣ ነው፡፡በሊቢያ ፣ በሶሪያ እና በየመን እስከዛሬ የቀጠለው ነውጥ ይህ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት አልፎ ገብቶ ሊያነኩር የሚፈልገው የውጭ ጉዳይ ቡድን ያስጀመራቸው ቀውሶች ናቸው፡፡ በእርግጥ የአሁኑ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሀገራቸው ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊን ከስልጣን ለማንሳት መሞከሯ ስህተት እንደነበር በወቅቱ ከተከራከሩ የዋሽንግተን መሪዎች አንዱ ሲሆኑ አሜሪካ ለሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ተቃዋሚዎች የምትሰጠው ድጋፍ ውጤታማነት ላይም ጥርጣሬ ነበራቸው፡፡ ድጋፉ ጽንፈኛ ጂሀዲስቶችን እያደለበ እንደሆነ ባይደን ያምኑ ነበር፡፡ነገር ግን ባይደንን ያልሰማችው አሜሪካ ዛሬም ድረስ ያላለቁ እና የማለቅ አዝማሚያም የማታይባቸው ሶስት ጦርነቶችን አስጀምራ ወጥታለች፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ የሊቢያን ጉዳይ “የህይወቴ ትልቁ ስህተት” ያሉት ሲሆን ያኔ ምክትላቸውን ባይደንን ቢሰሙ ኖሮ ይህን ስህተት ባልፈጸሙ ነበር፡፡ነገር ግን ኦባማ ከባይደን ይልቅ በሂላሪ ክሊንተን የሚመራውን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰምተው ስህተት ፈጸሙ፡፡ ያን ታሪካዊ ስህተት እንዲፈጸም ካደረጉት ሰዎች መሀከል ደግሞ አንዷ በዘመነ ኦባማ የአሜሪካ የተመድ ተወካይ እና የህወሓት የልብ ወዳጅ የሆኑት ወ/ሮ ሱዛን ራይስ ናቸው፡፡ሱዛን ራይስ የቀድሞው አለቃቸው እና በአፍሪካ የዋሽንግተን ወኪል አድርገው የሾሟቸው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን የአፍሪካ አዲሶቹ ተስፋዎች ብለው የሰየሟቸው ሶስት መሪዎች ማለትም የዩጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቪኒ ፣ የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ እና የኢትዮጵያው መለስ ዜናዊ ወደ ስልጣን ሲመጡ መንበሩን ያለማመዱ ዲፕሎማት ነበሩ፡፡ ከቀዝቃዛው የአለም ጦርነት እና ከአፓርታይድ ስርአት መወገድ በኋላ ወደ ስልጣን የመጡት እነዚህ ሶስት መሪዎች አሜሪካ በአፍሪካ የምትፈልገውን አይነት አገዛዛ ያሰፍናሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር፡፡
ታዲያ ከነዚህ ሶስት የአሜሪካ ተስፋዎች እና የሱዛን ራይስ የልብ ሰዎች መሀከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሞቱ ወቅት ስርአተ ቀብራቸው ላይ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ረዥም የአድናቆት መወድስ ያቀረቡት ወ/ሮ ራይስ ‹‹ መለስ ዜናዊ ከሰለጠኑት ሀገራት መሪዎች ተርታ የሚሰለፍ ነው›› ሲሉ አሞካሸተዋቸዋል፡፡ ወ/ሮ ሱዛን ራይስ አሜሪካ ሙአመር ጋዳፊን ከስልጣን የማውረድ ታሪካዊ ስህተትን ስትፈጽም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ከፍተኛ ቅስቀሳ ያደረጉም ናቸው፡፡ ወ/ሮዋ ከዚህም የሚቀድም አሳፋሪ ታሪክም ያላቸው ናቸው፡፡ እሳቸው ራሳቸው በህይወቴ የምጸጸትበት ትልቁ ስህተት የሚሉት የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ ሲፈጸም በዝምታ ከተከታተሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሹማምንት ዋናዋም ነበሩ፡፡ ዛሬ ላይ በፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ፖሊሲዎች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተደርገው የተሾሙት ራይስ ፣አሁንም በዋይት ሀውስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክበብም ተደማጭነት ያላቸው ሲሆን የእሳቸው የሩዋንዳ ስህተታቸው ጸጸት የአሁኑ የዋሽንግተን የውጭ ጉዳይ ቡድን ከመሬት ተነስቶ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ማጥፋት ሊፈጸም ነው የሚል ሪፖርት እንዲያወጣ ያስገደደውም ይመስላል፡፡
ይሁንና ሊቢያ፣ ሶሪያ እና የመን ላይ ስህተት ሲሰራ በቦታው የነበሩት ሱዛን ራይስ ብቻ አልነበሩም፡፡የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊከንም በቦታው ነበሩ፡፡ በተለይም የየመን ጦርነት ሲጀመር ብሊንከን የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። የሊቢያ እና ሶሪያ ጦርነት ሲጀመርም ዋይት ሀውስ ውስጥ ከነበሩ ከፍተኛ ሹማምንት መሀከል ይገኙበታል፡፡በካቶ ኢንስቲትዩት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ቴድ ጋለን የባይደን የውጭ ጉዳይ ቡድን በብዙ ችግሮች የተሞላ ነው ይላሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሊቢያ እና በሶሪያ ጉዳይ የሚሊተሪ አማራጭን በመጠቀም የሚተቿቸው ሲሆን የባይደን የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫንም በጦርነትና በኃይል አገዛዞችን የመቀየር ስልትን በመደገፍ የሚታሙ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
እንግዲህ እንዲህ አይነቱ ሹማምንት ናቸው አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመፍታት እየሞከሩ ያሉት፡፡ ፕሬዚዳንት ባይደንም ሆነ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ጉዳይ በጎ ሃሳብ ሊኖራቸው እንደሚችል ቢታመንም ቅሉ ነገር ግን በአስተዳደራቸው ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የስራ ባህሪ እና ሪከርድ ግን ስጋት የሚፈጥር ነው፡፡ከላይ እንዳየነው አንዳንዶቹ ለጁንታው የተለየ ፍቅር ያላቸው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በተሳሳተ የፖሊሲ አካሄድ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታም አሁን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በስፋት እየታየ ነው፡፡ በሉአላዊት ሀገር ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ገብቶ ከመፈትፈት አንስቶ ፤ ለጁንታው ወንጀሎች ከለላ በመስጠት ፤ የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመንግስት ላይ በማካሄድ፤ የሀገሪቱን ገጽታ የማጠልሸት ስራ በሚዲያዎቻቸው እንዲካሄድ በማድረግ፤ ኢኮኖሚያዊ ጫና በመፍጠር እንዲሁም በእርዳታ ስም ጁንታውን ለማስታጠቅ በመሞከር በርካታ የፖሊሲ ግድፈቶች እየፈጸሙ ነው፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለ ማርያም ደሳለኝ በህግ ማስከበር ዘመቻው መጀመሪያ ላይ በፎሬን ፖሊሲ መጽሄት ላይ እንደጻፉት ከሆነ ጁንታውን ከፌደራሉ መንግስት ጋር በእኩል ሚዛን ማስቀመጥ ስህተት ነው። የአሁኑ የዋሽንግተን እና የብራስልስ ፖለሲ አውጪዎች አዝማሚያ ግን ከዚያም አልፎ ጁንታውን እንደተበዳይ የማየት እና በማንኛውም መንገድ የመደገፍ ነው፡፡ይህ አካሄድ አንድም የተሳሳተ ነው ፤ ደግሞም ውጤቱ አደገኛ ነው ብለዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ምናልባትም ህወሓት የእጃቸው ስራ ስለሆነ ሊሆን ይችላል፡፡የብሄራዊ ጥቅሞቻቸው ዘብ ስለሆነም ሊሆን ይችላል። ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ግን ይህ አደገኛ አካሄድ እንዲጠናከር በዋሽንግተን እና ብራስልስ ያሉ የጁንታውን ጉዳይ የግል ጉዳይ አድርገው እየደገፉ ያሉ ግለሰብ ባለስልጣናት ተጠያቂ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የቀድሞው የስራ ባልደረባቸው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሊቢያ የሰሩትን አይነት የሚያስጸጽት ስህተት እንዳይሰሩ መረጃ መውሰድ ያለባቸው ከጁንታው ሎቢስቶች እና የምእራብ ደጀኖች ሳይሆን ከነባራዊው ሀቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ሆነ አለም የሚፈልገው የአሜሪካ መሪነት እንዲህ አይነቱ በጣልቃ ገብነት እና በጫና ላይ የተመሰረተ እንዳይደለም ፕሬዚዳንቱ መረዳት አለባቸው፡፡
የፔካ ሀቪስቶ ዲፕሎማሲ
የአውሮፓ ህብረት የህግ ማስከበሩ ዘመቻ ከተጀመረ በኋላ ስለ ሰላም እና ሰብአዊ ጉዳዮች ለመምከር የፊንላንዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሀቪስቶ በልዩ ልኡክነት ወደ አዲስ አበባ ልኮ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰውየው የተፈጠረውን ችግር በመፍታት ፈንታ የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረትን ግንኙነት አደጋ ውስጥ በመክተት የተዛባ ስራ ሰርተው ተመልሰዋል፡፡ሰውየው ከሁለት ጉብኝቶች በኋላ ለአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ያቀረቡት ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስትን ያስቆጣ ነበር፡፡ በእርግጥም የሰውየው ሪፖርት ህወሓትን ተጎጂ የኢትዮጵያን መንግስት ደግሞ ተጠያቂ ያደረገ ብዙ የተፋለሱ ነገሮች ያሉበት ሪፖርት ነበር፡፡የኢትዮጵያ መንግስት የሰውየውን ሪፖርት የቅኝ ግዛት መንፈስ የተጫነው ነው ያለ ሲሆን፣ ከአሁን በኋላም በልዩ ልኡክነት ወደ አዲስ አበባ እንዳይመጡ አሳስቦ ነበር። የአውሮፓ ህብረትም ሰውየው ከአሁን በኋላ የረባ የዲፕሎማሲ ስራ እንደማይሰሩ በማመኑ ይመስላል በምትካቸው ጀርመናዊቷን አንቴ ዌበርን ልኮ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተነጋግረዋል፡፡ አዲሷ የአፍሪካ ቀንድ የህብረቱ ልኡክ በቀጣናው ዙሪያ ሰፊ ልምድ ያላቸው ነው ተብሏል፡፡ ነገር ግን የልኡኳ ስራ እንደ ሀቪስቶ እና መሰሎቻቸው ባሉ መፍቀሬ ህወሓት ባለስልጣናት እንዳይበላሽ ህብረቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ማሳሰብ ይጠቅበታል። ከዚህም ባለፈ ህብረቱ የዋሽንግተኑን ቡድን ተከትሎ በሊቢያ እና በሶሪያ የፈጸመውን ስህተት አሁንም እንዳይደግመው ጉዳዩን ፍትሀዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ሊይዘው ይገባል፡፡
ማርቲን ፕላውት
ከባለስልጣናት በተጨማሪ በምሁር ደረጃ ጁንታውን የሚደግፉ ግለሰቦች ደግሞ በሌላ ጎን አሉ፡፡ከነዚህ መሀከል አንዱ ማርቲን ፕላውት ነው። ፕላውት በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ምሁር ነን ከሚሉ ሰዎች አንዱ ሲሆን ዛሬ ላይ በይበልጥ የሚታወቀው ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ባለው የሰላ ትችት እና አሁን ላይ ለጁንታው እያሳየ ባለው ልባዊ ድጋፍ ነው፡፡ ይሁንና የፕላውትን ነገር ልዩ የሚያደርገው ሌላም ጉዳይ አለ፡፡ ፕላውት በ2010 እ.ኤ.አ ለቢቢሲ በሰራው ዘገባ ህወሓት በትግሉ ወቅት በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ረሀብ ለተረጂዎች ይላክ የነበረውን የእርዳታ እህል እየሸጠ የጦር መሳሪያ ይሸምት እንደነበር ዘገባ ሰርቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ለጦር መሳሪያ የዋለው ገንዘብም ከ95 ሚሊየን ዶላር በላይ ይደርስ እንደነበር ፕላውት በወቅቱ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ታዲያ ይህን የጁንታውን አሳፋሪ ዘገባ የሰራው ፕላውት ዛሬ ላይ ጁንታው ያንኑ መሰል ድራማ ደግሞ ሊሰራ ሲሞክር ግን ዋነኛ ደጋፊው ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡
ሄርማን ኮህን
ሄርማን ኮህን የህወሓት የክርስትና አባት ናቸው፡፡ጁንታው ከበረሀ ታጋይነት ወደ መንግስትነት ሲሻገር እና ስልጣንን ሲረከብ አስተባባሪ የነበሩት ኮህን በወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩ ሲሆን ለ38 አመታት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ ቆይተዋል፡፡ሰውየው ታዲያ በእጃቸው ላይ ተወልዶ አይናቸው እያየ የጎረመሰው ህወሓት ከስልጣን ሲወገድ ማየት የተመቻቸው አይመስሉም፡፡ በቻሉት መንገድ በሙሉ ህወሓትን ደግፈዋል፡፡ በየጊዜውም እሳቸው ቀብተው የሾሙት ቡድን የሚከተለው የብሄር ፌደራሊዝም እና ህገ መንግስት በአግባቡ እየተተገበረ እንዳልሆነ በመተቸት ለህወሓት ሂሳዊ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን ሰውየው የበቃቸው ይመስላል፡፡ ‹‹የክልሎች ልዩ ሀይሎች ወደ ትግራይ ለህግ ማስከበር ዘመቻ የተጓዙት ህወሓት ሲበድላቸው ስለኖረ ነው›› በማለት የክርስትና ልጃቸው የእጁን የሚያገኝበት ሰአት እንደደረሰ አምነዋል፡፡
ጄቲል ትሮንቪል
ኖርዌያዊው ምሁር ከጁንታው ዋነኛ አፍቃሪዎች ግንባር ቀደሙ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚያመላልስ የስራ ግንኙነት አለኝ የሚለው ግለሰብ ከጁንታው መሪዎች ፔሮል ላይ ስሙ እንደሚገኝ የሚናገሩም አሉ፡፡ ግለሰቡ ወደ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚመላለስ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የጨረቃ ምርጫ ያሉትን የትግራይ ምርጫ ብቸኛ ታዛቢ ሆኖም ነበር፡፡ ይህ ተግባሩ ሰውየው ለኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ያለውን ንቀት በይፋ ያሳየበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ግለሰቡ ከጁንታው ደጋፊነቱ ባለፈው የኢትዮጵያ እና ኖርዌይ ግንኙነትንም ለማበላሸት ጥሯል፡፡ ለህይወቴ የሚያሰጋ ማስፈራሪያ ደርሶብኛል፤ ስሜም እየጠፋ ነው በማለት ግላዊ ጉዳዩ ውስጥ የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንዲገባ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡በወቅቱ የኖርዌይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ኢነ ኤሪክሰን ሶሬይደ ጉዳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩን ሳይሆን ፖሊስን የሚመለከት ነው በማለት ሰውየውን ኩም እንዳደረጉት ሳይንስ ኖርዌይ የተባለ ድረገጽ ዘግቦ ነበር፡፡የሆነ ሆኖ ግለሰቡ ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ህግ ማስከበሩ ከመቀሌ ጓዶቹ የሚደርሰውን የቅጥፈት ዘገባ ማሰራጨቱን ቀጥሏል፡፡
ዊሊያም ዴቪድሰን
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለራሳቸው የሊቅነት ማእረግ ከሰጡት ግለሰቦች መሀከል አንዱ ዊሊያም ዴቪድሰን ነው፡፡ ለእንግሊዙ ጋርዲያን እና ሌሎች አለምአቀፍ ሚዲያዎቸ ዘገባ ይጽፍ የነበረው ዴቪድሰን ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በጋዜጠኝነት ቢሆንም በኋላ ላይ በግጭቶች ላይ ዳሰሳ እና ትንተና ለሚሰጠው ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ተቀጣሪ ሆኗል፡፡ ግለሰቡ እንደ ብዙ ምእራባውያን ስለ ኢትዮጵያ ያለው ግንዛቤ ከሚያየው ላይ ብቻ የተመሰረተ እና በምእራባዊ መነጽር ብቻ የሚመለከት ግለሰብ እንደሆነ የሰራቸው ዘገባዎችም ሆነ የሚሰጣቸው ትንታኔዎች አመላካች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከተሰጠው ፈቃድ ውጪ ሌላ ተልእኮ ላይ ተሰማርቶ ያገኘውን ዊሊያም ዴቪድሰን ባለፈው ህዳር ወር ከሀገሪቱ ለቅቆ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡ሆኖም አሁንም ቢሆን ስለ ኢትዮጵያ ደግ ከማያወሩት ግለሰቦች አንዱ ነው፡፡
አሌክስ ደዋል
ብሪታንያዊው አሌክስ ደዋል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ላይ ግላዊ የሚመስል ጥላቻ ካላቸው ሰዎች መሀከል አንዱ ነው፡፡ ሰውየው ይህ ስሜቱ ኢትዮጵያን አስመልክቶ በሚጽፋቸው ጽሁፎች የሚታይ ሲሆን፣ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ሰሞኑን በቱፍት ዩኒቨርሲቲ ድረገጽ ላይ ያሰፈረው ጽሁፍ ነው። በጽሁፉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ኢምፓየር ለመገንባት እየጣሩ ነው በሚል የሚከሰው ደዋል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ሲረከቡ ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ላይ ነበረች ፤ ኢህአዴግ ዴሞክራሲያው እየሆነ ነበር፤ ከኤርትራ ጋርም ሰላም ለመፍጠር ዝግጅት ላይ ነበረች በማለት አስደናቂ ቅጥፈት ይጨምርበታል፡፡ከሁሉ አስደናቂው ውሸት ግን ዐብይ ወደ ስልጣን የመጣው በአብዛኛው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው የሚለው ቅጥፈት ነው፡፡ይህ ቅጥፈት ለውጡ እንዲመጣ ህይወታቸውን እና እድሜያቸውን ለገበሩ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስድብ ነው፡፡በጥቅሉ በጽሁፉ ውስጥ ሰውየው በህወሓት ከስልጣን መወገድ የተሰማው ብስጭት በይፋ የሚታይበት ግለሰብ ነው፡፡
በጥቅሉ ሲታይ ዛሬ ላይ ሊኖረው ከሚገባው በላይ አጃቢዎች እና ደጋፊዎች በምእራቡ አለም አግኝቷል፡፡አንዳንዶቹ ከጁንታው ጋር ባላቸው ግላዊ ጥቅም የተሳሰሩ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ በዚህ መልኩ የሀገራቸውን እና የግላቸውን ፖለቲካዊ አጀንዳ ለማስፈጸም የሚጠቅማቸው ዋነኛ መጋለቢያ ፈረስ ህወሓት በመሆኑ ነው ጥብቅና የቆሙለት ወይም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ባለፈው እሁድ በፌስቡክ ገጻቸው እንዳሉት ህወሓት በታሪክ ብቸኛው የገዛ ሀገሩን ለማጥፋት ተግቶ የሚሰራ ድርጅት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ጁንታውን ለማዳን በምእራባዊ ደጀኖቹ በኩል የሚደረገው ርብርብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዛቱት ጁንታውን እንደ አረም ከመነቀል የሚያድነው አይመስልም፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2013