የኢትዮጵያ ካንሰር የሆነው ህወሓት ባልጠበቀው ሁኔታ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ተነቅሎ በመማጸኛ ከተማው መቀሌ መሽጎ ዳግም በትረ ስልጣኑን ለመቆጣጠር ሰይጣን የሚጸየፈውን ወንጀል ሲሰራ ከርሟል። ይህ ጁንታ ቡድን ይባስ ብሎ መንግስት ለሰላም የዘረጋውን እንጅ እንደሽንፈት በመቁጠር ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ከጀርባው ወጋ። ይህንን ተከትሎ መንግስት ሳይወድ በግድ ላፉት ስምንት ወራት በክልሉ ህግን የማስከበርና የህሎና ዘመቻ ሊገባ ችሏል።
ነገር ግን መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ አሁን ላይ ክልሉን ለቆ ወጥቷል። “ለውሻ ከሮጡለት፣ ለልጅ ከሳቁለት” እንደሚባለው መንግስት ያለምንም ውጊያ ለትግራይ ህዝብ ሰላም ሲባል ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ አሸባሪው ሕወሓት በእርሱ ኃይል የተገኝ ድል በማስመሰል መንግስት ራያና ወልቃይትን ለቆ እንዲወጣ የሚሉ ሰባት ቅድመሁኔታዎችን አስቀምጧል።
ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ “እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ” እያለች እያስቸገረች ያለችው አሜሪካ መንግስት የትግራይ ክልል አከላለሉ ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት ይመለስ የሚል ትዕዛዝ ሰጥታለች። በዚህም አንዳንድ አንባቢዎቻችን ወደ ዝግጅት ክፍላችን በመደወል አሜሪካ ወደዚህ ይከለል ወዳዛ እንዳትሄዱ የማለት ምን ህጋዊ መሰረት አላት? በህገ መንግስቱ መሰረት የክልሎች ወሰን ተሰምሯል ወይ? የሚል ጥያቄ በማንሳት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ እንድንሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል። የዝግጅት ክፍላችንም በጉዳዩ ዙርያ ባለሙያ አነጋግሮ የሚከተለውን ምላሽ ይዞላቹህ ቀርቧል።
አንባቢዎቻችን ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ ምስጋናው ጋሻው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ የአስተዳደር ስርዓት ስር በየጊዜው የሚቀያየር የግዛት አስተዳደር ነበራት። ስለዚህ አሁን ያለው ህገ መንግስት ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት ወታደራዊው መንግሥት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ መዋቅር መሰረታዊ ለውጥ ተደርጎበት በዋናነት ቋንቋን መሰረት ባደረገ ሁኔታ የአስተዳደር ክልሎች ተመስርተዋል።
ከሰማኒያ በላይ የተለያየ ሐይማኖት፣ ቋንቋና ባሕል ያላቸው ሕዝቦችን መብትና ጥቅም ያስከብራል በሚል ዋና ዋና በሚባሉትና በርካታ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው ብሔሮች ዙሪያ ውስጣዊ የአስተዳደር ሥርዓቱን ማዋቀር በወቅቱ የሃገሪቱን የመሪነት ሚና የተረከቡት ኃይሎች ዋነኛ ሥራ ነበር።
በዚህም ለዘመናት ኤርትራን ጨምሮ በ14 ክፍላተ ሃገራት የተዋቀረው የአስተዳደር ሥርዓት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በአዲሱ ቋንቋን መሰረት ባደረገ የፌደራል አስተዳደራዊ አወቃቀር አንዲተካ ተደርጓል። ይህም የሆነው ሃገሪቱ የምትተዳደርበት ሕገ መንግሥት ከመጽደቁ በፊት በተቋቋመው ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት አማካይነት ነበር ይላሉ።
መምህሩ የወቅቱ አከላለል 14 ክልሎች እንዲፈጠሩ ያደረገ ሲሆን በሽግግሩ ወቅት በአዋጅ ቁጥር 7/1984 መሰረት አዲስ የክልል አወቃቀር ሲታወጅ፤ ህወሓት የነበረውን ወታደራዊና የፖለቲካዊ የበላይነት ተጠቅሞ በተለያዩ ክፍለ ሃገር ግዛት ስር የነበሩ ግዛቶችን ቆርሶ በራሱ ክልል ስር ከልሏል። ስለዚህ አሁን ያለው የክልሎች አከላለል በህገ መንግስቱ መሰረት የተደረገ አለመሆኑን ይናገራሉ
ህወሓት በሴራ እነዚህን ግዛቶች ወደ ክልሉ የማካለል ስራ ሲሰራ የነበረው የደርግ መንግስት ከመውደቁም በፊት እንደነበር አቶ ምስጋናው ጠቁመው፤ በትጥቅ ትግል ወቅት ህወሓት እየተቆጣጠረ የመጣቸውን አካባቢዎች ወደ ትግራይ ክልል እያጸና ነው የመጣው። ለአብነት የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢ የማንነት ጥያቄ ብናይ ከ1970ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ከደርግ መንግስት ጋር በነበረው ጦርነት አንድ ጊዜ ደርግ ሌላ ጊዜ ህወሓት ወይም ሌሎች የትጥቅ ትግሉን ተቀላቅለው የነበሩ እንደነ ኢህዲን የመሳሰሉት በተለያየ ጊዜ ቦታውን ሲቆጣጠሩት ነበር። ነገር ግን ህወሓት ቤተመንግስትን ከተቆጣጠረ በኋላ በጦርነት ጊዜ ሲያዙ ሲለቀቁ የነበሩ እንዚህንና መሰል አካባቢዎችን ወደ ትግራይ ክልል እንዲካለሉ ማድረጉን ይናገራሉ።
ከአፋር፣ ከጎንደር፣ ከወሎ ክፍለ ሃገራት ቆርሶ የወሰዳቸው አካባቢዎች ህገ መንግስትን መሰረት ያደረጉ ሳይሆኑ ጁንታው በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካና ወታደራዊ ኃይል ተጠቅሞ በኃይልና በማናለብኝነት የወሰዳቸው አካባቢዎች እንደሆኑ መምህሩ ጠቅሰው፤ በአዋጅ ቁጥር 7/1984 መሰረት አዲስ የክልል አወቃቀር ሲታወጅ 14ቱ ክፍለ ሀገራት ወይም በ1987 ዓ.ም ህገ መንግስቱ ሲወጣ በህገ መንግሰቱ አንቀጽ 47 ላይ የተዘረዘሩ ዘጠኝ ክልሎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጭምር በህገ መንግስቱም ሆነ በአዋጁ የአንዱ ክልል ወሰን እዚህ ነው፣ እዚያ ነው የሚል ድንበር በክልሎች መካከል አልተሰመረም። ነገር ግን በህገ መንግስቱ አዲስ ክልሎች ሊፈጠሩበት የሚችል እድል ተቀምጧል። በዛ መሰረት እንደ ሲዳማ አይነት አዲስ ክልል ተፈጥሯል። ነገም ይፈጠራል። ስለዚህ ህገ መንግስቱ ለነባር ክልሎችም ሆነ አዲስ ለተዋቀረው ለሲዳማ ክልል ይሄነው ወሰንህ ብሎ ያስቀመጠው ድንበር አለመኖሩን ተናግረዋል። ነገር ግን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች በወሰንና በማንነት ጉዳዮች ላይ አለመግባባት ሲፈጠር የሚፈታበት አግባብ ላይ ግልጸነት እንደሚጎለው ጠቁመው፤ በቤኒሻንጉልና በአማራ፣ በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ፣ በአፋርና በትግራይ፣ በአፋርና በሶማሌ ወዘተ በሁሉም ክልሎች በሚባል መልኩ ወያኔ ባሰመረው የክልል አከላለል የሚነሱ አለመግባባቶች አሉ።
ስለዚህ ይሄንን ጉዳይ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበት እድል አለ። ችግሩ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ የሚፈታው በአገር ውስጥ ጉዳይ ብቻ ነው። ነገር ግን አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብታ ወዳዛ ይከለል ወደዚህ ይከለል እያለች በውስጥ ጉዳያችን እየገባች የምታቦካው ከወደ ጀርባ የግል ጥቅሟን ለማሳካትና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ለሚሰሩ ኃይሎች ጋሻ ጃግሪ መሆኗን ነው የሚያሳይ ብለዋል።
በአጠቃላይ አሜሪካ በቀጠናው ላይ ያላትን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማስጠበቅ ካልሆነ በቀር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያስገባት የአለም አቀፍም ብሎም የአገር ውስጥ የህግ መሰረትም የለም። የአሜሪካ አቋም ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጥስ ነው። ነገርግን የአሜሪካን ፍላጎት በዚህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በህዳሴው ግድብም፣ መንግስት በወሰደው ህግን የማስከበር ዘመቻ ጣልቃ መግባቷ ሲታይ ከዛ በላይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄንን መረዳት አለበት።
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል፡፡
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2013