በአገራችን አዙሪት በሽታ ይሁን ወይም አይሁን ይህ ፀሀፊ ባያውቅም የጤና እንዳልሆነ ግን ይገነዘባል። መገንዘቡም ከመሬት የወጣ ወይም ከሰማይ የወረደ ሳይሆን “ምን እንደ ጦስ ዶሮ ያዞርሀል/ሻል” ከሚለው እድሜ ጠገብ አበሻዊ አባባል ነው። ከዚህ ባህርይን፣ ተግባርን፣ እንቅስቃሴን፣ ጤናን ወዘተ በአንድ እቅፍ ቅስጥ አድርጎ ከተነገረ አባባል ከርእሰ ጉዳያችን ጋር ሊሄድ የሚችለውን ፍሬ ነገር ስንመዝ የምናገኘው ትርጉም ከጤና መጓደል ባለፈ የፖለቲካ ዝንፈትም ነውና አደጋው በግለሰብ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን አገርንና ህዝብንም ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችል መሆኑን ነው።
የአገርና ህዝብን አመራር ሀላፊነት ደግሞ የወደቀው “መንግሥት” በሚባለው ተቋም ትከሻ ላይ ነውና ያ መንግሥት እንደ ጦስ ዶሮ አዙሪት ውስጥ ከገባ፤ አዙሪት ከተጠናወተው ጉዳቱ መጠነ ሰፊ ይሆናል፤ (ወደዱም ጠሉም አብረው ናቸውና) ሰላማዊ ዜጎችንም ይረብሻል፤ ዲፕሎማሲን ያቀጭጫል፤ የታሪክ ተጠያቂነትን ያስከትላል።
ነገሩ “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ውሀ ይጠጣል” እንደሚባለው ነውና ጥሩው ይደፈርሳል፤ ሰላማዊ የሆነው ይናጋል፤ ሰፈር መንደሩ ይበጠበጣል። ይህ ደግሞ በዘዋሪቷ (የጦስ ዶሮዋ) ግብፅና አጫፋሪዋ ሱዳን እየታየ ነውና ችግሩን ለመረዳት ቅጠል መበጠስ ወይም ሳር መንጨት አያስፈልግም።
አዙሪት አንዱ መገለጫው መንቀዥቀዥ ነው። መንቀዥቀዥ እንደ አዙሪት ሁሉ በሽታ ነው/አይደለም የሚለውን እንኳን ብንተወው አቅል የማጣትን ሁኔታ ያሳያልና ይህም በግብፅ ሲታይ እንደኖረው ሁሉ እየታየም ነው። አቅል የመሳት ሁኔታ ደግሞ ወደ ለየለት እብደት ሁሉ ሊያመራ ይችላልና ካበደው ጋር የሚያብድ መኖር ስለሌለበት ወደ ስራ መግባቱ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አመራጭ ይሆናል – ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ታይቷልና ስለተገቢነቱ ማረጋገጫ ሊሆን ይችላል።
ይህ የአዙሪት፣ የመንቀዥቀዥ፣ አቅል የመሳት . . . ባጠቃላይ የጦስ ዶሮነት ባህርይ ከነዘርማንዘሩ የሰፈረው ግብፅና ተዛዥዋ ሱዳን ላይ ስለመሆኑ (እያዘንንም፣ እየታዘብንም፣ እየተናደድንም . . . ቢሆን) እየተመለከትን ነው። ማረጋገጫችን ደግሞ የግብፅ የዙረት አባዜ ከሰሜን ዋልታ እስከ ደቡብ ዋልታ፤ ከፀሀይ መውጫ እስከ ፀሀይ መጥለቂያ፤ ከዳር እስከ መሀል . . .፤ ባጭሩ ምንም አይነት ገደብ ወይም አቅል በሌለው ሁኔታ፤ ትንሽም እንኳን የጥሞና ጊዜ ለሯሷም ሆነ ታኮዋ (ሱዳን) ሳትሰጥ እንደ ጦስ ዶሮ የመዞሯ ጉዳይ ነውና በጉዳዩ ኢትዮጵያ የማሸነፏን ያህል ለወንድምና እህት አፍሪካዊያኑ አገራት ታዝናለች።
ሰውየው (ነጋዴ ነው) ሽንኩርት በሽልንግ ገዝቶ ወደ ሌላ ገበያ ሄዶ ሸጦ ሲመጣ “ስንት ሸጥክ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦለት “ሽልንግ” ሲል ይመልሳል፤ “ስንት ገዝተህ?” ለሚለውም “ሽልንግ” የሚል ነው መልሱ። በመልሱ የተገረሙት እንደገና ሌላ ጥያቄ ያቀርቡለታል፤
“ምን አተረፍክ?”
“ዘጥ ዘጥ”
በግብፅና ሱዳን በኩል እየታየ ያለው ይሄውና ይሄው ብቻ ነው። ሁሌም ትርፋቸው ዘጥ ዘጥ እንጂ ሌላ ሆኖ አያውቅም። ወደ ሰሜን አቀኑ ወደ ደቡብ፤ ወደ ምስራቅ ነጎዱ ወደ ምእራብ የእስከዛሬው ትርፋቸው ከዘጥ ዘጥ አልፎ፤ ተግባራቸውም ከጦስ ዶሮዋ ተግባር ተለይቶ አያውቅምና “የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ ወደ ስራ መግባት እንጂ ሌላ ምን ማድረግ ይቻላል?
በመሰረቱ “ምን እንደ ጦስ ዶሮ ያዞርሀል/ሻል” የሚለው ሌሎች ብዙ አቻዎች ያሉት ሲሆን “ምን እንደ ባለጌ ወንበር ያሽከረክርሻል/ሀል”፣ “ምነው እንደ ራስ ሆቴል በር ተሽከረከርክ” እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው።
ዛሬ ላይ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድባችን ማጠናቀቂያ ላይ ሆነን፣ የግብፅንና ታኮዋ ሱዳንን የዘመናት መንቀዥቀዥ አስበን . . . “ምን እንደ ጦስ ዶሮ ያዞርሀል/ሻል”ን ስንመረምረው መልእክቱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
አስተውል፣ ረጋ በል፣ ፍሬውን ከገለባው፣ እውነቱን ከሀሰቱ፣ ብስሉን ከጥሬው ለይ ወዘተ ማለት ሲሆን ግብፅና ታኮዋ የሳቱት መሰረታዊ ጉዳይ ይኸው ሲሆን፤ ትርፋቸውም ዘጥ ዘጥ ይሆን ዘንድ ግድ ያላቸውም ይኸው እንደ ጦስ ዶሮ የመንቀዥቀዣቸው ጉዳይ ነው።
የሥነመንግስት ፍልስፍና እንደሚያስተምረው እንደ መንግስትና አገር መንቀዥቀዥ አይመከርም። በተለይ እንደ የመንግስት አካልና አመራር የሚፈለገው ስክነት፣ የጥሞና ጊዜ፣ አስተውሎት እንጂ መንቀዥቀዥ ለመንግስትም ሆነ አመራሩ የተሰጠ መክሊት አይደለም።
በዲፕሎማሲውም ዘርፍ እንደ ጦስ ዶሮ መንቀዥቀዥ ለመንግስት አመራር የተሰጠው አይደለም፤ ወይም አልተፈቀደም። መክሊቱ በሳል አመራር፣ ሰጥቶ መቀበል፣ ፍትሀዊነት፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነትንና የመሳሰሉትን ህዝባዊ፣ አገራዊና አለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላቸውን መርሆዎች መከተል፣ ማክበርና ማስከበር እንጂ የሽልንግ ሽንኩር ገዝቶ መልሶ ሽልንግ መሸጥ አይደለም።
ምናልባትም የ”ዘጥ ዘጥ” አትራፊውን ነጋዴ ጉዳይ ከንግድ (ኢኮኖሚክስ) አኳያ ብንመለከተው አቶ ዘጥ ዘጥ ከአሁኑ የግብፅና ታኮዋ የጦስ ዶሮነት ተግባር የተሻለ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን። ምክንያቱ ደግሞ በንግድ አለም፣ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ማትረፍና አለማትረፍ እንዳለ ሁሉ መክሰርም አለና አቶ ዘጥ ዘጥ እንደነ ግብፅ ባለመክሰሩ ይመሰገናል፤ ወይም አስተዋይ ነጋዴ ነው ማለት ነው – ቢያንስ አልከሰረም።
እየተነጋገርን ያለነው ግብፅና ታኮዋ ሱዳን ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ያስቆምላቸው ዘንድ ለአንድ ሚሊዮነኛ ጊዜ “አቤት” ማለታቸውና የፀጥታው ምክር ቤት “እኔ አያገባኝም። ጉዳያችሁ እዛው በአፍሪካ አንድነት በኩል ጨርሱ” ሲል ክሱን ቀድሞውኑ ኢትዮጵያ “የአፍሪካ ህብረት ይዳኘን” ስትል ወደ ነበረው መድረክ መመለሱ ነው።
ይህ ብቻም አይደለም ገራሚውና አስገራሚው ጉዳይ፤ ከሁሉም ከሁሉም ብዙዎችን ያስደመመው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ልክ ከውሳኔው በኋላ የውሃ ሀብትን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጠቀሙ ለአፍሪካ የወደፊት የጋራ ተጠቃሚነትና ትብብር መሰረት መሆኑን በመግለፅ “Africa: Water Courses Can Be The Foundations for Cooperation” የሚል የጽሑፍም የምስልም መግለጫ ማውጣቱ ነው። (“በኢኮኖሚክስ ሕግ አቶ ዘጥ ዘጥ ይሻላል” ያልንበት ምክንያት እዚህ ጋ ከትፈ ሲል!!!)
ከሰሞኑ ደግሞ የግብጹ መሪ አልሲሲ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እንድታሸማግላት እስራኤልን መጠየቋ ስንሰማ ዘጥ ዘጡ እንደቀጠለ ለመረዳት ችለናል፡፡ ሆኖም ግን እስራኤል እዛው አፍሪካ ህብረት ጉዳይሽን ጨርሺ ብላ ኩም አድርጋ መልሳታለች፡፡
በመጨረሻው መጨረሻ – ውሾቹ ይጮሀሉ፣ ግመሉ ይሄዳል!!!! ቸር እንሰንብት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2013