በመልካም ማሳ ውስጥ የሚበቅል አረም ሳይፈለግ የበቀለ ከመሆኑም ባሻገር ምግብና ውሃ በመሻማት ሰብሎች እንዲቀጭጩ ያደርጋል፡፡ አረም ያልተገባውንና የራሱ ያልሆነውን በጉልበት በመውሰድ የሰብሎችን ጤና ያውካል፤ያቀጭጫል ይባስ ሲልም ህልውና ያሳጣል ፡፡ በዚህ የተነሳም የሰው ልጆች በምግብ እህል እጦት እንዲቀጡና በድርቅና ረሃብ እንዲረግፉ ምክንያት ይሆናል፡፡
አሸባሪው ህወሓትና አረም አንድ ናቸው፡፡ ሳይፈለጉ በቅለው ለሌሎች መከራና ችግርን የሚዘሩ፤ የራሳቸው ያልሆነን ሃብትና ንብረት በግፍ የሚነጥቁና ሌላውን መና የሚያስቀሩ፤በመኖራቸው ጉዳት እንጂ ምንም ጥቅም የሌላቸው ከንቱዎች ፡፡ ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ‹‹አረሙን ከስንዴው ለይተን እንነቅለዋለን›› ሲሉ አሸባሪው ህወሓትን ከአረም ጋር አመሳስለው የገለጹት፡፡
አሸባሪው ህወሓት አረም ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ሥነምግባርና ሥነ ልቦና ውጪ የሆነ ወፍ ዘራሽ ፍጥረት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ነጻነት እና ሉዓላዊነት ሲሉ ህይወታቸውን ለመስጠት የማይሳሱ፤ግፍና በደልን የሚጠሉ፤ሁሉንም በአንድ ዓይን የሚመለከቱና እንግዳ ተቀባይ ሕዝቦች ናቸው ፡፡ አሸባሪው ህወሓት ግን የተለየ ነው ፡፡ ገና ከጥንስሱ ጀምሮ በሴራና በተንኮል ያደገ፤ከመስጠት ይልቅ መንጠቅን የተካነ፤ ከአንድነት ይልቅ መለያየትና መከፋፈል የሚያረካው የክፋት ተምሳሌት ነው፡፡ ብሔርን ከብሔር ፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት እያጋጨ ህልውናውን ማስቀጠል የሚፈልግ ከፋፋይ ፍጥረትም ነው፡፡ ካለው ላይ ቀንሶ ተካፍሎ መብላትን መለያው ካደረገው ከኢትዮጵያውያን ሥነምግባር በተለየ መልኩ በሰው ስቃይ የሚረካ ፤በሰዎች ረሃብና እርዛት ህልውናውን ማስቀጠል የሚሻ እና በሺዎች ዕልቂት ላይ ማንነቱን የገነባ አረምም ነው፡፡
ይህ አረም ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያውያንን በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል ኢትዮጵያዊነትን ሲያዳክም ቆይቷል ፡፡ ለውጭ ባዕዳን ተንበርካኪ በመሆን የኢትዮጵያውያንን ጥቅም አሳልፎ ሰጥቷል፤ የቻለውንም ያህል ዘርፏል፡፡ ድርጊቱን በተቃወሙት ላይ ለመስማት የሚዘገንኑ ግፎችን ፈጽሟል ፡፡ ጥፍር ነቅሏል፤ በወንድ ልጅ ብልት ላይ የላስቲክ ውሀ አንጠልጥሏል፤ንጹሃንን ከአራዊት ጋር አስሯል፡፡ በደረሰባቸው ስቃይ ብዙዎቹ ለአእምሮ ህመም ተዳርገዋል ። ሽባ ሆነዋል ። እግራቸው ተቆርጧል ። በማዕከላዊ ፣ በቃሊቲ ፣ በቅሊንጦ ፣ በሽዋ ሮቢትና በሌሎች “ማረሚያ” ቤቶችና ስውር ማሰቃያ ቦታዎች ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ ፈጽሟል፤አስፈጽሟል ።
በዚህ ሁሉ ግፍና መከራ የተማረረው ሕዝብም ይህንን አረመኔ ቡድን ከሥልጣኑ መንቅሮ መቀሌ እንዲሸሸግ ቢያደርገውም ቡድኑ በሰራቸው ግፎች ከመጸጸት ይልቅ ዳግም የጥፋት ሾተሉን ስሎ ኢትዮጵያውያንን አቁስሏል። በሁሉም የአገሪቱ ክፍል እሳት በመለኮስ አገሪቱ እንድትነድ የቻለውን ሁሉ አድርጓል ፡፡ ከኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበርም አገሪቱ እንድትፈራርስ በብርቱ ደክሟል ፡፡ ይባስ ብሎም የህልውናው መክሰሚያ የሆነውን ጥቃት በመከላከያ ሠራዊት ላይ በመፈጸም ከሃዲነቱን በገሃድ አሳይቷል ፡፡ በዚህም በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ በየዋሻው ለመደበቅ ተገድዷል ፡፡ እንዳያንሰራራም አከርካሪው ተመትቷል፡፡
ሆኖም ለትግራይ ሕዝብ ቀናኢ የሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ በማሰብ ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮት ከነበረው የትግራይ መሬት ለቆ መውጣቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዳግም የጥፋት መርዙን መርጨት ጀምሯል ፡፡ የትግራይ ሕዝብን በማደናገርና ‹ተከበሃል› የሚል ማደናገሪያ በመፍጠር ህጻናትን እና አረጋውያንን ሳይቀር ለጦርነት በማሰለፍ ላይ ይገኛል ፡፡ ከራሱ ህልውና በስተቀር ለሕዝብ ህይወት ደንታ የሌለው ይህ ቡድን የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ እንዳይገባ በመከልከል ጭምር ኢሰብዓዊና አረመኔያዊ ድርጊቱን እየገፋበት ይገኛል፡፡
የአሸባሪው አረመኔያዊ ድርጊት ያበሳጨው የአዲስ አበባ ነዋሪ በትላንትናው ዕለት በነቂስ በመውጣት ቡድኑ በሕዝብ ላይ የሚፈጽማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ኮንኗል፤የአገሪቱ የህልውና መሰረት ለሆነውም የመከላከያ ሠራዊት ያለውን አጋርነቱን አሳይቷል ፡፡ በሰልፉም ላይ ‹‹የኢትዮጵያ አንድነት ይጠናከራል››፤ ‹‹ ኢትዮጵያውያን ለማፍረስ የሚሞክሩ ወገኖች ፈርሰው ይቀራሉ››፤ ‹‹መከላከያ ታማኝ የህልውናችን መሰረት ነው››፤ “የትግራይ ህዝብ አካላችን ህወሓት ጠላታችን “፤‹‹ የጁንታው ቡድን ከስሩ ይነቀል ›› የሚሉና መሰል አገራዊ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያውያን በጁንታው ድርጊት ምን ያህል እንደተማረሩና ጁንታውንም ለመንቀል መክፈል ያለባቸውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ በአጠቃላይ የህልውና አደጋ የሆነውን አሸባሪው የህወሓትን ቡድን እንዳይመለስ አድርጎ መንቀል ለነገ ይደር የማይባል ሥራ ነው!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2013