ለዛሬው ጽሁፌ ሁነኛ መነሻ እንዲሆነኝ የኢፌዲሪ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በህግ ማስከበር ወቅት የተናገሩትን አስታውሼ ልነሳ! የጀግናን ስሜት፣ ንግግርና ተግባር መዋስ መልካምነቱ አጠያያቂ አይደለምና ነው ይኽንን የመረጥኩት።
ጄኔራሉ የአሸባሪውን የህወሓት ጁንታ የቁልቁለት ጉዞ አስመልክተው ሲናገሩ ወገኖቼ እንዲህ ያለ ነገር በዘራችሁ አይድረስ ብለው ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት“አንድ ትልቅ ሃገር ሲመራ የነበረ ፓርቲ፣ በሌብነት በዘረፋና በጭቆና በህዝብ አክእንትፍ ተብሎ ተተፍቶ ወደ መቀሌ ሲሰደድና የአንድ ክልል አስተዳዳሪ ሲሆን፣ ይኽም ትምህርት አልሆንህ ብሎ የለመደው የዝርፊያና እኔ ካልገዛሁ አገር ትፍረስ የሚል የተሳሳተ ዕሳቤው የማይሞከረውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከጀርባ በመውጋት የሃገር ክህደት ፈጽሞ ከክልል አስተዳዳሪነትም ወደ በረሃ ሽፍታነት ሲቀየር” እንዲህ ያለ ውርደት በዘራችሁ አይድረስ።
“አጉል የበላይነትን የለመደ አካል እኩል እንሁን ስትለው የተበደለ ይመስለዋል የሚለው የዶክተር ዐብይ አሕመድ የአንድ ወቅት ንግግርም ለጁንታው ስግብግብ ባህሪ ጥሩ መገለጫ እንደሆነ ይሰማኛል” ሽብር ሴራና ዘርፊያ መለያው የሆነው ይሄ አሸባሪ ድርጅት በመላ ኢትዮጵያውያን የነጻነት ታጋዮች ክቡር መስዋዕትነት ያገኘውን አገር የመምራት ዕድልም ዜጎችን ለማሰቃየት፣ አገር ለመዝረፍና ለአጉራዘለል ባህሪዎቹ ተጠቅሞበታል።
አሸባሪው ህወሓት በበበረሃ በኖረበት17 ዓመታት ሙሉ ሴራ ሲጎነጉን፣ ሸፍጥ ሲሰራ፣ የተንኮል ዕቅድ ሲነድፍ፣ የጠልፎ መጣል ስልት ሲያቀነባብር፣ ያለምንም ድካምና ዋጋ እንዲሁም ዕውቀት የስልጣን ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ የሚያስችለውን የሀሳብ ቀመር ሲቀምርና የግድያና ፍጅት ሂሳብ ሲያሰላ የኖረው ሰው በላ ቡድን ነው። ህወሓት በአውደ ውጊያ ካሳለፋቸው ዓመታት ይልቅ በየዋሻውና በየሸለቆው አድፍጦ የጥፋት ሴራ ሲጠነስስ የነበረባቸው ዓመታት በብዙ እጥፍ ይበልጣሉ።
የግራ ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱትን ሲያገኝ የሶሻሊስትነት ካባ ደርቦ በመቅረብ የቀኝ ርዕዮተ ዓለም ከሚያራምዱት ፊት ደግሞ ማርክሲስት ሌኒንስት ካባውን ሳያወልቅ የሊበራልነት ካባ በላዩ ላይ ደርቦ በመታየትና እንደ እስስት ቆዳውን በመቀያየር በመስሎ አዳሪነት ባህሪውም የሚያክለው የለም።
አሸባሪው ህወሓት ገና ስሙን ሳይቀይር ተሓህት/ ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ/ ይባል በነበረበት ወቅት ግገሓት/ ግምባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ/ ከተባለው ከእሱ በፊት ተመስርቶ በትግራይና በኤርትራ አዋሳኝ መሬቶች ላይ ይንቀሳቀስ በነበረው የታጠቀ ድርጅት ጋር ሙሉ በሙሉ ውህደት ለመፈፀም ስምምነት ላይ ይደርሳል። ቀጥሎም ሁለቱ ድርጅቶች ማለትም ተሓህት-ህወሓት እና ግገሓት ውህደት ወደሚፈፅሙበት ቦታ ምስራቅ ትግራይ ዘገብላ ተብላ ወደ ምትጠራው ቦታ ሰራዊታቸውን ወስደው ካሰፈሩ በኋላ አመሻሽ ላይ የተሓህት-ህወሓት አመራሮች ቀን ሲሸርቡት የዋሉትን ሴራ ለሰራዊታቸው በጠቅላላ በምስጢር እንዲተላለፍ አደረጉ።
ይህም ሴራ እያንዳንዱ የተሓህት-ህወሓት ታጋይ ከግገሓት ታጋይ ጋር ጥንድ ጥንድ እየሆኑ እንዲተኙና ግገሓቶች እንቅልፍ ወስዷቸው የተኩስ ትዕዛዝ እስኪተላለፍ በንቃት እንዲጠባበቅ የሚል ነበር። ከዚያም እኩለ ሌሊት ላይ የግገሓት ሰራዊት በእንቅልፍ ላይ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ የተሓህት-ህወሓት ታጋዮች ከጎን ከጎናቸው ከተኙ የግገሓት ታጋዮች ላይ እንዲተኩሱ በምልክት ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ለውህደት የመጣው የግገሓት ሰራዊት ከነመሪዎቹ በእንቅልፍ ላይ እንዳለ ተጨፍጭፎ ሙሉ በሙሉ ተደመሰሰ።
አሸባሪው ህወሓት ደርግ እንዲረሽናቸው የሚፈልጋቸውን በከፍተኛና ዝቅተኛ የመንግስት አመራር የሚገኙ የትግራይ ብሄር ተወላጆችን ስም ዝርዝር በቀላሉ ሊሰበር በሚችል ኮድ በማስፈር እና ለህወሓት የሰሩትን ስራ ከጎን በመፃፍ ሐሰተኛ ደብዳቤ አዘጋጅቶ የከተማውን የህቡዕ እንቅስቃሴ ከሚመራው ታጋይ ለሊቀመንበሩ አባይ ፀሃዬ የተላከ በማስመሰል ሶስት ታጋዮች ደብዳቤውን ይዘው ወደ አክሱም ከተማ እንዲገቡ ካደረገ በኋላ ራሱ በተዘዋዋሪ መንገድ ጠቁሞ በደርግ ደህንነቶች ቁጥጥር ስር እንዲውሉ አስደርጓቸዋል። ከዚያም ለአባይ ፀሐዬ እንደተላከ ተደርጎ የተዘጋጀው ደብዳቤ ከደርግ ደህንነቶች እጅ ይገባና ወደ መቀሌ ተልኮ ኮዱ ተሰብሮ ሰም ዝርዝራቸው ሰፍሮ የተገኙት በከፍተኛና ዝቅተኛ የመንግስት አመራር ውስጥ የሚገኙ ዕልፍ አዕላፍ የትግራይ ተወላጆች እየታደኑ ወደ ወህኒ ተወስደው አሰቃቂ ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ ያለ ኃጢያታቸው እንዲረሸኑ ተደርጓል።
በጦር ሜዳ ተዋግቶ ከማሸነፍ ይልቅ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ አድፍጦ ሴራ መጎንጎን የሚቀናው ህወሓት ደርግን ከትግራይ ህዝብ ነጥሎ እሱ ሰፊ ድጋፍ የሚያገኝበትን ሌላ ሴራ ጠንስሶ በመተግበር አረመኔያዊነቱን በተግባር ያስመሰከረ የሽብር ድርጅትም ነው። ይህም “የሀውዜን ጭፍጨፋ” በመባል የሚታወቀው ነው። ህወሓት በጠራራ ፀሀይ በገበያ ቀን ሰራዊቱን በሀውዜን ከተማ እንዲያልፍና ከፊሉ ደግሞ በገበያተኛው መካከል እንዲሰራጭ በማድረግ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ለደርግ የደህንነት ቢሮ ጥቆማ በመስጠት ህዝቡን በአውሮፕላን ቦምብ አስጨፍጭፏል። ይህን ተግባርም አስቀድመው ባዘጋጁት የቪድዮ ካሜራ በቀጥታ በመቅረፅ ለዓለም አሰራጭተው እንወክለዋለን በሚሉት የትግራይ ህዝብ ሞት የፖለቲካ ትርፍ አጋብሰው የዝርፊያ መንገዳቸውን አደላድለዋል። አሸባሪው ህወሓት በበረሃ አያለ ህዝቡን ለሰራዊትነት ሲመለምል ፈቃደኛ ያልሆኑ ወጣቶችን ቀሚስ አልብሶ በአደባባይ እያዞረ በህዝቡ ፊት ያሸማቅቃቸው እንደነበርም በታሪክ የተከተበ ሌላኛው ሀቅ ነው። የዚህን ድርጅት ሴራና ተንኮል በዚህች አጭር ጽሁፍ መጠቅለል አይቻልምና ሌሎች የሚነሱ ብዙ ጉዳዮች እንዳሉም ታሳቢ ይደረግልኝ።
ይህ ኃይል በስልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት አካባቢም በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ሲያደርስ የቆየው ኢፍትሃዊነት፣ አድልዎና የጭካኔ ተግባር በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ይሁንና ይኽንን ጭቆናና ኢፍትሃዊነት ያልተቀበሉ ኢትዮጵያውያን የአሸባሪው ህወሓት ሴራ ግድያና ጭፍጨፋ ሳይበግራችው ባደረጉት አኩሪ ትግል ተዋርዶና ተንቆ ወደ መቀሌ እንዲፈረጥጥ አድርጎታል። ያዳቆነ ሰይጣን ሳይቀስስ አይለቅም እንዲሉ ይኸው አሸባሪ ድርጅት ካለፈ ስህተቱ መማር ባለመቻሉ በለመደው የሴራ መንገድ የጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን አካል በሆነው ሰሜን ዕዝ ላይ ከጀርባው ጥቃት ፈጽሞ ሂሳቡን አወራርዷል።
በዚህም የዚህ አሸባሪ ቡድን አከርካሪ ተሰብሮ ዳግም እንዳያንሰራራ ብሎም ለሽብር ሲጠቀምባቸው የነበሩ መሳሪያዎች ከእጅ እንዲወጡ ተደርጓል። በዚህም የተነሳ አሁን አሸባሪው ህወሓት አገር ለማፍረስ የሚያገለግሉ ጥርሶቹ የተነቀሉበት አሮጌ አንበሳ ሆኗል።
ከዚህ እውነታ አሁንም መማር ያቃተው ይኽ የሽብር ኃይል አሁን እያደረገ ያለው የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ተግባሩ ህፃናትንና አዛውንቶችን ወደ እሳት መንዳት፣ ህዝብን በእሳት መማገድ ከዚያም ሲዘል ጭፍን ደጋፊዎቹን በአሜሪካና በአውሮፓ ጎዳናዎች ላይ እየተንከባለሉ እንዲያለቅሱ የማድረግ የቁልቁለት ጉዞ ሆኗል። የጽሑፌን ርዕስ ከእምበር ተጋዳላይ ወደ እምበር ተንከባላይ ያልኩትም በዚሁ መነሻ ነው!
ቢቂልቱ ከቱሉ ዲምቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2013