ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገጠማትን የውጭና የውስጥ አስቸጋሪ ፈተና ለመሻገር ጥረት እያደረገች ትገኛለች። በውስጥ እየገጠማት ካለው ውስብስብ ችግርና ፈተና ባሻገር በውጭ እየገጠማት ያለው ፈተና ቀላል የማይባልና ፤ የሀገር ልዕላዊነትን የሚፈታተን ነው። ይቺ ሉዕላዊት ሀገር የውስጥ ችግሮቿን በራሷ ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ከቁብ ለመጻፍ የማይፈልጉ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት በሀገር በውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ጣልቃ በመግባት ጫናን በመፍጠር ማዕቀብ እንዲጣል ለማድረግ በየጊዜው የሚያሳዩት አቋም እጅግ ፈታኝ እየሆነ ነው።
ለዚህም ማሳያው ለአሸባሪው ህወሓት ጥብቅና በመቆም፤ ህወሓት በዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ጭካኔ የተሞላው ግፍና በደል በዝምታ በማለፍ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እና ማዕቀብ እንዲደረግ የሚያደርጉት ግፊትና ጥረት እየጨመረ መምጣቱን ነው። አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ለአሸባሪው ህወሓት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩና ከሽብር ቡደኑ ጎኑ መቆማቸው በግልጹ በሚያሳብቅባቸው መልኩ ጥብቃ ሲቆሙ በገሃዱ ዓለም እየተስተዋለ ነው ።
የጥፋት ቡድኑ ህወሓት በዜጎች ላይ የፈጸማቸውን ግፍና በደል እንዳላየና እንዳልሰማ በዝምታ በማለፍ የሚያደርጉት ጥረት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የማይካድራ ንጽህን ዜጎችን ጭፍጨፋ፤ በዓለም አቀፍ የወንጀል ህግ ላይ ስለተቀመጠውን ዕድሜያቸው ያልደረሱ ህጻናት ለጦርነት ማሰለፉን እና ሌሎችም ዘግናኝ ድርጊቶች እያዩ እና እየሰሙ ዝምታን መምረጣቸው የራሳቸውን የሆነ ድብቅ ዓላማ እንዳላቸው አመላካች ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ሉዕላዊነት በሚዳፈር መልኩ ጫናን በመፍጠር ማዕቀብ እንዲጣል ለማድረግ የሚያደርጉት ሸፍጥ ግንባር ቀደም ሆነው ይታያሉ። ሚዛናዊነት የማይታባቸው ለአንድ ወገን የቆሙ መሆናቸውነን ከሚያሳብቁባቸው ስህተቶቻቸው መሃል መንግሥት በትግራይ ያደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ ሆነ እያደረገ ያለውን ሰብዓዊ እርዳታ እንኳን እውቅና መስጠት አለመፈለጋቸው ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ባሳለፍነው ሳምንት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት አንዳንድ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ባለስልጣኖች እንዲሁም አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ግለሰብ ባለስልጣኖች ጉዳዩ የግላቸው እስኪመስል ድረስ ለአንድ ወገን ያደላ አቋምና አመለካከት በቋሚነት በማስተጋባት ኢትዮጵያን የማዋከብና የማጨናነቅ አቋማቸውን አጠናክረው የቀጠሉበት ሁኔታ እጅግ አስተዛዛቢ ሆኖ ቀጥሏል ማለታቸው የሚታወስ ነው::
ይሁንና ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለውን የውስጥና የውጭ ችግር ለመፍታት የበኩሏን ጥረት እያደረገች ነው። በዚህ ረገድም ያለውን ነባራዊ ሁኔታና ያላትን ጽኑ አቋም በየጊዜው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ለማሳወቅ ጥረት ታደርጋለች። ወትሮውኑም ቢሆን ከሀገራቸውን ጎን መቆማቸው በየጊዜው እያስመሰከሩ የሚገኙት በውጭ የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያ የዲያስፖራ አባላት የሀገራቸውን ሉዕላዊነት በማስከበር፤ ጥቅም ለማስከበር የተሰለፉት ናቸውና የምዕራቡ የዓለም ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገው ተፅጽኖ ለመመከት እና ጫናው በማርገብ ረገድ በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ።
ባለፉት ዓመታትም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ የነበረው ሁኔታ በመቃወም በሀገር ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ልማት እንዲረጋገጥ ለማድረግ የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ መቆየታቸው የሚታወስ ነው:: በተለይ ከለውጡ በኋላ በሀገሩ ላይ ያለው ተስፋ የለመለመው የዲያስፖራው ማህበረሰብ ከሀገሩ ጎን በመቆም ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆኑን እያሳየ ይገኛል። ለዚህም በመላ ዓለም የሚገኙ የዲያስፖራ አባላት በተፈጠረው ንቅናቄ በሀገር ውስጥ ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የራሱን አስተዋፅኦ በማድረግ አሻራው እያሳረፈ ይገኛል። ለአብነትም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ለገበታ ለሀገር፣ ለኮቪድ 19 መከላከያ፣ ለልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች፣ በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ለሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም እና ለመከላከያ ሰራዊት የተለያዩ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እየተሳተፈ እንደሚገኝ የሚታወስ ነው።
አሁን ላይ አለም አቀፍ ጫናን ለመመከት የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ብዙ ሥራዎች እየሰራ ይገኛል። ይህንን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆምና እጁን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሳ የተለያዩ ሰልፎችን በማድረግ ዲያስፖራው ለሀገሩ ያለውን ተቆርቋሪነት በማሳየት ላይ ይገኛል።
በሀገር ውስጥ ጉዳይም አሸባሪው ህወሓት እየፈጸመ ያለውን ግፍና ጨካኔ የተሞላበት ተግባር በመቃወም ላይ ይገኛል። በአውሮፓ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመው ዲፌንድ ኢትዮጵያ ሰሞኑን በወጣ መግለጫ ያሳየው አቋም የሚያመላክተው ይህንኑ ነው። ዲፌንድ ኢትዮጵያ የተሰኘው ማህበር ባለፉት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ሂደት ውስጥ እንደምትገኝ ጠቅሶ ፣ የህወሓት ቡድን ግን ይህን ለውጥ ለማደናቀፍ ይሰራ እንደነበረና ከዕኩይ አላማው እንዲመለስና የሰላም ሃይል እንዲሆን በፌዴራል መንግስቱ በኩል ልዩ ልዩ ጥረቶች ቢደረግም እንዳልተሳካ ጠቁሟል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ የአሜሪካን መንግስት፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ አካላትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፖለቲካ ወገንተኛና ነጻ በሆነ መንገድ በትግራይ የሚካሄደውን የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቶችና መልሶ ግንባታ ሂደቶችን እንዲደግፉ፣ በትግራይ ለተፈጠረው ችግር ዋነኛ መንስኤውን እንዲመረምሩ፣ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲያከብሩ፣ እንዲሁም በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ በሚዘግቡበት ወቅት ሚዛናዊነትን እንዲከተሉና ግጭት ጫሪነትን እንዲያስወግዱ ጠይቋል።
ከዚህ በተጨማሪ የዲፕሎማሲ ሥራን በዲጂታል ዘርፍ እንዲታገዝ በማድረግ ዘመኑ ይዞት የመጣውን ዕድል እና መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባም ብዙዎች ይስማሙበታል። በዚህ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ስዊድን፣ ኒውዝላንድ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ስፔን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጃፓን፣ ሲንጋፖር፣ ኖርዌይና ሩስያ ውጤታማ የዲጂታል ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ አገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያ መላክተው በተለይም ዲያስፖራውና ዲፕሎማቶች በበይነ መረብ እና በሌሎች ሚዲያዎች አገርና ህዝብን በመወከል ግንኙነቶችን በማድረግ የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ።
በተመሳሳይ ሰሞኑን በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የውጭ ጫናዎችን እና ጣልቃ ገብነቶችን በመቃወም እንዲሁም ህፃናትን ለውትድርና እየተጠቀመ ባለው የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ላይ ጫና እንዲደረግ የሚጠይቅ የትዊተር ዘመቻ እየተካሄደ ነው::
በአጠቃላይ ዲያስፖራው እያደረገ ያለውን ጥረት ማበረታታትና መደገፍ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት ነው።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013