የመጨረሻ ክፍል
ባለፉት ተከታታይ እትሞች የጋብቻ እና ፍቺ ሕጋዊ ውጤቶችን ከተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንፃር ስናስቃኛችሁ ቆይተናል። ለዛሬም በጉዳዩ ዙሪያ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር ከሆኑት የህግ ባለሙያ አቶ እንዳልካቸው ወርቁ ጋር የነበረንን የመጨረሻ ክፍል እነሆ ።
ስለጋብቻ መፍረስና ውጤቶች
የሀገር እና የህብረተሰብ ምሶሶ የሆነው ቤተሰብ በጋብቻ አማካኝነት የሚመሰረተው እስከ ተጋቢዎች እድሜ ፍጻሜ ድረስ አብሮ ለመኖር ነው። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ይህ የተመሰረተው ጋብቻ ሊፈርስ ይችላል። በዚህ ጽሑፍ ክፍል አንድ ላይ እንደተገለጸው ጋብቻ የሚፈጸመው በሕግ በተደነገገ ስርዓትን በመከተል ነው። ይህ ስርዓትን ተከትሎ በሕግ እውቅና አግኝቶ የተመሰረተ ጋብቻ ሲፈርስም ሕግን ተከትሎ መሆን አለበት። ጋብቻው የተፈጸመው በየትኛውም አይነት ስርዓት ቢሆንም የጋብቻው መፍረስና የሚያስከትለው ውጤት ግን አንድ ዓይነት ነው።
በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 ላይ ጋብቻ ስለሚፈርስባቸው ምክንያችን በመዘርዘር አስቀምጧል። እነኚህም፡-
1ኛ ከተጋቢዎቹ አንዱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ከሆነ፣
2ኛ ከተጋቢዎቹ አንዱ በፍ/ቤት ለመጥፋቱ ውሳኔ
የተሰጠ እንደሆነ፤
3ኛ በሕጉ ጋብቻ ለመፈጸም እንደ ቅድመሁኔታ የተቀመጡት ነገሮች ሳይሞሉ ጋብቻው የተፈጸመ እንደሆነ እና ጋብቻው እንደፈረሰ ውሳኔ ሲሰጥ እና
4ኛ የጋብቻ ፍቺ ውሳኔ ሲሰጥ ጋብቻው ይፈርሳል። ቀጣዩ ጽሑፍ ካሉት አራት የጋብቻ መፍረስ ምክንያቶች አንዱ በሆነው ፍቺ ላይ ትክረቱን ያደረጋል።
ስለፍቺና ውጤቶች
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞረው በሕጋዊ መንግድ ተመስርቶ የነበርውን ጋብቻ ለማፍረስ አንደኛው ምክንያት ፍቺ ነው። ጋብቻ በህብረተሰቡና በመንግስት ጥበቃ የሚደረግለት ተቋም ነው። የዚህ የጥበቃው ዋናው ምክንያት ትዳሩ ስላማዊና ጤናማ በሆነ መልኩ ቀጥሎ የህብረተሰቡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ነው። ነገር ግን ከተጋቢዎቹ አቅም በላይ በሆነ ወይም ሌላ ምክንያት ተጋቢዎቹ ትዳራቸው እንዳይቀጥል ማድረግ የሚሳናቸው ጊዜ ያጋጥማል። በእንደዚህ አይነት ጊዜ ደግሞ በሕጋዊ መሠረት የተመሰረተው ጋብቻ ሕጉን በጠበቀ መሠረት በሰላም እንዲለያዩ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ለዚህም የተሻሻለው የቤተሰብ ህጎችን ፍቺ እንዴት እንደሚካሄድ፣ በማን እንደሚካሄድ እና ውጤቶች በዝርዝር ያስቀመጠው። በዚህም መሠረት በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ፍቺ በሁለት መንገዶች ሊከናወን እንደሚችል በአንቀጽ 76 ላይ ይገልፃል። ይህም 1ኛ ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት ሲወስኑና ይህንኑ ለፍርድ ቤት አቅርበው ውሳኔያቸው ተቀባይነት ሲያገኝ። 2ኛ ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱም ተጋቢዎች በአንድነት ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ በፍርድ ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ ነው።
ሀ/ በስምምነት ፍቺ ስለመፈጸም
በስምምነት ፍቺ ማድረግ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ከተቀመጡበት ሁለት አይነት የፍቺ ማካሄጃ መንገድ አንዱ ነው። ባልና ሚስት በስምምነት ተፋትተው ወሳኔያቸውን ያጸድቅላቸው ዘንድ ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላሉ። ባልና ሚስቱ የፍቺውን ውጤትም አብረው ተስማምተው በተመሳሳይ መልኩ ከፍቺ ስምምነታቸው ጋር ለፍርድቤት አቅርበው ማጽደቅ ይችላሉ። ለፍቺ ስምምነት ያደረሳቸውን ምክንያት ከፈለጉ ይገልጻሉ። ነገር ግን እንዲገልጹ አይገደዱም።
ባልና ሚስቱ ፍቺው ላይ እና ውጤቱ ላይ ተስማምተው እንደሚያጸድቅላቸው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ፍርድ ቤቱ በጋራም ሆነ በተናጥል ስለ ጥያቄያቸው ያነጋግራቸዋል፣ እንዲሁም የመፍታት ሀሳባቸውን እንዲለውጡ ይጠይቃቸዋል። ከዚህም አልፎ የበለጠ አስበውበትና በሰከነ አዕምሮ ተወያይተው እንደመጡ ለማስቻል እስከ ሶስት ወር የማሰላሰያ ጊዜ እንደነገሩ ሁኔታ ሊሰጣቸው እንደሚችል በአንቀጽ 76(2) ተገልጿል። ይህን የሶስት ወር ማሰላሰያ ጊዜ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው እንደ ነገሩ ሁኔታ እያየ ነው።
ፍርድ ቤቶች ተጋቢዎቹ በስምምነት ተፋተው መጥተው ፍቺው እንዲጸድቅ ሲጠይቁ ይህን ፍቺ ከማጸደቃቸው በፊት ጋብቻ በዘፈቀደ እንዳይፈርስ እና ጸንቶ እንዲቆይ ለማድረግ ፍርድቤቶች ሊያደርጓቸው የሚገቡ መርሃግብሮችን ሕጉ በአንቀጽ 78 እና 80 ላይ አስቀምጦታል። እነዚህም ተጋቢዎቹ የፍቺ ሀሳባቸውን እንዲለውጡ መጠየቅ፣ የማሰላሰያ ጊዜ እንደነገሩ ሁኔታ ሶስት ወር የማይበልጥ ጊዜ መስጠት፣ ፍቺው ትክክለኛ ፍላጎታቸው መሆኑን እና በነፃ ፍቃዳቸው የሰጡ መሆኑን ማረጋገጥ እና ስምምነቱ ከሕግና ሞራል ጋር የማይቃረን መሆኑን ማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው።
በስምምነት የመፍታት ጉዳይ ሲነሳ ውጤቱም አብሮ መታየት አለበት። ከጋብቻው የተወለዱ ልጆች፣ በጋብቻው ወቅት የተፈራ የጋራ ሀብትና ንብረት፣ ለትዳር ጥቅም የተገባ እዳና አከፋፈሉ እና የመሳሰሉ ጉዳዮች እንዴት እንደሚሆን ሊገለጽ ይገባል። ባልና ሚስቱ ስለፍቺው ውጤት ያደረጉት ስምምነት የልጃቸውን ደህንነትና ጥቅም በበቂ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ወይም የአንደኛውን ተጋቢ ጥቅም የሚጎዳ ሆኖ ካገኘው ፍ/ቤቱ የፍቺውን ስምምነት ብቻ በማጽደቅ የፍቺውን ውጤት በተመለከተ ጉድለቶቹን እንዲያስተካክሉ ወይም ተገቢ መስሎ የታየውን ውሳኔ ይሰጣል። ይህም የሚያሳየን በስምምነት ፍቺ ውስጥ የፍ/ቤት ሚና እንዳለ ነው።
ለ/ የፍቺ ጥያቄ በመቅረቡ ምክንያት
ስለሚፈጸም ፍቺ
ይህ አይነት ፍቺ አንደኛው ተጋቢ ብቻ ወይም ሁለቱም ተጋቢዎች ፍቺ ፈልገው ጠይቀው ነገር ግን ስለፍቻቸው ሆነ ስለውጤቱ ያደረጉት ስምምነት የሌለበት ነው። ስለሆነም የፍ/ቤት ሚና በዚህ አይነት ፍቺ ስምምነት የማጽደቅ ሳይሆን በተጋቢዎቹና በሽማግሌዎቹ በመረዳት ቢቻል ትዳሩን ማቃናት ካልሆነ ግን ፍቺውን የሚያስከትለውን ውጤት መወሰን ይሆናል። በመሆኑም በስምምነት ከሚደረገው የፍቺ አይነት ይልቅ በዚኛው ላይ የፍርድቤት ሚና ከፍ ያለ ነው።
በአንቀጽ 82 ስር ፍርድቤቱ ዘርዝርና ሰፋ ያሉ ሀላፊነቶች የተሰጡት ሲሆን ከፍርድቤቱ ሌላ በተጋቢዎቹ የሚመረጡ አስታራቂ ሽማግሌዎች በጉዳዩ ላይ እንዲገቡበት የማድረግ እድል አለ። የአስተራቂ ሽማግሌዎቹን የስራ ክንውን ሪፖርቶች የመቀበልና ለሽማግሌዎቹ የስራ መመሪያ መስጠት የፍርድቤቱ ኃላፊነት ስለመሆኑ አንቀጽ 119 እስከ አንቀጽ 122 ድረስ ባሉት ድንጋጌዎች ተመልክቶ ይገኛል። ፍርድቤቱ ባልና ሚስቱን በተናጠልም ሆነ በአንድነት በማነጋገር የፍቺው ጥያቄያቸውን ትተው አለመግባባታቸውን በስምምነት እንዲቋጩት ያግባባል። ይህን ሞክሮ ያልተሳካለት እንደሆነ ባልና ሚስቱ ከፍ/ቤት ውጪ ራሳቸው በሚመርጡት ሽማግሌዎች አማካኝነት ጉዳያቸውን በእርቅ እንዲጨርሱ ሊያደርግ ይችላል። ባልና ሚስቱ በመፋታት ቆርጠው በሽማግሌም አለመስማማታቸውን መፍታት ካልቻሉ ፍርድቤቱ ከሶስት ወር ያልበለጠ የማሰላሰያ ጊዜ ሊሰጧቸው ይችላሉ።
ፍርድቤቱ ባልና ሚስቱ ለየብቻ ወይም በጋራ አናግሮአቸው ያልተስማሙበትን ነጥብ እንዲፈቱ ጠይቀዋቸው፣ በራሳቸው በመረጡት ሽማግሌዎች ጉዳያቸውን አሳይተው ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጠይቀዋቸው እንዲሁም ከሶስት ወር ያልበለጠ የማሰላሰያ ጊዜ ሰጥተዋቸው በዚህ ሁሉ ጥረት ጥረቱ ፍሬ ካላፈራ የሽማግሌዎቹ የመጨረሻ ሪፖርት ከደረሰው ወይም የተሰጠው የማሰላሰያ ጊዜ ከአለቀበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የፍቺ ውሳኔ ይሰጣል።
በአንቀጽ 82(5) እና (6) ላይ ፍ/ቤቱ ስለሚሰጠው ጊዜያዊ ትዕዛዝ ይገልፃል። ፍርድቤቱ አቤቱታው እንደቀረበ ወዲያው ባልና ሚስቱ ስለሚተዳደሩበትና ስለሚኖሩበት ሁኔታ፣ ስለልጆቻቸው አጠባበቅ ስለሚኖሩበት ስፍራና ስለአኗኗራቸው እንዲሁንም ስለንብረታቸው አስተዳደር ተገቢ መስሎ የታየውን ትዕዛዝ ይሰጣል። ይህም የጋራ ንብረቱን የያዘው ሰው ንብረቱ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የልጆች አስተዳደግ እና አኗኗር ችግር እንዳይገጥመው እንዲሁም በጋራ የሚኖሩ ከሆነና ቅራኔያቸው ከፍ ያለ ከሆነ በጋራ መሆናቸው የባሰ ችግር እንዳይፈጠር ጠቀሜታ አለው። ፍርድቤቱ በጋራ ከሚኖርበት አንዳቸው መውጣት ያለባቸው መሆኑን ካመነበት ተጋቢዎቹ ያላቸው ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት በማድረግ የጋራ መኖሪያቸውን ለቆ መውጣት የበለጠ የሚጎዳው የትኛው መሆኑን በመመርመርና የልጃቸውን አጠባበቅና ጥቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ሊወስን እንደሚገባ ሕጉ ይደነግጋል።
ለረጅም ጊዜ መለያየት መፋታት ሊያመላክት ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ባልና ሚስት ሕጋዊ መንገድ የመሰረቱት ጋብቻ በሕጋዊ መንገድ ሳያፈርሱ በመለያየት የየግል ኑሯቸውን ለረዥም ጊዜ መኖር ይጀምራሉ። ይህ አይነቱ መለያየት የፍቺ አይነት ውጤት እንዳለው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 20938 በአመልካች ወይዘሮ ሸዋዬ እና በተጠሪ ወይዘሮ ሳራ መካከል በነበረው ክርክር ‘‘በወይዘሮ ሳራና በአቶ ይልማ መሀል የነበረው ጋብቻ በሕጉ በተቀመጡ የጋብቻ ማፍረሻዎች ባይፈርስም በስር ፍርድቤት ወይዘሮ ሳራ የሰጡት ቃል መፍረሱን የሚያሳይ ነው። ወይዘሮ ሳራና አቶ ይልማ በጋብቻው መቀጠል ባለመቻላቸው ተጣልተው ተለያይተው በየፊናቸው የየራሳቸውን ኑሮ ሲኖሩም ነበር። ለጋብቻው መፍረስ የሚያበቁ ምክንያቶች መኖራቸውንና አቶ ይልማም ወይዘሮ ሸዋዬን ማግባታቸውን ወይዘሮ ሳራ ያውቁት ነበር። ሆኖም ሁለቱም የየራሳቸውን ኑሮ እየኖሩ ስለነበር ወይዘሮ ሳራ አቶ ይልማ ወይዘሮ ሸዋዬን ማግባታቸውን ቢያውቁም ሟች በህይወት እያሉ ጋብቻውን ‘በጋብቻዬ ላይ የተፈፀመ ሕገወጥ ጋብቻ ነው’ ብለው አልተቃወሙትም። ስለዚህ የስር ፍርድቤቶች ይህን ባረጋገጡበት ሁኔታ ‘ወይዘሮ ሳራ ሟች እስከሞቱበት እለት ሚስት ነበሩ’ ብለው መወሰናቸው ትክክለኛውን የሕግ አተረጓጎም የተከተለ አይደለም። ፍቺ መፈፀሙን የሚያሳይ ማስረጃ አለመቅረቡ ብቻ አንድን ጋብቻ የፀናና ውጤት የሚያስከትል ነው ሊያስብለውም አይችልም። ባለመግባባት ተለያይተው ፍቺ ለመፈፀም የሚያስችል ምክንያት የነበራቸው ተጋቢዎች የየራሳቸውን ኑሮ በየበኩላቸው ጀምረው ከኖሩ በኋላ ባል ወይም ሚስት ናቸው ሊባሉ አይችሉም’’ በማለት ወስኖላቸዋል።
ሐ/ የፍቺ ውጤቶች
ፍርድቤቱ ፍቺውን ከወሰነ በኋላ የፍችውን ውጤት በተመለከተ ባልና ሚስቱ እዲስማሙ ይጠይቃቸው። እዚህ ላይ የምንረዳው ነገር ፍቺውን ፍርድቤቱ ከወሰነ በኋላ የፍቺውን ውጤት ማለትም ስለልጆቻቸው፣ ስለጋራ ንብረታቸው እንዲሁም የጋራ እዳዎቻቸውን በተመለከተ ተስማምተው እንደወሰኑ ፍርድቤት በጠየቃቸው መሠረት ተስማምተው ሊወስኑ እንደሚችሉ ነው። ነገር ግን ባልና ሚስቱ የፍቺው ውጤት ላይ ያልተስማሙ ከሆነ ፍርድቤቱ በራሱ ወይም በሽማግሌዎች ወይም ፍርድቤቱ በሚሾሟቸው ባለሙዎች አማካኝነት ወይም አመቺ መስሎ በሚታየው በማንኛውም ዘዴ የፍችውን ውጤት ይወስናል።
በዚህ ጽሑፍ ክፍል ሁለት ውስጥ ለመግለጽ እንደተሞከረው ተጋቢዎች በጋብቻ ውላቸው ውስጥ የጋብቻው መፍረስ በንብረት በኩል የሚያስከትሉ ውጤቶችን አስቀድመው ሊወስኑ ይችላሉ። ነገር ግን የጋብቻ ውሉ የሌለ እንደሆነ ወይም በሕግ ፊት የማይጸና ከሆነ ፍርድቤቱ በሕግ በተቀመጠው መሠረት የፍቺውን ውጤት ይወስናል። በዚህም መሠረት በመጀመሪያ ደረጃ የግል ንብረት ክፍፍል ይካሄዳል። በተጋቢዎች እጅ ያሉ ንብረቶች ሁሉ የጋራ ንብረት እንደሆኑ ስለሚገመት እያንዳንዱ ተጋቢ ይህ ንብረት የግሌ ነው የሚለውን የማስረዳት ሸክም የሱ ወይም የሷ ይሆናል። የግል ንብረቱ መሆኑን ያስረዳው ተጋቢ የግል የሆነውን ንብረቱን ይወስዳል። ይህ የግል ንብረቱ የሆነው ነገር ከጋራ ንብረታቸው ጋር የተቀላቀለ ስለመሆኑ የተረጋገጠ ከሆነ ከግል ንብረቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ ወይም ንብረቱን ከጋራ ንብረታቸው ውስጥ ይወሰዳል። የየግል ንብረታቸውን ወስደው ከጨረሱ በኋላ የጋራ ንብረት ክፍፍል ከማድረጋቸው በፊት ዕዳዎችን መክፈል ይቀጥላል። በቅድሚያ ለትዳራቸው ያለባቸውን ዕዳ ከጋራ ንብረታቸው ይከፍላሉ ይህ የጋራ ሃብት እዳቸውን የማይቻል ከሆነ ከግል ንብረታቸው ይከፍላሉ። ነገር ግን አንዳንዴ ንብረቱ የግል ነው የጋራ የሚለው ላይ ጭቅጭቅ ይነሳል። ለምሳሌ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 46606 በአመልካች አቶ ገብረስላሴ አማረ እና ተጠሪ ወይዘሮ አብረኸት ተጫነ መካከል በነበረው የፍቺ ክርክር ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቶል። የአመልካች እና የተጠሪ ጋብቻ የፈረሰው መጋቢት 24 ቀን 2000 ዓ.ም ነው። አመልካች የኮንዶሚኒየም ቤቱን የተመዘገበው ተጠሪን ከማግባቱ በፊት ቢሆንም እጣ የወጣለት ከተጠሪ ጋር የፀና ጋብቻ በነበረበት ወቅት ነው። ጋብቻው ፀንቶ እስካለ ድረስ ተጠሪን ከማግባቱ በፊት ስለተመዘገበ ብቻ ቤቱ የግል ንብረቱ እንደማይሆን በተሻሻላው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 62/1/ ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻል በመሆኑ አመልካች ያቀረቡት ክርክር የሕግ መሠረት የሌለው ነው። በመሆኑም የኮዶሚኒየም ቤቱ የጋራ ንብረት ነው። ጋብቻው ከፈረሰ በኋላ የሚከፈለው ክፍያ አመልካችና ተጠሪ በጋራ የመክፈል ግዴታ አለባቸው። በተመሳሳይ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 51893 በአመልካች አቶ እንዳልካቸው ዘለቀ እና ተጠሪ ወይዘሮ ብሁዓለም መንግስቱ መካከል በነበረው ክርክር የኮዶሚኒየም ቤት ጋር በተያያዘ ከጋብቻ በፊት በአንደኛው ተጋቢ ምዝገባው የተካሄደው ቢሆንም የቤቱ ዕጣ የወጣው ብሎም የቤቱ ሽያጭ ውል የተደረገው በጋብቻ ጸንቶ በነበረበት ወቅት መሆኑ በተረጋገጠ ጊዜ ለቤቱ መገኘት ምክንያት የሆነው ተጋቢ ቤቱ የግል መሆን አለበት በሚል የሚቀርብ ክርክር ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት ወስኗል።
ያለባቸውን እዳ ከፍለው ከጨረሱ በኋላ ወይ የጋራ ንብረት ክፍፍል ይሄዳሉ። በመረህ ደረጃ የጋራ ንብረታቸውን ባልና ሚስቱ እኩል ይከፋፈላሉ። ነገር ግን በልዩ ሁኔታ በአንቀጽ 84 ላይ እንደተጠቀሰው ፍርድቤቱ ለፍትህ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በካሳ መልክ ለአንደኛው ተገቢ ከሌላኛው ተጋቢ ድርሻ ላይ ቀንሶ ለሌላኛው ሊሰጥ ይችላል። ይህን የጋራ ንብረቶቻቸውን ሲከፋፈሉ በመጀመሪያ በዓይነት በዓይንት እንዲካፈሉ ይደረጋል። ይህ ክፍፍል ሲደረግ ለእያንዳንዱ ተጋቢ ይበልጥ ጠቃሚነት ያላቸውን ንብረቶች እንዲያገኙ ጥረት ይደረጋል። ይህ ሲሆን የእኩልነት መርሁን ለማስከበር ልዩነቱን በገንዘብ ሊካስ ይገባል።
ልጆቻቸውን በተመለከተ በስምምነታቸው መሠረት የሚኖሩበት ቦታ እና ቀለባቸውን ይወስናሉ። ነገር ግን ካልተስማሙ ፍርድቤቱ ለልጆቹ አመቺ የሆነውን እና መብታቸውን በሚያስከበር መልኩ ውሳኔ የሚሰጥ ይሆናል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013