ስልጠናቸውን፣ ምርምራቸውን ወይንም የእንጀራ ገመዳቸውን ከዲፕሎማሲ ሙያ ጋር ያስተሳሰሩና ያቆራኙ የመስኩ ቤተሰቦች አዘውትረው ከሚጠቅሷቸው አባባሎች መካከል “ሀገር ሲጠብ የኤምባሲ ጽ/ቤት ይሆናል” የሚሉት ብሂል አላቸው። አባባሉ የሙያውን ጠቀሜታና የተልዕኮውን ክብደት አግዝፎ ስለሚያሳይ ቢተነተን ብዙ ያጽፋል። ከዘመን ጋር የሸበተውና የዓለማችን ሀገራት በሙሉ የግንኙነታቸውን ጥበብና የብልጠት ብቃት የሚያሳዩበት ይህ “በፕሮቶኮል የተሸፈነ” ዘርፍ የዕድሜውን ርዝመት ያህል የተልዕኮው የአድማስ ጥግም እንዲሁ የተለጠጠ ስለሆነ በጋዜጣ ዐምድ ወርድና ስፋት ልክ ተንትኖ መመርመር በእጅጉ ፈታኝ ስለሚሆን ጉዳዩን በማጥበብ ከሀገራዊ ዐውዳችን ጋር መፈተሹ ይሻል ስለመሰለኝ ይህንኑ መንገድ ለመከተል እሞክራለሁ።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በነበራቸው የፓርላማ ውሎ መጻኢውን አዲሱን የመንግሥታቸውን አቋም ካስታወቁባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ “ቁጥራቸው ከስልሳ በላይ ከሆኑትና በውጭ ሀገራት ከሚገኙት የኤምባሲ ጽ/ቤቶቻችንና የቆንስላ ቢሮዎቻችን መካከል ቢያንስ ግማሽ ያህሉ ሊዘጉ እንደሚገባ” የጥቆማ ያህል መልዕክት አስተላልፈዋል። የእርምጃ አወሳሰዱ ከሃምሳ ከመቶ ከፍ ሊል እንደሚችል “ቢያንስ ግማሹ” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ዋቢ ይሆነናል።
ማንኛውም መንግሥት ሉዓላዊነቱን የሚዳፈሩ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ፣ የጎላ የአዲዮሎጂ መስመር ልዩነት በላኪና በተቀባይ ሀገራት መካከል ሲስተዋልና መሸካከር ሲከሰት ወይንም የሀገራት ኢኮኖሚ የኤምባሲ ጽ/ቤቶችን በጀት መሸከም ሲሳነውና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሀገራት የከፈቷቸውን የውጭ ሚሲዮን ጽ/ቤቶችና የዲፕሎማቶቻቸውን ቁጥር በፈለጉት ቁጥር የመቀነስ መብት አላቸው። ጥቅሙ የሚያይል ከመሰላቸውም እንዲሁ ጽሕፈት ቤቶቻቸውን በማስፋትና የመልዕክተኞቻቸውን ቁጥር በርከት በማድረግ የዲፕሎማሲውን ጡንቻ ሊያፈረጥሙ ይችላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስረግጠው እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያም እንዲሁ የሚሲዮን ጽ/ቤቶቼ ወጪ አንገዳገደኝ፣ የዲፕሎማቶቼ በጎ ተጽእኖ ፈጣሪነትም ስላሳሰበኝ፤ “ዲፕሎማቶቹ ጋዜጣ ለማንበብ ከሆነ እዚሁ በሀገራቸው ቁጭ ብለው ሊያነቡና በዓመት አንዴ ወይንም ሁለቴ ከርዕሳነ ብሔራቱ ጋር ቀጠሮ ሲኖራቸው በደርሶ መልስ ጉዞ ተልዕኳቸውን ተወጥተው ሊመጡ ስለሚችሉ ቁጥራቸውን እከረክማለሁ” ብትል መብቷ ስለሆነ ለምን ይሄንን ወሰንሽ ሊባል አይገባም።
መሠረታዊው አተገባበር ላይ ልዩነት ባይኖርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንደበታቸው እንዳረጋገጡልን እንዲዘጉ የሚታሰቡት የሚሲዮኖች ቁጥር ብዛት ብዙ ሲያነጋግርና ሲያደነጋግር መባጀቱን ግን መሸሸግ አይቻልም። በተለይም ውሳኔው ከበጀት ወጪ መናር ጋር ብቻ ተያይዞ መገለጹ ብዥታውን ጠንከር አድርጎታል። ይህ ጸሐፊም ከውጭ ያሉ በርካታ ወዳጆቹ አጥብቀው ጉዳዩን አጣራልን ስላሉት ያገኘው ምላሽ አጥጋቢ ባይሆንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት የሥራ ኃላፊዎችን ማነጋገሩ ግን አልቀረም።
እርግጥ ነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገለጸው ምክንያት አንዱና ቁንጽሉ ሊሆን እንደሚችል ይጠፋናል ተብሎ አይገመትም። ግርታው የተፈጠረው በሚሲዮን ጽ/ ቤቶቹ ከሚከናወኑት ተግባሮች አንጻር ሲታይ “ቁጥራቸው እንዲቀነስ የተፈለገበት የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ” እንደምን ዋና ምክንያት ሊሆን ቻለ የሚለው ነው። በተለይም ወደ ኋላ ግድም ተመልሼ ለማንሳት እንደምሞክረው የካሁን ቀደሙን የሀገራችን የአምባሳደሮች ሹመት ተሞክሮን ልብ ብሎ ላጤነ ሰው እነማን በምን መስፈርት ሲሾሙ እንደኖሩ “ውስጣችንን እያበገነ የሚወጣው የትንፋሽ ነበልባል” በጥሩ ማስረጃነት ሊጠቀስ ይቻላል። “በሆድ ይፍጀው” ትዝብት ስናልጎመጉም የከረምንበት ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍርጥ ተደርጎ መነገሩ ጥቂትም ቢሆን ተንፈስ እንድንል የረዳን ይመስለናል።
እ.ኤ.አ በ1961 ዓ.ም በበርካታ ሀገራት ዘንድ አሜንታና ይሁንታ ያገኘው የቪዬና የጋራ መግባቢያ ሰነድ (Vienna Convention on Diplomatice Rlatioions) በሀገራት መካከል የሚደረጉትን የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶች ጥቅም አንዱ ነጥብ ከሌላኛው ጋር ተወራራሽ ቢሆንም በአምስት ዋና ዋና ዘርፎች መድቧቸዋል። የመጀመሪያው ጥቅም ቀደም ሲል በብሂሉ ለማስታወስ እንደተሞከረው ግንኙነቱ ተራ ግንኙነት ሳይሆን የሀገር ውክልና ጉዳይ ስለሆነ የግንኙነቱ እሴት ከፍ እንዲል ያደርገዋል። ሁለተኛው ጥቅም የዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሚደነግጉት አግባብ መሠረት በተቀባዩ ሀገራት ውስጥ ያሉ ዜጎች ክብር እንዲጠበቅ ምክንያት መሆኑ ነው። በሦስተኛ ደረጃ ላኪው ሀገር ከተቀባዩ ሀገር ጋር በተለያዩ የጋራ ጥቅሞች (ኤኮኖሚ፣ ባህል፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የልማት ትብብርና ርዳታ ወዘተ.) ለመተጋገዝ ማስቻሉ ነው። አራተኛው በሀገራቱ መካከል ይበልጥ ለመቀራረብና ለመተዋወቅ ስለሚያግዝ ነው። አምስተኛው ጥቅም በየሀገራቱ የሚመደቡት ዲፕሎማቶች አስገዳጅ ሁኔታ ካላጋጠመና በተለያዩ ምክንያቶች መሸካከር ተፈጥሮ ካልተቃቃሩ በስተቀር አንዱ የሌላውን የሉዓላዊነት ክብር ተዳፍሮ መልካም ገጽታውን እንዳያጠለሽ ማገዙ ይጠቀሳል።
በዚህ ዕድሜ ጠገብ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መስክ ዝርዝር ጉዳዮችን ጠልቆ በመግባት ሐሰሳ ማድረጉ የጋዜጣውን የመሸከም አቅም መፈታተን ስለሚሆን ወደራሳችን ወቅታዊ ጉዳይ ተመልሶ “መልካችንን በራሳችን መስታወት መመልከቱ” የተሻለ ይሆናል። የእስከ ዛሬው የዲፕሎማቶቻችን ስምሪት ይከናወን የነበረው በዋነኛነት የትምህርት ዝግጅትና የብቃት አቅም እየታየ ብቻ ሳይሆን አንድም ከሽረት ወደ ሹመት፣ አንድም መንግሥት ለባለውለታዎቹ ግለሰቦች ተቆርቋሪ ሆኖ ወይንም “ጥፋታቸው” ተሸፈፍኖ እንዲዳፈን በሹመት ስም ለማራቅ፣ አንድም የብሔረሰቦችን “የተዘነጋን ኩርፊያ” ለማረጋጋት፣ አንድም የፖለቲካ ስብጥርን “ለማሳመር” በጥቂቱም ቢሆን በሚገባ ታስቦበት ተገቢው ሰው በተገቢው ቦታ ይመደብ እንደነበር “ጌቶቻችን እንዳይቆጡ እንጂ” እውነቱ ከዚህ የራቀ አልነበረም።
የስምሪቱ መስፈርት ይህንን ከመምሰሉ የተነሳ ብዙዎቹ የኤምባሲ ጽ/ቤቶቻችንና አብዛኞቹ ዲፕሎማቶቻችን በየሀገሩ ከነበሩት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር የነበራቸው የሻከረ ግንኙነት ሀገሪቷን እስከምን ደረጃ አድርሷት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የሚውለበለብባቸው የሀገር ተምሳሌት ጽ/ቤቶች በራሳችን ዜጎች ሲዋረዱ፣ ዲፕሎማቶቻችንም ከዜጎቻቸው ጋር “የሌባና ፖሊስ ድብብቆሽ” እየተጫወቱ ስለመኖራቸው ያልመሸበት የትናንቱ ታሪካችን ነበር። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በዘመነ ተማሪነቱ አሜሪካን ካለው የሀገሩ ኤምባሲ ጽ/ቤት ጋር “በየዋህነት የግላጭ” ግንኙነት በማድረጉና “መቀራረብን በመስበኩ” የደረሰበትን መገፋትና መገለል በተመለከተ የግለ ታሪኩን መጽሐፍ ለንባብ ሲያቀርብ በዝርዝር ያስታውሰዋል። ኤምባሲ ጽ/ቤት ገና ባልተከፈተባት በሊቢያ (ሲርት) በተገኘበት አንድ አጋጣሚም “ኢትዮጵያዊ በመሆኑ” ብቻ የደረሰበት መንገላታትና መገለል ምን ያህል ስሜቱን ጎድቶት እንደነበር አይዘነጋውም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊታጠፉ በሚችሉት የኤምባሲ ጽ/ቤቶቻችን ምትክ በቀዳሚ መፍትሔነት ለመጠቆም የሞከሩት በርካታ የሀገሪቱ ተቆርቋሪ ዜጎች በየሀገሩ ስለሚገኙ እነርሱ ክፍተቱን እንደሚሸፍኑ የጥቆማ ያህል ሃሳቡን ነካ አድርገው ማለፋቸው ይታወሳል። ስለ አደረጃጀታቸውና ስለ አፈጻጸሙ ለጊዜው ዝርዝሩ ተብራርቶ ባለመቅረቡ ሃሳብ ለመስጠት ቢያዳግትም ጉዳዩ በመንግሥት በኩል በቀላሉ ታይቶ እንደማይታለፍ ለመገመት ግን አይከብድም።
መፍትሔ አከል ጥቆማዎች፤
የመዘጋት ውሳኔ ስለሚተላለፍባቸው የኤምባሲና የቆንጽላ ጽ/ቤቶች ማንነትና እንዴትነት ጉዳይ የተቆረጠ መረጃ ስለሌለ እንዲህና እንዲህ ቢሆን ለማለት ያዳግታል። ነገር ግን የትም ሀገር ይሁን የት ውሳኔው ሲተገበር አብሮ ሊታዩ የሚገባቸውን አንዳንድ ጥቁምታዎች በደምሳሳው አመላክቶ ማለፉ ይበጅ ይመስለኛል።
ሀገሬ ተመክራና ተዘክራ ጆሮ ካልሰጠችባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ለተለያዩ የውጭ ሀገራት ዋና ዋና ቋንቋዎች ልጆቿን በስፋት ያለማሰልጠኗ ድክመቷ ብቻም ሳይሆን ስናማት እንድንኖርም ምክንያት ሆኖናል። የገዘፈ ስም ኖሮት የኮሰሰ ተግባር ሲፈጽም የኖረው አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “የውጭ ቋንቋዎች ዲፓርትመንት” ለበርካታ ዐሠርት ዓመታት በውጭ ቋንቋዎች ውክልና ሲያስተምር የኖረው የእንግሊዘኛ ቋንቋን (ስለ ተማሪዎቹ ችሎታ ለጊዜው ተከድኖ ይብሰል) ብቻ እንደነበር እኔን መሰል የእርሱ ውጤቶች የምናስታውሰው የትንናትም የዛሬም እውነታ ነው።
በአረብ ሀገራት ተከበን የአረብኛ ቋንቋ ብርቅ ሆኖብን፣ በእንግሊዘኛ ይማራሉ እየተባልን ተምረውበታል የሚባለው ቋንቋ ራሱ ባዕድ ሆኖብን የኖርንባቸውን ዓመታት ዞር ብለን በጸጸት ስናስታውስ በእፍረት እንድናቀረቅር ግድ ይለናል። ለይስሙላ ያህል በትርፍ ጊዜና በፈቃደኝነት “የጀርመንኛ፣ የጣሊያንኛ፣ የአረብኛ ትምህርት ለመማር የሚፈልጉ…” የሚል ማስታወቂያ እየተለጠፈ የግብር ይውጣ ተግባር ሲፈጸምም በዘመነ ተማሪነታችን ማስተዋላችን አልቀረም።
እነሆ ያ “የምን ግዴለሽ ዘመን” መቶ እና ሁለት መቶ ፍሬ አፍርቶ ሃሳባቸውን በአደባባይ መድረኮች ላይ በድፍረት ለመግለጽ እንኳን “ዐይናፋር” የሆኑ በርካታ ዲፕሎማቶችን ስላፈራን “በኮክቴሎች ግብዣና በሚዲያ ፊት አታቅርቡን” የሚሉ “የሀገር ወኪሎችን” በገፍ ለመመልከት ተገደናል። ውጤቱም በዓለም መድረኮች ፊት ምን ስም እንዳሰጠን የሚታወቅ ነው። መንግሥትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዚህ ጉዳይ ላይ እንቅልፍ አጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ማሳሰቡ በቀዳሚ ማስታወሻነት እንዲታይ አደራ እናሸክማለን።
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ጠንካራ የሃሳብ ቋት ብድኖች (Think Tank Groups) ቢደራጁ የሚዘጉትን የኤምባሲ ጽ/ቤቶች ክፍተት ከሞላ ጎደል ሊሸፍኑ ስለሚችሉ ይሄም ጉዳይ በአግባቡ ቢፈተሽ አይከፋም። በተለያዩ ምክንያቶች (ለትምህርትም ሆነ ለንግድ ወይንም በነዋሪነት) በየሀገሩ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ከወዲሁ በአካባቢያቸው የማሕበረሰብ መዋቅር (Community) ማደራጀቱ አጥብቆ ቢሰራበት ጽ/ቤቶች ሲዘጉ የዜጎች መሠረታዊ መብቶችም አብረው እንዳይዘጋጉና ሌላ ያልተጠበቀ የተያያዥ ችግሮች አደጋ እንዳይከሰት በቅድመ ጥንቃቄነት ሊታሰብበት ይገባል።
በውጭ ሀገራት የተማሩ ዜጎች በማሕበራት እንዲደራጁ መንግሥት ድጋፍ ቢያደርግም ሥራዬ ብሎ ሲያግዛቸው ግን አይስተዋልም። ሲኒዬር አምባሳደሮች በተደራጀ አግባብ በማኅበርም ሆነ በሌላ መልኩ ቢሰባሰቡ በረጂም ዘመናት አገልግሎታቸው ባካበቱት ተሞክሮና ምክር ከፍተኛ ሀገራዊ አገልግሎት ሊሰጡ ስለሚችሉ ጊዜ ሳይሰጠው ቢሰራበት ጥቅሙ የትየሌሌ ነው። በተቀዳሚነት መሠራት ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በተለያዩ ዘርፎች መደበኛውን ዲፕሎማሲ ሊያግዙ የሚችሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኖች መፈጠር በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ይመስለናል። በዚህ ጉዳይ ይህ ጸሐፊ ባለፉት ዐሥር ዓመታት የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባል ሆኖ ባገለገለባቸው ወቅቶች የተማራቸውና የተገነዘባቸው በርካታ ጉዳዮች ስላሉ በሚቀጥሉት ጽሑፎች ለመዳሰስ ይሞከራል።
ችግሮቻችን በስፋት ተዳሰው መፍትሔዎቹ የሳሱ መምሰላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የርእሱ ጉዳይ በአንድ ጽሑፍ ብቻ መቋጨት ስለሌለበት በርግጡ የሀገራችን የዲፕሎማሲ ጉዞ ሽቅብ አድጓል ወይንስ በቁልቁለት ጉዞ ላይ ነበር? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ በድፍረትና በእውቀት ልንወያይበት ይገባል። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013