ከቀናት በፊት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ላይ ያስፈሯቸውን ጉዳዮች ቃኘት ቃኘት ለማድረግ ሞክሬ ነበር። ሁሉም በሚያስብል ደረጃ እውነት አሸናፊ ነው የሚል ጽንሰ ሐሳብ የያዘን መልዕክት ነበር። ለወዳጅም ለጠላትም ሲያጋሩ የነበረው። በተለይ ቀልቤን ሰቅዘው ከያዙት መልዕክቶችና የደስታ መግለጫዎች መካካል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገጽ ላይ ያገኘሁት የደስታ መልዕክት ‹‹የኢትዮጵያ አምላክ አይተኛም፤ አያንቀላፋምም›› የሚል ሲሆን፣ ይህ ትርጉሙ ብዙ ነው። ምን ብትሉኝ ደግሞ አምላክ የሚቆመው ከተጨቆኑት ጎን ነው። አምላክ የሚታደገው ፍርድ የጓደለባቸውን ነው። አምላክ የሚሟገተው የያዙት እውነት በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ከተቀለባቸው ወገን ነው።
አርቲስቱ ‹‹ሳንጃው ጸብ አይመርጥም፤ ልቁረጠው አለ እንጂ የራሴን ውሃ ጥም›› ነበር ያለው! አዎ እኛ ኢትዮጵያውያን ጸብ ይሉትን ኋላቀር አካሄድ በጭራሽ ምርጫችን እንደማናደርግ መንግስታችን ደጋግሞ በአባይ ውሃ ጉዳይ በእንወያይ፤ እንነጋገር መርሁ ማሳወቁ አንዱ ማሳያ ነው ብዬ አምናለሁ።
እርግጥ ነው በአባይ ጉዳይ ግብጽ በምትሻውና እንድንፈስ በቀደደችልን ቦይ እንደማንሄድ ጠንቅቃ ታውቃለች። አካሄዷ መሰሪነትን ያነገበ በመሆኑ ይህን ባህሪዋን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ የለም። ምክንያት ቢባል በአባይ ጉዳይ ፍትህ አልባ በሆነና ባረጀ ብሎም በጃጀ አካሄድ ድርድር ለማድረግ ብሎም በዚህ አሳሪ ህጓ ሊጠረነፍ የሚሻ ኢትዮጵያዊ እንደማይኖር ራሷም የምታውቀው ቢሆንም፤ ይህንኑ ያረጀ ዜማዋን ከማቀንቀን ተቆጥባ አታውቅም ።
በውሃ ግድብ ታሪክ፣ ብዙ ድርድር፣ ብዙ ጭቅጭቅና ብዙ ውይይት የተካሄደበት ግድብ ቢኖር የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ በፀጥታው ምክር ቤት ቀርበው የተናገሩለት በኢትዮጵያውያን ላብ፣ እንባ እና ደም እየተገነባ ያለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብቻ ነው። ይህ የሕዳሴ ግድብ ብዙ ደባና ብዙ ሸፈጥ፤ ብዙ ሴራና ብዙ ተንኮል ተጠንስሶበታል ። እረ እንዲያውም አለፍ ሲልም ዛቻና ማስፈራሪያም ሁሉ ተሞክሮበታል።
ሁሌም ቢሆን የሴራና የተንኮል ባለቤቷ ግብጽ ስትሆን፣ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ከፍጻሜው እንዳይደርስ በየጊዜው የምታዘጋጀውን የሴራ ድፍድፍ ደግሞ አንዳች ሳታቅማማ በመጨለጥ የምትታወቀው ሱዳን የሚሏት የግብጽ ተከታይ ናት። ግብጽ የሕዳሴ ግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ተከታታይ አስር ዓመታት አንዳንዴ በግልጽ በአደባባይ ቆማ በማን አለብኝነት ሴራ ስትሸርብብን፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሳር ውስጥ እባብ ሆና ስታደባብን ዛሬ ላይ ደርሰናል።
እርግጥ ነው ስታደርስብን የነበረው ደባ ሁሉ ወላፈኑ ሳይገርፈን አላለፈም፤ ግን ደግሞ አልወደቅንም። የየአገራቱ መሪዎች ለኢትዮጵያ ጀርባቸውን እንዲሰጡ ብዙ ጥራለች። አገራችንም ውስጥ በመግባት አንዳችንን በአንዳችን እንድንነሳ እርስ በእርስም እንድንባላ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። ወገን ወገኑን በማባረር የተፈናቃይ ቁጥር መበራከቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። አረብ አገራትንማ እንደ አሻንጉሊት ለማዘዝ ሁሉ ሲዳዳት ከርሟል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የሩቁን ትታችሁ በቅርቡ ከአረብ አገራት ወደ አገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር ልብ ማለቱ ብቻ በቂ ነው።
አገሪቱ በባህሪዋ ከሳሽ ብሎም ልክ እንደሱዳን ሁሉ ቃላአባይ ናት። ያልተገባትን ለመውሰድ በየአገራቱ ደጃፍ ትንከራተታለች። ብዙዎቹም አጀንዳዋ በማር የተለወሰ በመሆኑ ተሳስተው በራቸውን በርገደው ያስገቧታል። የአይጥ ምስክር ዲንቢጥ እንዲሉ ደግሞ መስክር ትሆናት ዘንድ ሱዳንን በነገር ሁሉ ከጎኗ ሻጥ ማድረግን አትዘነጋም። ሱዳን በበኩሏ የራሷ የሆነ አቋም ስለሌላት እንደ በቀቀን የግብጽን አጀንዳ ስታስተጋባ ዓመታትን በማስቆጠር ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ልክ የዛሬ ዓመት የመጀመሪያውን የህዳሴ ግድብ ውሃ መሙላቷ ይታወሳል። ይህን ያደረገችው ደግሞ እኤአ በ2015 በሱዳን ካርቱም ላይ የሶስቱ አገር መሪዎች ተገናኝተው በህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ በደረሱት የመርህ ስምምነት መሰረት ነው። አሁን ደግሞ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት በተሳካ መልኩ አከናውናለች።
ይህ ጉዳይ ያብከነከናት ግብጽ ወይም ሱዳን ብቻ ሳይሆኑ ከእነዚህ አገራት ጀርባ በመሆን ደጀንነታቸውን በየአጋጣሚው የሚገልጹ አገራትም መኖራቸው ለእኛ ኢትዮጵያውያን በፍጹም አይጠፋንም። የህዳሴ ግድቡ ሲሰራ ለጌጥ አይደለም። ከተገነባ ኃይል ለማመንጨት ውሃ መያዝ አለበት፤ ውሃ እየያዘ ነው ሲባል ግን ትን የሚላት ግብጽ ዛሬም ክሷን ታቆማለች ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።
ለግብጽና ሱዳን ዛሬም ቢሆን ልናስታውሳቸው የምንፈልገው ሃቅ አለ። የአባይ ወንዝ መነሻው ኢትዮጵያ ነው፤ ለዚህ ተፋሰስ አገራችን አበርክቶዋ ሲሰላ 86 በመቶ ነው። አቀንቃኙ ‹አባይ የግሌን ባልኩኝ ለጋራ› እንዳለው፤ ይህ ሁሉ መብት የኢትዮጵያ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያ ብቻዬን ልልማ፤ ልበልጽግ ሳትል በጋራ በፍትሃዊነት አብረን እንልማ ማለቷ ሁለቱ አገሮች ዛሬም ሊረዱን አልቻሉም።
ግብጽ ዛሬም ኢትዮጵያን በጃጀና በገረጀፈ ህጓ ጠርንፋ ለመያዝ ይዳዳት ይሆናል። ግን ኢትዮጵያ ዛሬ ሳይሆን ድሮም ቢሆን በየትኛውም አይነት ሁኔታ ትሁን ጥቅሟን አሳልፋ ለማንም ሰጥታ አታውቅም። አባቶቻችን ትናንት ታላቅ ተጋድሎ ፈጽመው ነጻ የሆነችውን አገር ለእኛ አስረክበውናል። ዛሬ ደግሞ ምንም እንኳ እንደጥንቱ አይነት ጦር ሜዳ ሊያውለን የሚያስችል ጦርነት ባይገጥመንም በአባይ ጉዳይ ለሚመጣ የትኛው ጉዳይ ማንም ሊያስቆመን እንደማይችል አገር ቤት ካሉ ዜጎች ጀምሮ በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ዘርፍ በሚያብል ደረጃ ተጋድሏቸው የላቀ ነው።ሁለተኛውም የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት የተከናወነውም በዚሁ የኢትዮጵያውያን የተጋድሎ ውጤት መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም።
ቅድስት ሰለሞን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013