ገና ከጅምሩ ከቀደሙት ምርጫዎች በብዙ መመዘኛዎችና አውዶች ስለሚለይ ስድስተኛ ሳይሆን አንደኛ ያልሁት ብሔራዊ ምርጫ ውጤት ያልጠበቅሁትና ዱብ እዳ ሆኖብኛል። ግምቴን ከንቱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ስህተትም እንደነበር አረጋግጦልኛል። በምርጫው አጠቃላይ ውጤት ብልጽግና በአብላጫ ድምጽ እንደሚያሸንፍ፤ አዲስ አበባን በጠባብ ልዩነት ሊያሸንፍ ኢዜማና ባልደራስ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የከተማውንና የፓርላማውን መቀመጫዎች እንደሚይዙ፤ በአማራ ክልል አብን የክልሉንም ሆነ የፓርላማውን መቀመጫዎች ሊያገኝ ይችላል፤ አስረኛ ክልል ሆኖ በተቋቋመው የሲዳም ክልል የሕዝቡ የአመታት የክልልነት ጥያቄ ስለተመለሰለት ሙሉ በሙሉ ሳይሆን ከፍተኛ የክልልና የፓርላማ መቀመጫዎችን እንደሚያገኝ ፤ በደቡብ ክልል በርካታ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ አቅርበው ምላሹን አጥጋቢ ሆኖ ስላላገኙት ብልጽግና በድምጻቸው ሊቀጡት ይችላል ። ስለሆነም ኢዜማና ሌሎች በክልሉ የተወዳደሩ ፓርቲዎች በርካታ መቀመጫዎችን ያሸንፉ ይሆናል ፤ በተቀሩት ክልሎችና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደርም ብልጽግና አብላጫ ድምጽ እንደሚያገኝ ተፎካካሪዎችም ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ወንበር ያገኛሉ ብዬ ገምቼ ነበር ። ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ፕሮፌሰር በላይ እጅጉ ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ ፤ እነ አንዷለም የሽዋስ ግርማ ክቡር ዶ/ር አንማው ወዘተረፈ፤ ከባልደራስ እንዲሁ በርካቶች እንደሚመረጡ እርግጠኛ ነበርሁ። ሆኖም ግምቴ ሁሉ ስህተት ነበር ። ለግምቴ ከ10 ማርክ ብሰጥ የማገኘው ዜሮ ነው ። ይህ ብዙዎችን በድንጋጤ ክው ድርቅ አርጎ ያስቀረው ምርጫ እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ !? ትክክለኛውን መልስ ለመስጠት ሰፊ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ቢሆንም የግሌን ምን አልባትና ትዝብት ላጋራ ።
የምርጫው ውጤት በዚህ መልኩ እንዲጠናቀቅ ካደረጉ አበይት መግፍኤዎች ፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተበታተነና በተከፋፈለ ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባታቸው ፤ በአብላጫ ድምፅ/ፈርስት ፓስ ዘ ፖል/የተዋቀረው ኋላ ቀር የምርጫ ስርዓት ፤ በኦሮሚያ ክልል ኦነግና ኦፌኮ በራሳቸው ምክንያት በምርጫው አለመሳተፋቸው ፤ በሀገሪቱ ሕልውና በተደቀኑ አደጋዎች የተነሳ ሕዝብ ጠንካራ መንግስት እንዲኖር ከልብ መሻቱ ፤ መራጩ ሰላምንና መረጋጋትን ማስቀደሙ ፤ ብልፅግና ፓርቲ ስልጣን ላይ ሆኖ የመወዳደር ብልጫ/አድቫንቴጅ/ ያለው መሆኑ ፤ የዶ/ር ዐቢይ የመሪነት ተክለ ሰብዕና ፤ በትግራይ ክልል የተካሄደው ዘመቻ በ14 ቀናት በድል መጠናቀቁ ፤ የሕዳሴን ግድብ ጨምሮ በሀገሪቱና በአዲስ አበባ የሜጋ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ፤ በአዲስ አበባ የተማሪዎች ምገባና ዩኒፎርም ፤ የአነስተኛና ጥቃቅን ስራዎች ፤ የከተማ የሴፍቲኔት ስራዎች ፤ ወዘተረፈ ብልጽግና የፓርላማ የክልሎችንና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትን መቀመጫዎች ጠራርጎ ለመውሰዱ የየራሳቸው አስተዋጾ ነበራቸው ። ምንም እንኳ የምዕራባውያን አለማቀፍ ሚዲያ ትግራይ ጦርነት ላይ ሆኖ ፤ ኦነግና ኦፌኮ ወይም 20 በመቶ የሚሆነው መራጭ ያልተሳተፉበት ብሎ ሊያጠለሸው ቢሞክር ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሕዝብ ከሞላ ጎደል ተቀብለውታል ። እውቅና ሰጥተውታል ። ገዢው ፓርቲም ባልተለመደ ሁኔታ በአሸናፊነቱ ከመፎለልና ከመፎከር ይልቅ ያሸነፈው አንድ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያ ናቸው በማለት የአብረን እንስራ ጥሪ ከማስተላለፍ ባሻገር ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁመውና ሒደቱን አምነው በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪዎች መቀመጫ ባያገኙም በካቢኔ በፌደራል ተቋማት በክልሎችና በፍርድ ቤቶች ተመድበው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ቃል ገብቷል።
የዚህን ጉደኛ ምርጫ ውጤት አበክረው በይነዋል ብዬ ከፍ ብዬ የዘረዘርኋቸውን ምክንያቶች በአለፍ ጠቀም እንመልከት። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሞላ ጎደል ሁሉም ሶሻል ዴሞክራት ሊበራል ዜጋ ተኮር ወይም በማንነት ላይ የተመሠረቱ ሆነው እያለ ቢያንስ ወደ ሶስትና አራት ትላልቅ ፓርቲዎች ሰብሰብ አለማለታቸው በሁለት መልኩ ዋጋ አስከፍሏቸዋል ። የመጀመሪያው ያላቸውን ውስን ፋይናንስና የሰው ኃይል ሰብሰብ አድርገው መቀናጀት ስላልቻሉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው እንዳይወጡ ከማድረጉ በላይ በተበታተነ ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባታቸው የመራጮቻቸው ድምጽ እንዲባክን አድርጓል ። ቀደም ሲል ከነበሩት ከ150 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ወደ 50 የሚጠጉ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድን መስፈርት አሟልተው የመወዳደሪያ ምልክት ወስደው በእጩነት ተሳትፈዋል ። መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም የየራሳቸው ደጋፊና መራጭ አላቸው ። በመሆኑም የመራጮች ድምጽ ለዚህ ሁሉ ፓርቲ ሲበተን አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው ብልጽግና ፓርቲ ነው ። በአዲስ አበባ የሆነውን እንደ አብነት ብንወስድ ፤ ኢዜማ አብን ባልደራስ እናት ነእፓና ሌሎች ሰብሰብ ብለው ተቀናጅተው ባለመወዳደራቸው ድምጽ ባክኖባቸዋል። ይህ የተፎካካሪዎች ድክመት አብላጫ ድምጽ ያገኘ አሸናፊ ይሆናል/ፈርስት ፓስት ዘ ፓል/ከሚለው የምርጫ ስርዓት ጋር ተጃምሎ ለብልጽግና ሰርግና ምላሸ ሆኖለታል ። ተፎካካሪዎች እንደ 97ቱ ቅንጅት ሰብሰብ ብለው ወደ ምርጫ ገብተው ቢሆን ኖሮ የተሻለ እድል ይኖራቸው ነበር ። እኛም በውጤቱ እንዲህ ቆሌያችን አይገፈፍም ነበር ። ከፍ ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርሁት፤ አወዛጋቢውና ጥንታዊው የእንግሊዙ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ የሚያልፍበት ስርዓት አንድን ወገን ብቻ ተጠቃሚ በማድረግ የቀሩትን በሞላ ተሸናፊ በማድረግ የሚያገል/ዜሮ ሰም ኮምፒቲሽን/ስለሆነ ይህ የፍትሐዊነት ጥያቄ የሚያስነሳ ስርዓት ለመጭው ምርጫ ይሻሻላል ተብሎ ይጠበቃል ። አዎ ለዜጎች የተሻለ ውክልናን የሚያረጋግጠውንና አለማቀፍ ተቀባይነት ያለውን ተመጣጣኝ ውክልና/ፕሮፖርሽናል ሬፕሬዘንቴሽን/የሚያሰፍነውን የምርጫ ስርዓት መከተል ዘመኑንም ትውልዱንም የሚዋጅ አማራጭ ነውና ። ሆኖም ምርጫው ፍጹም ነጻ ተአማኒና ፍትሐዊ ነበር እያልሁ አይደለም ። ከሚዲያ አጠቃቀም ጀምሮ ፤ በተወሰነ ደረጃ እዚህም እዚያም የመንግስትና የፓርቲ መደባለቅ ፤ ጫናና ወከባ መኖሩ አይካድም ። ሆኖም ጀማሪ ስለሆን የሚጠበቅ ነበር ማለት ይችላል ።
በኦሮሚያ ክልል ኦነግና ኦፌኮ በራሳቸው ምክንያት በምርጫው አለመሳተፋቸው የኦሮሚያ ብልጽግና ከ170 በላይ መቀመጫዎች ባሉት መልክዓ ብቻውን ሽምጥ እንዲጋልብ አግዞታል ። ኦነግ እንደ ግራምጣ ለሁለት መሰንጠቁን ተከትሎ በተፈጠረ ውዝግብ በኦቦ ዳውድ ኢብሳና በእነ ኦቦ ቀጀላ መርዳሳ አንጃዎች መካከል የተፈጠረው ንትርክና መካሰስ ረጅም ጊዜ በመውሰዱና የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ መቋጫ እስኪያገኝ ተጨማሪ ጊዜ በመውሰዱ ምርጫ ቦርድ ዘንድ የደረሰው ዘግይቶ የእጩዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ ስለነበር እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሕጋዊ መስፈርቱን አሟልቶ ከቦርዱ የምስክር ወረቀት ያገኘው የእነ ኦቦ ቀጀላ ቡድን ለምርጫው በእጩነት እንዲመዘገብ አስተያየት አቅርበው ነበር ። ሆኖም የእጩዎች የምዝገባ ጊዜ አልፎ ስለነበር ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊያስተናግደው አልቻለም ። ሌላው ከዚህ በፊት በተካሄዱ የይስሙላ ምርጫዎች ሲሳተፍ የኖረው ኦፌኮ ደግሞ በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ አባሎቼ ካልተፈቱ በምርጫ አልሳተፍም የሚል ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ራሱን አግልሏል። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም እነ ፕሮፌሰር መረራ ከምርጫው እንዳይወጡ በግል ለማግባባት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን በአንድ መድረክ ሲናገሩ ተደምጧል። የምዕራባውያን ሚዲያ ግን ኦነግም ሆነ ኦፌኮ በመንግስት ሆን ተብሎ እንደተገፉ አድርጎ ለማሳየት ይሞክራል። ፕሮፍ ከቅርብ አመታት ወዲህ ምን እንደነካቸው እንጃ በምርጫው ማግስት ብቅ ብለው በአንድ አመት ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ ጠየቁ ተብሎ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር ። በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የዚህን ታሪካዊ ምርጫ ቅድመና ድህረ ሒደት ሰንዶና ቀምሮ በመጽሐፍ መልክ ቢያዘጋጀው መልካም ነው እላለሁ ። ለዚህ ምርጫ ሒደት በስኬት መጠናቀቅ የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ባስተላለፉት መልዕክት እንውጣ ።
እንደ መውጫ
ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ ባለፈው ሳምንት በስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጃ የምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጊያ ስነስርዓት ላይ ፤” ምርጫው አልጋ በአልጋ በነበረ ሁኔታ አልተካሄደም። ዜጎች በርካታ ሥጋቶች ውስጥ ሆነው የተሳተፉበት ነው ። ሁላችሁም እንደምታውቁት ይኼ ምርጫ ቀላልና አስደሳች በሚባል ወይም ደግሞ ውጤቱ ይኼ ነው በሚል ትንበያ ሁኔታ የተደረገ አይደለም። አገራችን በብዙ ውጣ ውረዶች በምታልፍበት ጊዜ ብዙ ተለዋዋጭ ሒደቶች ውስጥ እየተላጋች የፀጥታ ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው በሚባልበት ጊዜ ፤ ዜጎች የዜግነት መብታችንን መጠቀም መቻል አለብን ብለው በንቃት የተሳተፉበት ምርጫ ነው ። ይኼንን አድርገናል ይኼንን ቆጥረናል ብሎ የማሳወቅ ሒደት ብቻ ሳይሆን፤ ከሒደቱ ሁላችንም የምንማርበት ወደፊት ለመሄድ ደግሞ አገራችን ሁልጊዜም በምርጫ ብቻ ሥልጣን ከአንድ እጅ ወደ አንድ እጅ እንደምታዘዋውር ደግመን የምናረጋግጥበት ሒደት መሆኑን የምታዩበት ይሆናል ብዬ አምናለሁ።…”ማለታቸውን የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል ።
በዚህ ስነ ስርዓት በክብር እንግድነት እንዲገኙ ሲጋበዙ አንገራግረው እንደነበር በመናገር ንግግራቸውን የከፈቱት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ፤ “በአገሪቱ የታየው የፀጥታ መደፍረስ የፖለቲካ ችግሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ሁኔታ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ የአገሪቱ የቆዳ ስፋት ትልቅነት ፈታኝ መሆኑን በመጥቀስ ቦርዱ የተንቀሳቀሰበት ወቅት ፈታኝ ነበር ። ሆኖም ምርጫው እንደተወራለት ወይ ደግሞ እንደተሟረተበት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ስላደረጋችሁ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ለቦርዱ አባላትና ኃላፊዎች ለሠራተኞች በዚህ ተግባር ላይ ለተሳተፉት በሙሉ በኢትዮጵያ ሕዝብና በራሴ ስም ምሥጋና አቀርባለሁ ። ቦርዱ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርጫ ለማካሄድ በመቻሉ ብቻውን ድል ነው ። ይፋ በሆነው ውጤት መሠረት ያሸነፋችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ፤ በምርጫው አሸንፎ መንግሥት የሚመሠረተው ኃይል ኢትዮጵያውያንን በሙሉ እኩል የሚያስተዳድር እንዲሆንም ይጠበቃል ፤” ብለዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር ! ! !
አሜን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም