መርድ ክፍሉ
ካለፉት ሶስት ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ የግጭትና የሞት ዜና መስማት የየለት ተግባር ሆኗል። ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት ተስኗቸው በተለያዩ ጊዜያት የድረሱልን ጥሪ ሲያሰሙም ቆይተዋል። ይህን ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል ተብሎ በመንግስት የተፈረጀው የህወሀት ቡድን ሲሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በሽብርተኝነት እንዲጠራ ተወስኖበታል። ይህ የሽብርተኛ ቡድን በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ሀይሉን አጠናክሮ ግልፅ ጦርነት መክፈቱ ይታወሳል። ይህ ሽብርተኛ ቡድን በውጭ ሀይሎች በመታገዝ በፕሮፓጋንዳና በሌሎች መንገዶች አገር የማተራመስ ስራውም ቀጥሎበታል።
ለመንደርደሪያ ይህን ያክል ከተመለከትን በዚህ ዙሪያ ወደታዘብነው ጉዳይ እንግባ። የፌደራል መንግስት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ በትግራይ ክልል የተናጥል ተኩስ አቁም በማድረግ የአገር መከላከያ ሀይሉ እንዲወጣ አድርጓል። ይህን ተከትሎ ታዲያ የሽብርተኛው የህወሀት ቡድን ከተደበቀበት ዋሻ በመውጣት በአሸናፊነት መንፈስ ለድጋሚ ጦርነት እየሸለለ ይገኛል። የሽብርተኛ ቡድኑን ሽለላ እየተቀባበሉ የሚዘግቡት የውጭ መገናኛ ብዙሀንን ወደ ጎን ትተን በዚሁ አገራችን ሽብርተኛ ቡድኑን የሚደግፉ ሰዎች ያስገርሙኛል። ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል በተደረገው ዘመቻ ረሀብ፣ መደፈር፣ ሞት እንዲሁም ሰብዓዊ ቀውስ መፈጠሩን መዘንጋት አሁን ጦርነት እንዲነሳ ፀሎት በማድረግ ላይ ናቸው። እነዚህ ሰዎች እኮ አዲስ አበባ በየጭፈራ ቤቱ ዳንኪራ የሚደልቁ ናቸው…።
በአማራ ክልል ላይ የሽብርተኛ ቡድኑ ጥቃት በመሰንዘሩና ለቀጣይ ጦርነት ነጋሪት በመጎሰሙ የአማራ ክልል ነዋሪ በክተት አዋጅ ተሰባስቦ ለመዋጋት ወደ ግንባር እየዘመተ ይገኛል። በዚህ ክተት አዋጅ አዛውንቶች ሳይቀሩ ወደ ግንባር ሄደው ህወሃትን ለመፋለም ታጥቀው ዘምተዋል። ይህ ሁኔታ ለተመለከተ የውጪ ወረራ የመጣ እንጂ ለርስበርስ ጦርነት የዘመቱ አይመስልም። በተጨማሪም ሌሎች በአገሪቱ የሚገኙ ክልሎች ለዘመቻው ልዩ ሀይላቸውን እያዋጡ ይገኛሉ። ምን ያህል ህወሃት አገር በመራበት ወቅት ኢፍትሀዊነትና ጭቆና ተንሰራፍቶ እንደነበር አንዱ ማሳያ ተደርጎ መውሰድ ይቻላል።
አንዳንድ ወገኖች ከጦርነቱ ይልቅ ፖለቲካዊ ድርድር ቢደረግ ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ መቀነስ ይቻላል የሚል አስተያየት እየሰጡ ይገኛሉ። ሁኔታውን ለተመለከተ ግን ጉዳዩ እንኳን በጦርነት በድርድር ሊፈታ እንደማይችል ነው። ምክንያቱም አማራ ክልል በጉልበት የተወሰደብኝን መሬት ይዣለውና አለቅም ሲል ሽብርተኛ ቡድኑ ደግሞ ግዛታችን እስከሆነ ድረስ ያለንን ሀይል ተጠቅመን እናስለቅቃለን እያለ ይገኛል። ፌደራል መንግስቱ በጉዳዩ ላይ ምን ሳይል ሽብርተኛ ቡድኑን ለማጥፋት ጥረት እያደረገ ይኛል። አሸናፊ ማን እንደሚሆን ለማየት ያብቃን።
እዚህ ጋር ሳልጠቅስ የማላልፈው የትግራይ ህዝብ አላማና ግቡ ከህወሃት ጋር አብሮ መሞት ወይስ እራሱን ማዳን የሚለው ነገር እስካሁን ውሉ አለመለየቱ ነው። ህወሀት ህፃናትን ለጦርነት እያሳተፈ ሲሆን ይህንንም ነገር አለም አቀፉ መንግስት በዝምታ አልፎታል። በትግራይ ውስጥ የሚኖረው ህዝብ ምን እያሰበ እንደሆነ ማወቅ ባይቻልም ለቀጣይ አስርት አመታትን በከፋ ድህነት ውስጥ ሆኖ በእርዳታ ለማሳለፍ ይገደዳል። ቀድሞ እንደነበረውም በየቦታው እየተሰደደ የድህነት ኑሮውን ያሳልፋል። ከነዚህ በፊት ግን አሁን ሰከን ብሎ ማሰብ ከቻለ በተወሰነ መንገድ ችግሩን ማቃለል ይችላል የሚል ግምት አለኝ።
‹‹ከጦርነት ድርድር ይቅደም›› የሚል አንድም ሰው መጥፋቱ ግን ግርም ይላል። ሁሉም ወደ ርስበርስ ግጭት ለመግባት እንዲህ ያጎበገጎበው ቆይ ተለዋጭ አገር አዘጋጅቶ ነው ወይስ ሌላ ነገር አለ…። በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ በተፈጠረው ቀውስ ምን ያህል የኑሮ ውድነት እንደመጣ በግልፅ የሚታይ ነገር ነው። በቀጣይም ይህ ጦርነት ከቀጠለ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ታድያ ወደ ከፋ ድህነት ለመግባት ይህን ያክል መጣደፍን ምን አመጣው። ቢያንስ ሁሉም እንደ አንድ ህዝብ ቢያስብ እያልኩ እመኛለው….ነገር ግን የህዝቡን ለመበታተን መሯሯጥ ሳይ ተስፋ እቆርጣለው። አንዳንዴማ ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው ቃል ፅሁፍ ላይ እንጂ ከሰው አፍ መጥፋቱን ሳይ ወደ ፊት የአገሩን ስም የማያውቅ ትውልድ እንዳይፈጠር እሰጋለው..።
ከዚህ በተጨማሪ የሚያስተዛዝበው ጉዳይ በትግራይ ያለው የህወሃት አሸባሪ ቡድን ህፃናትን እየመለመለ ወደ ጦር አውድማ እያሰማራቸው መሆኑ ነው። ሰሞኑን የኢትዮጵያ የሴቶች፣ ወጣቶች እና ሕፃናት ሚኒስቴር አሸባሪው የህወሃት ቡድን ህፃናት ወታደሮችን በጦር ግንባር እያሰለፈ መሆኑን በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው ጥሪ አቅርቧል።
ይህ አሸባሪ ቡድን ህፃናት ወታደሮችን ከፊት በማስቀደም ጥቃት ለማድረስ ሙከራ ሲያደርግ እንደነበረ የወጡ ሪፖርቶች፣ የቪዲዮ ምስሎች እና የተለያዩ ሥዕሎች ታይተዋል። እነዚህ ማስረጃዎች በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚያስቆም የጦር ወንጀል መሆኑ በኢትዮጵያ ላይ መጥፎ ገፅታ የሚያጠላ ነው። ከዚህ ባለፈም ከውጭ ጠላቶቿ ጋር በማበር መንግስት ሰብአዊ መብት እንደጣሰ ለማሳበቅና ለማዋረድ እንዲሁም ሃገር ለማፍረስ ያለውን ጥልቅ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ መሆኑን ስንረዳ አጀብ ሴራ የሚያስብል ነው።
ከውልደቱ ጀምሮ በሴራ የተጠመቀው አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከመንግስት የተሰጠውን ጦርነት የማብረድ የተናጠል ውሳኔ ሲፈልገው እንዳልነበር፣ አሁን መልሶ ላም ባልዋለበት ኩበት መልቀም እንደሚባለው መከላከያ ሰራዊት ጦርነት ባቆመበት ሁኔታ ለጦርነት መነሳቱ ይህ ቡድን የሀገሪቱን ስልጣን በተቆናጠጠበት ወቅት ምን ያህል እብሪተኛና በህዝብ ላይ ጉዳት ሲያደርስ ነበር ለማለት ጠንቋይ መቀለም አይጠይቅም።
ሌላው የምንመለከተው ስለ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነው። የኮሮና ቫይረስ ጊዜውንና ባህሪውን እየቀያየረ አለምን ማሸበር ቀጥሏል። ከኖቭል ኮሮና እስከ ዴልታ የዘለቀው የቫይረሱ ስርጭት ኢትዮጵያንም እያመሰ ይገኛል። ቫይረሱ ወደ አገሪቱ ከገባ ጀምሮ በመንግስት በኩል ህብረተሰቡ ጤንነቱን እንዲጠብቅ የተለያዩ መመሪያዎች ሲሰጡ ቆይተዋል። ከዚህም ውስጥ እጅን ቶሎቶሎ መታጠብ፣ እርቀትን ጠብቆ መቆም ወይም መቀመጥ፣ አለመጨባበጥና ግዴታ ካልሆነ ከቤት አለመውጣት ይገኙበታል። ይህንንም ህብረተሰቡ ተግባራዊ እንዲያደርግ በመገናኛ ብዙሀንና በአደባባይ ትምህርት ሲሰጥም ሰንብቷል። ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ በገባ ሰሞን ሁሉም ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ቢነገረውም ‹‹ኮሮና ወጣትን አይዝም፣ ኮሮና በባህላዊ መንገድ መከላለከል ይቻላል›› በሚል መንፈስ ግዴለሽነቶች በብዛት ይስተዋሉ ነበር። እነዚህ ግዴለሽነቶች የብዙ ሰው ህይወት ቀጥፈዋል።
ቫይረሱ የገባ ሰሞን በየመንገዱ በሚገኙ የእጅ መታጠቢዎች አካባቢ ህብረተሰቡ ተራርቆ ከመታጠብ ይልቅ ተፋፍጎና ተደራርቦ ሳሙና እየተዋዋሰ ሲታጠብ ማየት የተለመደ ነበር። ነገር ግን በየአካባቢው የነበሩ በጎ ፈቃደኞች ነገርየው ትክክል አመሆኑን ቢያውቁም በይሉኝታ ሰበብ ዝም ብለው ያልፋሉ። በሌላ በኩልም በሸማች ማህበራት ሱቆች፣ በእህል ማስፈጫ ቤቶች እና ሌሎች ብዛት ያላቸው ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ ያለ ጥንቃቄ የሚደረጉ ነገሮች ቢኖሩም የፀጥታ አስከባሪ ፖሊሶች በዝምታ ሲያልፉ ተስተውሏል።
ሌላው ደግሞ በህዝብ ትራንስፖርት መስጫ መኪናዎች ውስጥ በአሁን ወቅት መጨናነቆች አየታዩ ሲሆን ከተሳፋሪዎቹ መካከል ማስነጠስና የማሳል ሁኔታ ሲኖር መስኮት እንዲከፈትና ያስነጠሰው ወይም ያሳለው ሰው አፉን እንዲሸፍን የሚናገር ሰው አይታይም። በተመሳሳይም በመንገድ ላይ በጉንፋን ይሁን በሌላ ምክንያት አፉን ሳይሸፍን ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ እንደሱ አይደረግም የሚል ሰው የለም ምክንያቱም ይሉኝታ ጠፍሮ ማህበረሰቡን ስለያዘ ነው። ይህ ሁኔታ በመንግስት መስሪያቤቶች አካባቢም ይስተዋላል። በቢሮ ውስጥ አንድ ሰው ቢያስነጥስ ወይም ቢያስለው ወዲያው ጉንፋን ነው…ብርድ ነው ብሎ ሲያስተባብል አይ አደለም ሌላም ሊሆን ይችላል ተመርመር ብሎ የሚከራከር ሰው አይታይም ምክንያም በይሉኝታ ተሸብቧልና…ነው።
በጤና ጣቢዎችና ክሊኒኮች ኣካባቢ የተለያዩ ህመሞችን ታመው የሚመጡ ሰዎች ይበዛሉ። የህክምና ባለሙያዎችም አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ ሲሯሯጡ ይስተዋላል። ነገር ግን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሲደረግ አይታይም። ታካሚዎች ለመታከም በሚመጡበት ወቅት ነርሶች የሚገባውን ጥንቃቄ በተለይ አፍ መሸፈኛና የእጅ ጓንት ሲያደርጉ አይስተዋልም። ይህን ሁኔታ ሁሉም የሚያስተውለው ጉዳይ ቢሆንም በምን አገባኝ መንፈስና በይሉኝታ ተይዞ ሲናገር አይታይም። በዚህም በሆስፒታሎች አካባቢ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ሆኗል።
በምንኖርበት ሰፈር ይሁን በመስሪያ ቤቶች አካባቢ አብዛኛው ሰው ሲበላም ሆነ ሲወራ ተጠጋግቶ ነው። አንዳንዴም በወሬ መሀል የእጅ ንክኪዎች አይጠፉም። ይህ ሁኔታ ለበሽታው ተጋላጭነት እንደሚጨምር ቢታወቅም በይሉኝታ ተይዘን እያደረግነው እንገኛለን። ከዚህም ሌላ የገንዘብ አጠቃቀማችን የእጅ በእጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ገንዘብ ስንሰጥም ሆነ ስንቀበል ምንም አይነት ጥንቃቄ አናደርግም። ከሰው ገንዘብ ስንቀበል ወይም ስንሰጥ እጃችንን ሳኒታይዘር ስንቀባ አንታይም። ከላይ ከተዘረዘሩት ወጪ ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በይሉኝታ ምክንያት ለኮሮና በሽታ ሊያጋልጡን እንደሚችሉ ይታወቃል። በተለይ በገበያ ቦታዎች ላይ አሁንም ድረስ ያለው ግፊያና ግርግር ገደብ ሊበጅለት ይገባል።
እነዚህ ሁሉ ነገሮች ኅብረተሰቡ በኮሮና ወረርሽኝ ላይ ምንም አይነት ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ያሳያል። በጣም አስገራሚው ነገር የኮሮና ክትባት መከተብ እንደ ውግዘት የሚያይ ሰው መብዛት ነው። ክትባቱን የወሰደ ሰው ያስተላልፍብናል በሚል ምንም በጥናት ያልተረጋገጠ ወሬ የሚያስወሩ ተበራክተዋል። በሌላ በኩልም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች መቀነስ ነፃነት የሰጣቸው ሰዎች ያለጥንቃቄ ኑሯቸውን እየገፉ ነው። ጤና ሚኒስቴር ‹‹ዴልታ›› የተባለው የቫይረሱ ዝርያ ወደ አገሪቱ ሊገባ ስለሚችል ጥንቃቄ ቢልም የሰማው ያለ አይመስልም። የኮሮና ወረርሽኝ በቀጣይ ከተባባሰ ወጥቶ መስራት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ስለሚደረስ ካሁኑ ብንጠነቀቅ ይበጃል።
ታዲያ ጦርነት በአንድ ጎን ኮሮና በሌላ ጎን ወጥረው ይዘውን ወደ ከፋ ድህነት እየተገባ መሆኑን ግን ሰው እያስተዋለው ይሆን? የኑሮ ውድነቱ ከመጨመሩም በላይ ከመኖር ወደ አለመኖር የሚሸጋገረው ሰው እየተበራከተ ነው። በየጊዜው የሚጨምረው የሸቀጥና የቤት ኪራይ ዋጋ እንዲሁም የስራ እጥነት ቁጥሩ ሲታይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ያስፈራል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም