በዛሬው የአዲስ ዘመን ዱሮ አምዳችን አዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1962 ዓ.ም ሀምሌ ወር መጀመሪያ አካባቢ ይዟቸው ከወጣ ዘገባዎች መካከል ዘሙኑን ይመለከቱበታል፤ ከዚህ ዘመን ጋርም ያነጻጽሩበታል፤ ቁምነገር ይገበዩበታል ያልናቸውን ልዩ ልዩ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
የተባበሩት መንግስታት ስለሰው ልጅ ማሰብ አለበት
– ኡታንት
ኒውዮርክ/ ሮይተር/ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአይዶሎጂ ልዩነትና በአገሮች አለመግባባት በንትርክ ጊዜውን ስለሚጨርስ ስለጠቅላላው የሰው ልጅ ደህንነት እንደተፈለገው ለመስራት አለመቻሉን የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ኡታንት አስገነዘቡ።
ዋና ጸሀፊው አስተያየታቸውን የሰጡት በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ የአለም ወጣቶች ጉባኤን ከትናንት በስቲያ በከፈቱበት ወቅት ነው።
በአለም ውስጥ በየጊዜው በሚፈጠሩት የአገሮች አለመግባባትና በሚነሱት ጦርነቶች ምክንያት አብዛኛው የአለም ህዝብ ገና ከችግር ያልወጣና የኑሮው ደረጃ ያልተስተካከለ መሆኑን ኡታንት ገልፀዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ቢሆን እስከዚህ ድረስ የሰው ልጅ በቀጥታ ድምጽ የሌለው መሆኑን አስረድተዋል። ይሄውም አባል አገሮች ቃል ኪዳናቸውን ባለማክበራቸው ነው ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመበትን ፳፭ ኛ አመት ምክንያት በማድረግ በድርጅቱ አማካይነት በተዘጋጀው የአለም ወጣቶች ጉባኤ ላይ ከ፩፻፲ ሀገሮች የተውጣጡ ፮፻ ወጣቶች ተገኝተዋል።
የወጣቶቹ ጉባኤ ገና ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ሲሆን በልዩ ልዩ የኢንተርናሽናል ጉዳዮች ላይ
ቀርበናል፡፡
ውይይት ያደርጋል። ጉባኤው ስራውን ከመቀጠሉ በፊት ፲፰ አባሎች ያሉበት የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ መርጧል። አብዛኞቹ ወጣቶች ከ18 አስከ ፳፭ አመት እድሜ ያላቸው ናቸው።
ህምሌ 4 ቀን 1962
ወይዘሮ ሙላቷ ፋንቄቦ እንዳይለቀስላቸው ተናዘው ሞቱ
ያገራችን ለቅሶ ልማድ የተለያየ ቢሆንም አንዱ ክፍል ሙሾ ገጣሚ በገንዘብ ገዝቶ ከብዙ አመቶች በፊት የሞቱትን የሟቹን ዘመዶች ስምና ሙያ እየጠቀሱ ግጥም እየገጠሙ የተሰበሰበውን ህዝብ እንባ በእንባ ማራጨት ደረት መድቃትና ፊት መንጨት በጠቅላላው እዚህ ግባ የማይባል ስቃይ የሚታይበት መሆኑ አይካድም። የኢትዮጵያ ተዋህዶ ሃይማኖት መሪዎች ከማስተማር አልፈው እስከ መገዘትም የደረሱበት ጊዜ ጥቂት አይደለም።
ወይዘሮ ሙላቷ ፋንቄቦ ስለዚህ ጉዳይ ከማረፋቸው አስቀድመው ሙሾ ገጣሚ ገዝተው እንዳያለቅሱና እንዳያስለቅሱ በማለት ኩነዛዜያቸው ጋር አያይዘው ‹‹ ልጆቼና ዘመዶቼ የሆናችሁ ሁሉ ጥቁር ልብስ የለበሰ ጥቁር ከረባት ያሰረ የተረገመ ይሁን›› ሲሉ ተናዘው በተወለዱ በ87 አመታቸው ሀምሌ 7 ቀን 62 ዓ.ም አረፉ።
በኑዛዜው መሰረት የቀብሩ ስነ ስርአት ያለ አንዳች ዋይታ እንባ በማፍሰስ ብቻ ተፈጽሟል። በስነ ስርአቱም ላይ ብጽእ አቡነ ፊልጶስ ተገኝተው የሟችን ኑዛዜ በመደገፍ ጠቃሚ ምክር ለሀዘንተኞቹ አሰምተዋል። ከብጹእነታቸው ንግግር ቀጥለው ከቤተዘመድ አንደኛ ‹‹ ወይዘሮ ሙላቷ ልጆቼን መርቄያቸዋለሁ፤ እናንተም መርቁልኝ ከሳልስቴም በሁዋላ ጥቁር ልብስ የለበሰ ጥቁር ከራባት ያሰረ የተረገመ ይሁን›› ብለው መናዘዛቸውን ለለቀስተኛው ገልፀዋል።
ህምሌ 15 ቀን 1962 ሽክን ያለች የዶሮ ወጥ ለመብላት የቡና ቁርስ በድቁስ ለመቅመስ የሚያስፈልገው በርበሬ ነው። በርበሬን ቀምመው የሚያዘጋጁት ሴቶች እንደመሆናቸው መጠን ከሚነግዱትም አያሌዎቹ ሴቶች ናቸው። በርበሬ እንኳን ለብዙ ጊዜያት አብረውት ሊኖሩ ቀርቶ ገዝተው ቀምመው እስከሚያሰፈጩትም ሌላው ቀርቶ ሲበሉት ያለውን ማስነጠስና ማቃጠል የቤት እመቤቶች ሁሉ የሚገነዘቡት ነው።
ታዲያ የበርበሬ ነጋዴዎቹ ሴቶች እያቃጠላቸውምን? ወይስ እንዳያቃጥላቸው የሚያደርጉት መከላከያ አለ? ከ፲አመት በላይ በበርበሬ ነጋዴነት የኖሩት አሁንም በመነገድ ላይ ያሉት ወይዘሮ ኢዩቴ ሰጠኝ ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገሩ ‹‹ እስከ አሁን ድረስ እንዳያቃጥለኝ ያደረግኩት መከላከያ የለም። በርበሬ ነውና ማቃጠሉ አይቀርም። ሆኖም ስራውን እንደጀመርኩት ሰሞን የምሰቃየውን ያህል በአሁኑ ወቅት አይሰማኝም። ምክንያቱም ለምጄዋለሁና ብለዋል። ወይዘሮ ኢዮቴ የበርበሬ ዋጋ ክረምት በመሆኑ በጣም ከፍ ያለ ሳይሆን በመጠኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በርበሬ ነጋዴዋ ልጆች እንዳሏቸው ነግረውናል። ሆኖም ቁጥራቸውን ገለጡልን ብንላቸው ስላሴ የሰጠኝን ያህል ሞልተውኛል በማለት መልስ ሰጥተዋል።
ሀምሌ 16 ቀን 1962
32 ሰካራሞች እያንዳንዳቸው 50 ብር ተቀጡ
አዲስ አበባ፤ (ኢ-ዜ-አ-) የአዲስ አበባ ፭ኛ ፖሊስ ጣቢያ ያለ ሰዓት በሚዘዋወሩና ከመጠን በላይ በመጠጣት አቅማቸውን ባልመጠኑ ጠጪዎች ላይ ባደረገው ቁጥጥር ፴፪ ሰዎች በሰዓት እላፊ ተይዘው ፮ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ እያንዳንዳቸው ከማስጠንቀቂያ ጋራ ፶ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው መሆኑን የጣቢያው አዛዥ ገለፁ።
ከዚህ በቀር በሕዝብ መተላለፊያ መንገዶች፤ በዋና አደባባይ ዙሪያ፤ በመኖሪያ ሠፈሮች አካባቢ ያለ አንድ ምክንያት በሥራ ፈትነት ” ይቺን ያገኘ ይጪኝ ይብላ” እያሉ በማወናበድ ሕዝብን የሚያስቸግሩ ፵፰ የካርታ ቁማርተኞች ተከሰው እያንዳንዳቸው ከብርቱ ማስጠንቀቂያ ጋር ፶ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ መቀጫውን ባይከፍሉ፤በ፪ ወር እሥራት እንዲቀጡ የተፈረደባቸውን መሆኑን የ፭ኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ሻምበል ደጀኔ መሸሻ በተጨማሪ አረጋግጠዋል።
ሀምሌ 2 ቀን 1962
የዓመቱ ምርጥ መምህራን ምስክር ወረቀት ተቀበሉ
የአዋሳ ታቦር ትምህርት ቤት ” የዓመቱ ምርጥ መምህራን” ተብለው ለተመረጡ ሦስት መምህራንና ለ፳፭ የትምህርት ኮሚቴ አባሎች ባለፈው እሑድ ምስክር ወረቀት ሰጠ፡፡
በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ግራዝማች ከበደ ወ/መድኅን የጠ/ግዛቱ ጸሐፊ፤ ብርጋዲየር ጄኔራል ቀልቤሳ ቤካ የጠ/ግዛቱ ፖሊ ዋና አዛዥ፤ እንዲሁም የተማሪዎች ወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተው ነበረ፡፡
ከዚህ በቀር ትምህርት ቤቱ ” ሁሉም ይማር ” በሚለው ዓላማ መሠረት ማንበብና መጻፍ ላስተማራቸው ፵ ለሚሆኑ መሃይምናን በዚያው ቀን ከትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር የተላከላቸውን የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡
የምስክር ወረቀቱን የሰጡት የጠ/ግዛቱ ጸሐፊ ግራዝማች ከበደ ወልደ መድኅን ናቸው፡፡ ከምስክር ወረቀቱ አሰጣጥ ቀደም ብሎ የትምህርት ቤቱ ዲሬክተር አቶ ታምርአየሁ ለማ ስለትምህርት ቤቱ አቋም ገለጣ አድርገዋል፡፡
ሀምሌ 1 ቀን 1962 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም