አዲስ ዘመን ትናንት፣ አዲስ ዘመን ዛሬም ነው፡፡ ሰው እንጂ በዕድሜ ዘመን ያለ ትውስታና ትዝታ አያረጅም። ትናንት አዲስ የነበረው ዘመን ዛሬም ሕያው ነው። ከትናንቱ ለዛሬ ትውስታችን እንዲሆነን ሸሁ «1 ሺህ 340 ዓመቴ ነው» ሲሉ ሽንጣቸውን ገትረው በልበ ሙሉነት የተናገሩትን እናስታውስ፡፡ ከእሳቸው ጋር ቆይታ ያደረገው የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛም ቢጠይቃቸው፤ «ከአሕመድ ግራኝ ጋር ብዙ ጊዜ እንገናኝ ነበር፣ አፄ ቴዎድሮስንም አውቀዋለሁ» ይላሉ፡፡ በ20 ኪሎ ምስር ላይ 30 ኪሎ አፈር እየጨመረ ስለሚሸጠው ነጋዴም ከተጻፈው እናንብብ። ከማያባራው የአንባቢያን የጥያቄ ውሽንፍር ላይ ከቆመው የጳውሎስ ኞኞ ደብዳቤዎችም ጥቂቶችን እናስታውስ፡፡
1 ሺ340 ዓመቴ ነው የሚሉ ሰው ተገኙ
1 ሺ 340 ዓመት ዕድሜ ያለው ሰው በሕይወት ይኖራል ብለን ባናምንም ወሬው እንዳያመልጠን ከአዲስ አበባ ወደ አባኮራ ሰፈር ሄድን። ከሸሁ ቤት ደረስን። እንግዳ መጣ ሲባሉ ከአጣና አልጋቸው ላይ ተነሱ። የሱሪያቸውን ጥብጣብ ሸምቅቀው ታጠቁ። ጋቢያቸውን አደገደጉ፤ ቁልፍ የበዛበትን ካቦርታቸውን ደረቡ። ደህና የቆመጥ ምርኩዛቸውን ይዘው ወደ ውጭ ወጡ።
ሸሁ በሰፈራቸው የተከበሩ ናቸው። በተናገሩ ቁጥር የሰፈሩ ሴቶች “መጀን ያላህ ተዓምር” ይላሉ። ዙሪያችንን የከበቡን ሕጻናት ሸሁን እንደ አንድ ተዓምር ይመለከቷቸዋል። ሸሁ ዓይናቸውን አውኳቸዋል እንጂ በምንም ያልደከሙ ናቸው። ሲስቁ እንዳየነው የሸሁ የታች ጥርሶች ከመበለዛቸው በስተቀር ገና የሚያገለግሉ ናቸው።
ከሸሁ ጋር ጭውውት ጀመርን። “ትክክል ዘንድሮ 1ሺ 340 ዓመት ሞላኝ” አሉን። ስማቸው ሸህ ሙሳ ኪን ሐጂ መሆኑንና አባታቸው ዓረብ፣ እናታቸው የጅማ ሰው መሆናቸውን ነገሩን። ሸህ የተባለውን ማዕረግ መቼ እንዳገኙት ብንጠይቃቸው ገና በልጅነቴ ስወለድ ነው አሉን።
ሸሁ እንደሚሉትና የሰፈሩ ሰውም አሜን ብሎ እንደተቀበለው የተወለዱት በ 617 ዓ.ም ነው። “በ 1 ሺ 340 ዓመት ዕድሜዬ ኢትዮጵያን የገዟትን ነገሥታትና መሳፍንት አውቃለሁ” አሉን። ስለግራኝ መሐመድስ ያውቃሉ አልናቸው። “አዎን አውቀዋለሁ ፤ ብዙ ጊዜ እንገናኝ ነበር። ቀይ ግምጃ የመሰለ ሰው ነው፤ ፈረሱ የሚበላው የወይራ ግንድ ነበር። አንዴ ጃንጀሮ ከሚባል ሀገር መጣና ገረዱን ትቶ ወደ ከፋ ሄደ። ከጥቁር ወንዝ አጠገብ ቆመና የጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን አየ፤ ከዚያ ከፋ ምን ይከፋ አለና ተመለሰ” አሉን።
አፄ ቴዎድሮስንስ ያውቋቸዋል አልናቸው። “ቴዎድሮስ አንዴ ወደ እኛ መጣና በከፋና በጅማ መሐል አለፈ” አሉን።
የተወለዱ ጊዜ ገንዘብ ነበር ስንላቸው “በጨው እንገበያይ ነበር። እኔ ግን ስወለድ ጀምሮ ጫት እየበላሁ ነው ያደግሁት” አሉን። በእድሜዎ ስንት ሚስት አግብተዋል ብንላቸው “ሁለት ብቻ” አሉ። ሚስቶችዎም እንደርስዎ ባለዕድሜ ነበሩ አልናቸው። አይደሉም አሉን። ሁለት ልጆች ወልደው እንደነበርና ሁለቱም በምኒልክ ጊዜ መሞታቸውን ነገሩን።
ሸሁ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሁሉ የሰጡን መልሶች ትክክል አይደሉም። የሰፈሩ ሰው ግን ሸሁ በእርግጥ 1 ሺ 340 ዓመት ዕድሜ አላቸው ብሎ ያምናል።
(አዲስ ዘመን መጋቢት 23 ቀን 1957 ዓ.ም)
እህልና አፈር ደባልቀው የሸጡት ተፈረደባቸው
እህሉን ከአፈር ቀላቅሎ የሸጠው ታደሰ ፀጋዬ በተከሰሰበት ወንጀል በ3 ወር እስራት እንዲቀጣ የሞረት ወረዳ ፍ/ቤት ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት ፈረደ፡፡
ተከሳሹ በሞረት ወረዳ ግዛት ሰኔ 17 ቀን 1964 ዓ.ም በአንጭቆረን በዋለው የቅዳሜ ገበያ ከግማሽ በላይ አፈር የሆነ 50 ኪሎ ክብደት ያለው ምስር ነው በማለት አቶ መንግሥቴ ለተባሉት ሰው በ10 ብር ከሸጠ በኋላ፤ ወደ ሌላ ጆንያ እስኪገለብጥ ድረስ ከሥፍራው ጠፍቶ ነበር፡፡
ከሠላሳ ኪሎ የሚበልጥ አፈር የተቀየጠበትን ምስር የገዙት አቶ መንግሥቴ ባቀረቡት አቤቱታ፤ ተከሳሹ ተፈልጎ ወዲያውኑ ተያዘ፡፡ በዚህም አፈጻጸም፤ ሞረት ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሶ ቀርቦ በሰጠው የእምነት ቃል ድርጊቱን ከማመኑም በላይ በማስረጃ ስለተረጋገጠበት፤ ፍ/ቤቱ በ3 ወር እስራት እንዲቀጣ የፈረደበት መሆኑን ሕግ አስከባሪው የአሥር አለቃ ለገሠ አርጋው ገልጠዋል፡፡
(አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 1964ዓ.ም)
አንድ ጥያቄ አለኝ
-ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
*የሞት መድኃኒት ምንድነው?
የሻምበል ባሻ ሽፈራው ምስክር
-መቀበር ነው፡፡ ከተቀበሩ ወዲያ ሞት መግደል አይችልም፡፡
*ሰኔ 13 ቀን በወጣው ዓምድዎ ስለሰው ሞት ዜና በራዲዮ ሲነገር የሚያስከፍሉት ሰባ ብር ነው ያሉት ሰባ አምስት ብር መሆኑን እንደገና ይግለጡልን፡፡
ከኢትዮጵያ ራዲዮ ትራፊክ
-ከምኔው አደገ? ግሩም አስተዳደግ ነውና ይኸንኑ እወቁላቸው፡፡
*አንዳንድ ወንዶች ለጊዜው ጥሩ ለመምሰል ቅልስልስ ይሉና ጥቂት ቆይተው ይለወጣሉ፡፡ ለምን እንዲህ ይሆናሉ?
አዜብ ብርሃኔ
-ድመት ጭራዋን የምታወዛውዘው የምትፈል ገውን ጣፊያ እስኪጥሉላት ድረስ ነው፡፡ አንዳንዱም ወንድ እንዲያ የሚሆነው የሚፈልገውን እስቲያገኝ ድረስ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ጣፊያውን እንዳገኘች ድመት ጠባዩን ይለውጣል፡፡
*ዶሮ በአንድ እግሯ የምትቆመው ስትፀልይ ነው የሚሉት እውነት ነው?
ስንታየሁ ማንደፍሮ
-መታረድና ሞት እንደሆን አይቀርላት ለምኑ ነው የምትፀልየው? ጽድቅና ኩነኔ ስለሌለባት መፀለይዋ አይደለም፡፡
(አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 1964ዓ.ም)
*ውሻ ሁል ጊዜ በፊት ለፊት በር የማይጮኸው ለምንድነው?
ዐቢይ ወንድሙ ተፈሪ
-ጠላት በጓሮ በር ነው የሚያጠቃው እያለ፡፡
(አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 1957ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2017 ዓ.ም