የአትሌቲክሱን ችግር አውቆ ለመፍትሔ የሚሠራ አመራር ሊመጣ ይገባል-የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር

ኢትዮጵያ ከታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ አንስቶ በስመጥር አትሌቶቿ ብቃት በስፖርቱ ዓለም ለዘመናት ስትከበር የኖረች ሃገር ናት። ለዚህ ደግሞ ጀግኖች አትሌቶች ሊመሰገኑ ይገባል። የሚሊዮኖችን አደራ ተሸክመው በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚሮጡ ብርቅዬ አትሌቶች ከሌሉ ስፖርቱ የለም። ስለዚህ ለእነሱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና በየትኛውም ሁኔታ ቅድሚያ መስጠት ስፖርቱን የሚመራው ፌዴሬሽን ኃላፊነት ነው።

ይሁን እንጂ እንደየጊዜው ዘመናዊና ምቹ ሁኔታን ለአትሌቶች ከመፍጠር ይልቅ ዕንቁ አትሌቶችን የሚያስከፉና ሀገርም ውጤት እንድታጣ የሚያደርጉ አስተዳደራዊ ችግሮች በየዘመኑ ፌዴሬሽን ውስጥ ጠፍቶ አያውቅም። እንዲህ አይነት አስተዳደራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ከዚህ ቀደም አትሌቲክሱንና አትሌቶችን መረዳት አልቻሉም በሚል ወቀሳ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በስፖርቱ ባለፉ ባለሙያዎች እንዲመራ መደረጉ ይታወቃል። ይሁን እንጂ በአትሌትነት ዘመናቸው የተሳካላቸው አትሌቶችም ከችግር የፀዳ የፌዴሬሽን አመራር ለመሆን ሲቸገሩ በግልጽ ይታያል።

አትሌቶች ዛሬም ድረስ ትክክለኛውን የፌዴሬሽን አመራር እንዳላገኙ ቅሬታ ያቀርባሉ። ከቀናት በኋላ በሚካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 28ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ግን ሁነኛውን የስፖርት መሪ ለማግኘት ተስፋ አድርገዋል።

ጠቅላላ ጉባኤውን ተከትሎ በሚደረገው የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና የፕሬዚዳንት ምርጫ፤ የስፖርቱን ቁልፍ ችግር አንጥሮ በማውጣት ለመፍትሔ የሚሠራ ሰው ወደ አመራርነት ሊመጣ እንደሚገባም የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፅኑ አቋም አለው። የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አትሌት የማነ ፀጋዬ፣ አዲስ የሚሰየመው ሥራ አስፈጻሚ ትኩረት ሊያደርግ ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል አንገብጋቢውና በቅርቡ በተደረገው የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ የታየው የብሔራዊ ቡድን አትሌቶችና አሠልጣኞች የመምረጫ መስፈርት መሆኑን ይናገራል።

አትሌቶችን ለሥነልቦና ጫና እየዳረጋቸው የሚገኘውና ውድድሩ እስከሚካሄድበት ሰዓት ድረስ ማን ሊመረጥ ይችላል የሚለውን አለማወቅ ከባድ ችግር ሲፈጥር ታይቷል። አትሌቶች በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ለውድድር ከሄዱበት አዝነው መመለሳቸውም ይታወሳል። ስለዚህ ይህ ችግር ሊፈታ የሚገባው ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ነው አትሌት የማነ የሚናገረው።

ሌላኛው በየጊዜው እየተባባሰ ያለና መፍትሔም ያላገኘው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ጉዳይ ሲሆን፤ የነበሩትም ከአገልግሎት ውጪ በመሆናቸው አትሌቶች ልምምድ ለመሥራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለማለፍ እየተገደዱ ነው። ለወራት በእድሳት ምክንያት የተዘጋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ለዓመታት ወደ ሥራ ባለመመለሱ አትሌቲክሱን እየፈተነው ይገኛል። በሜዳው ምክንያት መሙ አገልግሎት እንዳይሰጥ መደረጉ ለእግር ኳስ ሲባል አትሌቲክሱን ያሳጣል የሚል ስጋት ያሳደረበት የማነ ‹‹እንደ ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና የአትሌቲክስ ክለቡ መብራት ኃይል ያሉት መም በመገንባት አስተዋፅዖ ለማድረግ እየሞከሩ ቢሆንም መንግሥትስ ምን አደረገ?›› ሲልም ይጠይቃል።

እንደ የማነ ገለፃ፣ የፌዴሬሽን አመራሮች ከመንግሥት ጋር በመሆን ስፖንሰር አፈላልገው ብዙ መሥራት የሚችሉ ቢሆንም አንድም መፍትሔ ሳይዘይዱ የሥራ ዘመናቸውን ማጠናቀቃቸው የእነሱ እንጂ የሌላ አካል ድክመት አይደለም። ይህ ችግር በሀገር ውጤት ላይ የራሱ ተፅዕኖ እያሳረፈ በመሆኑ በስፖርቱ ትልቅ ስም ያላት ኢትዮጵያ ክብሯ ከእጇ እንዳይወጣም ስጋት አለው።

‹‹የእነ አበበ ቢቂላ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ማሞ ወልዴ ሃገር ልምምድ መሥሪያ የላትም መባሉ አሳፋሪ ነው። በኢትዮጵያ የሚሠሩ በርካታ ማናጀሮች እንደመኖራቸው ካምፕ እንዲሁም የማዘውተሪያ ስፍራ እንዲገነቡ ማድረግ ሲገባ እነሱን የሚያሳድድ ሕግ እያወጡ ስፖርቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን ተደርጓል›› የሚለው አትሌት የማነ፣ በመሆኑም መጪው ሥራ አስፈጻሚ ስፖርቱ ላይ የሚሠሩ አካላትን የሚያርቅ አካሄድ ሳይሆን የሚነሱ ቅሬታዎችን በመፍታትና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ አትሌቲክሱን እንዲጠቅሙ መሥራት እንዳለባቸው ተናግራል።

ከምርጫ መስፈርትና ከማዘውተሪያ ስፍራዎች አለመኖር ጋር በተያያዘ አትሌቶች ላይ እየደረሰ ካለው ጫና ባለፈ የብሔራዊ ቡድን መፍረስም ሌላኛው የአትሌቲክሱ ራስ ምታት ነው። በተለይም በሜዳ ተግባራት ችግሩ ጎልቶ የሚታይ በመሆኑ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው መሆኑንም ያብራራል። አመራሩ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ከማስተዳደር ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ የማሳደር አቅምም መፍጠር አለበት ሲልም አሳስቧል። ይኸውም ኢትዮጵያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት ውጤታማ የሆኑበትና አሁን ላይ በመጥፋት ላይ የሚገኙትን የመም ረጅም ርቀት ሩጫዎች ጨምሮ አሉታዊ ሚና የሚጫወቱ ዓለም አቀፍ ውሳኔዎችን የማስቀልበስ ችሎታን ያዳበሩና በተቋሙ እስከማገልገልም ሊደርስ የሚችል ነው።

የመጪዎቹ አራት ዓመታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስን ዕጣ ፋንታ የሚወስነው ቁልፍ በመራጮች እጅ ላይ ነው። ስለዚህም ድምፅ ያላቸው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ድምፃቸውን ስፖርቱን ለመለወጥ ቃል ለገቡት ብቻም ሳይሆን ቃላቸውን በተግባር መለወጥ ለሚችሉ አካላት ሊሰጡ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ በአደራ ጭምር መልዕክቱን አስተላልፏል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You