ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀቶች፣ ከረጅም ርቀቶች እስከ ማራቶን ባሉ ፉክክሮች ዓለምን ያስደመሙ በርካታ ከዋክብት አትሌቶች መፍለቂያ ነች። በዚህም ትልልቅ ማናጀሮች፣ አሰልጣኞች እንዲሁም የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች ዘወትር ትኩረታቸው በነዚህ ከዋክብት አትሌቶች ላይ ነው።
ኢትዮጵያውያን ከዋክብት በዓለም አትሌቲክስ የገዘፈ ስም ቢኖራቸውም በረጅም ዓመታት ስኬታማ ጉዟቸው ታላላቅ የስፖርቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ የሥልጠና ካምፕ አለመገንባታቸው በብዙዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ ነበር። ከሰሞኑ ግን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሆን ለስፖርቱም ተስፋ የሚሰጥ የሥልጠና ካምፕ በኢትዮጵያዊ ባለሙያ ተመስርቶ ወደ ሥራ ለመግባት በመንደርደር ላይ ይገኛል።
የዓለማችን ግዙፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ ዓለም አቀፍ ተወካይ የሆነው ኢትዮጵያዊው ዮናስ አያና፣ ታላቅ ራዕይ ሰንቆ በተነሳው የርሆቦት ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ማኔጅመንት የአትሌት ተወካይና መሥራች ነው። የናይኪ ተወካይ በመሆን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ለዓመታት ከሠሩ ባለሙያዎች መካከል ብቸኛው ኢትዮጵያዊም ሲሆን፤ በርካታ ወጣትና ስኬታማ አትሌቶችንም በሠሩ ማፍራት ችሏል።
ለአብነት ያህልም በፓሪስ ኦሊምፒክ የ800 ሜትር ብር ሜዳሊያ ባለቤቷ አትሌት ጽጌ ድጉማ፣ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ቡዳፔስት ላይ በ1ሺ500 ሜትር ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አትሌት ድርቤ ወልተጂ፣ በተመሳሳይ ቡዳፔስት ላይ በ10ሺ ሜትር ለሀገሯ የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት እጅጋየሁ ታዬ፣ በ2022 የዩጂን ዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው፣ በቅርቡ ተስፈኛ አትሌት በመባል በዓለም አትሌቲክስ የተመረጠችው ሲምቦ ዓለማየሁ እና እህቷ ማርታ ዓለማየሁ እንዲሁም በ2022 የቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና አሸናፊው ሳሙኤል ተፈራ ተጠቃሽ ናቸው።
ዮናስ አያና አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ ማራቶን በማዞር ፈጣን ሰዓት የሚያስመዘግቡ አትሌቶችን የማፍራት እንቅስቃሴ ጀምሯል። የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የምንጊዜም ተፎካካሪ የሆኑት ኬንያዊያን በርቀቱ ትኩረት አድርገው በመሥራት የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ተቆጣጥረው ለመቆየት ችለዋል። አንጋፋው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ እና በቅርቡ በሞት የተለየው ወጣቱ ኬልቪን ኪፕቱም ደግሞ በናይኪ ተጀምሮ የነበረውን ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የማጠናቀቅ ፕሮጀክትን ሊያሳኩ ከጫፍ መድረስ ችለዋል።
በማራቶን በተለይም በኦሊምፒክ መድረክ በሁለቱም ጾታ በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ በመሆን ጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ እና ፋጡማ ሮባ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ አላቸው። ይሁን እንጂ የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ደጋግመው በመስበርና በዓለም አቀፍ መድረኮች አሸናፊ በመሆን ኬንያውያን አትሌቶች ባለፉት በርካታ ዓመታት የበላይነቱን ይዘዋል። ይህ ቁጭት እንደፈጠረበት የአትሌት ተወካዩ ዮናስ ይናገራል።
አቅምና ብቃት ያላቸው አትሌቶች በኢትዮጵያ በመኖራቸው ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የማጠናቀቅ ፕሮጀክትን ከግብ ለማድረስ እንደሚቻል በማመን ዮናስ ትልቅ አላማ ሰንቆ ተነስቷል። ይህንን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመውን ፕሮጀክት ለመቀላቀል የሚችሉ አትሌቶችን ለመመልመልም ትናንት ታኅሣሥ 06/2017 ዓ.ም በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ አትሌቶችን ያካተተ የመጀመሪያውን ውድድር ሰንዳፋ ላይ አካሂዷል። በቀጣይ ደግሞ የተሻለ የአትሌቲክስ ተሰጥኦ እንዳለ በሚታመንባቸው የትግራይ ክልል፣ የደብረብርሃን እና አሰላ አካባቢዎች ላይ ውድድሮችን በማድረግ 10 የወንድና 10 የሴት አትሌቶችን ወደ ካምፕ በማስገባት ዝግጅቱ የሚጀመር ይሆናል። በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሀገራቸውን የሚያስጠሩ እንዲሁም የፕሮጀክቱን ዓላማ የሚያሳኩ አትሌቶችን ለመፍጠር ይሠራል።
ፕሮጀክቱ ሥራውን ለማከናወንም አትሌቶች የሚከትሙበት ካምፕ ያዘጋጀ ሲሆን፤ ለሁለቱም ጾታ ምቹ የሆነ ማረፊያ፣ አመጋገብ እንዲሁም በሥርዓት የሚመራ ሥልጠና ለማድረግም ዝግጅቱን አጠናቋል። ልምድ ያላቸው የማራቶን አሠልጣኞችን ጨምሮ የተለያዩ ባለሙያዎችም ተሟልተው በተደራጀና ውጤታማ ሊያደርግ በሚችል መልኩ ፕሮጀክቱ የሚቀጥልም ይሆናል። በዚህ ሂደትም ግዙፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ናይኪ እንዲሁም የውድድር አዘጋጅ የሆነው ጎላዞ በአጋርነት ይሳተፋሉ። የማራቶን አትሌቶች ምልመላው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የመም አትሌቶች በመስፈርቱ መሠረት ዕድሜና ተሰጥኦን መሠረት ባደረገ መልኩ ተመልምለው ፕሮጀክቱን የሚቀላቀሉ ይሆናል። በኢትዮጵያ በርካታ ማናጀሮች ከአትሌቶች ጋር የሚሠሩ ቢሆንም ካምፕ በመክፈት ረገድ ግን ይህ በስፖርቱ ታሪክ ቀዳሚው ይሆናል።
ኢትዮጵያ ለስፖርቱ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት እንዲሁም መልከዓ ምድር ያላት መሆኑ ለመሰል ዓላማ ምቹ እንደሚሆን ታምኖበታል። ነገር ግን ከማዘውተሪያ ስፍራ አንጻር(የመም እና የጎዳና) ከፍተኛ ችግር መኖሩ ሥልጠናው ላይ ፈተና ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ። በመሆኑም ሀገርን እያስጠራ ለሚገኘው ስፖርት መንግሥት እገዛ ቢያደርግ መሰል ተቋማትም ሊበረታቱ እንደሚችሉም ነው የአትሌት ተወካዩ ዮናስ የተናገረው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም