ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአድዋ ጦርነት በመቀጠል የኢትዮጵያዊያን አንድነትና ትብብር የታየበት ዳግማዊ አድዋ ሲሉ ብዙዎች ይገልጹታል። በአድዋ ጦርነት ወቅት አባቶቻችን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ብለው አንድነታቸውን አጠናክረው የውጭ ወራሪን በመመከት ጊዜ የማይሽረው ታሪክ ሰርተው ዛሬን አስረክበውናል። የእኛ ትውልድ ደግሞ ያንን ወርቃማ የአንድነት መንፈስ በመላበስ ታሪኩን በልማት ለመድገም በአንድ ልብ ነበር የተነሱት። የሁለቱም ትውልዶች ግብሩ ይለያይ እንጂ ውጤቱ ኢትዮጵያን ታላቅነት ማረጋገጥ ነው። ልዩነቱ አባቶቻችን ደም ማፍሰስ አጥንት መከስከስ ሲጠበቅባቸው፤ ይሄ ትውልድ ደግሞ ላቡን ማንጠፍጠፍ ነው የሚጠበቅበት። የህዳሴ ግድብ በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሁሉንም ህዝቦች ቀልብ መግዛት የቻለ፣ ሁሉን በአንድ ያሰባሰበና ያስተባበረ ፕሮጀክት ነው።
ለግድቡ ግንባታ ከጫፍ እስከ ጫፍ የዘለቀ ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ ተፈጥሯል። ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የነበረው የአንድነት መንፈስ ከትናንቱ ዛሬ ጠንክሮ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የሚደረገው ግስጋሴ እንደቀጠለ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ተጓቶ የነበረው ቢሆንም፤ ከባለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በሚደንቅ ሁኔታ እየተጓዘ ይገኛል።
በተለይ ደግሞ ከፍትህም ከርትዕም ያልተዛመደው የግብጽ እና ሱዳን ጩኸት የግድቡን ግንባታ ለማሰናከል ለሚደረጉ ጥረቶች እጅ ሳይሰጥ ትናንት ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ማከናወን ተችሏል። በቅርቡም ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል የማመንጨት የሙከራ ፍተሻ የሚጀምሩ መሆኑን ሰምተናል። ይሄንኑ ተከትሎ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በተለያየ መልኩ የተሰማቸውን ስሜት እየገለጹ የሚገኙ ሲሆን፤ የታላቁ ህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ የፈጠረባቸው የደስታ ስሜት ካጋሩን መካከል ወጣት አለማየሁ መስፍን ይገኝበታል።
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ቱርፋት እንደሆነ የሚያመላክተው ወጣት አለማየሁ፤ ‹‹እኔን ጨምሮ›› ይህ ትውልድ እድለኛ ነው እንዲህ ያለ ዘመን ተሻጋሪ ሃብት ተገንብቶ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተንደረደረ መሆኑ ልዩ ስሜት የፈጠረበት ስለመሆኑ ይገልጻል። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ትልቅ ነው፤ ‹‹ከዚህ ባሻገር ሌሎች ጎላ ጎላ የሚሉትን ፋይዳዎችን እንዳሉት አምናለሁ›› የሚለው ወጣት አለማየሁ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ከአስር ዓመት በፊት የመሰረት ድንጋይ ሲጣል ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል አገራዊ መግባባትን የፈጠረ መሆኑን ያስታውሳል። በመንግስት ቁርጠኝነት የመጀመሪያው ዙር ውሃ ሙሌት ሲደረግም በተለየ መልኩ የአንድነት ስሜቱን ከፍ ብሎ የታየ ነበር። በሀገር ውስጥ ሆነ ከሀገር ውጪ ያሉብንን ጫናዎች በመቋቋም እና በድል በመወጣት ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት ተጠናቆ ብስራቱን ለመስማት መቻሉን ያመላከታል።
‹‹ይሕ ትልቅ ድል ነው። ምክንያቱም በአሁን ወቅት ሀገራችን ትልቅ ተጽእኖ ውስጥ፣ ጫና ውስጥ የምትገኝ ናት›› በማለት የሚናገረው ወጣት አለማየሁ፤ “ከሀገር ውስጥ በትግራይ ክልል የሚገኘውን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት የሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል፤ ከውጪ የግብጽና የሱዳንን የውሸት ፕሮፖጋንዳ አምኖ በመቀበል የሚደረጉ ጫናዎች ይጠቀሳሉ። በተለይ ደግሞ የውጪዎቹ ተጽእኖዎች እጅ ለመጠምዘዝ የሚደረጉ ሙከራዎች፣ ሉአላዊነትን ለመድፈር የሚደረጉ ሩጫዎች፣ በስውር የሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች እጅግ ፈታኝ ነበሩ። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ መሰናክሎች በማለፍ የመጣውን እንቅፋት ሁሉ እጅ ሳይሰጥ ሁለተኛውን ዙር ሙሌት ማከናወን ከመቻል በላይ ለእኔ ስኬትም፣ ድልም የለም።”
ወጣት አለማየሁ በዚህ ደረጃ ደግሞ አሸናፊ መሆን የተቻለው እንዲያው ዝም ተብሎ አለመሆኑን ይናገራል። የመጀመሪያውና ዋነኛው መንግስት በአደባባይ ሆነ ከመጋረጃ ጀርባ የሚደርሱበትን ጫናዎች፣ የማንበርከኪያ ጡጫዎችን ህመሙን በመቻል ለሀገርና ለህዝብ በታማኝነት የቤት ሥራዎቹን ማከናወን በመቻሉ እንደሆነ ይጠቅሳል።
ሌላው ህዝቡ በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ውስጥ ባሉ ባንዳዎች እና በውጪ ሀይሎች በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጠሩ አጀንዳዎች፣ ህዝብ ከህዝብ፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት የሚደገሱ አፍራሽ ድግሶችን በተደጋጋሚ ማለፍ በመቻሉ ነው። በውጪ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም የእነዚህን የእፍኝት ልጆችን ሴራ ቀድሞ በመረዳት በአብሮነት መቆም በመቻላቸው እንዲሁም፤ የተለያየ የፖለቲካ አቋም እያራመዱ ነገር ግን ሀገርን በማስቀጠሉ ረገድ ብሎም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከፓርቲ በላይ እንደሆነ በመገንዘብ በአንድነት መቆም የመቻላቸው ድምር ውጤት መሆኑን ያብራራል።
“ስለዚህ ሁለተኛውን ዙር ሙሌት እንዲህ በሆነ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ማከናወን ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ከልማቱ እፍታ ተቋዳሽ የማንሆንበት ምንም አይነት ምክንያትም አይኖርም። ከጀመርነው ግስጋሴ ሊያቆመንም የሚችል አንዳችም ኃይል አይኖርም። ይሄንኑ ደግሞ በመጀመሪያው ዙር አሁን ደግሞ በሁለተኛው ዙር አረጋግጠናል” ሲል ተናግሯል።
በሃምሌ 1967 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆነው ስንታየሁ ግርማ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በመጠናቀቁ የፈጠረበትን ደስታ ለመግለጽ ቃላቶች ጉልበት የሚያጡበት መሆኑን ይናገራል። በዚህ ደረጃ ስሜቱ ጥልቅ ምክንያት የአባይ ወንዝ ፈጣሪ ለኢትዮጵያዊያን የሰጠው ድንቅና ውድ ስጦታ ቢሆንም አገሪቱ መጠቀም አለመቻሏን ተከትሎ ሁል ጊዜው ቁጭት የሚፈጥርበት መሆኑ ነው። “የአባይ ወንዝ ለሀገሩ ባዳ ሆኖ ለዘመናት ሲፈስ፣ የእናት ምድሩን ለም አፈር ጠራርጎ እየወሰደ ለሌሎች ሀገራት የልማት፣ የእድገት፣ የብርሃን መሰረት በመሆን ሺህ ዓመታት አስቆጥሯል።
‹‹የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው›› ከሚል የቁጭት ምሳሌያዊ አነጋገር ውጪ የአገሩን ህዝቦች በጥም የተቃጠለውን ጉሮሮ አላረሰረሰም። ስለዚህ በታላቁ ወንዛችን ከትውልድ ትውልድ የነበረውን ይሕን መሰል ቁጭት በተለያዩ ዘመናት ለመወጣት ቢታሰብም አልተቻለም ነበር። ይሕ መሆኑ እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ ቁጭት ሲፈጥርበት ኖሯል። ነገር ግን በ2003 ዓ.ም ግን ያውም በዚህ ትውልድ አባይን ከመዝለፍ፣ ከመተቸት እንዲሁም በእርሱ ከመቆጨት የምንላቀቅበትን ጡብ ማስቀመጥ ተችሏል። አባይን ለመገደብ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ተከትሎ ከዳር እስከ ዳር መላው ኢትዮጵያዊያንን በታላቅ ሀገራዊ ስሜት የመልማት፣ የማደግና የመበልጸግ መንፈስ ያንቀሳቀሰበት ስሜት ዛሬም እንደ አዲስ ከውስጤ የሚጠፋ አይደለም” ይላል መምህር ስንታየው ።
‹‹በጊዜው በዚህ መንፈስ ያውም በራስ አቅም የማይሞከር የሚመስለውን ለመሞከር ስንነሳ የውጪ ሃይሉ በጥርጣሬ መንፈስ የተመለከቱን መሆኑን›› ያስታወሰው ስንታየሁ፤ በአምስት ዓመት ለማጠናቀቅ ታስቦ ስራ ሲጀመር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በልቡ ተስፋ አርግዞ ነበር፡፡ አንድ አባት እንዳሉት ለዚህ ግድብ ድጋፍ ያላደረጉት ኢትዮጵያዊያን “በማህጸን ያሉ ህጻናት እና በመቃብር ያሉ ሙታኖች ብቻ ናቸው” ያስታውሳል፡፡
በጊዜው የነበረው መንግስት የሁሉን ድጋፍ ያተረፈን ይሕን ፕሮጀክት በተጀመረበት መንፈስ፣ ለማጠናቀቅ በተቀመጠለት ጊዜ ጨርሶ ወደ አገልግሎት ማሻገር ላይ የታየው ዳተኝነት የተረገዘውን ተስፋ እንዲጨናገፍ ያደረገ እንደነበር ያብራራል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ፤ እርሳቸው የግንባታውን ሂደት በማስመልከት ለህዝብ የገለጡት እውነት ዳግም ወደ ተስፋ እንዲመለስ አድርጎታል። ከግንባታው ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ቴክኒካል ችግሮችንእንዲስተካከሉ ከማድረግ በሌብነት የድሆች መቀነት በመፍታት የሚደረጉ ቡድናዊ ስርቆቶችን በማጥራት ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲጓዝ በመደረጉ እንደሆነ ሁሉም የሚዘነጋው አይሆንም። በመንግስት በኩል በተለየ ሁኔታ የታየው ቁርጠኝነት ደግሞ ዛሬ የግድቡ ሁለተኛው ዙር ሙሌት በማጠናቀቅ ወደ ሌላ ምዕራፍ መሸጋገር እንዲቻል ያደረገ መሆኑን ይጠቅሳል።
ዶክተር ዐብይ እና መንግስታቸው በህዳሴው ግድብ እንዲህ አይነቱን ቆራጥ አቋም መውሰድ ባይችሉ ኖሮ የአንደኛው ዙር ሙሌት ሆነ የሁለተኛው ዙር ማከናወን የማይታሰብ መሆኑን አስረግጦ ይናገራል። መንግስት ሀገርን አስቀድሞ ማሻሻያዎቹን በማድረግ ግንባታውን ባይጀምር ኖሮ የአለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ጫናዎች በዚህ ደረጃ ባልበረቱ ነበር ሲልም ይሞግታል።
ቀደም ሲል ወንበር ላይ የነበሩት አካላት የሀገርን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ ባንዳዎች በመሆናቸው ጀምሮ እንጂ ገንብቶ በማጠናቀቅ ሀገርን እንደማያሳድጉ አብጠርጥረው ያወቋቸዋል። እንደ ‹‹ትሮይ ፈረስ›› እየጋለቡ ቤተመንግስት ያስገቧቸው እነርሱ እንደሆኑ ታሪክ ይመሰክራል። አሁን ያለው መንግስት ግን በሀገር ሉአላዊነት የማይደራደር እና የኢትዮጵያ ልጅ እንደሆነ ከመገንዘባቸው እንደሚመነጭ ይናገራል። ይሄንኑም በተለያዩ ተግባራት አይተው የተረዱ በመሆኑ፤ እነዚህ ኃይሎች መንግስትን ለማዳከም ዲፕሎማሲያዊ ጫናውም ሆነ በሰብዓዊ መብት ስም ማዕቀብ ለመጣል እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ ይናገራል። ስለዚህ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለጊዜያዊው ጫና እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሸብረክ ሳይል እስከ ፍጻሜው እጅ ለእጅ ተያይዞ መጓዝ ያስፈልጋል። ጊዜውም ይሄንኑ ይጠይቃል፤ ያስገድዳል ሲል ሀሳቡን ይቋጫል።
“ታላቁ የህዳሴ ግድባችን እንደ አድዋ የነጻነታችን ምልክት ነው” ሲል አስተያየቱን የሚጀምረው ደግሞ አብነት ሞሲሳ ነው። የውጪ ሀገራት ጫና የበረታው የኢኮኖሚ የበላይነቱን ስለያዙ እንደሆነ የሚያመላክተው ወጣት አብነት፤ መንግስት የሁለተኛውን ዙር ሙሌት እንዳያደርግ የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉበት እንደነበረ ሁሉም የሚያውቀው መሆኑን ይገልጻል።
በዚህ ደረጃ ደግሞ ጫናዎቹ የበረቱት የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ አይቀሬነቱን በማመን ብሎም፤ ኢትዮጵያ ሁልግዜ የእነርሱ እጅ ጠባቂ ሆና ድህነቷ በመጠቀም እንደፈለጉ ለማድረግ ከማሰብ እንደሆነ ይናገራል።
በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እውነታውን በመገንዘብ እና በመንቃት ታላቁ የህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ተግባር ላይ ከእስከዛሬው በተለየ ሁኔታ መሳተፍ ይኖርበታል። ቦንድ ከመግዛት ጀምሮ በሙያው፣ በጉልበቱ፣ በእውቀቱ ….. ተሳትፎ በማድረግ የዜግነት ግዴታውን በመወጣት የነጻነት ተምሳሌታችንን ታላቁን የህዳሴ ግድብ እጅ ለእጅ ተያይዘን ማጠናቀቅ ይኖርብናል፤” ሲል ወጣት አብነት ጥሪውን ያቀርባል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013