የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመረችበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ አገራት በዋናነት ከሱዳን እና ግብፅ ጋር ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ አቋም በመያዝ መፍትሄ ለማምጣት ስትደራደር ቆይታለች፡፡ ነገር ግን ግብፅ ፕሮጀክቱን በጥሩ ህሊና ከመቀበል እና ለጋራ ልማት እንደ እድል ከመቁጠር ይልቅ እጅግ ጠብ አጫሪ በመሆን በሁሉም መንገድ የፕሮጀክቱን ሂደት ለማደናቀፍ ከመጣር አልተቆጠበችም፡፡ ግብፅ ኢትዮጵያውያን ግድቡን እውን እንዳያደርጉ ለማድረግ የተቻላትን ሁሉ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ከነዚህም መካከል ጉዳዩን አለማቀፋዊ ይዘት እንዲኖረውና በውይይትና በድርድር ሰበብ የሌሎች ሀገራትን ጣልቃ ገብነት በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚደረግ ሙከራ አንዱ ነበር፡፡ በዚህም በርካታ ውይይቶችና ድርድሮች ተካሂደው በግብፅ በኩል በነበረው ግትርነት መፍትሄ ሳይገኝለት እስካሁን ዘልቋል፡፡
ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ የፕሮጀክቱ እቅድ ሲጀመር አንስቶ ድርድሩና ውይይቱ በሂደት የደረሰበትን ሁኔታ አስመልክቶ በአንድ ወቅት ለኪነጥበብ ባለሙያዎች ማብራሪያ በሰጡበት መድረክ ተገኝቼ ሙሉ ገለፃውን በአንክሮ ለመከታተል ችዬ ነበር፡፡ በድርድሩ ሂደት የተስተዋሉ እሳቤዎችን ለምሳሌ ግብፅ እኔ ብቻ ልጠቀም ባይነቷን፣ የሱዳንን የተምታታና ወላዋይ አቋም እንዲሁም የኢትዮጵያን የማይናወጥ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ አንድ ባንድ ያስረዱበት ወቅት ስለነበር እንደሚከተለው ላቀርበው ወደድሁ፡፡
የአባይ ወንዝ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የተከበረ፣ የተዘመረለትና ቀን ተሌሊት ያለማቋረጥ ሲጓዝ የኖረ የታላቁ ናይል ተፋሰስ አካል ነው፡፡ የታችኛው የናይል ተፋሰስ የሆኑት ግብፆችም በወንዙ ላይ የአስዋን ግድብ ገንብተው ለበርካታ ዘመናት ሲጠቀሙበት የኖሩ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን የበይ ተመልካች ሆና በራሷ የውሃ ሃብት መጠቀም ሳትችል ሁለተኛውን ሚሊኒዬም ተሻግራለች፡፡ የአባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ዝናባማ ተራሮች ተነስቶ፣ ወደ ሱዳን እና ወደ በረሃማዋ ሀገር ግብፅ የሚገባ በመሆኑ የሁሉም ሀብት እንደሆነ ኢትዮጵያም የምታምንበት ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጰያ በተደራደረችባቸው መድረኮች ሁሉ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ማተኮሯ ከባለቤትነት በዘለለ ሳይንሱም ተፈጥሮም የሚያሳየው ጉዳይ ነው፡፡
የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እሳቤም የተነሳው ከወንዙ መነሻና ምንጩ ባሻገር እስከመድረሻው ያለውን ሁኔታ በዝርዝር ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ አባይ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች በኩር ስለሆነ ከጎኑ ተከዜን፣ ባሮ አኮቦን፣ ሌሎች ገባር ወንዞችን ይዞ ነው ወደ ናይል የሚገባው፡፡ ናይል ሲገባም ጠቅላላ የወንዙን ፍሰት 86 በመቶ ይሸፍናል፡፡
በርግጥ ከ10 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በአባይ ወንዝ ላይ የጀመሩት “ፋይናንሱም እኛው፣ መሃንዲሱም እኛው” በሚል መንፈስ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሃብታም ድሃ ሳይል፣ ሽማግሌውም ወጣቱም ልዩነት ሳይፈጥር ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ገንዘብ በማዋጣት፣ አልያም በጉልበቱ ተሳትፎ በማድረግ አጠናቆ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎትን እውን ለማድረግ ነው፡፡
ነገር ግን በወቅቱ ግብፆች ድርቅ ሊመጣብን ነው በማለት ጩኸት አሰምተዋል፣ አማላጅም ልከዋል፣ ወደ ክስም ሄደዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሁን እስከደረሰበት ደረጃ ድረስ ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ህዝብና መንግስታት ትኩረት መሳብ የቻለ፣ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙ በላይኛውና በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት መካከል የፖለቲካ ውጥረት የፈጠረና ለሰላምና መረጋጋት አሳሳቢ ጉዳይ የነበረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ጉዳዩ የተቆረጠ ሃሳብ ስለሆነ ይህን ፕሮጀክት እውን ከማድረግ የሚያግድ አንዳችም ምክንያት አልነበረም፡፡
ኢትዮጵያ መሰረታዊ ፍላጎቷን የምታረጋግጥበትን ይህንን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከጥንስሱ ጀምሮ የምትቃወመው ግብፅ የግድቡ ግንባታ እንዳይጠናቀቅ ለማድረግ የተለያዩ የማሰናከያ መንገዶችን ስትጠቀምቆይታለች፡፡ የተለያዩ ሃያላን መንግስታትን፣ አለም አቀፍ ድርጅቶችን፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ድርጅቶችን መከታ በማድረግም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ጥራለች፡፡
የኢትዮጵያም አቋም መሰረታዊ ፍላጎትን ከማሟላት በዘለለ የሌሎች አገራትን ጣልቃ ገብነት በአሉታዊ ሳትመለከት የላይኛውና የታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍን ዲፕሎማሲ ለመከተል ስትል ከሶስቱም ሃገራት የተውጣጡ ባለሙያዎችና ገለልተኛ አካሎች በፕሮጀክቱ ጎጂነት ወይም ጠቀሜታ ዙሪያ ጥናት እንዲያደርጉበት ባስቀመጠችው ሃሳብ መሰረት ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳንና ከግብፅ ከእያንዳንዳቸው ሁለት ባለሙያ፣ እንዲሁም ከአለም ባንክ፣ ከዩናይትድ ኪንግደም እና ከሌሎች ሀገሮች የተውጣጡ አራት ባለሙያዎች፣ በድምሩ አስር ባለሙያዎችን ያካተተ አለም አቀፍ የባለሙያዎች መድረክ (International Panel of Experts) ተመስርቶ ወደ ጥናት ከተገባ በኋላ የተገኘው ውጤት ግድቡ ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ምንም ጉዳት እንደማይኖረው አረጋገጡ፡፡ ይህንን ግን ግብፅና ሱዳን ሊቀበሉት አልቻሉም፡፡
በግብፅ በኩል የቀረበው ሃሳብ ግድቡ አደገኛ ስለሆነ ይቁምልን ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በጥናት የተረጋገጠው አደጋ እንደማያመጣ ስለሆነ ግንባታው ሊቆም አይችልም የሚል አቋም ተያዘ፡፡ በሱዳን በኩል ደግሞ የጥናቱን ውጤት ለመቀበል ጊዜም እንዳልወሰደባቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ከዓመት በኋላ ሌላ የሶስትዮሽ ድርድር ሲካሄድ ግብፅ ይዛ የቀረበችው አዲስ የመደራደሪያ ሃሳብ ለዘመናት ስትጠቀምበት በነበረው የውሃ መጠን ስሌት እንደሆነ አቀረበች፡፡
ግብፅና ሱዳን ቀደም ሲል በቅኝ ግዛት ዘመን ተፈራርመውት የነበረው ሁለቱ ሀገራት ብቻ ሙሉ በሙሉ የወንዙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ሌሎች ሀገራት ግን የእግዜር ውሃ አላቸው በሚል ከጥቅሙ ያገለለ ስምምነት ነበር፡፡ ይህ ስምምነት እውን እንዲሆንም ፍላጎት አላቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ኢትዮጵያን የሚመለከት ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ልትቀበለው አትችልም፡፡ በመሆኑም በእነዚህና ሌሎች ጉዳዮች የተነሳ የጥናቱ ጉዳይ እስካሁን ድረስ ተስተጓጉሎ ይገኛል፡፡ ግድቡ ግን በቀን ለ24 ሰዓታት፣ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተሰራ በመሆኑ የግብፆች ጩኸት እስካሁን አላባራም፡፡
ከዚህ በፊት ግድቡ መሰራት የለበትም በማለት ሲከራከሩ ቆይተው፣ የግድቡ ግንባታ እየገፋ ሄዶ ውሃ መያዝ የሚችልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ደግሞ ሙሌቱ መዘግየት አለበት በሚል አዲስ መከራከሪያ ወደማቅረብ ተሸጋገሩ፡፡ በዚህም ጉዳይ የማይናወጠው የኢትዮጵያ አቋም ግድቡን መሙላት በመሆኑ፣ የመጀመሪያውን ሙሌት በስኬት አከናወነች፤ ሁለተኛውንም ደገመች፡፡
ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ደግሞ የግብጽ ጩኸት ሱዳንንም በማከል በአዲስ መልኩ ቀጠለ፡፡ ጉዳዩን አንድም ለአረብ ሊግ ከዚያም ለፀጥታው ምክር ቤት እስከማቅረብ ደረሱ፡፡ ኢትዮጵያም አቋሟን ምንጊዜም ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ለአፍታም ሳታፈገፍግ ሁለተኛውን ሙሌት በስኬት አከናወነች፡፡
ግብፅ ግን አሁንም ኢትዮጵያን ከተፋሰሱ በረከት ተቋዳሽ እንዳትሆን ጥረት ከማድረግ አልቦዘነችም፡፡ በዚህም ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ተደራዳሪዎችና የጥበብ ሰዎች ቀልባቸውን ከህዳሴው ግድብ ላይ ሳይነቅሉ ለእያንዳንዱ ለሚሰነዘረው የውሸት ጩኸት እና ክስ ምላሽ በመስጠት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
ይህን የመሰለው የግብፅ አቋም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያወላውል በመሆኑ ለተከራካሪም፣ ለተሟጋችም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለአብነትም ባለፈው ዓመት ከተስተጓጎለው ድርድር በኋላ ግብፅ ኢትዮጵያን በድርድር መርታት ስለማይቻል ሶስተኛ ወገን ያሸማግለን በሚል ሃሳብ ወደ አሜሪካ መንግስት አመራች፡፡ የአሜሪካም መንግስት እኔ ታዛቢ በሆንኩበት ተደራደሩና ጉዳያችሁ ይሳካላችኋል የሚል ሃሳብ ለኢትዮጵያ አቀረበች፡፡ ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በጥሩ ዲፕሎማሲ አብራ ስትሰራከነበረው በዓለም ትልቁ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር – ከአሜሪካ የመጣን ጥሪ፣ መነሻው ከግብፅ ቢሆንም – ለመቀበል ሳትግደረደር የልማት ሃሳቧን አቀረበች፡፡
በዚህ ድርድር ግን ኢትዮጵያን የገጠማት ከሽምግልና ይልቅ ወደ አንድ ወገን ያደላ፣ አስገዳጅነት ባህሪ ያለው በመሆኑ ግብፅ ይዛ የመጣችው ሃሳብ ለሽምግልና ሳይሆን በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለማስጣል አይነት መሆኑን ኢትዮጵያውያን ተደራዳሪዎች በመረዳታቸው ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ ጠንካራ አቋም ያዙ፡፡
በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ማካሄድ መጀመሯን በይፋ ለተፋሰሱ ሃገራ በመግለጿ ጩኸቱ እንደአዲስ አገረሸ፡፡ የፀጥታው ምክር ቤትም ያለስልጣኑ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እንዲመክር ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ግብፆችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ተላለፈ፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለፀጥታው ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ የምክር ቤቱ ኃላፊነት ጸጥታን በሚያደፈርሱ ጉዳዮች ላይ መምከር እንጂ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብን በሚመለከት መወያየት ባለመሆኑ ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም የግብጽና ሱዳን ፍላጎትም በቅኝ ግዛት ውል ሰበብ ውሃውን ለብቻቸው የመጠቀም ፍላጎት ነው፤ አንዱ እየጠጣ ሌላው የሚጠማበት አካሄድ አግባብ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል። በመጨረሻም የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራት የህዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ይቀጥል የሚል ድጋፍ ማሳየታቸውም ታውቋል፡፡
በርግጥም ጉዳዩ እልባት ማግኘት የሚችለው ሦስቱ ሀገራት በአፍሪካ ኅብረት ታዛቢነት በሚካሄድ ውይይት እንጂ በሌሎች ማናቸውም ሀይሎች ጣልቃ ገብነት ሊሳካ እንደማይችል የታመነበት ጉዳይ ነው፡፡ ግብፅና ሱዳንም ጉርብትናን፣ አብሮ መልማትን ሊማሩ ይገባል፡፡
ዘላለም ግርማ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013