ኢትዮጵያውያን የአንድነትና ማንነት መገለጫ አድርገው የሚያዩት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከቱሩፋቱ ተቋዳሽ ለመሆን ሁሉም በጉጉት የሚጠብቀውና እንደአይኑ ብሌንም የሚያየው መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዜጎች ሀብት ግንባታው ተጀምሮ ዛሬ ላይ ደርሶ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መከናወኑ ለመላው ኢትዮጵያውያን ከድልም በላይ የሆነ ስኬት ነው፡፡ከዚህ በኋላም በውጭ ኃይሎች በተለይም በግብጽ የአደናቃፊነት ጉዞ እና ሌሎችም ጎታች ሁኔታዎችና ትርክቶች ቦታ አይኖራቸውም፡፡
መላው ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን በሚያጣጥሙበት በዚህ ወቅት ስለግድቡ ማውሳታችን ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ተደራሽነቱን ከማስፋት በተጨማሪ፤ በቱሪዝም ኢንደስትሪው ላይ ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለው በርካቶች የሚናገሩለትን ጉዳይ ለማንሳት ነው፡፡ የቱሪዝም ኢንደስትሪውን ተከትሎ የሚፈጠረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ በማደረግ ሀገሪቱን ወደ አንድ የእድገት ደረጃ በማሸጋገር የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡
በቱሪዝም ኢንደስትሪ ላይ የተሰማሩ አካላት እና የታሪክ ተመራማሪዎች ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የቱሪዝም መዳረሻነት የሚናገሩት ይሄንኑ ነው፡፡ የታሪክ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደሚሉት፤ ትልቁ የኢትዮጵያ ፀጋ አባይ ነው፡፡ አባይ ሲወሳ ትልቁ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚነሳው ትልቅ ውሃ ነው፡፡ በምግብ ውሃ እራስን ለመቻል አባይን ብቻ ሳይሆን የአባይን ተፋሰስን የሚያካትቱ ወንዞችን ሁሉ ለመሥኖ በማዋል የግብርና ሥራው ይከናወናል፡፡
ግድቡ ለእድገት አንድ ምሰሶ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይሉ ከማመንጨት ባለፈም፤ አባይ ሲገደብ ትልቁ ነገር ሰው ሰራሽ ኃይቅ በመሆኑ በራሱ መስህብ ነው፡፡ አካባቢው በተፈጥሮ ለምለም በመሆኑ አካባቢውን በደንብ በመጠበቅ ለቱሪዝም ማዋል ይቻላል፡፡
የታሪክ ሙህሩ እንዳሉት፤ አባይ ጨዋማ ያልሆነ ንጽህ ውሃ ነው፡፡ የአካባቢውም የአየርፀባይ ተሰሚና ምቹ ነው፡፡በዓለም ትልቁ በሆነው ወንዝ ላይ መዝናናትም በራሱ ትልቅ ስሜት
አለው፡፡ አባይ በመሆኑ ብቻ በተጨማሪ ደግሞ የአባይ ፏፏቴ፣የአባይ ምንጭም ሌላው መስህብ ነው፡፡ ከክረምት እስከ በጋ ድረስ ቱሪስቱ መሳብ ይችላል፡፡ይህ ትልቅ ፀጋ ባለው ቦታ መዝናናት በተለይም ከውጭ ለሚመጣው ቱሪስት ልዩ ይሆናል፡፡
ባዶ ቦታውን በማልማት ደግሞ ሌሎች የቱሪዝም ዕድሎችን ማስፋት ይቻላል፡፡ለአብነትም በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በግድቡና በሐይቁ አካባቢ በአማራ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መካከል አላጥሽ ፓርክ፣ በመሰራት ላይ ያሉት ጎርጎራ፣ ጣና እና ወንጪ እነዚህ ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ቱሪስቱ እየጎበኛቸው እንዲሄድ ማደረግ የሚቻልበት ዕድል እየተፈጠረ በመሆኑ ቱሪስቱ ከአዲስ አበባ ከተማ፣ ወንጪ፣ ህዳሴ ግድብ፣ ወደ አልጥሽ ፓርክ ይሄዳል፡፡
በአላጥሽ ፓርክ ደኑና በውስጡ በስፋት የሚገኙት ዝሆን፣ አንበሳና ሌሎችም የዱር እንስሳት ልዩ መስህቦች ናቸው፡፡ ቱሪስቱ በአልጣሽ ፓርክ ላይ ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ጎረጎራ፣ጎንደር ሰሜን ተራሮች ፓርክ በመሄድ ያሳልፋል፡፡የቱሪስት መዳረሻዎችን በዚህ መልኩ በማያያዝ የቱሪስት ቆይታውን ማራዘም ከተቻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምንም ሆነ ገጽታን በመገንባት ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል፡፡ የህዳሴ ግድቡ የሚፈጥረው መስህብም የዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡
ግድቡ በሚገኝበት አካባቢ ታሪካዊ የሆኑ መስህቦች ጥቂት ካልሆኑ ያን ያህል ሰፊ የሆነ ነገር አለመኖሩን የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ ከቅርስና ጥበቃ ጋር ተያይዞ ሊሰራ የሚችለው የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶችን የመጠበቅና የማጎልበት ለቱሪስትም ፍጆታ እንዲውል በማድረግ ሊሰራ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
አንድን ሀገር ትልቅነት የሚለካው ደግሞ በኢኮኖሚ አቅም እንደመሆኑ የግድቡ መጠናቀቅ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም እንደሚያሳድገውም ጠቁመዋል፡፡ ግድቡ አልቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር አካፍሉን እንግዛ የሚሉ ጎረቤት ሀገሮች መኖራቸው አይቀሬ ስለመሆኑ እና ይሄም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ጡንቻ ከፍ እንደሚያደርገውን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከላይኛውና ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንጠቀም በሚል እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በመቀጠል ግድቡን ዳር ማድረስ እንዳለባት እና እያንዳንዱ ትውልድ የየራሱን ሚና ከተወጣ የውጭውንም የውስጡንም ጫና በብቃት ሊወጣ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ግርማ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ግድቡ ለኃይል ምንጭነት ያለው ጠቀሜታ ከተሰጠው ጉልህ ስፍራ በተጨማሪ በቱሪዝም ኢንደስትሪ ውስጥ በርካታ ጠቀሜታ አለ፡፡ ለምሳሌ፣ የቱሪዝም ኢንደስትሪው ዋና ተግባሩ የምግብና የመጠጥ፣መዝናኛና የሥብሰባ ማካሄጃ አገልግሎቶች መስጠት ሲሆን፣አገልግሎቶቹም በሎጅ፣ሪዞርቶች፣ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ውስጥ ነው የሚሰጠው፡፡
የዓለምአቀፍ ተሞክሮዎች የሚሳዩት በነዚህ የአገልግሎት መስጫዎች ውስጥ ደግሞ ለአንድ ሰከንድም ቢሆን የመብራት አገልግሎት መቋረጥ የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ የኃይል ምንጯ ውሃ ሆኖ ነገር ግን ጠንካራ የሆኑ ግድቦች ባለመኖራቸው ከፍተኛ የሆነ የኃል መቆራረጥ ችግሮች ያጋጥሟታል፡፡ይህ ደግሞ ለቱሪዝም ኢንደስትሪው ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል፡፡መሰረተ ልማቱ የተሟላ ባለመሆኑም ደፍሮ የቱሪዝም ኢንደስትሪው ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያለው ለማግኘት ያስቸግራል፡፡
ዋና ዋና የሚባሉ የኢትዮጵያ የቱሪስት ሀብቶች ደግሞ በገጠራማው አካባቢ ነው የሚገኙት፡፡ ባሌ፣ ላልይበላ፣ አክሱም፣አርባምንጭ፣ደቡብ ኦሞ፣ ጅንካን ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡በነዚህ አካባቢዎች መሠረተልማቶች በተለይም መብራት ቋሚ የሆነ አገልግሎት እየተሰጠባቸው አይደለም፡፡በነዚህ አካባቢ ለቱሪዝም ኢንደስተሪው የሚሆኑ ግንባታዎችን ለማካሄድ ቅድሚያ የሚጠየቀው መሠረተልማት ነው፡፡የግድቡ መጠናቀቅ የቱሪዝም ኢንደስተሪው የኢንቨስትመንት ክፍተት ለመሙላት ትልቅ አቅምና ተስፋ ነው፡፡
ግዱቡ ኃይል በማመንጨት የነበረውን የኃይል አቅርቦት ከመቅረፍ በተጨማሪ በራሱም የቱሪዝም መስህብ ሆኖ ጥቅም ይሰጣል፡፡ በግድቡ ዙሪያ ከ50 በላይ የሚሆኑ ደሴቶች ይኖራሉ፡፡ ደሴቶቹ የውሃ ላይ መዝናኛዎችን በመፍጠር የቱሪስት ከተሞችን ለመመስረት ምቹ ይሆናሉ፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋርም በውሃ በማስተሳሰር ጉርብትና እና አብሮነትን በማጠናከር ፋይዳውን የጎላ ያደርገዋል፡፡
‹‹በግሌ የገድቡን ጠቀሜታ የማየው በቱሪዝም ኢንደስትሪው የሚስተዋለውን የኃይል አቅርቦትና መቆራረጥ ችግር በመፍታት፣ በህዳሴው ላይ የሚሰሩ ደሴቶች የቱሪስት ከተሞች ወይንም መናኻሪያ ወይም አገልግሎት መስጫ መሆኑ፣ከጎረቤት ሀገራት ጋር ትስስር
ለመፍጠር ምቹ መሆኑን ነው›› የሚሉት አቶ ስለሺ፤ በአካባቢው የታሸገ ውሃም ሆነ ምግብ በማቅረብ ላይ ለተሰማሩ የሥራ ዕድል በመፍጠርና ዜጎችንም ተጠቃሚ በማድረግ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አገልግሎት ሰጭዎች ሲኖሩ ቱሪዝሙን ይደግፋሉ፡፡ ቱሩስቱም የተለያዩ አገልግሎቶችን በቅራቢያው ማግኘት ሲችል የተሟላ መስተንግዶ በማግኘቱ ይደሰታል፣ ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ስለሺ ማብራሪያ፤ በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት እየፈለጉ ከመሠረተልማት፣ከመሬት አቅርቦትና ሌሎችም ተያያዥ ነገሮችን ሲያነሱ የነበሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ባለሀብቶቹ የአንድ የቱሪስት መዳረሻ ባለቤት መሆን ይችላሉ፡፡ ከህዳሴ አስተባባሪ ጽህፈትቤት ጋር በቅርበት ለመሥራት የሥራ ዕቅዳቸውን ወይንም ፕሮፖዛላቸውን አቅርበው ትላልቅ በሆኑ የቱሪዝም ኢንደስትሪ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት ይችላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም እንደሚለው ደግሞ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ይውላል የሚለው እሳቤ እንዳለ ሆኖ ለኃይል ማመንጫነት የሚጠራቀመው ወይንም የሚያዘው ውሃ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ከሌላኛው አካባቢ ጋር በውሃ ትራንስፖርት ለማገናኘት አቅም ይፈጥራል፡፡ ባለው ሁኔታም ጉባ ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ የሚሆንበት ዕድል አስተማማኝ ይሆናል፡፡ አሁን ላይ የሚታዩ የፀጥታ አንዳንድ ችግሮች ወደፊት አይኖሩም፡፡
ከዚህም በተጓዳኝ በኢትዮጵያ በአስር አመት የቱሪዝም ዕቅድ ከሚገነቡ የቱሪስት ከተሞች አንዱ በግድቡ አካባቢ የሚገነባ መሆኑን፣ በዓለም ላይ ረጅሙ የሚባለው ወንዝ ከተፈጠረበት ሀገር ሲወጣ ለመዝናኛም፣ ለእይታም፣ ሊታረፍበትም የሚቻልበት መሆኑን ማሳያም ጭምር ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሲደመሩ ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቶ ከሚያስገኘው የኢኮኖሚ ጥቅም ባልተናነሰ በቱሪዝም ኢንደስትሪውም ጥቅም አንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡
እንደ ጋዜጠኛ ሄኖክ ገለጻ፤ የግድቡ ተፋሰሶችም እይታን የሚስቡ በመሆናቸው በአረንጓዴ በማልማትና ግድቡንም ከደለል በመታደግ መሥራት ይጠበቃል፡፡ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ መስህቦች የሚገኙበትን የጉባና አካባቢው ቀጠና ላይ አዲስ የኢትዮጵያ የውሃ ቱሪዝም የመስህብ ሀብት እውን ይሆናል፡፡ ከቱሪዝም አኳያ ብዙ ተስፋሰሶች የሆኑ ነገሮች ይፈጠራሉ፡፡
ለዚህ ደግሞ፣ በዚህ ግድብ ምክንያት የቱሪዝም ኢንደስትሪው ትልቅ ዕድል እየመጣለት ነው በመሆኑም ግድቡ ከኃይል ማመንጫነት ባለፈ ለቱሪዝም ኢንደስትሪው ያለውን ፋይዳ በህዝቡ ውስጥ ግንዛቤ በመፍጠር ሊጠቀምባቸውን ዕድሎች አውቆ እንዲዘጋጅ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ መንግሥት ለቱሪዝም ኢንደስትሪው ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ ያለውን ሥራ ካጠናከረ በግድቡ አካባቢ በጥቂት አመታት ጊዜ ውስጥ ጠንካራ የሆነ የቱሪዝም መሰረተልማት ይኖራል፡፡
አሁን በዓለም ላይ ባለው የውሃ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ አንዱ ከፍታዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴዋን ከአባይ ጋር አቆራኝታ መንቀሳቀስ ይኖርባታል፡፡ ይህ ሲሆን ባዕድ የሆነ የውጭ ስሜት አይኖርም፡፡ በቱሪዝም የመበልጸግ ዕድል እውን ማድረግ እንዲሁም ከኣካባቢው ጋር የተጣጣሙ ሥራዎችን መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013