የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ቀን አንስቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ካለችው ላይ ቆጥቦ ቦንድ በመግዛትና ስጦታ በመስጠት አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በግድቡ ግንባታ ግብፅና ሱዳን በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም የኢትዮጵያ መንግስት አለም አቀፍ መርህን በተከተለ መንገድ ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የግድቡ ግንባታ አንድም ሰከንድ ሳይቋረጥ እየተፋጠነ ይገኛል፡፡ የግድቡ ግንባታ ተፋጥኖ የውሃ ሙሌት ላይ በመድረሱ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያው ዙር ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀው ለሁለተኛው ዙር ሙሌት ዝግጅት በማድረግ ነበር፡፡
በተያዘው ዓመት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት አስረኛው አመት ሲከበር ሁለተኛው ዙር የግድቡ ሙሌት የተፋሰስ አገራቱን ባማከለ መንገድ እንደሚከናወን መነገሩ ይታወሳል፡፡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የክረምቱን መግባት ተከትሎ ተጀምሮ ትናንት ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡ አገሪቱ አሁን ባለችበት የውጭ ተፅዕኖ ውስጥ ይህ ሙሌት መከናወኑ የአሸናፊነት ስነ ልቦናን መልሶ የፈጠረ ሲሆን በተለይ አገሪቱን እየመራ ለሚገኘው መንግስት ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ከሚፈጥረው የስነ ልቦና አሸናፊነት በተጨማሪ ማህበረሰቡ በራሱ አቅም ሌሎችን የልማት ስራዎች መስራት እንደሚችል ያነቃቃ መሆኑን የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ሙሌቱ በመንግስት ላይ የሚፈጥረው የስነ ልቦና መነቃቃት የስነልቦና ባለሙያ የሆኑት አቶ ሻረው አለማየው እንደሚናገሩት፤ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር ሙሌት መጠናቀቅ እንደ መንግስት ብዙ ፋይዳ ያለው የስነልቦና መነቃቃት ይፈጥራል፡፡ መንግስት የህዳሴው ግድብ በብዙ ችግር ውስጥ ያለፈ እንደመሆኑ መጠን ከሚጠይቀው ኢንቨስትመንትና አጠቃላይ ከነበረው ማህበራዊ ፖለቲካ አንፃር የመጀመሪያው ነገር ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ የአባይን ወንዝ የሚጋሩ አገራት በሚያሳድሩት ጫና እንዲሁም አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ሆኑ ሌሎች ተቋማት የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደመሆኑ ሙሌቱ እንደ ትልቅ ድል እንዲታይ ያደርገዋል፡፡
ሌላው መንግስት የሚያስበው በአገሪቱ ብዙ የፕሮጀክቶች መጓተት ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገርና ለህዝብ ከሚሰጡት ጥቅም በላይ ፕሮጀክቶቹ ለግሰቦች ገንዘብ መብያ ሲሆኑ እንደሚታይ ይናገራሉ፡፡ የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ለሌሎች ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ መንግስት እንደ ስንቅ ሊቆጥረው እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ የህዳሴ ግድቡ ፕሮጀክት ግዙፍነት አንፃር የሚያመጣው ውጤት ትልቅ ሲሆን አንድ ስራ ተጀምሮ መጠናቀቅ ይችላል የሚለው ነገር በመንግስት በኩል እንዲፈጠር ያደርል፡፡ በተጨማሪም ግድቡ እንዳይሰራ የተለያዩ ሙከራዎች ከውጪ ሀይሎች በኩል ይስተዋላል፡፡ አገር በቀል ኢኮኖሚ እገነባለው ለሚል መንግስት ከፍተኛ የስነ ልቦና ድል እንደሚፈጥርለት ያመለክታሉ፡፡
በአገሪቱ ህዝብ የየእለት እንቅስቃሴ ውስጥ ብዙ የሀይል መቆራረጦች አሉ፡፡ ይህ ሲባል የሰው የየእለት እንቅስቃሴ በሀይል መቆራረጥ ምክንያት ብዙ ነገሮች ይስተጓጎላሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት እንደ እንቅፋት የሚቆጠረው በቂ የሀይል አቅርቦት አለመኖር ነው፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት የግድቡ ግንባታ እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ መንግስት በውጪና በውስጥ ያሉበትን ጫናዎችና ችግሮች ተቋቁሞ እንዲሁም ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንዲህ አይነት ስራዎችን መስራት ከቻለ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ሌሎች ቀጣይ ፕሮጀክቶችን ከዚህ በላቀና ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ለመስራት የሚችልበትን ስነልቦናዊ ድል ማግኘት እንደሚችል አቶ ሻረው ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ አቶ ሻረው አባባል፤ አገሪቱ ለአፍሪካ የነፃነት ምልክት ተደርጋ የምትወሰድ ነች፡፡ ብዙ ጊዜ የአገሪቱን ባንዲራ የአፍሪካ አገሮች የነፃነት ምልክት አድርገው በመቁጠር እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ የአገሪቱ ባንዲራ ለሌሎች አገራት ባንዲራ መሰረት ቢሆንም ብዙዎቹ ተፈጥሯዊ ሀብቶቻቸው እንዲሁም የውጪ የገንዘብ ፍሰትን መጠቀምና በሌሎች አገራት ይሁንታ እንደሚንቀሳቀስ ለማየት ተችሏል፡፡ በራስ በመተማመን ለሌሎች እንደ አድዋ ድል ሆኖ እንዲቆጠር ማድረግ ይቻላል፡፡ የአድዋ ድል ለብዙዎች ፖለቲካዊ ነፃነት ማምጣት የቻለ ሲሆን የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ለመጠናቀቅ መቅረብ የኢኮኖሚ ድል ለማምጣት በር የሚከፍት ነው፡፡ በተመሳሳይም ዲፕሎማሲያዊ ድልን በተወሰነ መልኩ ያሳድገዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የህዳሴ ግድብ ግንባታና የውሃ ሙሌት በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ መወሰኑ ሌላኛው የዲፒሎማሲ ድል ተደርጎ እንደሚቆጠር አቶ ሻረው ያመለክታሉ፡፡ ይህ ድል የኢትዮጵያን ማደግ የሚፈልጉ ወይም አገሪቱን እንደ ተምሳሌት ለሚያዩ ጥሩ ተነሳሽነትና በራስ የመወሰንን አቅም ከፍ ያደርጋል ተብሎ እንደሚታሰብ ይጠቅሳሉ፡፡
የታላቁ የህዳሴ ግድብ የተለያዩ ፈተናዎችን አልፎ አሁን ያለበት ደረጃ መድረሱ ህልም ሊመስል ይችላል፡፡ አገሪቱን የተለያዩ ፈተናዎች ተጋርጠውባት የግድቡን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡ በአገር ውስጥ ባሉ አፍራሽ ሀይሎች ርብርብ እያደረጉ ነበር፡፡ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መጠናቀቅ የመንግስት አቅምና የህዝቡን ብርታት የሚያሳይ መሆኑን የስነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ራቦ ይገልፃሉ፡፡ አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ አለም ሁሉ የሚያውቀውን ግድብ ውሃ ሙሌት ይቅርና ምንም መታሰብ በማይቻልበት ወቅት በአገር ውስጥና በውጭ ባሉ ጠላቶች የአንድነት ህልውናው ጥያቄ ውስጥ በገባበት ወቅት እንዲሁም ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እየተፈታተኑ የግድቡ ሁለተኛ ዙር መሞላት የአገሪቱን ታላቅነት ያሳየ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
“ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት መጠናቀቁ የመንግስትንና የህዝብን የአሸናፊነት ስነልቦና ከፍ በማድረግ ረገድ ፋይዳ ይኖረዋል” የሚሉት አቶ ብርሃኑ፤ መንግስት በአገሪቱ ማንኛውንም ግድብ በተባለበት ጊዜ የማጠናቀቅ ስራም ለማሳደግ እየሰራ ነው፡፡ በዚህም ብዙ ፕሮጀክቶች በአስገራሚ ፍጥነት ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡ ቀደም ብሎ ፕሮጀክቶች ተጀምረው በተባለበት ጊዜ ማጠናቀቅ አልተለመደም ነበር፡፡ ብዙ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አላልቅ ብለው መስሪያ ቤት እስከመሆኑ መድረሳቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ አሁን ላይ ግን ይህን መጓተት ለማስቀረት የሚታዩት ተነሳሽነቶች ለውጥ እያመጡ ናቸው፡፡ የህዳሴው ግድብ የመንግስትን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ያስመሰከረ እንዲሁም የተለያዩ ጫናዎች ሲመጡ የመንግስትን የማይናወጥ አቋምን ያሳየ ነው፡፡ አገርን ለማልማትና በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስቀመጥ የመንግስትን ጥረት ያስመሰከረ ፕሮጀክት ነው፡፡ አገሪቱ የራሷን የመልማት መብት ተጠቅማ ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ መስራት እንደሚቻል ያስመሰከረችበት ፕሮጀክት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታና ውሃ ሙሌት ያሳየችው አቋም ሌሎች የአፍሪካ አገራት በአገር ውስጥ ለሚያካሂዱት ልማት ያለማንም ጣልቃ ገብነት ማከናወን እንደሚችሉ የስነ ልቦና ጥንካሬ የሰጠ መሆኑ አቶ ብርሃኑ ይገልፃሉ፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነት በውስጥ ልማት ላይ ለውጥ እንደማያመጣ ኢትዮጵያ ያሳየችበት ፕሮጀክት ነው፡፡ የግድቡ መገንባት ለኢትዮጵያም ሳይሆን ለአፍሪካ አገራት ትልቅ ፋይዳ ያለው ሲሆን የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቅ ደግሞ ለሌሎች ፕሮጀክቶች መነቃቃት እንደሚፈጥር ያመለክታሉ፡፡ የሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ለመንግስት ከፍተኛ የሆነ የአሸናፊነት ስነልቦና እንደሚሰጠውም ይጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም አገሪቱን የመምራትና የማስተዳደር ሞራል ይጨምርለታል፡፡ ቀጣይ ትውልድ በገዛ አገሩ ሳይዋረድና በሌሎች ሳይታዘዝ መስራት የሚችልበት የመጀመሪያው እድልና ፋና ወጊ የሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊያንን ቆራጥነት የታየበት በመሆኑ ለመንግስት ትልቅ የአሸናፊነት ስነ ልቦና እንደሚሰጠው ይናገራሉ፡፡
ሙሌቱ በማህበረሰቡ ላይ የሚፈጥረው የስነ ልቦና መነቃቃት የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ወደ መጠናቀቁ መድረስ በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ የአሸናፊነት ስነ ልቦናን ይፈጥርለታል፡፡ እንደሚታወቀው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተከናወነ ያለው በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዋፅኦ መሆኑን አቶ ሻረው ይናገራሉ፡፡ ለግድቡ ግንባታ ከልጅ እስከ አዋቂ ገንዘብ በማዋጣት እና እናቶች ካላቸው አነስተኛ ገንዘብ አወጥተው በመሆኑ የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቅ የተለየ ትርጉም እንደሚኖረውም ያስረዳሉ፡፡ የመጀመሪያው በማህበረሰቡ ዘንድ የይቻላል ስሜትን የሚፈጥር ሲሆን ፕሮጀክቱ ወደ ግንባታ ከገባ በኋላ በነበሩ ብልሹ አሰራሮች አመኔታ ጠፍቶ ነበር፡፡ የሙሌቱ መጠናቀቅ ህብረተሰቡ በግድቡ ግንባታ ላይ የነበረውን አመኔታ እንዲመልስ በር ይከፍታል፡፡ ሁለተኛው ነገር ማህበረሰቡ ግድቡ ‹‹የኔ›› ነው የሚል ስሜት በውስጡ የያዘ በመሆኑ የሁለተኛው ዙር ሙሌት መጠናቀቅ ለማህበረሰቡ የስነልቦና ደስታን ለመፍጠር ፋይዳ እንዳለው ይጠቅሳሉ፡፡
በአገሪቱ የሚኖሩት ዜጎች ብዙ አመታት በኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ ሲሰቃይ የነበረ ነው፡፡ ግድቡ ተጠናቆ ከአገር አልፎ ለውጪ ሲሸጥ የማህበረሰቡን ችግር የመፍታት አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም የስነ ልቦና አሸናፊነት ብቻ ሳይሆን የተግባር አሸናፊነትን እንደሚፈጥር ያመለክታሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ የመተሳሰሪያ ገመዶች በተለያዩ ምክንያቶች እየላሉ ነበር፡፡ ከቅርብ አመታት ውስጥ እየተፈጠሩ የመጡትን የመተሳሰሪያ ገመዶች እንደ ማጥበቂያ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ያብራራሉ፡፡ ሁሉም ሰው ‹‹ግድቡ የኔ ነው›› በሚል ያለውን አዋጥቶ የውጭ ጫናዎች ሲመጡ በጋራ ቆሞ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ህዝቡ በተለያዩ ፅንፎች ውስጥ ሆኖ የሚታይ ሲሆን የግድቡ ውሃ ሙሌት በተወሰነ መልኩ ይህን ሁኔታ ጤናማ የሆነ የአገር ወዳድነት ስሜትና ብሄራዊ መንፈስን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል ያብራራሉ፡፡
በማህረሰቡ በኩል ቀደም ብሎ ጀምሮ ‹‹ግድቡ የኔ›› ነው በሚል መንፈስ የተንቀሳቀሰው ለአፉ ሳይሆን በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ራቦ ይጠቅሳሉ፡፡ ለግድቡ ግንባታ ሁሉም ህብረተሰቡ ካለው በማዋጣት አሁን ያለበት ደረጃ አድርሷል፡፡ ማህበረሰቡ ግድቡን እንደ አይኑ ብሌን በመመልከት ዘብ የቆመ ሲሆን በአሁኑ ትውልድ ታላቁን ግድብ በራስ አቅም መሰራቱ በራሱ የስነ ልቦና ልዕልና እንደሚያመጣ ይጠቅሳሉ፡፡ ማህበረሰቡ ቀና ብሎ በኩራት የሚሄድበት ትልቅ ፕሮጀክት ሲሆን ከድህነት ለመላቀቅ ለሚደረገው ጉዞ ፕሮጀክቱ የራሱ አስተፅኦ ያለው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ማህበረሰቡ ሌሎች ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ጊዜ እንደሚጠናቀቅ እንደ ማሳያ እንደሚወስደው አቶ ብርሃኑ ይጠቅሳሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ደግሞ አገሪቱን ከከበባት ጨለማ የሚወጣበት በመሆኑ የአሁኑ ሁለተኛው ዙር ሙሌት መጠናቀቁ እንደ ትንሳኤ ሊወሰድ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቅ የመጀመሪያው የልማት መንገድ በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዞ ጉዞ የሚደረግበት የማንነት ማሳያ ነው፡፡ ለማህበረሰቡ ከፍተኛ የሆነ ትርጉም የሚኖረው በመሆኑ የሚመጣውን ትሩፋት በመተንተን አንድ ወጥ የሆነ አቋም ለመያዝ በር እንደሚከፍትም አስረድተዋል፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013