በሀገራችን ታሪክ እስካሁን እንደ ሕወሀት በሀገርና በሕዝብ ላይ ግፍና በደል የፈፀመ አለ ማለት አይቻልም። ለጥፋት የተፈጠረው አሸባሪው ሕወሀት በሥልጣን ከቆየበት ጊዜ ጀምሮ ብቻ ሣይሆን በጫካ ሲጠነሰስም የሚፈጸማቸው ግፎች ለመናገር አሰቃቂና ዘግናይ ናቸው። ይህ ድርጊቱ በተለይ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በይፋ ሊገለፅ የሚችል መሆኑ ማንነቱን በይፋ እንዲመሰከር መንገድ የከፈተ ነው።
ቀድሞም ቢሆን የለየለት ሴራን በመጎንጎን ሥልጣን ከመቆናጠጥ ባሻገር ለ27 ዓመታት የሥልጣን ዕድሜውን ያራዘመው ይህ ቡድን፤ በሕዝብ ትግል ሥልጣኑን ለቆ መቀሌ ከከተመ በኋላ ሀገር በማተራመስ፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በመሸረብ ዳር እስከ ዳር እሣት በመለኮስ ሀገር እንዳትረጋጋ በማድረግ ሲያወክ ቆይቷል።
ይህ አልሳካ ሲለው በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ብቻ ሣይሆን በሠራዊቱ ልጆች ላይ ያደረሰው ግፍና በደል፣ በማይካድራ ንፁሀን ዜጎች ላይ ያደረሰው ጨፍጨፋ የሚዘነጋ አይደለም። የንፁሀን ደም በማፍሰስ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚያደርገው ጉዞ መክኖ፣ ከመኖር ወደ አለመኖር መቀመቅ ገብቷል። ነገር ግን ደግሞ በጣት የሚቆጠሩ ርዝራዦች እንዳይሆኑ ሆነው ተርፈዋል።
ፈጽሞ ከጥፋቱ መማር የማይችለው ይህ ቡድን በጥፋት ላይ ሌላ ጥፋትን እየጨመረ፤ በሀገሩና በገዛ ወገኑ ላይ ግፍና በደልን መፈፀሙን ተያይዞታል። ከጥንስሱ ጀምሮ የሐሰት ፕሮፖጋንዳን በመንዛት፣ በሐሰት ፕሮፖጋንዳው ተወዳዳሪ የለሽ በመሆኑ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በውትወታ የድረሱልኝ ኡኡታ ጥሪ በማሰማት ዳግም ለማገገም ተፍጨርጭሯል።
መንግሥት በትግራይ ያለውን ውጥረት ለማርገብ በማሰብ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት የተናጥል ተኩስ አቁም ሥምምነት ላይ በመድረሱ መከላከያ ሠራዊቱን ከመቀሌ ማስወጣቱ ይታወቃል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነቱ የተፈረጀው አሸባሪው ሕወሓት ደግሞ ይህንን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከተደበቀበት ጉድጓድ ወጥቶ ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንዲሉ ወደ ቀደመው ድርጊቱ በይፋ ተመልሷል።
በትግራይ ንፁሀን ዜጎች እና የኤርትራ ስደተኞች ላይ የጭካኔ ብትሩን በማሳረፍ ሕፃን እና አረጋውያንን ሣይለይ ግፍና በደል እየፈፀመ ይገኛል። በተለይ እኩይ ዓላማውን አልደገፉም ያላቸውን ተጋሩዎች ሣይቀር በአሠቃቂ ሁኔታ በመግደል አረመኔነቱን እያሳየ ነው። ይህ አልበቃ ብሎት የተኩስ አቁም ሥምምነቱን አልቀበልም በማለት ሽንፈቱን ረስቶ በአማራ ክልል በኩል ትንኮሳና ወረራ በመፈፀም ሌላ ጥፋት ለመፈፀምና ዕድሜውን ለማሳጠር እየፈጠነ ይገኛል።
ቆሜለታለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብ ሥቃይና መከራ እያበዛ፤ የሕዝብን ሠቆቃ ከቁብ ሲያቆጥር ከጠብ ጫሪ ድርጊቱ መቆጠብ አልቻለም። የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት በጦርነት አሸንፎ መቀሌን እንደተቆጣጠረ ለማስመሰል ሞክሯል። መከላከያ ከመቀሌ ከወጣ በኋላ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያለአንዳች ይሉኝታ እንዳሻው እየፈነጨ፣ ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ለማፍረስ እንደማይተኛ ሲያስተጋባ ሰምተናል። የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶችንና የሃይማኖት ሰዎችን ከፊት ለፊት በማሰለፍ ትንኮሳና ወረራ ለመፈፀም ባለችው የተሞጠጠች አቅሙ ጥረት አድርጓል።
ባለፉት ጊዜያት ከደረሰበት ሽንፈት እና የሞራል ኪሣራ ተምሮ፤ በረሃብ እያለቀ ነው እያለ ለሚጮህለት የትግራይ ሕዝብ ከመድረስ ይልቅ ተጨማሪ ሥቃይና ሠቆቃ እየፈጠረ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እያስከተለ በግፍ ላይ ግፍ እየደራረበ ይገኛል። በጥፋቱ ላይ ጥፋት እየጨመረ እንዳሻው ወደ ፈለገበት አቅጣጫ በእውር ድንብር እየተጓዘ አይኑን ጨፍኖ ንፁሀን ዜጎችን ለጦርነት እየማገደ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው።
ቀደም ሲል ጦርነት ባህላዊ ጨወታ ነው እያለ ሲያናፋ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ፣ አይሆኑትን ሆኖ መቀመቅ ወርዶ ማለቃቀሱ የቅርብ ጊዜ ትዝታው ቢሆንም ያንን ሁሉ ረስቶ፣ ከሕዝቡ እና ከመንግሥት ተደብቀው ነፍስ የዘሩ በመሰላቸው ኃይሎች አለሁ የሚለውን ለማያወቁት እየዘፈነ በማሳመን ምንም እንዳልተፈጠረ ዛሬም ሌላ ጦርነት እንዲኖር ለማድረግ ከወዲያና ወዲህ በመቅበዝበዝ ወረራን እየፈፀመ ነው።
አሸባሪው ሕወሀት ጉድ ተብሎ ብቻ ሊታለፍ የማይችል እጅግ አሣፍሪና አደገኛ ተግባርን እየፈፀመ ይገኛል። ሕፃናትን በሐሽሽ በማደንዘዝ ወደ ጦርነት እንዲገብ በማድረግ የእሣት እራት እንዲሆኑ አድርጓል። ሃይ ባይ የለሽ የሆነው ትህነግ በትግራይ ምድርና ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለው ግፍ ሣይበቃ፤ ግፉን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ አካል አድርጎ ለዓለም በማሳየት ላይ ይገኛል። ይህ አያያዙ ሕዝቡን ካለበት ችግር ሊያወጣው ቀርቶ፤ ይባስ ብሎ አረጋውያንን ሣያስቀር ሁሉንም ለጦርነት በማሰለፍ በሕዝብ ውስጥ በመከለል ለመደበቅ እየሞከረ ነው።
ሕጻናት፣ ሴቶችን፣ አዛውንቶችና የሃይማኖት ሰዎች በዚህ የወረራ ፈፀምኩባቸው ባላቸው ቦታዎች ከፊት እያሰለፈ በእነሱ ደም ወደ ሥልጣን ለመመለስ ያለውን ፍላጎት እያሳየ ነው። በዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ ዕድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ሕጻናት በጦርነት ማሰለፍ ወንጀል ሆኖ ሣለ በማንአለብኝነት እያሰማራ ይገኛል። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ድርጊቱን ከመውቀስ እና ከማውገዝ ይልቅ ዝምታን መርጧል።
ይህ የጥፋት ቡድን መንግሥትን በመኮነን የሚገዳደረው የለም። የትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ተደርጓል፤ የትግራይ ሕዝብ በረሃብ ሊያልቅ ነው ሲል ነበር። ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንዲሉ ታዲያ እነዚህን ትግራይንና ትግራዋይን ለጦርነት እየማገደ የሚገኘው ትህነግ ለሕዝቡ ያለውን ተቆርቋሪነት ለማሳየት ይሆን? በውጭ የሚኖሩ ተጋሩ ዲያስፖራስ ሲያስተጋቡ የነበረው ጩኸት አሁን መልሱን አግኝቶ ይሆን? የሚለውን መጠየቅ አስፈላጊ ነው። በአሁኑ ወቅት የትግራይ ሕዝብ ከመከራና ሥቃይ የሚያወጣውን ዜጋ ይፈልጋል።
መቼም ቢሆን አሸባሪው ሕወሀት ለትግራይ ሕዝብ ሥቃይን እንጂ ሌላ ይዞ መጥቶ አያውቅም። ሥቃይና መከራ እንጂ ዕድገትና ብልጽግና አላመጣም። አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ በሕዝቡ ላይ በተለይም ሕፃናትን እና አረጋውያንን ለጦርነት በማሠለፍ እየፈፀመ ያለው ግፍ በዓለም ተወዳዳሪ የሌለው መርገምት የወረደበት ቡድን ነው ለማለት ያስገድዳል። በርግጥም በየትኛውም ዓለም ሕፃናት ቀጣይ ትውልድ በመሆናቸው በጦርነት ሊሳተፉ ቀርቶ፤ በአዋቂዎች በሚካሔድ ጦርነት ውስጥ እንዳይጎዱ ከለላ ይደረግላቸዋል። የሕወሀት አሸባሪ ቡድን ግን ከዓለም አስተሳሰብ የተነጠለ በመሆኑ፤ ሕፃናቱን ወደ ጦርነት በመማገድ እሣቱን እየሞቀ የአጥፊነት ሱሱን እያወራረደ መሆኑ ሲታሰብ በርግጥም ቡድኑ የሰዎች ስብስብ ሰው ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል።
እየሩስ አበራ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013