እሩቅ ሳንሄድ የእድር እና እቁብ አባላትን እንመልከት። የአንድ አካባቢ ነዋሪዎችን እንይ። የተቋም ሠራተኞች፣ የንግድ ስፍራዎች፣ ትምህርት ቤቶች ፣ … በመመልከት አዲስ አበባ የብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ መሆኗን መመስከር ይቻላል። ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ እንደየአቅሙ ሁሉም የሚኖርባት ከተማ መሆኗን መግለጽ ቀላል ነው። ይህንን ሃቅ የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፤ ነዋሪዎችም አጣጥመዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ሠራተኛ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ፤ አዲስ አበባ የመንግሥት መናገሻና የሃገሪቷ የፖለቲካ ማዕከል በመሆኗ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ተሰባስበው የኖሩባት ከተማ መሆኗን ይናገራሉ። የመንግሥት መስሪያቤቶች እና ፖሊሲ የሚመሩ ማዕከላት የሚገኙባት ከተማ በመሆኗ በሃገሪቱ ደረጃ ትልልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የሚወሰነውም በአዲስ አበባ ነው።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና ትላልቅ የአፍሪካ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች መወሰኛ ለመሆን የቻለች ከተማ ናት። ይህን ተከትሎ የከተማዋን ፖለቲካዊ ህይወት የሚያሳድግ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ እና ከመላው ዓለም የመጡ የኤምባሲ ተቋማትን ያቀፈች እና በጣም በርካታ ዲፕሎማቶችን እንዲሁም የውጭ ዜጎችን የያዘች ከተማ ናት።
ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ማዕከል ከመሆኗ ባሻገር የመንግሥት መቀመጫነቷ እና መናገሻነቷ እንዲሁም በዘመናት በሄደችባቸው የእድገት ጎዳናዎች ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ኢትዮጵያዊያን ሰፍረዋል። ተድረዋል ፣ ወልደው አሳድገዋል። ልጆቹ ደግሞ የኢትዮጵያን መልክ በአዲስ አበባ የበለጠ እያደመቁ እና እያጎሉ ለዘመናት ተጉዘው አሁን ላይ ከተማዋ በጣም ዝንቅ የሆነ ህብረት እንዲኖራት ማስቻላቸውን አመላክተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ እንደገለጹት ፤ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች ብሎ መጠየቅ ለሚፈልግ ሰው ምላሹ ‹‹አዲስ አበባን›› የሚል ከሆነ ትክክል ነው። አዲስ አበባ ውስጥ የሌለ ሃይማኖት ፣ የማይነገር ቋንቋ ፣ የማይታይ ባህልና ብሄረሰብ የለም። ይሄ ሁሉ መስተጋብር አዲስ አበባን የባህሎች ፣ የማንነቶችና የሃይማኖቶች መገለጫ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል። ይሄ መስተጋብር እየተሻሻለ ለዘመናት ተጉዞ አሁን ላይ በጣም በብዙ በዝርዝር ሊጠና የሚችል የፍቅር እና የአንድነት ግንኙነት ፈጥሯል።
መርካቶ በንግድ የተሰማሩት የከተማ ነዋሪዎች ከመላው ኢትዮጵያ ከሚመጡ ሰዎች ጋር የፈጠሩት የራሱ ውብ የሆነ ቀለም አለው። ፒያሳ አካባቢ የጥንቱ የአዲስ አበባ መልክ እንደሚስተዋል ይናገራሉ። እንጦጦ አካባቢ ብዛት ያላቸው የሃይማት ተቋማት ያሉበት አሁን ደግሞ የለማው የእንጦጦ ፓርክ የሚገኝባት ናት። ወደ ቦሌ አካባቢ ደግሞ ትንሽ ዘመናዊነት እና ዓለም አቀፋዊነትን የተላበሰ አካባቢ መሆኑን አንስተዋል። እነኝህ ሁሉ በየጊዜው የሚከናወኑ የከተማዋ እድገቶች አዲስ አበባ ኢትዮጵያዊያንን እያቀፈች ፣እየጨመረች ፣ ከሁሉም አቅጣጫዎች ሁሉንም እያካተተች የባህሎች መቅለጫ መሆን ችላለች።
አዲስ አበባ ከተፈጠረችበት ጊዜ አንስቶ ወደ ከተማዋ የመጡ ብሄር ብሄረሰቦች በመተባበር እና በመደጋፍ በኢትዮጵያ ይመሰላሉ። በገባር ወንዞች የተደራጀ ትልቅ ወንዝ ደግሞ መልሶ መለየት እና መነጣጠል እንደማይቻል ረዳት ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።
አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መልክ ያላት እና ከብሄረሰቦች ባህል መዋሃድ ባለፈ እጅግ በረቀቀ መልኩ በፍቅር ፣በጋብቻ እና በመሳሰሉት ሁኔታዎች የተዋሀዱ ሰዎች መኖሪያ ከተማ ናት። ገበያ ፣ ሆቴል ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት… ወዘተ የሚሄድ ማንኛውም ሰው ማነህ ከየት ነህ ብሎ የሚጠይቀው የለም። ይሄ በጣም አስፈላጊና በመላው ኢትዮጵያ ሊሰፋ ፣ ልናራባው እና ልናባዛው የሚያስፈልግ መልካም ተሞክሮ ነው። በዚህም አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ትልቅ ምሳሌ ናት።
አዲስ አበባ የአንድነት ምሳሌ ከተማ መሆኗን የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ፣ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ያጋጠሙትን የመለያየት እና የመራራቅ ዝንባሌ በእንጭጩ ለመቅጨት ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ከአዲስ አበባ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ህብረ ብሄራዊነት እንዲሁም አብሮና ተባብሮ የመኖር ባህል መኖሩን የምታስረዳው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የቀበሌ ቤት ተከራይ የሆነችው ወጣት ሄለን ወንድይፈራው ሃጎስ ናት። በመኖሪያ በግቢያቸው ከ9 በላይ አባወራዎች ይኖራሉ። በእያንዳንዱ አባወራ ቤት ልጆች እና ዘመድአዝማድ ተዳምሮ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው የተለያየ እምነት ተከታይና የተለያየ ብሄር ያለው ሰው ይገኛል። ሁሉም ነዋሪ ግን በተለያዩ የበዓላት ቀናት በፍቅር ተጠራርቶ አብሮ እየበላና እየጠጣ በሚያስደስት መልኩ ያሳልፋል። ‹‹ፍቅራቸው ሁሉንም ዓይነት የመለያያ ገደቦች ያሸነፈ ነው።›› ስትል ጥንካሬያቸውን ትናገራለች።
‹‹ አንዲት እናት ለሥራ ወይም ለሌላ ጉዳይ ልጇን ጥላ ብትወጣ ግቢ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ሰው እስከምትመለስ ድረስ ልጁን ተንከባክቦ ያቆያል።›› ይሄ የአንዱ ልጅ የሁሉም ልጅ መሆኑን ማሳያ ነው።
በአንድ ግቢ የሚኖሩ የተለያዩ ብሄሮች እና ሃይማኖት ተከታዮች አንድነት እና መደጋገፍ የተለያዩ ችግሮችን ሲያጋጥሙ በቀላሉ ለማለፍ ያስችላል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከትንሿ የቀበሌ ቤት የመተባበር እና የመደጋፍ ተሞክሮ በመውሰድ ሀገሩን ከውጭ እና ከውስጥ ጠላቶቹ ሊከላከል እንደሚገባ ትመክራለች።
ሌላኛዋ ስለ አዲስ አበባ ህብረ ብሄራዊነት ሃሳቧን የሰጠችን ወጣት መሰረት ጌጤ ትባላለች። በሽሮ ሜዳ የባህል አልባሳት በመሸጥ ህይወቷን ትመራለች። አሁን ላይ የባህል አልባሳት የሚዘጋጀውና የሚሸጠው የሁሉንም ብሄረሰቦች እና ሃይማኖት መሰረት ያደረገ ነው።
‹‹አዲስ አበባ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ ከመሆኗም ባለፈ የተለያዩ የውጭ ሃገራት የሚኖሩባት ከተማ ናት ። ስለዚህ የውጭ ሃገር ዜጎች የኢትዮጵያን የባህል አልባሳት እየገዙ ይለብሳሉ። ውጭ ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው ገዝተው ይወስዳሉ። ስለዚህ የሁሉንም ብሄረሰብ ባህልና ሃይማኖት ለማስተዋወቅ ሁሉንም ዓይነት አልባሳት እናቀርባለን›› ብላለች።
ከዚህ በፊት የባህል አልባሳት የሚዘጋጀው በዶርዜ ማህበረሰብ ብቻ ነበር የምትለው ወጣት ጌጤ ፤ አሁን ላይ የሽመና ሥራውን የዶርዜ ማህበረሰብ ቢያዘጋጅም ከሽመና በኋላ እስከ ሽያጭ ባሉት ሄደቶች የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ይሳተፋሉ። ይህ ደግሞ በአዲስ አበባ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች አብረው እና ተባብርው የሚኖሩባት ብቻ ሳትሆን የሚሠሩባትም ከተማ መሆኗን አንዱ ማሳያ ነው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013