በዚህ ሳምንት ውስጥ ሆነው ካለፉ የታሪክ ክስተቶች መካከል በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን የምንቃኘው የኢትዮጵያን የመጀመሪያ ህገ መንግሥት ይሆናል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተፃፈ የመጀመሪያ ህገመንግሥት ይፋ የተደረገው ሐምሌ 9 ቀን 1923 ነበር። ህገ መንግሥቱ እንዴት ተዘጋጀ፣ ምን ምን ጉዳዮች ይዞ ነበር የሚሉና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን እንዳስሳለን።
ኢትዮጵያ በዘመናዊ መንግሥት ሥርዓት መተዳደር ከጀመረች ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ህጎች፣ደንቦችና መመሪያዎች እየወጡ ሲሰራባቸው ቢቆይም፣ በንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ከፀደቀው ከዚህ ህገ መንግሥት በፊት ተፅፎ የተቀመጠና የአገሪቱ ስርዓተ መንግሥት የሚመራበት ሰነድ አልነበረም።
በእርግጥ ከዚህ ህገ መንግሥት በፊት ፍትሀ ነገስት የሚባልና በነገስታት የሚሰጡ መተዳደሪያ ትእዛዞች ህጎች መመሪያዎች ያቀፈ ያልተጠረዘ ሰነድ እንደነበር የተለያዩ ሰነዶች ያስረዳሉ። ይህ ህገ መንግሥት ረቆ ተግባር ላይ እንዲውል ያደረጉት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በወቅቱ ህገ መንግሥቱን ማርቀቅና ሥራ ላይ ማዋል ስላስፈለገበት ምክንያት አስረድተውም ነበር። በዚህም የህገ መንግሥቱ ሥራ ላይ መዋል አስፈላጊነት ሲገልፁ አገሪቱ በህገ መንግሥት እንድትመራና ሌሎች ከንጉሱ በታች ያሉ ባለስልጣናት ለዚህ ህገ መንግሥት እንዲገዙና ህዝብ የመንግሥትን ሥራ እንዲያውቀውና በዚያ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ለማስቻል እንደነበር ገልፀዋል።
ንጉሱ ለአገሪቱ ህገ መንግሥት ያስፈልጋታል ብለው አምነው ወደ ተግባር ሲንቀሳቀሱ ህገ መንግሥቱን እንዲያዘጋጁ አልያም ደግም እንዲያረቁ ሁለት ሁነኛ ሰዎችን መርጠው ነበር። በማርቀቅ ሂደት ተመርጠው የተሳተፉት ተክለ ሀዋሪያት ተክለ ማሪያምና ብላቴ ጌታ ህሩይ ወልደ ስላሴ ነበሩ።
በህገ መንግሥቱ የማርቀቅ ሂደት ውስጥ ብዙ ክርክርና አለመግባባቶችም ተነስተው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይገልፃሉ። ህግ መንግሥቱ በወቅቱ ከነበረው የጃፓን ህገ መንግሥት ብዙ ጉዳዮችን ተወስዶ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በኢትዮጵያዊ ህዝብና ባህል መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲጣጣም የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ ተደርጎበታል። በእርግጥ በወቅቱ በወጣው ህገ መንግሥት ላይ የንጉሱ ሹማምንትና ባለስልጣናት በህገ መንግሥቱ ላይ ብዙ ጥያቄዎችን አንስተው አለመግባባት ውስጥ ገብተው ነበር።
በተለይም በስልጣንና በመሬት ባለቤትነት ዙሪያ የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተው ነበር። ከወቅቱ መሳፍንት አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣንና መሬት ለመሳፍንት፣ለመሳፍንት ልጆችና ልጅ ልጆች ብቻ መከፋፈል አለበት ብለው ያምኑ ነበር። በአንፃሩ ደግሞ መኳንንቶች የመሳፍንቱን ሀሳብ በመቃወም በኢትዮጵያ መሬትና ግዛት ውስጥ እስከኖረ ድረስ ሌላውም ሰው መብት ሊኖረው ይገባል የሚል ሀሳብ አንስተዋል።
በመጨረሻም በዚህ ሙግትና የተለያዩ ሀሳቦች መሀል የተዘጋጀውና የረቀቀው ህገ መንግሥት ለቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ቀርቦ ንጉሱ የመሳፍንቱን ሀሳብ ውድቅ አድርገው የመንግሥት አገልጋዮችና ህዝቡ የመብቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው በህገ መንግሥቱ ውስጥ እንዲካተት አድርገዋል።
ይህ ህገ መንግሥት ምንም እንኳን የመንግሥትና የሀይማኖት መለያየትን አለመግለፁ፣ የንጉሱ ስልጣን ገደብ በመለጠጡና፣ በተጠያቂነት ረገድ ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑ በብዙዎች ቢተችም እንደ አገር ተረቆና በህግ ደረጃ ሊተገበር ታስቦ ሥራ ላይ በመዋሉ ብቻ አድናቆትን ይቸሩታል። ይህ ብዙ ችግሮች ነበሩበት የተሰኘው ህገ መንግሥት በሥሩ 11 ምዕራፎችና 85 አንቀፆችን ይዟል።
ይህ የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ህገ-መንግሥት ቀደም ብሎ የነበረውን ፍትሀ ነገስትን ለመተካት የመጣ ህገ-መንግሥት ነበር። በሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም የተካሄደ ታላቅ ድግስ ላይ ነው እንዲጸድቅ የተደረገውም። በህገ መንግሥቱም ስለ ስልጣን ርክክብ ሁኔታዎች፣ ስለ አልጋ ወራሾች፣ የኃይለስላሴ(ንጉሱ) ስልጣን፣ስለግዴታዎች እና በኃይለስላሴ እውቅና ስለተሰጣቸው መብቶች፣ ስለ ኢትዮጵያ ፓርላማ፣ ስለ ሚኒስቴሮች እና የሥራ በጀት አወጣጥ የመሳሰሉ ዋና ዋና ሀሳቦች የተካተቱበት ነበር።
በህገ መንግሥቱ ላይ የተመለከቱ ዋና ዋና ነጥቦች ለመጥቀስ ያህል የኢትዮጵያ ወሰን ከጫፍ እስከ ጫፍ ድረስ ያለው የንጉሰ ነገስቱ እንደሆነ፣ ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚባል፣ የኢትዮጵያ ህዝቡም መሬቱም ሁሉ የንጉሰ ነገስቱ እንደሆነ፣የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መሆን የሚችለው ከንጉስ ሰለሞንና ከንግስተ ሳባ የመጣው የቀዳማዊ ሚኒልክ የዘር ሀረግ ከአፄ ሀይለ ስላሴ ዘር የተገኘ መሆን አለበት የሚለውና የንጉሰ ነገስቱ ክብር የማይቀነስ፣ ማዕረጉ የማይገሰስ መሆኑን በጥብቅ የሚገልፁ አናቅፆች ነበሩት።
በህገ መንግሥቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ እና በዚህ ዘመን እይታ የሚተቹ ብዙ አንቀፆችና ህጎች የተካተቱበት ነበር ከሚያሰኙ ጉዳዮች ዋንኛው ንጉሰ ነገስቱ ስልጣናቸው (ንግስናቸው) በፍፁም በሌላ አካል እንዳይነጠቁ የሚያዘውና ስልጣናቸውን ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርጉ መሆናቸው ነው። ይህ ህገ መንግሥት እስከ 1955 ድረስ ቆይቶ በሌላ ተለውጧል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013