ብዙዎችን በስነጥበብ ታሪክና በአጠቃለይ ታሪክ አስተምረው ለቁምነገር ያበቁ ናቸው። በርከት ያሉ ጥናትና ምርምሮችን በመስራት አገር ብሎም ግለሰቦች እንዲጠቀሙ ያደረጉም ስለመሆናቸው ይነገራል። በተለይም በአገር ወዳድነትና ታሪክ ነጋሪነታቸው እንዲሁም በአነቃቂ ንግግራቸው ብዙዎች ያውቋቸዋል። ከዚያ ሻገር ሲል ደግሞ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ አገራዊ አሻራቸውን በማሳረፍ ላይ የሚገኙ ናቸው። ከእነዚህ መካከልም የአንድነት ፓርክ የሙዚየሙ ፕሮጀክት አንዱ ሲሆን፤ አሁንም ያላለቀው የብሔራዊ ቤተመንግስትን ሙዚዬም አድርጎ፣ አድሶ ለህዝብ ክፍት ለማድረግ የሚሰራው የሳይንቲፊክ ኮሚቴው ሊቀመንበር ናቸው።
የቅርስና ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርም በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። ስለዚህም በዚህ ሁሉ የሥራ ጊዜያቸው ውስጥ በርካታ ልምዶችን አከማችተዋልና ከዚህ የህይወት ተሞክሯቸው ያጋሩን ዘንድ ለዛሬ የ‹‹ ሕይወት ገጽታ›› አምድ እንደግዳችን አድርገናቸዋል። ስለዚህም ከረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ልምድን ቅሰሙ ስንል ጋበዝናችሁ።
ስምንቱ ወንዶች
የተወለዱት በቀድሞው ጎጃም ክፍለአገር በአገው ምድር አውራጃ ኪላ ጊዎርጊስ በምትባል ስፍራ ሲሆን፤ በ1968 ዓ.ም ህዳር 30 ቀን ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ጎጃም አገራቸው ሆኖ ነው ያደጉት። ምክንያቱም አባታቸው መምህር በመሆናቸው ይዘዋወራሉና በአንድ ቦታ አልኖሩም። እንደውም አብዛኛውን የልጅነት ጊዜያቸውን ከጎጃም አልፈው ቤኒሻንጉልም የዘለቀ ነበር። ስለዚህም ከጉምዝ ማህበረሰብ፣ ከሺናሻውና ከአገው ጋር ብዙ ባህል እየለመዱ ነው የልጅነት ጊዜያቸው ያለፈው። ከእነዚህ ባህሎች ደግሞ ልዩ የሆኑ እውቀቶችን አግኝተዋል። ማደንና ዛፍ በፍጥነት መውጣት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የመጀመሪያ የልጅነት ጊዜያቸውን የሚያስታውሱበት በቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ በምትገኘው ዳንጉር ላይ ሲሆን፤ የአምስት ዓመት ልጅ ሆነው ነው ወደዚህ ስፍራ የመጡት። ምክንያታቸውም አባታቸው ናቸው። መምህር በመሆናቸው ሲዛወሩ አብረው ሄደው ይኖራሉ። እናም የልጅነት ሀ ሁ ን በዳንጉር እንዲጀምሩ ሆነዋል። ዳንጉር በረሀ ውስጥ ያለች በተራራ የተከበበች ቦታ ከመሆኗም በላይ የንጉስ ዳዊት ገዳም ያለባት፣ ትልቅ የንግድ ከተማ ነች። በዚህም ውድ ውድ ሰዓቶች፣ ቴፖችን ለመሸጥ እንዲሁም ከዳንጉር ደግሞ ወርቅና እንደ ጉሬዛ አይነት ያሉ የእንስሳት ቆዳን ለመውሰድ በርካታ ነጋዴና ሸማች ወደ ዳንጉር ይመጣል። ይህ ደግሞ ለእንግዳችን የተለየ የባህል ልምድ የቸራቸው ነበር።
በዚህ ቦታ ሲኖሩ ብዙ ባህላዊ ጨዋታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከልም የሺናሻዎች ባህላዊ ጨዋታ ልዩ ትዝታ የጣለባቸው ነው። በተለይም በዕለተ ጥምቀት የሚካኤል ታቦት ወጥቶ የሚደረጉ ትዕይንቶች ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያቀፈ ስለሆነ መቼም የማይረሳ የልጅነት ትዝታቸው እንደነበር አጫውተውናል። ይሁን እንጂ ዳንጉር ከዚህ በተቃራኒው ለልጆቹ ሳይሆን ለእናት አባት ፈታኝ ነገሮች ያሉባት ከተማ ነበረች። ኢህአፓ በስፋት የሚንቀሳቀስባትና እነርሱን የሚቃወም ሁሉ የሚገደልበት ነው። መምህራኑ ላይ ብዙም ጫና ባያሳርፉም የሚዘመረው መዝሙር ግን እነርሱን የሚሰድብ በመሆኑ ርዕሰ መምህሩን ገደሉት። ክሊኒክ የገባ መድሀኒትም ወዲያው ገብቶ ይወሰዳል። ስለዚህም በዚህ ሁኔታ መኖር አስጊ ስለሆነባቸው አባታቸው ዝውውር ጠይቀው በመተከል አውራጃ ጓንጓ ወረዳ ሴማ አቡነ ሀቢብ የምትባል ቦታ ገቡ።
በቤተሰቡ ውስጥ የሚኖሩት ከእናት በስተቀር ሁሉም ወንዶች ናቸው። ስምንት ወንድ በአንድ ቤት ውስጥ መኖሩ ደግሞ የሴት ሥራ የሚባል ነገር እንዳይታሰብ አድርጓል። ስለዚህም ባለታሪካችን ሦስቱን ወንድሞቻቸውን አዝለው የማሳደግ ሀላፊነትም ነበረባቸው። ቤት መለቅለቅ፣ ሽንኩርት መክተፍ፣ የከብት ጉሮኖ ማጽዳት፣ እበት መጠፍጠፍና መሰል እናት መታገዝ ያለባቸው ተግባራትንም በሚገባ ይከውናሉ። የወንድ ሥራም ቢሆን ብዙም አላመለጣቸውም። እንጨት ከጫካ ከመልቀም እስከ መፍለጥ ሰርተዋል።
በዚህም ቢሆን የተለየ ኑሮ ያልነበራቸው ባለታሪካችን ብዙ ደስተኛ የሚያደርጓቸውን ነገሮች እያደረጉ እንዳደጉ ይናገራሉ። በተለይም ጓንጓ በጣም በደንና በወንዝ የበለጸገች ለጥ ያለች ሜዳ ቢፈለግ የማይጠፋባት በመሆኗ ዓሳ ማጥመዱ ላይ በጣም ጎበዝ ሆነው እንዲያሳልፉ፤ በዋና ራሳቸውን ዘና እንዲያደርጉ እንዲሁም ጫካም ገብተው ቆቅ እንዲያጠምዱ ከዚያ ተለቅ ሲል ድኩላና መሰል እንስሳትን እንዲያድኑ በተፈጥሮ መጋቢነቷ አግዛቸዋለች። በተለይም በቅዳሜ ስሁር ዕለት ሁሉም ውሻ ይዞ ወጥቶ አደን ላይ ይውላልና እርሳቸውም በዚህ ራሳቸውን ደስተኛ ያደረጉበትን ጊዜ አይረሱትም።
አባታቸው መምህር ብቻ ባለመሆናቸው ደግሞ የበለጠ ደስተኛ የሚያደርጉ ጊዜያትን እንዲያሳልፉ እድል ሰጥቷቸዋል። ምክንያቱም አባት ከማስተማር ጎን ለጎን የማይሰሩት ሥራ የለም። በተለይም በግብርናው መስክ በብዙ መልኩ የሚሰሩ ናቸው። ከብት ያረባሉ፣ ንብ ያነባሉ፣ እርሻም ቢሆን መሬት እየተከራዩ ያርሳሉ። ስለዚህም ለእርሳቸው ትርፍ የሚባል ሰዓት የለም። በዚህም እንግዳችንም የአባታቸውን ፈለግ ተከትለው ስለሚጓዙ ብዙ ፈታ የሚሉበትን ጊዜ ያሳልፋሉ። በተለይ በዋናነት የሚሰሩት ከብት ማገድ ላይ ስለሆነ በሜዳው የሚቦርቁበትን ጊዜ ያገኛሉ። እንደውም በዚህ ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች በአብዛኛው አገዎች በመሆናቸው ከእናትና ከአባት በስተቀር ልጆቹ አገውኛ ጠንቅቀው ማወቅ ችለዋልና ቤተሰቡን ለመሸወድም ሆነ ቋንቋን ከማወቅ አንጻር ልዩ ልምድ እንዳገኙበት አይረሱትም።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው በባህሪያቸው አትንኩኝ ባይ፣ ሃይለኛ ፣ ክፋት ግን በውስጣቸው የሌለና ደፋር ናቸው። በድፍረታቸው የተነሳ ዛሬ ድረስ የማይረሳ ጠባሳ እንደተሰጣቸው ያስታውሳሉ። ይህ የሆነው ደግሞ ያልተገራ ፈረስ ሲጋልቡ ሉጓሙን ፈረሱ በጥርሱ በመበጠሱ ከፈረሱ ላይ ወደቁ። የግራ ትከሻቸውም አጥንት ተሰበረ። በዚህም ቦርሳ እንኳን መያዝ አይችሉም። ከአቅማቸው በላይ ጭምር የሆነ ሰው እንደሚጣሉና እንደሚማቱም ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ የልጅነት ጠብ ስለሆነ ወዲያው እንደሚረሱት ነው የነገሩን። በተለይም ይህንን ባህሪያቸውን የለዩት ምስራቅ ጎጃም አዋበል ወረዳ ሉማሜ ከተማ ነብርማ የምትባል አምራች ቀበሌ ውስጥ በመኖር ጊዜ እንደነበርም ያወሳሉ።
ታሪኮችን በተለየ መልኩ መስማት በጣም የሚወዱት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ የአያቶቻቸው ተጋድሎ ብዙ ነገር እንደሰጣቸው ያስባሉ። አጋነው የሚያወሩት፣ የአርበኝነት ታሪኮችና ተረቶች በጣም ይመስጧቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ። ሌላው ስለ እንግዳችን ስናነሳ በእድገታቸው ቀበጥ ሆነው አላሳለፉም። ከዚያ ይልቅ እንደ ማንኛውም የመምህርም የገበሬም ልጅ ሆነው እንዲያድጉ ተደርገዋል። ሁሉንም ባህል እያዩ ብቻ ሳይሆን እየኖሩት እንዲያልፉም ነው የሆኑት። ከዚያ ውጪ ደግሞ ሥራ ወዳድ የሚሆኑበት መንገድ ነው የተዘረጋላቸው። የተሰጣቸውን ሥራም ሆነ ጥናት አለመጨረስ ያስቀጣቸው የነበር ነው። ስለዚህም መስራት ልምድ ያደረጉና ዛሬ ድረስ በስራ ደከመኝ የማያውቁ መሆናቸውን ነው።
ከዳንጉር እስከ አዲስ አበባ በትምህርት በዳንጉር እያሉ ነው ከትምህርት ጋር የተተዋወቁት። አንደኛና ሁለተኛ ክፍልን በዚህ ተምረዋል። ሆኖም ሁለተኛ ክፍልን ግን በአግባቡ ተምረው እንዳላሳለፉት ያስታውሳሉ። ምክንያቱም በቦታው ላይ ተረጋግቶ የመማር እድሉ አልነበራቸውም። ስለዚህም አባታቸውን ተከትለው በሄዱበት መተከል አውራጃ ጓንጓ ወረዳ ሴማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ክፍልን ዳግም እንዲማሩ ሆነዋል። እስከ ስድስተኛ ክፍልም የቆየ የትምህርት ክትትል በዚህ ቦታ ነበራቸው። ከዚያ በዝውውር አባታቸውን ተከትለው ወደ ምስራቅ ጎጃም አዋበል ወረዳ ሉማሜ ከተማ በመግባታቸው ሉማሜ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን መከታተል ችለዋል። ቀጥለ ደግሞ አሁንም አባታቸው ሲዛወሩ ቤተሰቡም አብሮ ይጓዛልና እርሳቸውም በደጀን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘጠነኛና አስረኛ ክፍልን እንዲማሩ ሆነዋል።
ሌላው የትምህርት ቦታቸው በማቻከል ወረዳ አማኑኤል ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ሲሆን፤ ከ11 እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከፍተኛ ውጤት በማምጣትም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለዋል። በዩኒቨርሲቲው ሲገቡ የመጀመሪያ ዓመትን ያሳለፉት አጠቃላይ ኮመን ኮርሶችን በመከታተል ሲሆን፤ ይህ ጊዜ በተለይም ለገጠር ልጆች ብዙ አቅም የፈጠረ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከማስታወሻ እስክ ጥናት፤ ከትምህርት መስክ መረጣ እስከ ውጤታማነትና ቤተ ሙከራና ቤተ መጸሀፍት አጠቃቀም ድረስ ብዙ ትምህርት የወሰዱበት እንደነበርም ይናገራሉ።
ሁለተኛ ዓመት ላይ ሲገቡ የትምህርት መስክ እንዲመርጡ የተደረጉት እንግዳችን፤ ለዚህ ምርጫቸው የሁለተኛ ደረጃ የታሪክ መምህሮቻቸው ትልቅ አስተዋዕጾ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ። ምክንያቱም እነርሱ ታሪክ ትምህርት ላይ የተለየ ፍቅር አሳድረውባቸዋል። ይህ ደግሞ በውጤታቸው የፈለጉት የትምህርት መስክን መምረጥ ቢችሉም የመጀመሪያ ምርጫቸውን የታሪክ ትምህርት መስክን እንዲያደርጉ መርተዋቸዋል። በዚህ ውሳኔያቸውም አባታቸው ከመጠን በላይ ተናደው እንደነበርም አይረሱትም። ለምን ህግ እያለ፣ ለምን ኢኮኖሚክስና ሌሎች መስኮች እያሉ ማንም በተረት መልክ የሚነግርህን መስክ መረጥክም ብለዋቸው እንደነበርም አይዘነጉትም። ግን የትምህርት ፍቅሩ በውስጣቸው ስለነበር ዛሬ ድረስ በውሳኔያቸው እንደማይጸጸቱ አጫውተውናል።
እርሳቸው ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ በትምህርታቸው በጣም ጎበዝና ተወዳዳሪ ናቸው። አባት መምህር በመሆናቸው ለትምህርት ልዩ ትኩረት ይሰጣሉና በየመንፈቅ ዓመቱ ሳይቀር አወዳድረው ይሸልሟቸዋል። በተለይም ሰኔ ግም አለ ማለት ለእነርሱ አዲስ ልብስ ማን ይወስዳል የሚል ፉክክር ነጋሪት ነው። በግ ታርዶ ጭምር ነው የሚጠብቋቸው። ስለዚህም እነ ረዳት ፕሮፌሰርም ሽልማቱን ለመቀበል የማይቆፍሩት ድንጋይ አልነበረም። ሽልማቱ አዲስ ልብስ መሆኑ ደግሞ ሁሉንም ያጓጓ ነበር። በዚህም ብዙ ጊዜ ለማሸነፍ ከሌሎቹ ወንድሞቻቸው በላይ ያጠናሉ። በዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ አሸናፊና ተሸላሚ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። እንደውም ይህ ሁኔታቸው ምን እንዳቀመሷቸው ስለማይታወቅ እነርሱ ቤት ማንም አይወድቅም። ስለዚህም ዝም ብላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት ነው እስከመባል አድርሷቸዋል።
ባለታሪካችን በልጅነታቸው መሆን የሚፈልጉት አስተማሪ ወይም ወታደር ነበር። በተለይ አስተማሪ መሆንን ሁለት ምክንያት ይፈልጉታል። የመጀመሪያው በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ መምህራን አኗኗር ሲሆን፤ ከተማ ሄደው ዘና ከማለት ውጪ ምንም አይነት ግብርና ውስጥ አይገቡም። ስለዚህም ከከብት መጠበቅ ወጥተው በነጻነት ለመኖር ሙያውን መመኘታቸው ነው። ሁለተኛው የመምህራኑ ተጽዕኖ ሲሆን፤ በጣም የሚወዷቸውና የሚያከብሯቸው ሁለት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህራን አሉ። እናም እነርሱን ሲያዩ ሁልጊዜ የታሪክ መምህር መሆንን ያስባሉ። በስተመጨረሻም ይህንኑ መርጠው በዚህ መስክ እንዲሰሩ ሆነዋል።
አባታቸው የማንበብ፣ የማዳመጥ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ የዜና ማጠቃለያ ጭምር እንዲጽፉና እርሳቸው ሲመጡ እንዲያነቡላቸው ያደርጋሉ። በዚህም የመጸሐፍ ምርጫ ሳይኖራቸው እንኳን ነበር በቤት ውስጥ የተገኘ መጸሐፍትን የሚያነቡት። ይህ ደግሞ እውቀታቸውን በሁሉም መስክ እንዲያሰፉ እንዳገዛቸው የሚናገሩት ባለታሪካችን፤ በዚህ ልምዳቸው በመስራታቸው ዩኒቨርሲቲ ገብተው በከፍተኛ ውጤት ተመርቀው በዚያው ሲቀሩ ይወጣሉ በሚል ኢንቫሮመንታል ሂስትሪ እንዲያጠኑ ጭምር ቃል አስገብተዋቸው እንደነበር አይረሱትም። ሆኖም የትምህርቱ ክብደት በቀላሉ የሚያልፉት አይነትና ለማጥናትም አገራዊ ነገሮች የሌሉት መሆኑ እንዳይወስዱት አድርጓቸዋል። ነገር ግን መማር ይፈልጋሉና ኢንቫይሮመንታሉን ወደ አርት ሂስትሪ ቀይረው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አሁንም በከፍተኛ ውጤት መመረቅ ችለዋል።
የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የመመረቂያ ጽሁፍ ሰርተው ሲያቀርቡ እነ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ነበሩ ፈታኛቸው። በዚህም ለዲፌንስ ብቻ ከሦስት ሰዓታት በላይ እንደፈጁ አይረሱትም። ይህ ደግሞ ለቀጣይ ሥራቸው ጭምር ጥሩ ልምድና ትምህርት የቀሰሙበት እንደሆነ አጫውተውናል። ከዚያ በኋላ ግን ምንም እንኳን የውጪ ትምህርት እድልን በቻሉት ሁሉ ቢሞክሩም በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን አልቀጠሉም። ይሁን እንጂ እውቀት የሚያስጨብጡ በርካታ ስልጠናዎች ላይ ተሳትፈዋል። ከዚያ ባሻገር በሚሰሯቸው ፕሮጀክቶችና ምርምሮች እንዲሁም ከማስተማር ልምዳቸው ራሳቸውን በእውቀት እየገነቡ እንዳለፉ ያወሳሉ። በተለይ መምህር መሆን ሁልጊዜ መማር ነው ብለው ያምናሉና አሁንም ተማሪ ነኝ ብለውናል።
ታሪክን በሥራ ከፍተኛ ውጤት በዩኒቨርሲቲው ማምጣት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎች አማካኝነት ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች የመቅረት እድልን ይሰጥ ነበር። እናም ረዳት ፕሮፌሰርም ይህንን መስፈርት አሟልተው ከቀሩት ሁለት ተማሪዎች አንዱ ሆነው ነው ስራቸውን ‹‹ሀ›› ብለው በሚወዱት የትምህርት መስክ የጀመሩት። በእርግጥ ይህ እድል ሲሰጣቸው ቀላል ሆኖ አልነበረም። በትምህርት ውጤታቸው፣ በፍላጎታቸውና በሰሩት የመመረቂያ ጽሁፍ ምክንያት የሚመጥኑ ሆነው ስለተገኙ ነው። በዚህም ከ1991 ዓ.ም ጀምረው በረዳት ምሩቅነት የገቡ እስከ 2011 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲውን ሳይለቁም ለ20 ዓመታት በተለያየ ቦታ ላይ ማገልገል ችለዋል።
የታሪክ መምህርነታቸውን በ2003 ዓ.ም እንዳቆሙ ያጫወቱን ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ ከዚህ በኋላ በታሪክ መምህርነት መቆየቱ ብዙ ጫና ነበረበት። የመጀመሪያው ለትምህርት መስኩ የሚያስተምሩት መብዛቱ በተጨማሪነት ደግሞ የማህበራዊ ሳይንስና ታሪክም በአብይ ትምህርትነት ይሰጣል። ስለዚህም ሁለቱንም ይዞ መቀጠሉ በጣም ከባድ ስለሆነ ከዚህ ለመውጣት ያስወሰናቸው ጉዳይ ነበር። ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ በታሪክ ምክንያት መናቆሩና መካሰሱ ሰፋ። ከነበረው ስርዓት ጋር ተያይዞም ታሪክ ፖለቲካ ሆነና በብሔር ጭምር ተከፍሎ የእንትን ብሔርን ታሪክ በሁለት ክፍል ዘለለው፣ እከሌ ይህንን ተባለ፣ የእኛ ሀይማኖት ተነካና መሰል ጥያቄዎች መጉረፋቸው የኢትዮጵያን ታሪክ አላስተምርም የሚለው እንዲበዛ አደረገ። በተራ ሲሆንም እንዲሁ ፈቃደኝነቱ የሰፋ አልነበረም። ስለዚህም በዚህ መቀጠሉ ምቾት እንደማይሰጣቸው ራሳቸውን አሳመኑ።
በወቅቱ የቅንጅት ፓርቲ አባል መሆናቸውና የቅንጅት አባላት ሲፈቱ አቀባበል ማድረጋቸው በፖለቲካ አመለካከታቸው እንዲጠመዱ አድርጓቸዋል። ብዙ ክሶች በእርሳቸው ላይ ይሰነዘሩ ነበር። ስለዚህም ከዚህና መሰል ጫና ለመራቅ ሲሉ ማስተማሩን ትተው ሌሎች ሥራዎችን ወደመስራቱ ገቡ። ከእነዚህ መካከልም የታሪክ ትምህርት ክፍሉ ሄድ ሆነው ያገለገሉት አንዱ ነው። ቀደም ሲልም በትርፍ ጊዜ መምህር ስለነበሩ በስነጥበብና ዲዛይን ትምህርትቤት እንዲዛወሩ ጠይቀው ስለተፈቀደላቸው በአርት ታሪክ መምህርነታቸው እንዲቀጥሉ ሆኑ። አሁንም ድረስ በዚያ ያስተምራሉ።
በማስተማር ደረጃ ሁሉም እንደሚያደርገው በየዩኒቨርሲቲው እየተዘዋወሩ ያስተምራሉ። የድህረ ምረቃ ትምህርት ከተስፋፋ በኋላ ደግሞ በተለይ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጣም በሰፊው እየተመላለሱ መስራት ችለዋል። በተለይ ታሪክና ባህል የተሰኘው የትምህርት ክፍላቸው ጥሩ ስለነበር ውጤታማ ስራ እንደሰሩበትና ብዙዎችን ማፍራት እንደቻሉ ይናገራሉ። በተመሳሳይ ተማሪዎችንም ያማክራሉ። ምርምር መስራትም ዋነኛ ስራቸው ስለሆነ በርካታ ጥናታዊ ምርምሮችን አድርገዋል። እንደውም አራት የሚደርሱ ምርምሮች በአለማቀፍ የምርምር መጽሔት ላይ አሳትመዋል። ከ18 የሚበልጡት ደግሞ ባይታተሙም ወደ ሥራ ገብተው ውጤት ያመጡ ናቸው።
ከቅርስ ጥበቃ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የቅርስ እድሳት ሲደረጉ ኮንትራቶች በሚወጡበት ጊዜ ከሌሎች ጋር በመሆን ይሳተፋሉ። ከዚህ ውጪ ከ2011 ጥቅምት አካባቢ ጀምሮ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ይሳተፋሉ። ከእነዚህ መካከልም የአንድነት ፓርክ የሙዚየሙ ፕሮጀክት ላይ ሰፊ ስራ ሰርተዋል። አሁንም ያላለቀው የብሔራዊ ቤተመንግስትን ሙዚዬም አድርጎ፣ አድሶ ለህዝብ ክፍት የማድረጉን ፕሮጀክት ከፈረንሳይ መንግስት ጋር እየሰሩ ያሉት ነው። በዚህ ውስጥ የሳይንቲፊክ ኮሚቴው ሊቀመንበርና የፕሮጀክቱ ችፍ ሆነውም እያገለገሉ ይገኛሉ። ሌሎችም እንዲሁ የሚሳተፉባቸው ፕሮጀክቶች አሉ።
ከሚያዚያ 2011 ዓ.ም በኋላ ወደ የቅርስና ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርነት የገቡት እንግዳችን፤ በዚህም ከገቡ ከዋና ዳይሬክተሩ ጋር በመሆን ብዙ ለውጦችን ማምጣት የቻሉ ናቸው። ለዚህም በማሳያነት የሚነሳው ዋና ችግር የሆነውን አዋጅ ለማሻሻል የሄዱበት ርቀት ነው። አዋጁ ኢትዮጵያን ለሚያክል አገር፣ ቅርስ ከመመዝገብ እስከ መንከባከብና ማልማት ሁሉንም ሥራ ለቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን ሰጥቷል። በዚህም ክልሎች እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ ሆነዋል። ይህ ደግሞ በአሰራር ደረጃ ብዙ ክፍተቶችን ፈጥሯል። ስለሆነም ይህንን ከማስተካከል አኳያ አዋጁ ልዩ ጥናት ተደርጎ እንዲስተካከል ጸድቆ ለሚመለከተው የህግ አካል ቀርቧል። ይህም የሚሆነው በሁለት መልኩ ሲሆን፤ ብሔራዊ ቅርስና ክልላዊ ቅርስ በሚል ተከፍሎ ምዝገባውና መንከባከቡ እንዲሁም የልማት ጥያቄው በዚህ ደረጃ እንዲሰራ ማድረግ ነው።
የተጓተቱ ሥራዎችን በማስፈጸም በኩልም በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል። ለአብነት የተከበሩ የአለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ቤትን ከነበረበት ጉዳት ማውጣትና መታደግ ነው። ስለዚህም ብዙ ነገሮቹ ተጠናቀዋል። ከጥገና እስከ እቃ መመለስ የሚደርሱ ሥራዎችም አልቀዋል። አሁን የሙዚየም ግንባታውን በመስራት ላይ ሲሆኑ፤ መኖሪያና ስቱዲዮ የሆነው በጣም ጠባብ በመሆኑ ቱሪስት ለማስተናገድ እጅግ አዳጋች ነውና በጥንቃቄ መስራትን ይጠይቃል። ነገር ግን ይህም ቢሆን እያለቀ ስለሆነ በ2014 ዓ.ም ለጉብኝት ክፍት ይሆናል። አምስትም ሆነ አስር ሰው እንዲጎበኘው ይደረጋል። የጌዲዎን የባህል መልከአምድር በዩኔስኮ ለማስመዝገብም የፋይል እውቅናው ተጠናቆ ድምጽ ይሰጥበታልም። ስለዚህም ይህም ዋና ሥራቸው እንደነበር አጫውተውናል።
ያለው ሙዚዬም ኢትዮጵያን የሚመጥን ባለመሆኑ፤ እስከዛሬ ያለው የሙዚዬምና ተንቀሳቃሽ ኤግዚቢሽን ዳይሬክቶሬት ተብሎ መቀመጡ፣ ከዚህ ቀደምም ቢሆን በቅርስ አስተዳደር መምሪያ ሥር መተዳደሩ ሙዚዬሙ ብሔራዊነቱን እንዳያሳይ ሰፊ ችግር ፈጥሮበታል። ሌሎች አገራት ላይ ግን ትንሽ እንኳን ቢሆን በአዋጅ ደረጃ እራሱን ችሎ የተቋቋመ ነው። እናም ቅርስ ጥበቃና ሙዚዬሙ እንዲፋቱ በአዋጅ ደረጃ ራሱን ችሎ ብሔራዊ ሙዚዬሙ እንዲቋቋም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚዬም ማቋቋም አዋጅ በሚል ጸድቆ ወደመሚመለከታቸው አካላት መላኩ ትልቅ ለውጥ ያመጡበት እንደሆነ ያነሳሉ። የአርኬሎጂና የስነጥበብ ክፍሉንም ከማደራጀቱ እስከ እይታ ግንባታው ድረስ ሰፊ ሥራ መስራታቸውና ማጠናቀቃቸውም አንዱ ለውጥ ያመጡበት ጉዳይ እንደሆነም ነግረውናል።
የህይወት ፍልስፍና
መቦዘን ራስን ለቅኝ ግዛት መስጠት ነው ብለው ያምናሉ። ፈረንጆች እንደሚሉት ‹‹ የቦዘነ አዕምሮ የዲያቢሎስ መጨፈሪያ ነው ወይም ነገር ማጠንጠኛ ብቻ ነው›› ብለው ያስባሉ። ስለዚህም መቦዘን የለብንም የህይወት ፍልስፍናቸው ነው። መስራት ለራስም ትርፍ ነው ለሌላም መኖር ነው ነው የሚል አቋምም አላቸው። በህይወት የሰራነው ነገር ለዘላለም ሲያስተጋባልን ይኖራል። ህያውም ያደርገናልም ባይ ናቸው።
መልዕክት
በአገራዊ ጉዳይ ላይ ብዙ ማስታገሻ ሳይሆን ፈውስ ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራት መከወን ይኖርባቸዋል። የመጀመሪያው ከህገመንግስት ጀምሮ በጥልቀት ክለሳ መደረግ አለበት። ህገመንግስቱ ምን ምን ይጎድለው ነበር፣ ምን ምን ታሳቢ ተደርጎ ወደተግባር ተገባ የሚለውም መታየት ይኖርበታል። ምክንያቱም አገርን ማቆየት ይችላል አይችልም የሚለውን መልስ መስጠት አለበት። አገርን ህያው አድርጎ የተለያየ መንግስት ቢመጣ ማሻገር እንደሚችል ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የሚያስፈልጋትን ስርዓትም በአግባቡ መበየን ይገባል።
ብሔር ተኮር የሆነ የፖለቲካ ቋንቋና ሰዋሰውን መቀየርም ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ትልቅ የጋራ ጉዳይን እንዴት እንደምናስብ፣ እርስበርስ መተሳሰብን እንዴት እንደምናመጣ ማለም ይኖርብናል። ምክንያቱም አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ሁለት ነገር እንድንሰራ ተገደናል። አንደኛው ኢትዮጵያን ከመፈራረስ መታደግና ህልውናዋን ማረጋገጥ ላይ መስራት ሲሆን፤ ሁለተኛው የፖለቲከኞች የብሔር ሽኩቻን መዋጋት ነው። የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁሉንም አካታችና ህዝብን የለበሰ መሆን አለበት። ምክንያቱም አገርን ማሻገር በአንድ ብሔር ብቻ የሚመጣ አይደለም። የሁሉንም መረባረብና ሥራን ይጠይቃል። እናም መጀመሪያ እነዚህን ማረም ላይ መስራት ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን እንኳንስ ስራችን አንደበታችን እየለየን ይመጣል። ስለሆነም እዚህ ላይ መስራት ለነገ የሚባል መሆን እንደሌለበት ይመክራሉ።
ማንም ቢሆን የራሱን ክልል ጠፍጥፎ የሰራ ብሔር የለም፤ ማንም ቢሆን የራሱን ቦታ የፈጠረ ግለሰብ የለም። ስለሆነም ሁልጊዜ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ኢትዮጵያን አስቀድሞ ራስን የኢትዮጵያ አካል ማድረግ ያስፈልጋል። ከኢትዮጵያ ውስጥ ራስን ፈልጎ ማግኘት ይገባል። ይህ ሲሆን ሁሉ ነገር ለሁላችንም ይበቃል ይመጣል። ይህ ተወስዶብኛል የሚል እሳቤም ይቀራል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም ቦታ ላይ ሄዶ ማልማትና መኖር ይችላል።
ጊዜው ላወቀበት ትውልድና ላወቀበት ሰው ለአገሩ መስራት የሚችልበት ነው። እንደአሁን የሚመች ወቅት የለም። ምክንያቱም ሰው የሚያስፈልገው በተመቻቸ ጊዜ ሳይሆን በችግርም ወቅት ነው። እናም ሁሉም ዜጋ በተለይም ወጣቱ ለአገሬ ምን ልስራ እንጂ አገሬ ምን ሰራችልኝ ሳይል አሻራውን መትከል ይኖርበታል። ጊዜው እንዲያመልጠውም መፍቀድ የለበትም። ልማቱና የኢኮኖሚ ችግሩ ቢጫነንም ከፖለቲካው የቤት ሥራ አይከፋምና ይህንን ጥለን ላለማለፍ እንሞክር። እኛም የወረስነው የፖለቲካ የቤት ስራን እኛው ጨርሰን መቃረን የሌለባትን ባለታሪኳን ኢትዮጵያ ለተተኪው ትውልድ እንስጠው ሌላው መልዕክት ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013