ሁሉም ነገር ለከት አለው ። ማርም ሲበዛ ይመራል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢህአዴግ ካለው ለውጥ ፈላጊ ኃይል ጋር ያለ ልዩነት ተናቦና ተንሰላስሎ ህወሓት የገነባውን የጥል እያሪኮ በመጋቢት 2010 ዓ.ም አፍርሶ የዛሬውን አሸባሪ ህወሓትን ከ27 ዓመታት በላይ በብቸኝነት ይገዛው ከነበረው ግንባር በድርጅቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ሸርተት ሲያደርገው በሰላም ልዩነቱን ከማራመድ ይልቅ ወደ መማጸኛ ከተማው መቐሌ በመመሸግ ሀገሪቱን ከማተራማስ ባሻገር እንደ አጼ ልብነ ድንግል ምድርን 40 እየገረፉ ጦር አውርድ እያለ ፤ የሚላክለትን በጀት ከትግራይ ሕዝብ ጉሮሮ እየቀማ ከ200 ሺህ በላይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ሲያሰለጥንና ሲያስታጥቅ ፤ ሕገ ወጥ ምርጫ ሲያካሒድ ፤ ወዘተረፈ የለውጥ ኃይሉም ሆነ ሕዝቡ በልበሰፊነት ታግሶ ነበር ። ከ20 በላይ የሽምግልና ጥረቶችንም አድርጎ ነበር ። ህወሓት ግን እንደለመደው በጥቅምት 24፣ 2013 ዓም ከሀገሪቱ ሰራዊትና የጦር መሣሪያ 80 በመቶውን የያዘውን የሰሜን ዕዝ በውድቅት ሌሊት ያለ ልዩነት በመክዳት በማጥቃትና በመጨፍጨፍ የጦር መሳሪያ በመዝረፍ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲንቀሳቀስ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ተገዶ ወደ ጦርነት በመግባት በሁለት ሳምንት ውስጥ አከርካሪውን ሰብሮ የተዘረፈውን የጦር መሳሪያ በማስመለስ አንጸባራቂ ድል አስመዝግቦ ከስምንት ወራት ቆይታ በኋላ ለሰብዓዊነት ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያውጅም አሸባሪው ህወሓት ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ በአራት ግንባር ትንኮሳ ማድረጉ ፤ ኢትዮጵያውያንን ዳር እስከዳር እንደ አራስ ነበር በቁጣ ተነሱበት ። በአንድ ድምጽ ፦
”አውላላ ሜዳ ላይ የተኛውን በሬ ፣
ነካክተው ነካክተው አደረጉት አውሬ፤” ብለው ቀፎው እንደ ተነካ ንብ ወደ ሰሜን ተመሙ ። የህወሓት ጥቃት በአማራ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕልውና የተቃጣ ነው በማለት እንደ አድዋው ጦርነት በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘው በሕብረ ብሔራዊነት እምቤ ለሀገሬ አሉ ። አሸባሪው ህወሓት ጥቃቱን የአማራ ሕዝብ ብቻ አድርጎ ለማሳየት ያደረገው ሙከራ ከንቱ ከመሆኑ ባሻገር እንደ አድዋ ፣ ካራማራና ባድመ የሀገሩን ሉዓላዊነት ሕልውናና አንድነት በደምና ባጥንቱ ሊያጸና እንደገና ተማማለ ።
ህወሓት ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን እንደ ብረት ቀጥቅጦ ሲገዛ ተደራጅቶ ሲዘርፍ እርቃኗን ሲያስቀር ጎሳ እየመረጠ አልነበረም ። በግፍ ሲገል ሲያሰቃይ ገልብጦ ሲገርፍ ሲያስር ሲያግዝና ሲያሳደድ የነበረው ፤ ለምን ለጥ ሰጥ ብለህ አልተገዛህም ? ለምን መብትህን ትጠይቃለህ? ትቃወማለህ ? ሁለተኛ ዜግነትህን ለምን አምነህ አልተቀበልህም ? ሀገሪቱን ያለ አዛዥ ናዛዥ በአፈሙዝ እንዳሻኝ ብገዛ ብፈልጥ ብቆርጥ ምን አግብቶህ በሚል እንጂ ማንነትን እየለየ አልነበረም ። ዛሬ ለምንገኝበት ድህነት ኋላቀርነት የበይ ተመልካችነት ሥራ አጥነት ተስፋ ቢስነት ራዕይ አልባነት የዳረገን ሁላችንንም ያለ ልዩነት እንጂ በጎሳ እየለየ አልነበረም ። የጭቆና ቀንበር የጫነብን በሁሉም ኢትዮጵያዊ ጫንቃ ላይ እንጂ አማራን ኦሮሞን ሱማሌን ሲዳማን ወዘተረፈ እየመረጠ አይደለም ። ለ27 ዓመታት የፖለቲካ ምህዳሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶብን የኖረው ያለልዩነት በሁላችንም ላይ እንጂ ከፋ ሸካ ጋሞ እያለ አልነበረም። ትምክህተኛ ጠባብ አሸባሪ እያለ አፍኖ ደብዛ ያጠፋ በጨለማ ቤት ያስር ጥፍር ይነቅል ብልት ያንኮላሽ አንድ ኢትዮጵያዊው በገዛ ዜጋው ይፈጽመዋል ተብሎ የማይገመት ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ ስቃይ የፈጸመው በኢትዮጵያውያን ላይ እንጂ በላይ ቶሎሳ ኦቶሮ ሸምሱ እያለ እየመረጠ አልነበረም። በማዕከላዊ በቃሊቲ በቅሊንጦ በሸዋ ሮቢት በዝዋይና በሌሎች ስውር ማሰቃያ ቦታዎች ያጉር የነበረው ያለልዩነት እንደነበር የትላንት ታሪክ ነው።
በስማችን እየለመነ እየተረዳና እየተበደረ ያደኸየን ያቆረቆዘን የዘረፈን ያገለለን በእዳ እስከ አንገታችን እንድንዘፈቅ፤ ከድህነት አረንቋ እንዳንወጣ ያደረገን ያለልዩነት ሁላችንንም ነው። በእዳ ጀርባችንን ያጎበጠው ያለ ልዩነት ነው። ሌላው ይቅርና ከ60 ሺህ በላይ ልጁን ለገበረለት፤ በስሙ ሲምልለትና ሲገዘትለት ለነበረው የትግራይ ሕዝብ የተረፈለት ነገር ሌላ ዙር እልቂት መከራና ጦርነት ነው። ዛሬም የትግራይ ሕዝብ የውሃ ጥሙ እንዳልተቆረጠለት፣ ከከፋ ድህነት እንዳልወጣ፤ ከተረጅነትና ከተመጽዋችነት፤ ከአፈና ከጭቆናና ከአንድ ላምስት ጥርነፋ፤ ዛሬም ለአሸባሪው ህወኻት ምስ እንዲሆን ሩጠው ያልጠገቡ ልጆችን ደም እየገበረ ይገኛል። በአንጻሩ የአሸባሪው ህወሓት ገዥ ቡድንና ኔትወርኩ በአውሮፓና አሜሪካ በቅንጦት ኑሮ አለሙን ይቀጫል። ልጆቹን በእነዚህ ሀገራት ውድ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች አንደላቆና አፈላሶ እያስተማር የትግራዋይ ህጻናት ግን በአሽሽ እያሰከረ እብሪቱን ለመሞቅ ለእሳት ይማግዳቸዋል።
መቼም አሸባሪው ህወሓት ለ27/30/47 ዓመታት ያለ ልዩነት በመላው ኢትዮጵያዊ ላይ የፈጸመው ግፍ ዘረፋና ሁሉንም አይነት ወንጀል ተነግሮ ተተርኮና ተጽፎ አያልቅም። ዳጎስ ዳጎስ ያሉ ደርዘን ስንክሳሮች እንኳ አይበቁትም። ይሁንና ሁሉም በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸሙ ናቸው። ተጠቃሚው ገዥው የስብሀታዊ ስርወ መንግሥትና ጥቂት ጭፍራዎች ብቻ ናቸው።
የዕለት ደራሽ እርዳታ ለወር ቢዘገይ የትግራይ ሕዝብ የሆነውን አይተናል። የሕዳሴውን ግድብ አሽመድምዶት፣ ሜጋ ሜጋ የስኳርና የማዳበሪያ ፕሮጀክቶችን በቁማቸው ግጦ መለመል ያስቀራቸው ኩመራን ወዶ ቁምላቸውን ጠልቶ አይደለም። በኦሮሞና በአማራ በሲዳማና በወላይታ በጉራጌና በስልጢ በአፋርና በኢሳ በጉጂና በጌዲዎ ወዘተረፈ ልዩነት ጥላቻን የተዛባ ትርክትን ያራግብ የነበረው ከፋፍሎ ለመግዛት ስልጣን ላይ ለመቆየት እንጂ ለማንም ተቆርቁሮ እንዳልነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው ። በሽግግሩ ከኦነግ ጋር እልል በቅምጤ እንዳላለ የመንበሩን እርካብ ሲቆናጠጥ ግን አይንህን ለአፈር ብሎ ከስልጣን ኩርማኑ አባሮ ሰራዊቱን አታሎ አዋርዶና ትጥቅ አስፈትቶ አፍንጫህን ላስ ብሎታል ። በደህንነቱ ቦንብ እያፈነዳና ፈንጅ እያጠመደ አሸባሪው ኦነግ ነው እያለ ማሰቃያና እስር ቤቶችን በኦሮሞ ወጣቶች አጨናንቆ ነበር ። የኦሮሞ ሕዝብ ምልክት የነበሩ ፋና ወጊዎችን በግፍ ገድሏል ። ይሄን ሁሉ ህልቆ መሳፍርት የሌለውን ግፍ በኦሮሞ ላይ የፈጸመው ለአማራው ብሎ አይደለም ። አንድን ወገን ፣ ሀይማኖት ታሪካዊ ጠላቱ አድርጎ ማንፌስቶውን ቀርፆ ሲነሳ አላማው በትግራዋይ ዘንድ በተዛባ ትርክት የማታገያ ቁጭት መቀስቀስ እንጂ ለኦሮሞ ለአንድ ጎሳ ወይም ሃይማኖት ውግንና ስላለው አይደለም። ለአሸባሪው ህወሓት ስልጣኑን ተጥቅሞ በዘረፋ ካካበተው ሀብት ውጭ ወዳጅ የለውም ። ሀገር፣ ዜግነትና ጎሳም የለውም ።
ላለፉት 21 ዓመታት የቀን ሀሩር የሌሊት ቁር እየተፈራረቀበት፤ በቀበሮ ጉድጓድ የዕድሜውን ሲሶ ገብሮ ሲጠብቀው፤ በትግራይ ሕዝብ ደስታና ኀዘን ተካፋይ፤ በእርሻው በዘሩ በአረሙ በአጨዳውና በበራዩ እንዲሁም አንበጣን በመከላከል እንደ ቀንጃ ተለይቶት በማያውቀው፤ ከሬሽኑ እየቀነሰ ለልጆቹ ትምህርት ቤትና ጤና ተቋም ሲገነባ ፤ በኮቪድ 19 ለችግር ለተጋለጡ አሁንም ከእጅ ወዳፍ ከሆነች አበሉ ያካፈለ እሩህሩህና ለወገኑ ሟች የሆነ ሰራዊት በአረመኔውና ጉግማንጉጉ የትህነግ እፉኝት ቡድን ለማየት የሚዘገንንና ለመስማት የሚሰቀጥጥ ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ የፈጸመው አልተሳካለትም እንጂ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አቅዶና አልሞ እንጂ ከአማራ ጋር ጸብ አለኝ ብሎ አይደለም ።
መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲል ያወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም እንደ መልካም አጋጣሚ በመፍጠር በአፋር በኮረም በአበርገሌ(ዋግ ኽምራ)ና በወልቃይት ላይ ጥቃት የሰነዘርሁት በአማራ ላይ እንጂ ሌላውን አይመለከትም። ግጭቱም የትግራይና የአማራ ጉዳይ ብቻ ነው በማለት ለማደናገር እየሞከረ ነው። ሆኖም የዚህ አሸባሪ ስብስብ የግማሽ ክፍለ ዘመን የክህደትና የጸረ ኢትዮጵያ ታሪክ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተጨፈን ላሞኝህ እንደማለት የሚቆጠር ልግጫ ነው። በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት የፌዴራል መንግሥት አካል የሆኑ የአማራና የአፋር ክልሎችን ማጥቃት የፌዴራል መንግሥቱን እና ኢትዮጵያን ማጥቃት እንጂ የአንድ ወይም የሁለት ብሔር ጉዳይ አለመሆኑን ልቡ ያውቀዋል። ለዚህ ነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ፤ የኦሮሚያ የደቡብ የሶማሌ የሲዳማ የአፋር ወዘተረፈ ክልሎች ልዩ ኃይሎች ቀፎው እንደተነካ ንብ በአንድነት ሀገራቸውን ለማዳን የተመሙት። 10ሩ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በአንድነት ደጀንነታቸውን ያረጋገጡት።
በትህነግ / ኢህአዴግ ይመራ የነበረው አገዛዝ ስልጣን ላይ ለመቆየትና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲል ከትጥቅ ትግል ማንፌስቶው ጀምሮ የሸረበውን ሴራ በነፍጥ ወደስልጣን ከመጣ በኋላም ተቋማዊና መዋቅራዊ አድርጎ አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ልዩነትን፣ ጥላችን፣ ቂም በቀልን፣ ደባን፣ የታሪክ እስረኝነትን ሲጎነቁል፣ መሰሪነትን በተቋማትና በመዋቅሮቹ ሲዘረጋ መኖሩ ዛሬ ለምንገኝበት ሁለንተናዊ ቀውስ ተጠያቂ ያደርገዋል። ዛሬም ይህን የጨረታ ትዕምርቱን የሙጥኝ እንዳለ ነው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ተባባሪ ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ዳይሬክተር አበባው ይርጋ ፤ “ Ethnic Violence Challenging Ethiopian Universities “በሚል ርዕስ ለህትመት ባበቁት ወሽመጥ ቆራጭ ጥናታዊ ፁሑፋቸው ይሄንኑ ጥሬ ሀቅ ያረጋግጣሉ።“ የችግሩ ምንጭም ለ27 ዓመታት ስልጣን ላይ የቆየው ጎሳን መሰረት ያደረገው የፌዴራል ስርዓት እና ጎሳን ፖለቲካዊ politicization የማድረግ አባዜ ነው ።”
ይህን ያደረገው ደግሞ ለኢትዮጵያ ጎሳዎችና ብሔረሰቦች አስቦና ተጨንቆ ሳይሆን ስልጣን ላይ የመቆያው ብቸኛ ስልቱ ስለነበር ነው ።የኢሳቱ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ከኤርትራው ፕሬዚዳንት አይተ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ከአንድም ሁለት ፣ ሶስቴ ባደረገው የልብ ለልብ ጭውውት እና ሚስጥራዊ ሰነዶችን አገላብጦ የተረዳውን የምዕራባውያን ሚዲያዎች ከሰበር ዜና በላይ የሆነ ዜና ሲቀናቸው፤ አስገራሚ ፣ አስደንጋጫ ( bombshell ) የሚሉት አይነት ብዙዎችን ያነጋገረ ሚስጥር ከአንድ ዓመት ይፋ ባደረገው መረጃ፤ “የ87ቱ “ ሕገ መንግስት ! “ ከመፅደቁ በፊት የሽግግር መንግሥቱ የወቅቱ ፕሬዚዳንት መለስ ዜናዊ ረቂቁ የተጠናቀቀውን ሕገ መንግሥት ለአምላኩ ለአይተ ኢሳያስ አፈወርቂ ለማስባረክ ወደ አስመራ ያቀናል። አምላኩ ወዲ አፎም ረቂቁን ገለጥ ገለጥ ያደርግና በመገረም፣ በመደነቀ እየተመለከተው “ ይሄ እኮ ሀገሪቷን በጎሳ፣ በዘር ሊበታትን፣ ሊሸነሽን ሕዝቡንም ሊለያይ ይችላል … ! ? “ ብሎ ረቂቁን መልሶ ወደ ፊቱ ሲገፋለት ድንጉጡ መለስ፤ “ እንዲህ ካላደረግን ህወሓት በማዕከላዊ መንግሥት የበላይነትን ይዞ ስልጣን ላይ ሊቆይ አይችልም ። “ ብሎት እርፍ ፤ የሕገ መንግሥቱ ስውር ደባ እና አላማ የህወሓት የበላይነት ማስጠበቂያ እንጂ ይምልላቸውና ይገዘትላቸው ለነበሩ ጎሳዎች ጥቅም አልነበረም። አሸባሪው ህወሓት ከስልጣኑና ከዘረፋው ውጭ ኢትዮጵያ ብትፈርስ ብትበተን ጉዳዩ እንዳልሆነ ብናውቅም አሁን አሁን በአደባባይ አላማው ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደሆነ በድፍረት እየነገረን ከመሆኑ ባሻገር አማራንና አፋርን በማጥቃት ሀገሪቱን ለመበተን የተግባር እንቅስቃሴውን ካቆመበት ቀጥሏል ። ኢትዮጵያውያንም እንደ ጀግኖች አባቶቻቸውና እናቶች በቃ! ብለው ተነስተዋል ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር ! ! !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013