ስለሀገራቸው ፍቅር አውርተው አይጠግቡም። ክፉዋን ማየት ሳይሆን መስማት አይፈልጉም። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጉያዋ እቅፍ ውስጥ ሆነው ከግቷ እየጠቡ ማደጋቸውን ይናገራሉ። የእናትነት እና የልጅነት ፍቅራቸው ጽኑ ነው። በእርሷ መኖር እርሳቸው ኖረዋል፤ በእርሳቸው መኖርም እርሷ ኖራለች። ስለ ውለታዋ፤ ስለሰንደቅ ዓላማዋ ክብርና ፍቅር ሲሉ ወታደር ሆነው ተዋድቀውላታል። ደማቸውን አፍስሰውላታል፤ አጥንታቸውን ከስክሰውላታል።
ስለሉዓላዊነቷ ሲሉ አንድ እግራቸውን ማጣታቸው አኮራቸው እንጂ አላስቆጫቸውም። እግራቸውን ሳይሆን ነፍሳቸውን ሊሰጧት ቃል ገብተው የዘመቱ ወታደር ናቸው። ስለከፈሉት መስዋዕትነት የሚሰጣቸው የጡረታ ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ አይደንቃቸውም። እንደአቅማቸው ቸርችረው በመኖር ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል ያምናሉና። እርሳቸው የሚከፋቸው ኢትዮጵያ ሰላም ስታጣና ክብሯ ሲነካ ብቻ ነው። ለኢትዮጵያ ክብርና ነጻነት ሲሉ ብዙዎች ዋጋ መክፈላቸውን ይናገራሉ። የህዝቦች አንድነት ሲሸረሸርና የአባቶች ያደራ ቃል ዋጋ ሲያጣ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ውስጥ ሲወድቅ ማየት ለእርሳቸው ውርደት ነው።
ሰውየው ቆፍጣና ናቸው። ሰርቶ የማደር ስነልቦናቸው ከፍ ያለ ነው። በትንሿ ድባብ ስር ቁጭ ብለው አምስት ሺህ ብር የሚገመቱ የተለያዩ ሸቀጦቾን እየቸረቸሩ ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ። አቀራረቤ ሰርቶ የማደር ተሞክሯቸውን ያካፍሉኛል ብዬ ነበር፤ እርሻቸው ግን ከዋናው ጥያቄዬ እያፈነገጡ ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ማውራት በመፈለጋቸው ልጫናቸው አልፈለግኩም። በተቻለኝ መጠን የእርሳቸውንም የአምዱንም ጭብጥ አጣጥሜ ለማቅረብ የሞከርኩትን ጽሑፍ እነሆ ።
ወታደር ታደሰ ወልደጊዮርጊስ ይባላሉ። የስልሳ አራት ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው። ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ኳስ ሜዳ አካባቢ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት አቅራቢያ በሚገኘው አስር ሃዋሪያት ትምህርት ቤት ገብተው ፊደል መቁጠራቸውን ይናገራሉ። ለእናት ሀገራቸው ውለታ ለመክፈል ትምህርታቸውን ከስድስተኛ ክፍል አቋርጠው በ1963 ዓ.ም ውትድርና ይመዘገባሉ። የተመዘገቡት ኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ በፈጥኖ ደራሽነት ሲሆን ሃዋሳ ፖሊስ ማሰልጠኛ የመጀመሪያ ኮርሰኛ በመሆን ይሰለጥናሉ። ስልጠናቸውን እንደጨረሱ በቀድሞው ባሌ ክፍለ ሀገር ተመድበው መስራት ይጀምራሉ። በኤልከሬና በሌሎች ወረዳዎችም ለአምስት ዓመታት በመስራት የበረሃ ግዳጃቸውን ጨርሰው ወደ አርሲ ክፍለ ሀገር ይዛወራሉ። በወቅቱ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት እየተስፋፋ ሲመጣ ወታደር ታደሰም ከአዲስ ቅጥሮች ጋር አዋሽ አርባ ማሰልጠኛ ገብተው ከሰለጠኑ በኋላ በነበልባል ሰራዊት ውስጥ ታቅፈው ለሌላ ግዳጅ ወደ ኤርትራ መዝመታቸውን ይናገራሉ። ኤርትራ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ውስጥ ተሳትፈው ሀገራዊ አደራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።
በ1970 ዓ.ም እግራቸውን ቆስለው ጳውሎስ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ ይቆያሉ። በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያትም የግራ እግራቸው ከጉልታቸው በታች ይቆረጣል። የጉዳታቸው ደረጃ ታይቶ ወደ ጀግኖች አምባ እንዲገቡ ይደረጋል። ጡረታቸውም ይከበርላቸዋል። እዚያው እንዳሉ ሙያዊ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጎ መንግሥት ባመቻቸላቸው የሥራ እድል መሰረት ጥይት ፋብሪካ ውስጥ ተመድበው እንዲሰሩ ይደረጋል። ለአስራ አራት ዓመት በጥይት ፋብሪካዎች እየሰሩ ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ነበር። ኋላ ግን የኢህአዴግ መንግሥት ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ እርሳቸውና መሰል ጓደኞቻቸው ከሥራቸው እንዲሰናበቱ ይደረጋሉ። እስቲ ቀሪ ታሪካቸውን ከራሳቸው አንደበት እንረዳ።
‹‹ጥይት ፋብሪካ ውስጥ እስከ 1988 ዓ.ም ከሰራሁ በኋላ ምናልባት በታሪክ መንግሥት ሲባል እሰማለሁ፤ እኔ ግን መንግሥት የማልለው ወሮ በላ የወያኔ ቡድን ከሥራዬ አፈናቅሎኛል። በወቅቱ ከሥራ የተሰናበትነው ሁለት መቶ የምንሆን ሰዎች ነን። የወያኔ ሥራ አስፈጻሚዎች በሚያደርጉት መጥፎ ነገር ስሜታችን እየተነካ በስብሰባ ላይ እንናገር ነበር። ከምንናገረው እየተነሱ ማንነታችንን ከለዩ በኋላ መስሪያ ቤቱ በቦርድ ይተዳደራል በሚል የመዋቅር ማሻሻያ ይደረጋል አሉ። ከዚያም በርካታ ሰራተኞችን አስፈላጊ አይደላችሁም ብለው አሰናበቱን። እኛን ካሰናበቱ በኋላ ግን ቅጥር አወጣን ብለው የራሳቸውን ሰዎች ነበር የሰገሰጉበት።
ክስ መስርተን ስለመብታችን እየተሟገትን ከርመን ስንረታቸው መስሪያ ቤቱ ይግባኝ እያለ ጉዳዩን እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይወስደዋል። ለአስር ዓመት ያህል የተለያዩ የፍትህ ቢሮዎችን እያንኳኳን ብንከራከርም ከላይ በሚተላለፍ የፖለቲካ ውሳኔ ፍትህ ሳናገኝ ቀረን። በወቅቱ ካቀረብናቸው ጥያቄዎች ዋናው ከሥራ የተሰናበትነው ያለአግባብ በመሆኑ ወደ ስራችን እንመለስ የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የምንሰናበት ከሆነም የአገልግሎት ሂሳባችን በደሞዛችን ልክ ተሰልቶ ይሰጠን የሚል ነው። በመጨረሻ ግን ትንሽ ሳንቲም ጣል አደረጉብንና አሰናበቱን።
ይህ ብቻ አይደለም ቀደም ሲል የጦር ጉዳተኞችን የህክምና ወጪ የሚችለው መንግሥት ነበር። ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሄደን ካስጻፍን በኋላ ማንኛውም ድጋፍ ይደረግልን ነበር። ለምሳሌ አርቴፊሻል እግር የሚያሰራልን መንግሥት ነበር። ወያኔ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ግን ለሀገር ውለታ ያበረከቱ የቀድሞ የጦር ጉዳተኞች እንደጠላት ይታዩ ስለነበር ምንም አይነት ድጋፍ አይደረግላቸውም። ለጦር ጉዳተኛው ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት አስቁመው ለራሳቸው የወንበዴ ቡድን ብቻ ነበር ሁሉን የሚያደርጉት። እነርሱ ከመጡ በኋላ እኔም ማንኛውንም ነገር ጠይቄ ስለማላገኝ ትቼዋለሁ። አርቴፊሻል እግር መቀየር ስፈልግና ለሌላም የህክምና አገልግሎት በራሴ አቅም ለማድረግ እሞክራለሁ እንጂ የእነሱን አልጠብቅም።
ከሥራ ስሰናበት ምንም ነገር እጄ ላይ ስላልነበረኝ ሰማይ ተደፋብኝ። ቤተሰቤን በምን አስተዳድራለሁ ብዬ ግራ ተጋባሁ። ኋላ ግን አንድ ሰው የውጭ ዜጋ ቤት በጥበቃ ሰራተኝነት አስቀጠረኝ።
ፈረንጁ ሥራውን ጨርሶ ወደ ሀገሩ ሲገባ ባጠራቀምኳት ገንዘብ መነገድ ጀመርኩኝ። ትርፌን አላውቀውም እኔ የማውቀው እቃ እየገዛሁ መቸርቸሬን ብቻ ነው። ግን ኑሮዬን እያገዘኝ መሆኑን አውቃለሁ። ከዚህም ከዚያም በማገኛት ገንዘብ የወር አስቤዛዬን አንዴ እየገዛሁ መኖር ችያለሁ። ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ብዬም አልሰራም፤ ሰርቶ መግባቱ ብቻ የአዕምሮ ደስታ ይሰጠኛል›› ይላሉ ወታደር ታደሰ።
ወታደር ታደሰ የሚኖሩት ኤካ አያት ሁለት ኮንዶሚኒየም ሲሆን የሚሰሩት ስድስት ኪሎ ገንዘብ ሚኒስቴር አጥር ስር ነው። ሁልጊዜ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ሲሆን ከእቅልፋቸው ተነስተው ዝግጅታቸውን ከጨረሱ በኋላ ማልደው ወደ ስድስት ኪሎ ይገሰግሳሉ። ባለጎማዋን የእቃ መደርደሪያ ጋሪ ካደረችበት ቦታ እየገፉ መንገድ ዳር ያወጧትና ቀኑን ሙሉ ትንሿ ድባብ ስር ቁጭ ብለው ሲቸረችሩ ይውላሉ። ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን የእቃ መደርደሪያዋን ከሚያሳድሩበት ቤት አስገብተው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ። የሚኖሩበት አካባቢ ለትራስፖርት አስቸጋሪ በመሆኑ ቀደም ብሎ ከቤት መውጣት እና ቀደም ብሎ ከሥራ ቦታ ወደ ቤት መሄድ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሁኔታ ታዲያ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙበት እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
ወታደር ታደሰ ትዳር ከመሰረቱ ረጅም ዓመታትን አሳልፈዋል። በውትድርና ህይወት ውስጥ እያሉ ወደ አስመራ ከመዝመታቸው በፊት ነው ትዳር የያዙት። ሁለት ወንዶች ልጆችን አፍርተው ለቁም ነገር አብቅተዋል። የልጅ ልጅም ለማየት በቅተዋል። አሁን የሚኖሩት ከባለቤታቸው ጋር ነው። በወር የሚያገኙት የጡረታ ክፍያ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይገልጻሉ። ወር እስከ ወር ጥራጥሬ እየበሉ ለመኖር ቢያስቡ እንኳን የማይበቃ መሆኑን ይናገራሉ። ይህን አስቀድመው የተረዱት ቆፍጣና ወታደር ታዲያ እጃቸውን አጣጥፈው መቀመጥ አልፈለጉም። ኑሯቸውን አሸንፈው ለመኖር ይጥራሉ። ከዚያም ባሸገር ሥራ ሰርቶ መኖር የሚሰጠውን የህሊና እርካታ ለማጣጣም በቅተዋል። ሰርተው በማደራቸው ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዢ ፈጽመዋል። በዚህም ላይ ቀን በቀን በ8100 ሁለት ሁለት ብር ከሞባይላቸው ያስቆርጣሉ።
ስድስት ኪሎ ገንዘብ ሚኒስቴር አካባቢ ሰማያዊዋ ጥላ ስር ቁጭ ብለው እንደ ሶፍት፤ እስክሪፕቶ፣ ከረሜላ፣ ማስቲካ፣ ሲጋራ፣ የሞባይል ካርድ ወዘተ የሚሸጡት ታታሪ ሰው በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ይታወቃሉ። አላፊ አግዳሚው ደንበኛቸው ነው። ወታደር ታደሰ ማንኛውም ሰው በሥራ ላይ ከተሰማራ መኖር እንደሚችል ያምናሉ። አሁን እዚህ ሀገር ላይ የጠፋው በተለይም ወጣቱን ከሥራ ጋር የሚያስተሳስር እድል ያለመኖሩ እንደሆነ ይናገራሉ።
ወጣቱ ሱሰኛ እንዲሆንና ጊዜውን በአልባሌ ነገሮች እንዲያጠፋ 27 ዓመት ሙሉ ሲሰራ ነበር ይላሉ። ወጣቱ ሰርቶ የማደር ፍላጎት እንዳለውና በርካታ የሥራ እድሎችን መፍጠር እንደሚችል ያምናሉ። እንደእርሳቸው አባባል የወያኔ ወሮበላ ቡድን የወጣቱን ሞራል በማላሸቅ ጠያቂና ተቆርቋሪ ትውልድ እንዳይኖር አድርጓል። ‹‹ወጣቱን ካኮላሸነው ለሀገር የሚታገል ማንም አይኖርም እንደፈለግን እንዘርፋለን›› የሚል ስልት ነድፎ ሲሰራ ነበር ይላሉ።
የወያኔ ዘራፊዎች ቡድን እንኳን ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያስቡ ይቅርና በራሳቸው ሰዎች ደም ሳይቀር የሚነግዱ ናቸው። ኢትዮጵያ ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ እንድትደርስ ያደረጋትም የእነርሱ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ነው ይላሉ። በተረፈ ግን ኢትዮጵያ ከማንኛውም ሀገር የተሻለ የተፈጥሮ ሃብትና ጸጋ ያላት ሰርቶ ለመኖር የሚያስችል ምቹ የአየር ንብረት ያላት ሀገር ነች ይላሉ። ወታደር ታደሰ ንግግራቸውን ቀጥለዋል፤ እኔም በትኩረት እያዳመጥኳቸው ነው።
‹‹እኔ ስለኑሮዬ መጓደል አልጨነቅም። የማስበው ስለ ሀገሬ ነው። መንግሥት በሀገር ሰላምና ደህንነት ላይ ከማንም ጋር መደራደር የለበትም። በህወሓት አሸባሪ ላይ የተወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻም የረፈደ ይመስለኛል። መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተረባርቦ የሀገሩን ሰላም ማስከር እንዳለበት ይሰማኛል። የቆሰልኩላት ሀገሬ ዛሬ ህልውናዋ አስግቶኛል። ወጣቱ ከለውጥ ኃይሉ ጋር ተሰልፎ የሀገሩን ሰላም በማስከበር የኢትዮጵያን ህልውና ማረጋገጥ ይኖርበታል። ከዚያ በኋላ ነው ሰርቶ መኖር የሚቻለው።
ኢትዮጵያውያን ዜጎቻችን አሜሪካ ሀገር ሄደው ሰርተው መኖራቸው ደስ ቢለኝም አሜሪካ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከቆሙ አካላት ጋር መተባበሯ ያናድደኛል። አሜሪካ ለወያኔ የምትወግነው ተንበርክክው ስለሚገዙላትና ስለሚላላኳት ነው እንጂ ፈልጋቸው አይደለም። ኢትዮጵያ ካደገች ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እርሷን አይተው እንደሚነሱ ስለሚያውቁም ነው። ወያኔ ለእጅ አዙር ቀኝ አገዛዝ ስለሚመቻቸው ነው የሚፈልጉት።
“ወታደር የህዝብ አለኝታ፤ የሀገር መከታ ነው። ከራሱ በፊት የሀገሩንና የህዝብን ጥቅም ያስቀድማል፤ መልሶ በራሱ ህዝብ ሲጠቃ ማየት ያሳዝናል። በሰሜን ዕዝ ወታደሮች ላይ የተፈጸመውን ክህደት የምገልጽበት ቃላት የለኝም። 20 ዓመት ሙሉ ሰላማቸውን እየጠበቀ፣ እያረሰ፣ እያጨደ፣ ከደመወዙ እየቆረጠ ትምህርት ቤት እየገነባ ሲረዳቸው በነበረ ሰራዊት ላይ የፈጸሙበት በደል በጣም ያንገበግበኛል።” በማለት አስተያዬት ሰጥተዋል።
“ለዚህ ነው ከኑሮዬ በላይ ስለ ሀገሬ ጉዳይ የምጨነቀው፤ ሀገሬ ለእኔ እናቴ ነች። ሀገሬ ብዙ ጸጋ አላት፤ ይህንን ጸጋ ተጠቅሞ መለወጥ አለመቻላችን ያስቆጫል፣” ይላሉ ወታደር ታደሰ። ለዛሬ የወታደሩ ጽናትና የሀገር ፍቅር በሁላችንም ላይ እንዲጋባ በመመኘት ልሰናበት። ሳምንት ሌላ ባለታሪክ ይዤ እመጣለሁ። እስከዚያው ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2013