የአሸባሪው የህወሓት ግፍ፣ ጭካኔና አረመኔያዊ ተግባሩ ገደቡን ጥሶ ይፋ ከወጣ ሰነባብቷል። ከዕለት ዕለት የሚሰማውና የሚስተዋለው የዚህ ቡድን የክፋት ልክ በመጠንም ይሁን በዓይነት በዝቶና ገዝፎ በመፋፋቱ ለመስማትም ሆነ ተረጋግቶ ለማሰብ እስከሚያዳግት ድረስ ከህሊናችን ጋር እንድንሟገት ሰቅዞ ይዞናል።
ጠብመንጃ ነክሶ ከማለበት አንደበቱ የሚወነጨፉት የውሸትና የፈጠራ ቅጥፈቶችና ደም ባሰከረው ስብእና ቀልብያውን ስቶ በጨካኝ ጣቶቹ የሚስበው ቃታ የሺህ ንጹሐንን ደም በማፍሰስ የቆሌውን ሱስ በማርካት ላይ ይገኛል። በዚህም ብቻ ሳይወሰን ሽቅብ ተንጠራርቶ በሀገራዊ የሉዓላዊነታችን ሩሕ ላይ ጭምር ተጠናክሮ ሴራውን በማስወንጨፍ በሰላማችን ላይ ስለዘመተ የውሎ አምሽቷችን ክፉ መርዶ መራር እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።
የዚህ አሸባሪ ቡድን የክፋት ጭካኔ እንዲህ ነው ተብሎ ለመተንተን በሚያስቸግሩ ክስተቶች የተሞላ ስለሆነ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ለማመን እስከሚያዳግት ድረስ በየማለዳው የሚሰሙት አሰቃቂ ድርጊቶቹ የማንነቱን ልክ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ አጠናክሮ በከፈተው የግልጽ ወረራ ዐውደ ውጊያ ላይ ከፊት ለፊት ያሰለፋቸውን “ጡት ያልጠገቡ ሕጻናት” እና ታዳጊ ልጆችን ጉዳይ አስመልክቶ “የእኛ” የሚሏቸው ዓለም አቀፋዊ የሚዲያ ተቋማት ሳይቀሩ እየተቀባበሉ በማስተጋባት የቡድኑን የጭካኔ ተግባሮች በይፋ እየገለጡ ይገኛሉ።
በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትና በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን ድንጋጌዎች ውስጥ ሕጻናትን ለጦርነት መልምሎ ውጊያ ላይ ማሰለፍም ሆነ በጦርነት የተጠመዱ ተዋጊ ኃይሎችን እንዲያገለግሉ ማሠማራት በጦር ወንጀለኝነት እንደሚያስፈርጅ በግልጽ ተመልክቷል። ሀገራችንን ጨምሮ በርካታ የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊ ወጣቶችን በጦርነት ቀጣና ውስጥ ለውጊያ ማሰለፍ እንደማይገባ ተማምነው ስምምነታቸውን በፊርማቸው ይሁንታ ማረጋገጥ ብቻም ሳይሆን ለተግባራዊነቱም ተግተው እየሰሩ ይገኛሉ።
ተሻሽሎ ሥራ ላይ የዋለው የጄኔቫ ኮንቬንሽንም (Convention on the Rights of the Child and the Additional Protocols to the Geneva Conventions) እንዲሁ “ሕጻን ወታደሮች” በማለት የሚገልጻቸውና ዕድሜያቸው ከ15 በታች የሆኑ ታዳጊዎች የግድ በጦር ሜዳ መካከል ተገኝተው ቃታ እየሳቡ ስለሚዋጉ ብቻ ሳይሆን በዐውደ ግንባር እየተገኙም ቢሆን ለጦር ሠራዊቱ አባላት በመላላክና በማገልገል የሚሳተፉ ከሆነም ጠብመንጃ አንግበው ከሚዋጉት እኩል “ወታደር” እንደሚባሉ በዝርዝር ይገልጻል። ተፈጽሞ ቢገኝም የሚፈረጀው በጦር ወንጀለኝነት ነው።
አፍሪካዊያን ያጸደቁት የሕጻናት መብትንና ደህንነትን የሚደነግገው ቻርተርም (እ.ኤ.አ 1999 ዓ.ም) እንዲሁ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ለእርስ በእርስ ግጭቶችም ሆነ ለመደበኛ ጦርነቶች እንዳይመለመሉና በግጭቶች መካከልም እንዳይገኙ አስረግጦ ያሳስባል።
ራሳቸውን “የሰብዓዊ መብቶች መፍለቂያ ምንጭ” አድርገው እስከ መቁጠር የደረሱትና በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ገብተን ካልፈተፈትን እያሉ ጤና የሚነሱን እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት “ከመቆርቆርም አልፈው እንሞትለታለን” እያሉ በሚዲያ ተቋሞቻቸው ብቻም ሳይሆን በወሳኝ የፖለቲካ ጉባዔዎቻቸው ሳይቀር ስለ ሕጻናት መብቶች የሚለፍፉትን እውነታ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲቃረኑ ይስተዋላል። ለአብነት ያህልም ኖቬምበር 20 ቀን 1989 ዓ.ም በ194 የዓለም ሀገራት በመጽደቁ “Human rights treaty in history – with 194 countries as “states parties” ተብሎ አድናቆት የተዥጎደጎለትን (Convention on the Rights of the Child) በመባል የሚታወቀውን ስምምነት ሶማሊያንና ደቡብ ሱዳንን በማስተባበር ዛሬም ድረስ አልፈርምም ካሉ ሀገራት አንዷና ቀዳሚዋ ይህቺው አሜሪካ ተብዬዋ ነች። ለእምቢታዋ መሸፈኛ እንደ ድብቅ አጀንዳ የሰወረችውን ምክንያት በተመለከተ እ.ኤ.አ በ2014 “Child labor in US tobacco fields” በሚል ርዕስ የተሰራ አንድ የጥናት ጽሑፍ አጋልጧል።
ስለ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ዋነኛ ጠበቃ እንደሆነች ራሷ ለራሷ አምና ለተቀረው የዓለም ሕዝብም በኃይልም ይሁን በማግባባት “እመኑኝ” እያለች በጡንቻዋ፣ በዶላር ልግስናዋና በማግባባት ዘመቻ “ከእኔ ወዲያ ላሳር” በማለት ሀገራትን የምታስፈራራው አሜሪካ በሌሎች ሀገራት ጉዳይ ጣልቃ ካልገባሁ እያለች ኡኡታ የምታሰማው እያሳረራት ላለው የቤቷ ጉድ መፍትሔ ለመስጠት እንኳን እየተቸገረች መሆኑን ሁላችንም የምናውቀው “ፀሐይ የሞቀው” እውነት ነው።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን 10 ኪሎ ግራም ያህል የሚከብደውን፣ ሙሉ አውቶማቲክ የሆነውንና በደቂቃ እስከ 600 ጥይቶችን የሚተፋውን AK-47 በመባል የሚታወቀውን የክላሽንኮቭ ጠብመንጃና ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ምስኪን ሕጻናቱን በማሸከም ጦርነት ውስጥ የሚማግዳቸው ምን ያህል ርህራሄ ቢስ እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ነው። የመማሪያ ቁሳቁሳቸውን እንኳን በወጉ ለመሸከም የሚንገዳገዱት እኒህን መሰል ሕጻናት ከፊት ለፊት አሰልፎ እንደ ጋሻ መጠቀሙ የዘቀጠውን ዓላማ ቢስነቱንና የጭካኔውን ከፍታ አጉልቶ የሚመሰክር ነው።
ይህንን ያፈጠጠ እውነታ የሚያስተውሉት አንዳንድ ሀገራት ይህን መሰሉ የዘቀጠ የአሸባሪው ድርጊት እንዲገታ ከማገዝ ይልቅ እውነቱን ላለማየት ዓይናቸውን አሳውረው፣ ላለመስማትም ጆሯቸውን አደንቁረው አጀንዳ እየፈበረኩና እየለዋወጡ አንዴ በህዳሴ ግድብ፣ አንዴ በሰብዓዊ መብቶች አተገባበር ወዘተ. እያመካኙ “የግር እሳት” ሆነውብናል።
ከጉያው እየተነጠቁ ለዚህ አሸባሪ ቡድን በጋሻነት እንዲያገለግሉ የሚመለመሉትን ታዳጊ ልጆቹን በተመለከተ መላው የትግራይ ሕዝብ በተባበረ ድምጽ እምቢታውን ከመግለጽ ይልቅ ሰምቶ እንዳልሰማ በዝምታ ማለፉ “ከዚህ የከፋ ምን የጭካኔ ተግባር እስኪፈጸም” እየጠበቀ ነው ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። እነዚህ ብላቴኖች ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ከታጠቀና ከሰለጠነ ሠራዊት ጋር ገጥመውስ ምን ውጤት ሊያስገኙ ይችላሉ በማለትም እንሞግታለን።
በእጅጉ የሚያሳዝነውና የአሸባሪ ቡድኑ መሪዎች ይሉኝታ ቢስነት ከጭካኔ ጋር ከሚገለጽባቸው ተግባሮች መካከል አንዱ የድሃውን የትግራይ ሕዝብ ልጆች ለጦርነት እየማገዱ የእነርሱን ልጆች ግን በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ እያንደላቀቁ ማኖራቸውና ማስተማራቸው ነው። ይህንን እውነታ አደባባይ አስጥቶ እርቃኑን ከማስቀረት ይልቅ በአንዳንድ “አክቲቪስት ተብዬ” የራሱ ልጆች የትግራይ ሕዝብ መደነጋገሩና ግራ መጋባቱ ሌላው የእንቆቅልሹ ምሥጢር ነው።
ለትግራይ ሕዝብ ወዳጅ በመምሰል “እሳቱን እያራገቡ” ለአሸባሪው ቡድን የልብ ልብ የሚሰጡ “ቅጥር ሆድ አደር” ህሊና ቢስ የአንዳንድ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞችና በተራድኦ ድርጅት ሠራተኛነት ስም በደም የሚነግዱ መሰሪዎች ድብቅ ዓላማም ከጊዜ ወደ ጊዜ ገሃድ እየወጣ ስለመጣ ሕዝቡ ቆም ብሎ የጥሞና ጊዜውን በአግባቡ ቢጠቀምበት የሚበጅ ይመስለናል። ምንም የማያውቁና ለምን ዓላማ የእኩያን ጋሻ እንደሆኑ እንኳን ተገቢው እውቀት የሌላቸው ሕጻናት ልጆቹን እንደ አረር እየተጠቀሙ “በትራዤዲ ተውኔት” መፈንጠዝ ዞሮ ዞሮ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም።
ጉዳዩ በሕጻናት ጋሻነት ብቻ የተገደበ ሳይሆን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አረጋዊያን፣ በሃይማኖት ከለላ ስር ራሳቸውን የሸፈኑ አንዳንድ አዛውንቶችና ጎልማሶች የአሸባሪው ተባባሪ በመሆን በጦርነቱ ዐውደ ግንባር ላይ ፊት ፊት በመምራት ወይንም ቀድሞ በመጋፈጥ ስለሚከፍሉት ያልተገባ መስዋዕትነት ቆም ብለው ከህሊናቸውና ከታሪካቸው ጋር ሊመክሩ ይገባ ይመስለናል።
አሸባሪው ህወሓት ጠላትነቱ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ቆሜለታለሁ ለሚለው የትግራይ ሕዝብም ጭምር መሆኑን ደጋግሞ በተግባሩ አስመስክሯል። በሕዝቡ ጥላ ስር ተወሽቀው የሚንፈራገጡት የአሸባሪው ርዝራዦችም ሆኑ በተለያዩ ሀገራት አውራ ጎዳናዎችና አደባባዮች ላይ ነጋ ጠባ ሰልፍ መውጣትን የዕለት ተግባር ያደረጉ ዓላማ ቢሶች በምላሳቸውና በመፈክራቸው ለትግራይ ሕዝብ አንዳችም ፋይዳ ሊፈጽሙ እንደማይችሉም ደጋግሞ ተረጋግጧል።
እስከ መቼ የትግራይ ሕዝብ እንዳለቀሰና ልጆቹን ለተሳሳተ ዓላማ እንደገበረ ዘመኑን ይፈጃል? እስከ መቼስ በተራድኦ ድርጅቶች ዳረጎት ዘመኑን ይገፋል? እስከ መቼስ ክልሉ ዛላው ያማረ አዝመራ ሳይሆን ሞት የተደገሰበት የአረር ቀለህ ከምድሩ ላይ እያመረተ ይኖራል? ቆም ብሎ ለማሰብ ምራቅ የዋጡ አባቶች፣ ዕድሜና ታሪክ ያስተማራቸው አዛውንቶች፣ በዓላማ ቢስ መስዋዕትነት ወጥተው የቀሩ ልጆቻቸውን እያስታወሱ በሀዘን የሚማቅቁ እናቶችና ወጣቶች ተሰባስበውና መክረው ከዚህ እኩይ አሸባሪ ቡድን አፈና ነጻ ለመውጣት ጨክነው ለምን ሊታገሉ አልፈቀዱም?
ዛሬ እንደ ዕለት ክስተት የምንቆጥረው የአሸባሪ ቡድኑ ድርጊት ነገ ታሪክ ሆኖ ለመፃኢው ትውልድ ሲቀርብ ምን ሊባል እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም። እናቶች አልነበሩም ወይ? የሃይማኖት መሪዎችና ምሁራንስ ምን ብለው ነበር? አዛውንቶች ምን መክረው ምን ወሰኑ? እየተባለ መጠየቁ ስለማይቀር ዛሬ ወደ ህሊና ተመልሶ ይህንን የአሸባሪውን ቡድን ተልዕኮ ማክሸፍ ለትግራይ ሕዝብ የውዴታ ግዴታ እንደሆነ ሊታመን ይገባል። ሰላም ይሁን !
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2013