የዛሬው የዘመን እንግዳችን የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ጉዳይ እና የሃገራቸውን ጥቅም ለማስከበር በአለም አደባባይ ቆመው ከሚሞግቱ ምሁራን መካካል አንዱ ናቸው። በተለይም ዲጂታል የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ያለማንም ቀስቃሽነትና አስገዳጅነት በራሳቸው ተነሳሽነት የአረቡን አለም ሴራ በማጋለጥ ረገድ አሻራቸውን እያሳረፉ ያሉ ብርቱ ሰው ስለመሆናቸው ይነሳል። እንግዳችን ውልደታቸው ምንም እንኳን አርባ ምንጭ ከተማ ቢሆንም ገና የአንድ አመት እምቦቀቅላ ሳሉ ነበር በመምህራን ወላጆቻቸው የሥራ ጠባይ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ የመጡት። አንደኛ ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አፄ ዘርአያቆብ እና አብዮት ቅርስ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በመሬት ሃብት አጠቃቀምና አካባቢ ጥበቃ ትምህርት ክፍል ገብተውም በደን ልማት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ሴቭ. ዘ ችልድረን በተባለ የተራድኦ ድርጅት ውስጥ በመቀጠር አፋር ክልል ላይ መስራት ጀመሩ። ብዙም ሳይቆዩ ኤስ. ኦ. ኤስ ሳህል በተባለ አለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ አማካሪና ተመራማሪ ሆነው አርብቶአደሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን አከናወኑ። በተለይም በርካታ ጥናቶችን የሰሩት እኚሁ ሰው በአርብቶ አደር አካባቢ የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ምርምሮችን በማካሄድ ለመንግስትና መንግስታዊ የፖሊሲ ግብዓት ማቅረብ ስለመቻላቸው ይነገራል። በመቀጠልም ዲግሪያቸውን ወደ ተማሩበት መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በመመለስ ለአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ አስተማሩ። ይሁንና ብዙም ሳይቆዩ ጃፓን ሀገር የመሰልጠን እድሉን አገኙ። ለጥቂት ወራት ብቻ ይሰጥ በነበረው በዚሁ ስልጠና ታዲያ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች እንዲሁም አርብቶአደሮች አካባቢ የግጦሽ መሬት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችል ጥናት አከናወኑ። ይህም ጥናታቸው በመምህሮቻቸው ከፍተኛ ተቀባይነት አስገኘላቸው። በዚህም ምክንያት እዛው ጃፓን ሀገር በሚገኘው ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ተወዳድረው የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በአንድ ላይ የሚሰሩበትን እድል አገኙ። በኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ የኤዢያ አፍሪካ አካባቢ ጥናት የሚባል ትምህርት ክፍል ገብተውም በሀመር ህብረተሰብ ባህል፣ ቋንቋ እንዲሁም የግጦሽ መሬት አጠቃቀም ላይ መሰረት ያደረገ ጥናት በማድረግ ከፍተኛ እውቅና ማግኘት ቻሉ። ይኸው ጥናታቸው ታዲያ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ በመፅሃፍ ለመታተም ችሏል።
ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ግብርና ሚኒስቴር አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶአደሮች ዙሪያ ከጂ.ቲ.ዜድ እና ከኦክስፋም ጋር በቅንጅት በሚሰራ ፓይለት ፕሮጀክት ሽንሌ እና ጭፍራ በተባሉ ስፍራዎች ተመድበው መስራት ጀመሩ። ይሁንና ጥቂት እንደሰሩ ከባድ ድርቅ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቱ ተቋረጠ። በዚህም ምክንያት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው አፍሪካን ስተዲስ በተባለ ትምህርት ክፍል ውስጥ በመምህርነት ተቀጥረው ማገልገል ጀመሩ። ይህ ትምህርት ክፍልም የቀድሞ ‹‹አፍሪካ ኦሬንታል ምርምር ማዕከል›› የሚለው ስያሜው ወደ ‹‹የአፍሪካና ኤዢያ ጥናትና ምርምር ማዕከል›› በሚል እንዲቀየር እና የዶክትሬት መርሃ ግብሩ እንዲቀረፅ በማድረግ በኩልም የበኩላቸውን ሚና ተወጥቷል። በመቀጠልም በተቋሙ የማህበረሰብ ሳይንስ ኮሌጅ የጥናትና ምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍል ተባባሪ ዲን ሆነው መስራት ጀመሩ። በዚያው ትምህርት ክፍል እያሉ ከውሃና መሬት አያያዝ ጋር የተገናኙ የተለያዩ ፅሁፎችን መፃፍ ችለዋል።
እንግዳችን ምንም እንኳን የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ቢሆኑም ለማህበራባዊ ሳይንስም ከፍተኛ ፍቅር አላቸው። በተለይም ለኪነጥበብና ጋዜጠኝነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጡት እኚሁ ሰው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተሰጥኦአቸውን ማውጣት የሚችሉበትን እድል ይጠቀማሉ። በተለይም ከአባይ ወንዝ እና ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚያሳትመው ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ላይ በተነሳሽነት በሚፅፏቸው ፅሁፎች ከፍተኛ እውቅናን ማግኘት ችለዋል። ይህንን ተከትሎም እንደአልጀዚራ ባሉ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ እየተጋበዙ በአባይና በግድቡ ዙሪያ ትንታኔ በመስጠትም የሀገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ይህንን የግል ጥረታቸውን ያዩት የሠላም ሚኒስትሯም ተቋሙን እንዲያግዙ ጥሪያ ያቀርቡላቸዋል። ይህንን ጥሪ ተቀብለውም ካለፈው አመት ጀምሮ ከማስተማሩ ስራቸው ጎን ለጎን ሚኒስቴሩን በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በማማከር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ከዛሬው የዘመን እንግዳችን ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– አሁን አሁን አገራት መንግስት ለመንግስት ከሚያደርጉት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በላቀ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ስራ የበለጠ አዋጭ እየሆነ መጥቷል። እስቲ ስለ ዲጂታል ዲፕሎማሲ ምንነት እና ጠቀሜታው ይንገሩንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– እንደሚታወቀው አለም እየሰለጠነች፣ ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ እና ዘመናዊ የህይወት አኗኗር ዘይቤ ወደ ሁላችንም ቤት እየደረሰ በመጣ ቁጥር ወረቀት ላይ ብቻ የተመሰረቱ ስራዎቻችን እየተቀየሩ መጥተዋል። ዲጂታል የተባለው የመገናኛ ዘዴ ከተለመዱት የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች በተጨማሪ ሰዎችን በደንብና በቀላሉ በአጭር ጊዜ መድረስ የሚያስችል ነው። ይህ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተው ዲፕሎማሲ አገራት በበይነ-መረብ አማካኝነት ከአለም ጋር በሰኮንዶች ሽርፍራፊ መድረስ የሚችሉበት ነው። በበይነ-መረብ አማካኝነት ምልክት ማስተላለፍ የሚቻልበት ይበልጥ እየተስፋፋ መልካሙም ሆነ አሉታዊ ጎን በብዙ ሰዎች ዘንድ በቀላሉ የሚደርስበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ስለዚህ ዲፕሎማሲው በዚያው ልክ ራሱን ማዘመን አለበት የሚል እምነት አለኝ። ከተለመደው የዲፖሎማሲ ስራ ባሻገር ዲጂታል ዲፕሎማሲ ስርዓትን መዘርጋት ከተቻለ መንግስታትንም በስራቸው የሚመሯቸውን ህዝቦችንም ሆነ የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደርና በቀላሉ መድረስ ያስችላቸዋል።
አሁን ላይ በአካል ከሚደረገው ግብይት በላይ የዲጂታል ግብይቱ የበለጠ አዋጭ እየሆነ እንደመጣው ሁሉ ዲፕሎማሲውንም በአካል በመገኘት ከማስረዳት በላይ በየቀኑ ሰው ከያለበት ሆኖ አስፈላጊውን መረጃ ለማድረስ የሚያስችልና ተጠቃሚ የማድረግ ዘዴ ነው። ብዙ ሀገራት በዚህ ዘዴ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ያሉት። በእኛም ሀገር በመደበኛ መልኩ የሚካሄደውና የፀናው አቋማችን እንዳለ ሆኖ ከአገራት ጋር ባለን ግንኙነት በተለየ መንገድ ሃሳባችንና ፍላጎታችንን የምናደርስበት ዘዴ ያስፈልገናል። በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ህዝብ እድሜው በወጣትነት ውስጥ ያለ እንደመሆኑ ይህንን የህብረተሰብ ክፍል መድረስ የሚያስችለን የተለየ አሰራር መከተል ይጠይቀናል። የአለም ኢኮኖሚንም ደግሞ ቅርፅ እያስያዙ ያሉት ወጣቶች ናቸው። ለምሳሌ የአረብ ስፕሪንግም ሆነ በአለም ላይ የተከሰቱ ውጤታማ ተቋውሞዎችና ድጋፎችን ብታዪ ብዙዎቹ በወጣቶች ጭንቅላት ውስጥ የሚፈልቁ ናቸው። ምንአልባት በሌላው ሰው ግፊት ቢገቡም እንኳን ተቀብለው የሚስፈፅሙት ወጣቶች ናቸው። ስለዚህ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር መድረስ የሚቻለው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ነው።
እንዳልኩሽ እነዚህ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘዴዎች መልካምም ሆነ መጥፎ መረጃዎችን በቀላሉና በፍጥነት የሚያሰራጩ ናቸው። በመልካም ጎን ለመጠቀም ከምትቺያቸው ነገሮች አንዱ ደግሞ የሀገርሽን ብሄራዊ ጥቅምና ፍላጎት የምታንፀባርቂበት ዘዴ ነው። አሁን ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየሞከረ ያለው ነገር አለ። ነገር ግን አብዛኞቹ ሰዎች በግል ተነሳሽነት ነው የአገራቸውን ጥቅም ያስጠበቀ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ስራ እየሰሩ ያሉት። በተለይ ከአባይ ወንዝና ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በግለሰቦች የሚደረጉ የበይነ-መረብ እንቅስቃሴዎች በተደራጀ መልኩ የሚደረጉ አይደሉም። ለምሳሌ እኔ ብቻዬን ነው የምሰራው። አልጀዚራ ላይ ሄጄ የምከራከረው ደግሞ ከአል ሲሲ አማካሪዎች ጋር ነው። ብዙ ሰው ግን የኢትዮጵያ መንግስት ወክዬ የምናገር ነው የሚመስለው። ግን እኔ ይሆናል ብዬ የማምንበት ጉዳይ ይዤ ከምከራከር ይልቅ መንግስት በተቀናጀ መልኩ ቢሰራው ኖሮ ምን ያህል ውጤት ሊመጣ እንደሚችል ማሰቡ አይከብድም። በነገራችን ላይ ይህ የክርክር ሂደት በበይነ-መረብ በተደጋጋሚ ከሚያየው ውጭ በአንድ ጊዜ 10 ሚሊዮን ሰው ነው የሚከታተለው። ስለዚህ ይህንን እድል እኛ አልተጠቀምንበትም። በዛ ላይ በተናጠል የሚደረገው ነገር በቀጥታ ነጥቡ ላይ ትኩረት በማድረግ የአገርን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ላይሆን ይችላል።
በመሆኑም መንግስት እንደዚህ አይነት የመገናኛ ዘዴዎችን ቢጠቀም የበለጠ ሃሳቡን መግለፅ ይችላል። በክብ ጠረጴዛና በመደበኛ ሚዲያዎች የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርግ ሁሉንም ህዝብ ተደራሽ ማድረግ አይችልም። እንደዛም ሆኖ በፈለጉት መልኩ ሀሳቡን እየተረጎሙ የሚቀርብበት እድል በመሆኑ የተዛባ መረጃ የሚደርስበት እድል ሰፊ ነው። ስለዚህ በዚህ መልኩ የሚመጣብንን ጫና ማፍረስ የሚችለው የዲጂታል ዘዴዎችን በመጠቀም ህዝቡ ጋር መድረስ ሲችል ነው። በነገራችን ላይ በዚህ ዘዴ የምንጠቀመው ሰዎች ምንም እንኳን ጥቂት ብንሆንም ብዙ አረቦችን መድረስ አስችሎናል ብዬ አምናለሁኝ። አሁን ላይ ስለአባይ ያላቸውን አመለካከት በጥቂቱም ቢሆን መቀየር እየቻልን ነው። አብዛኞቹ አረቦች እኮ አባይ ከአስዋን የሚመነጭ ነው የሚመስላቸው። መሪዎቹ ሆን ብለው የህዝቡን አመለካከት ቢያበላሹትም እኛ ህዝቡ ጋር በዲጂታል መንገድ በደረስን ቁጥር ያንን የተዛባ አመለካከት እየቀየርን እንመጣለን። ሙሉ ለሙሉ የእኛን ሃሳብ ባይቀበሉት እንኳን ቢያንስ ቢያንስ እውነታውን ላማጣራት ጥረት ያደርጋሉ። ይህም የተሻለ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል። በአጠቃላይ በመደበኛ ሚዲያው ብቻ ሲደረግ የነበረው የዲፕሎማሲ ጥረት የሚደግፍ ስራ ለመስራት ያስችላል። ዲጂታል ዲፕሎማሲ ስራ ከነባሩ አካሄድ ጋር ስታነፃፅሪው ጊዜም፤ ወጪም ቆጣቢ ነው። ደግሞ በአንድ ጊዜ ሚሊዮኖችን ተደራሽ ማድረግ የምትቺይበትን እድል ይሰጣል።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ አንፃር ግብፅና ሱዳን ይህንን የመገናኛ ዘዴ ምን ያህል ተጠቅመውበታል ማለት ይቻላል?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– ከዚህ ይልቅ እኛ ለምን ወደኋላ ቀረን? ብለሽ ብትጠይቂኝ ደስ ይለኝ ነበር። እኛ ሁልጊዜም ወደ ኋላ የቀረን ነን። ለነገሮች ዋጋ አንሰጥም። ስለዚህ እንደምታይው የሃሰት ትርክት ተወልዶ ቆሞ መሄድ ከጀመረ በኋላ ነው ያንን ታሪክ ለማጥፋት ጥረት የምናደርገው። አሁን ያለንበት ጊዜ በነበረው አካሄድ መቀጠል አላስቻለንም። ቸልተኝነታችን ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው ያለው። ለምሳሌ ‹‹ኢንተር-አክቲቭ›› በሚባለው የግብፅ ኩባንያ አማካኝነት የኢትዮጵያን መንግስት የሚቃወሙና የሚሰራቸውን ስራዎች የሚፃረሩ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ቲዊቶችን፣ የፌስቡክ መልዕክቶችን ያስተላልፋል። በዚህ ድርጅት አማካኝነት ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ሃሰተኛ መረጃ በመርጨት ኢትዮጵያውያን እንዲከፋፈሉ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ስራ ሲሰሩ ነበር። ተደርሶባቸው እስከሚዘጋ ድረስ በሀገራችን ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ሲፈጥሩ ነበር። እኛ ይህንን እንኳን ቶሎ ደርሰን ማስቆም አልቻልንም ነበር። ፌስቡክ ነው ያስቆመው። ስለዚህ ይህ ሁኔታ እኛ የምንከተለው መንገድ ምንያህል ደካማ እንደሆነ ነው የሚሳይሽ። እርግጥ ነው፤ መንግስትም ሆነ አንዳንድ ሀገር ወዳዶች በተናጠል ይህንን ሃሰተኛ መረጃ የማጋለጥ ስራ ይሰራሉ። ግን ደግሞ መንግሰት በተቀናጀ መልኩ የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ የሚጎዱ ሰዎችን የማጋለጡ ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ለምሳሌ የደህንነት ስራውን ከዚያ ጋር ማቀናጀትና ማስቆም ያስፈልጋል። ልክ እንደ እነሱ ሁሉ መደላደሎችን በመፍጠር እውነተኛ ሃሳቦችን ይዘን ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልገናል። በተለይም የአባይን ውሃ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ መጠቀም የምንችልበትን መንገድ መፍጠርም ተገቢ ነው። ይህም ማለት እሳቱን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ከዚህ በኋላ እሳቱ ዳግም እንዳይነሳ የማድረግ ስራ መስራት መቻል አለብን። ቢነሳም ደግሞ አንቺ ብቻ ሳትሆኚ በጋራ ተባብሮ የሚያጠፉ ወዳጆችን ማፍራት ላይ መስራት ብዙ ይጠበቅብናል።
እርግጥ ነው አሁን ላይ በዚህ መልኩ ለመስራት የተሻለ ነገር እንዳለ አውቃለው። ነገር ግን ከእነሱ አንፃር ሲታይ በጣም ደከም ያለ እንቅስቃሴ ነው እያደረግን ያለነው። ለድክመታችን አንዱም ቦታ አለመስጠታችን ብቻ ሳይሆን በሌላ መልኩም ደግሞ የመሰረተ ልማት አለሟሟላት ችግር መኖሩ ነው። ለምሳሌ ምን ያህሉ ሰው ነው የኢንተርኔት አቅርቦት ያለው? ስንቱ ሰው ነው መብራት የሚያገኘው? የትኛውስ የህብረተሰብ ክፍልን ነው ስማርት ፎን የመግዛት አቅም ያለው? የትኛውስ ሰው ነው ጉዳዩን በብቃት ማስረዳት የሚችለው? ምን ያህሉ ዜጋ ተምሯል? የትኛውስ ነው እውነተኛ የሀገር ፍቅር ያለው? ብለሽ ከጠየቅሽ በጣም ኋላ የቀረን መሆኑን ትረጃለሽ። ከዚህ አንፃር ግብፅና ሱዳን ከእኛ በብዙ የተሻሉ ናቸው። እኛ ጋር ሌላውን ሁሉ ትተሺው ከመከፋፈል አልፈን በጋራ በአንድ ጉዳይ እንኳን መስማማት አቅቶናል። ይህንን ድምር ችግር ስታይው ከእነሱ ጋር የሚነፃፀር ቦታ ላይ አይደለም ያለነው። በመሰረቱ ከእነሱ ጋር መነፃፀሩም ያንን ያህል ተገቢ አይደለም። ግን ባለን አቅም ለመስራት ጥረት ማድረግ አለብን። በተለይም በሃሰት ላይ ተመርኩዘው የተሰሩ ትርክቶችን መምታት አንዱ ጉዳይ ነው። ከዚህ በላይ ግን ከእነሱ በላይ በየጊዜው አጀንዳ መፍጠር ነው የሚገባን። ሁልጊዜ ከእነሱ አጀንዳ እየተሰጠሸ እሱን ከስር ከስር ለማጥፋት መጣር አዋጭ አይደለም። አንቺ የራስሽን አጀንዳ መፍጠር ያስፈልጋል። አንቺ ጠረጴዛሽ ላይ ባስቀመጥሽው አጀንዳ ላይ እንዲነጋገሩ ማድረግ መቻል አለብን።
አዲስ ዘመን፡– ከቴክኖሎጂው ባሻገር የአረቡን አለም በገዛ ቋንቋቸው የመድረስና እውነታውን እንዲያውቁ በማድረግ ረገድ ያለው ክፍተት እንዴት ይገለፃል?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– ከምንም በላይ ተነሳሽነት ይፈልጋል። እንዳልኩሽ እኔ በየአረቡ ሚዲያ የምከራከረውና የምፅፈው ማንም አስገድዶኝ አይደለም። በዚሁ ልክ በቋንቋ ረገድ ያለብንን ክፍተት መሙላቱ ላይ ብዙም አሳሳቢ ነው ብዬ አልወስደውም። ምክንያቱም በጊዜ ሂደት እያደገና እየተለወጠ የሚመጣ ነው ብዬ ስለማምን ነው። ሚዲያ ላይ ስትቀርቢ ደግሞ ማንበብና ሙሉ መሆን እንዳለብሽ እሙን ነው። ለዚህ ደግሞ ዋናው ፍላጎት ነው እንጂ በእውቀት ካሰብሽው ከእኔ በብዙ መልኩ የተሻሉ ሰዎች አሉ። ግን ደግሞ ተማሩ የምትያቸውና በልምድና በእድሜ የበሰሉት ሰዎች ምን ያህል ተተኪ ትውልድ አፍርተዋል? ብለሽ ብትጠይቂ እምብዛም ሆኖ ነው የምታገኚው። ትልቁ የእኛ ክፍተት ይህ ነው። ሚዲያውን ጥቂት ሰው ብቻ እንዲቆጣጠር የሆነበት ምክንያት ይሄ ነው። አንዳንዱ ደግሞ ከምቾት ስፍራው መውጣት አይፈልግም። ያለችውን እውቀት እያሽሞነመነ መሄድ ነው የሚፈልገው። ከዚህም ባሻገር በዲጂታል መገናኛ ዘዴዎች ላይ ብዙ የመፃፍ ባህሉ የለንም። ይህንን ስልሽ ቋንቋ ማወቅ አያስፈልግም ለማለት አይደለም። ነገር ግን በምትቺው ቋንቋ እንኳን በተገቢው መልኩ መፃፍ ከቻልሽ ትልቅ ነገር ነው። አንዳንዱ ራሱን ለመመርመር ዝግጁ አያደርግም፤ ጥቂት የማይባለውም ‹‹እሳሳታለሁም›› ብሎ በመስጋት ራሱን ይቆጥባል።
በሌላ በኩል ምቹ ሁኔታዎች የሉም። እርግጥ እንደእኔ አይነት ሰው በግድ በር አንኳክቶ የሚሄድ አለ። አንዳንዱ ደግሞ መቀስቀስ ይፈልጋል። በተጨማሪም የትምህርትና የምርምር ተቋማት ሃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ ነው ማለት አይቻልም። በተለያየ ቋንቋ ስለሀገራቸው የሚሞግቱ ሰዎችን የሚደግፉበት ስርዓት አልተዘረጋም። በተለይም ሙግታቸው ውስጥ ፍሬ ያለው ሃሳብ እንዲኖርና በመረጃ የተደገፈ እንዲሆን በማድረግ ረገድ እንደተቋም የተሰራው ነገር የለም። በአጠቃላይ የእነዚህ ሁሉ ድምር ችግሮች ጥርቅም ነው ባይ ነኝ። ብዙ ጊዜያችንን እሳት በማጥፋት ላይ ነው የምናሳልፈው። ከዚህ መውጣትና ተቋም መገንባት መቻል አለብን። አሁን ላይ ከውጭ ጉዳይ ጋር ስለምንሰራ በመንግስት በኩል ፍላጎት እንዳለ ለማየት ችያለሁ። ግን ለዚህ ሁላችንም ማገዝ ይገባናል። በተለይ አሁን ያለንበት የፖለቲካ ስርዓት ማገዝ ለሚፈልግ ሰው ብዙ ምቹ ሁኔታዎች አሉ። እድሉንም ያገኘውም ሰው ቢሆን በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል የሚል እምነት አለኝ። አለበለዚያ ለሚሰራ ሰው ቦታው መልቀቅ ይገባል። እርስ በርስ ከመጠቋቆምና ከመወነጃጀል መውጣት አለብን። ምክንያቱም ይህ አካሄድ ለሁላችንም ብዙም አዋጭ ባለመሆኑ ነው። ሁሉም የየራሱን አሻራ ማሳረፍ አለበት። ለዚያ ደግሞ በመጀመሪያ ፈቃደኝነቱ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– በአለም ላይ ድርንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንዞች ምክንያት ወደ ግጭት የገቡ ሀገራት አሉ? በዚህ ረገድ የአባይ ወንዝ ጉዳይ በዚህ ደረጃ የተለየ ለምን ሊሆን ቻለ?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– በአለም ላይ በርካታ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንዞች አሉ። ነገር ግን ውሃው የሚፈስባቸው ሀገራት ስምምነት መሰረት በጋራ መጠቀምን መሰረት ያደረገ ሂደት የሚከተሉ ናቸው። አብዛኞቹ ሀገራት በዚህ ረገድ ውጤታማ የሆኑ ስምምነቶች ተደርሶባቸው የሚጠቀሙባቸው ናቸው። ለምሳሌ በጣም ባላንጣ ናቸው ብለን የምናስባቸው ፓኪስታን እና ህንድንን ብንወስድ በስምምነት በጋራ ነው ውሃውን የሚያለሙትና የሚጠቀሙት። በዚህ ደረጃ ትልቅ የግጭት መንስኤ የሆኑ ወንዞች መካከል ኤዢያ ላይ የሚገኘውና ኔኮንክ የተባለ ወንዝን መጥቀስ እንችላለን። ይህ ወንዝ ቻይና፣ ቬትናም፤ ካምቦዲያ፣ ታይላንድ ላይ የሚፈስ የውሃ ክፍል ነው። እነዚህ ሀገራት የኔኮንክ ኮምሽን አቋቁመው ችግሮቻቸውን በጋራ ይፈታሉ። የተወሰኑት ሀገራት ደግሞ የኮሚሽኑ አባል ባለመሆናቸው በአጠቃቀም ላይ የሚነሱ ችግሮች አሉ። ግን ልክ እንደአባይ ስር የሰደደ ግጭት ውስጥ የገቡበት አጋጣሚ የለም።
በተመሳሳይ ወደ አፍሪካ ስንመጣ ለምሳሌ ሴኔጋል፣ ኒጀር ደቡብ አፍሪካ ብዙ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንዞችን የሚጋሩ ሀገራት አሉ። እነዚህ ሀገራት በስምምነትና በመነጋገር ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡበት ሁኔታ ነው ያለው። እናም አብዛኞቹ በትብብር መንፈስ የሚሰራባቸው ናቸው። የአባይን ጉዳይ ትንሽ ለየት ያደረገው አንደኛ ለመተባበር የሚፈልግ አገር ባለመኖሩ ነው። በተለይም ግብፅና ሱዳን ሌሎች ሊኖራቸው የሚገባውን የመጠቀም መብት ያለመቀበል ችግር አለባቸው። አሁን ላይ ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም በተደጋጋሚ የሚያነሱት የሌላውን ተጠቃሚነት ካለመቀበል የመነጨ ነው። እነዚህ ሀገራት በ1959 ዓ.ም ውሃውን ለሱዳንና ለግብፅ ከተከፋፈሉ በኋላ የተወሰነ ደግሞ ለትነት አድርገው ውል ከተዋዋሉና ቃል ካሰሩ በኋላ ያንን ያከበረ ህግ ኢትዮጵያ ከፈረመች በኋላ ነው መስማማት የምንችለው የሚል ሃሳብ በተደጋጋሚ ያነሳሉ። የሶስትዮሽ ውይይቱ ውጤታማ ሳይሆን እየተጓዘ ያለው ግብፅና ሱዳን የብቻ ተጠቃሚነታቸውን ለዘላለም ማስቀጠል ስለሚሹ ነው። ይህንን ደግሞ መቀበል በጣም ከባድ ያደርገዋል። ምክንያቱም ከትብብር መንፈስ የራቀ በመሆኑ ነው። ሌሎች ሀገራት ግን የሚተባበሩት የውሃውን መጠን በመለካት ወይም የውሃ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያየ በማድረግ ነው። የተለያዩ መላ ምቶችን በማስቀመጥ ሁሉን ያማከለ የስምምነት ማዕቀፍ ይዘው ስለሚንቀሳቀሱ ነው አለመግባባታቸውን መፍታት የቻሉት። ሱዳንና ግብፅ ግን እነሱ የትስማሙትን ስምምነት እንድንቀበልላቸው ነው የሚፈልጉት። ዜሮ ውሃ ድርሻ እንዲኖር የሚስማማና የሚፈርም ሞኝ ሀገርና መንግስት መቼም አይኖርም።
መሰረቱ ክርክሩም ራሱ የሞኝ ነው የሚመስለው። የአባይ ውሃ የመጠቀሙ ጉዳይ መከራከሪያ ሃሳብ መሆኑ በራሱ አስደናቂ ነው። ይሄ የግብፅና የሱዳን አቋም የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ሰብዓዊ ክብር የሚነካ ነው። ‹‹ምንም ውሃ አትጠጣም፣ ሁሉንም እኛ ነን መውሰድ ያለብን›› ነው የሚለው ነገር ፈፅሞ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ በጥቅሉ ስናየው አብዛኞቹ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጋር ያሉ ግንኙነቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ሀገራት እንደየኢኮኖሚውና እንደመጠቀም አቅሙ ሊጠቀም ይችላል። ግን የሌላውን የመጠቀም መብት ባልገደበ መልኩ የተደረጉ ስምምነቶች ናቸው። የአባይ ወንዝ ጉዳይ ግን ከዚህ የተለየ ነው። የግብፅና የሱዳንን መብት ብቻ ያስጠበቀ፤ ነገር ግን ዘጠኝ ሀገራትን መብት ያላማከለ መሆኑ ከባድ ያደርገዋል። ከዚያም ባሻገር ቁጭ ብለን ተስማምተን እንነጋገር ቢባልም ለመቀበል ፍቃደኛ ያለመሆን ችግር ስለሚታይበት ነው የተቃርኖና ያለመግባባት መነሻ ሆኖ የቀጠለው።
አዲስ ዘመን፡– ከብዙ ጭቅጭቅና ንትርክ በኋላ ሶስቱ ሀገራት በእ.ኤ.አ 2015 ዓ.ም በመርህ ለመስራት ተስማምተው ነበር። ይሁንና ሁለቱ ሃገራት ስምምነቱ መሬት ላይ እንዳይወርድ የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈጠሩ ቆይተዋል። ይህ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– አንቺ ያነሳሽው በመርህ ላይ የተመሰረተው የሶስቱ ሃገራት ስምምነት ውሃውን በፍትሃዊነት በጋራ ለመጠቀም ነው ካርቱም ላይ የሀገራቱ መሪዎች የተስማሙት። ይህም በትብብር የተሟሸ ድርድሮችን ለማካሄድ መነሻ የሚሆን ሰነድ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን። ችግሩ ግን ሌላ ድርድር ለማድረግ ቀርቶ እሱኑ እያከበሩ አለመሆኑ ነው። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያው ዙር ውሃ ሲሞላ በጣም ከፍተኛ የሆነ አተካሮ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ብሷል። ሶስት ጊዜ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያደረሰ ሁኔታ ተፈጥሯል። በሚገርም ሁኔታ ግን እነዚህ መሪዎች ሰምምነት ባደረጉበት ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ሳይቀር አስቀድመው ተነጋግረው ነበር። የታላቁ ህዳሴ ግድብ አሰራር ሂደቱ በራሱ ግንባታው ውሃን መሙላት እንደቅድመ ሁኔታ ነው የተቀመጠው። የዲዛይኑ ባህሪ በራሱ ውሃ መሙላትን አጣምሮ ግንባታውን በእኩል ደረጃ የሚኬድበት ነው። እነሱ ይህንን መርህ ጠብቆ ለመስራት ፈቃደኞች አይደሉም። ከዚያም ባለፈ በስምምነቱ አዋጅ ላይ በግልፅ የተቀመጠ ጉዳይ ነው። ይህንንም መሪዎቹ በግልፅ ተስማምተውበታል። እንግዲህ መሪዎቹ ሳያነቡ ሳይገባቸው የሀገራቸውን ጥቅም የሚጎዳ ነገር አይፈርሙም። ከዚያም ባሻገር የባለሙያዎች ቡድን ከእያንዳንዱ ሀገር ተወጥቶ ግድቡ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት እንዲያጠና ሳይቀር ነው ስምምነት ላይ የደረሱት። ከእያንዳንዱ ሀገር አምስት አምስት ነፃና ገለልተኛ የውሃ ባለሙያዎች እንዲደራጁ ተደርጎ ነበር። እነዚህን ሰዎች ያመጧቸው ራሳቸው ሀገራቱ ናቸው። የሀገራቸውን ጥቅም አይጎዳም ብለው ተስማምተው ያፀደቁት ስምምነት ነው። የውሃ ሙሌቱ ስራ ከግድቡ ግንባታ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው።
በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደምናየው ኢትዮጵያ አስገዳጅ ህግ ሳትፈርም ውሃ መሙላት የለባትም የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ይህንን የሚሉት እንግዲህ ቴክኒካል ባለሙያዎቹ ተስማምተውበት ምክረ-ሃሳብ ለመሪዎቹ የሰጡበት፤ መሪዎቹም ምክረ-ሃሳቡን ተቀብለው ያፀደቁትን ስምምነት ነው። እናም ለምን ሁልጊዜ እንደ አዲስ ጉዳዩን እንደሚያነሱት ግልፅ አይደለም። አንድ አንዴም በጣም መስመር አልፎ የሚሄድበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ይህ ጉዳይ አይመለከተውም። ምክር ቤቱ የሚመለከተው በሀገራት መካከል ያሉ የፀጥታ ጉዳዮች ለመፍታት የሚቀመጥ ጉባኤ ነው። እንደዚህ አይነት ጉዳዮችን ማንሳት ከጀመረ በጣም ብዙ አይነት አጀንዳዎች ተቀብሎ የምክር ቤቱን ስራ ያስተጓጉላሉ ማለት ነው። እንደምታውቂው ይህ ጉዳይ ወደ ምክር ቤቱ ሁለት ጊዜ ሄዶ ተመልሷል። መጨረሻ ላይ ምክርቤቱ ተሰብስቦ በተመሳሳይ ጉዳይ ቀርቦ ተመልሶ ወደ አፍሪካ እንዲመጣ ነው ሃሳብ የተሰጠበት። በነገራችን ላይ እኛ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት እንዲሄድ ባንፈልግም ለእኛ ግን ትልቅ እድል ነው የፈጠረልን። በተለይም ሰሞኑን የተደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ ያላትን መርህን እና ትብብርን መሰረት ያደረገ የውሃ አጠቃቀም ፍላጎት በግልፅ ለአለም ሀገራት ያሳየችበት ነው። ለብዙ ሀገራትም ትምህርት ነው። ይህ ጉዳይ ተመልሶ እንዳይመጣም ያስገነዘበ ነው። በርካታ ሀገራት ከእኛ ጎን ተሰልፈዋል። ኢትዮጵያ እያራመደች ያለችው ችግሮች በአፍሪካውያን መፈታት አለባቸው የሚለውን አቋም በኢንጂነር ስለሺ አማካኝነት አስረግጣ የተናገረችበት ነው። በተለይም ቋሚ የሚባሉት አብዛኞቹ ሃገራት የደገፉበት ሁኔታ ነው ያለው።
ኢትዮጵያ መርሁን ይዛ ነው የተከተለችው። እነሱ ግን ይህንን መርህ የመከተል ፍላጎት የላቸውም። ብዙ ጊዜ እንዳውም ከዚያ መርህ እንደሚወጡ ይዝታሉ። መብታቸው ቢሆንም ግን ዘለቄታዊ መፍትሄ አያመጣም። አንዳንድ ጊዜ ይሄ ጉዳይ የግብፅና የሱዳን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአረብ የደህንነት ስጋት ነው ብለው ጉዳዩን የማስፋት ሁኔታዎችንም እናያለን። እኔም ራሴ በቀረብኩባቸው ክርክሮች ይህንኑ አቋም ነው ሲያራምዱ የተመለከትኩት። አንድ ጊዜ እንዳውም ከአል-ሃራም ከተባለው ተቋም ኃላፊ ጋር ነው የተከራከርነው። ይህ ሰው ‹‹ወታደራዊ አማራጭን እንደአንድ አማራጭ እንወስዳለን›› ብሎ ሲናገር ነበር። ጋዜጠኛዋ ‹‹የአንተን ሃሳብ ንገረኝ ስትለኝ›› ኢትዮጵያ የማይነቃነቅ ፍትሃዊ የሆነና ትብብርን መሰረት ያደረገ ውይይት መቀጠል እንዳለበት የምታምን መሆኑን ነው ያስረዳኋቸው። ጉልበት ደግሞ እንጠቀማለን ካሉ ደግሞ ከማንም የማይተናነስ ጀግኖች እና ታጋዮች መሆናችንን ማወቅ ይኖርባቸዋል የሚል መልስ ነው የሰጠኋቸው።
እናም ብዙዎቹ ንግግራቸው ስምምነትና በመነጋገር ችግርን መፍታት ሳይሆን ፀብ አጫሪ የሆነ መንገድን ነው የሚከተሉት። ድርድሩን በማቆም ፖለቲካዊ ቅርፅ እንዲይዝ በማድረግ ከግብፅና ከሱዳን አልፎ የአረብ የውሃ ደህንነት ስጋት እንዲመስል አድርገውታል። ከዚያም አልፎ የቀጠናው ስጋት እንደሆነ በማቅረብ ነው ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚሹት። ከዚህ አንፃር በፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን አጀንዳ ካደረጉባቸው ስብሰባዎች ውስጥ በተለይ ሶስተኛው የዚያ መገለጫ ነው። እንደሚታወቀው ያንን ጥያቄ ያቀረበችው የአረብ ሊግ የወቅቱ ፀሃፊ የሆነችው ቱኒዚያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ረቂቅ አዘጋጅታ የአረብ የደህንነት ስጋት ነው ብላ ወስና ነው ያቀረበችው። ስለዚህ ጉዳዩን አለምአቀፍ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ ከውሃ አጠቃቀም ወጥቶ ፖለቲካዊ አንድምታ እንዲኖረው የማድረግ አዝማሚያ ነው የሚከተሉት። በአጠቃላይ እነሱ የሚከተሉት ስትራቴጂ መርህና መመሪያ መሰረት ያላደረገ የፖለቲካ መስመር ነው። ‹‹እኛ ብቻ እንጠቀም፣ እኛ ብቻ እንኑር። ለሌላው ሰው ህይወት ሕይወት አይደለም፣፤ የሌላው ሀገር ጥቅምና ፍላጎት አያገባንም ብቻችንን እንደግ›› የሚል አቋም ነው ያላቸው። ይህ ደግሞ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም። አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ አልፎ ደቡብ ሱዳንም በወንዙ ላይ ግድብ እንደምትገነባ አስታውቃለች። ስለዚህ ግብፅና ሱዳን ይህንን ግትር አቋማቸውን ዳግም ሊፈትሹ ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡– በተለይ በግብፅ በኩል የሚታየው የፀብ አጫሪነት መንፈስ ከወሬ ባለፈ ወደ ተግባር ሊቀየር የሚችልበት እድል አለ ብለው ያምናሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– እነሱ እኮ ዘመናቸውን ሁሉ ፀብ የሚያጭሩ ተግባራትን ሲፈፅሙ ነው የኖሩት። ታቅበው አያውቁም። ግብፆች ኢትዮጵያን ለማጥፋትና ለማተራመስ ከሱማሌያው ዚያድ ባሬ ጀምሮ በወታደርም፣ በቁስም ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር ። ሁልጊዜ እዚህ ሀገር በተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ የግብፅ እጅ አለበት። አሁንም ጭምር ታጣቂ ሃይሎችን በማደራጀት፤ ሃይማኖትን በመጠቀም ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጥረት አድርገዋል። እነሱ አስገዳጅ ህግ በማስፈረም ብቻ ሳይሆን ፍላጎታቸውን የሚያሳኩት በኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ መንግስት እንዳይኖር በማድረግ ጭምር ነው!። ምክንያቱም ህዝቡ ተረጋግቶ ስለሀገሩ ማሰብና መነጋገር ከቻለ ትልቁ ህልማችን እውን ሊሆን አይችልም። ካልተረጋጋሽ ልማት ላይ ሃሳብሽን ሰብስበሽ መስራት አትቺይም። መረጋጋት ከሌለ በህዝቦች መካከል መከፋፋል ካለ መንግስት እንደመንግስት ሆኖ የልማት ስራዎችን አይሰራም፤ ህዝቡንም ተጠቃሚ ሊያደርግ አይችልም።
ይሄ ፕሮጀክት ደግሞ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የቀጠናውንም የሃይል ፍላጎት የሚመልስ ነው። ከመጀመሪያውም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የመሰረት ድንጋይ ሲጥሉ ግብፅና ሱዳን በግንባታው ሂደት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። ይህም ኢትዮጵያ በተናጠል ለማደግ እንደማትፈልግ ያስመሰከረ ከመሆኑም ባሻገር እንዲህ አይነት ቀጠናዊ አንድምታ ያላቸው ፕሮጀክቶች የመገንባት ፍላጎቷ ለራሷ ብቻ ሳይሆን በጋራ ለመልማት ካላት ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ማሳያ ነው። እርግጥ ነው ሱዳን በተወሰነ መልኩ ድጋፍ ታደርግ ነበር። ከአልበሽር መነሳት ጋር ተያይዞ ለግብፅ ተላላኪ የሆነ መንግስት እንዲመሰረት ሆኗል። አሁን በግብፅ ፍላጎት የሚዘወር ጭንቅላት ያላቸው መሪዎች ከመሆኑ የተነሳ ስምምነቱ እንዳይሳካ ጥረት አድርገዋል። ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ በጋራ እንገንባ በጋራ እንጠቀም ሁሉም ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት ቀጠና እንፍጠር ስትል ነበር። አሁንም በዚያው አቋማ ቀጥላለች። በተግባር በቀጠናው ካሉ ሃገራት ጋር በመሰረተ ልማትና በንግድ የመተሳሰሩን ሂደት በተነሳሽነት እያሳካች ነው ያለችው። በቀጠናዉ ሰላም እንዲሰፍን ግጭት ባለባቸው ሃገራት ሰላም አስከባሪ ሃይል ከመላክ አንስቶ ፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዲኖር አድርጋለች። ይሁንና ኢትዮጵያ የምታደርገው ጥረት እንዳይሳካ ግብፅ ብዙ ጥረት አድርጋለች።
የሚገርመው ኢትዮጵያ በራሷ በጀትና በራሷ የተፈጥሮ ሃብት ላይ የምትገነባው ፕሮጀክት ለዓለም ህዝብ ያሳወቀች ብቸኛ ሀገር ናት። መንግስታችንም የመጀመሪያው መንግስት ነው ራሱ እየሰራ ‹‹የጋራ ፕሮጀክት ነው በጋራ እናልማው›› ያለው።‹‹ ችግር ሊያመጣ ከቻለ በጋራ እንነጋገርበት›› ያለም ብቸኛ መንግስት ነው። ስለዚህ ይህንን ያህል ርቀት የተጓዘ መንግስት ቢሆንም እነዚህ ሀገራት ግን ላለመስማማት ራሳቸውን አዘጋጅተው ነው የሚኖሩት። ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ብቻ ከዘጠኝ ጊዜ ባላይ ውይይቶች እንዲቋረጡ አድርገዋል። ይህም ማለት ውጤት እንዲገኝበት አይፈልጉም። አፍሪካ ህብረት የማደራደርም የማስተዳደር አቅም እንደሌለው አድርገው የህብረቱን ሉዓላዊነትና ክብር በማጉደፍ የራሳቸውን ፍላጎት የሚያስፈፁሙላቸውን ምዕራባውያንን በማስገባት ሞክረዋል። ይህም የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ጥቅምና የማደግ ፍላጎት ማጨናገፍ ነው ትልቁ ተልኳቸው አድርገው እየሰሩ ያሉት። ስለዚህ ከግብፅና ሱዳን ስምምነት መጠበቅ ከዝንብ ማር እንደመጠበቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡– የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን ጠንካራ አቋም ይዞ ከማደራደር አኳያ ክፍተት እንዳለበት ይህም ደግሞ የአረብሊግ የጉዳዩ ባለቤት ሆኖ እንዲቆም እድል ሰጥቶታል ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ። ህብረቱ ጥርስ የሌለው በመሆኑ ሁሉም እንደፈለጉ እንዲደፍሩት አድርጓልም ይላሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይሰማማሉ?
ረ/ ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– ልክ ነው፤ በዚህ ሃሳብ ተገቢነት እኔም አምናለሁ። እንዳልሽው ጠንካራ ሆኖ ጉዳዩን የራሱ ጉዳይ አድርጎ በቁርጠኝነት በአኔ አባል ሃገራት መካከል ያለ አጀንዳ በመሆኑ የአረብ ሊግን ‹‹ዞር በሉ›› ማለት አልቻለም። በተለይም እነዚህ ሀገራት በሃይማኖትም፤ በባህልም የተሳሳሩ በመሆናቸውና ከአንድ ወንዝ ውሃ የሚጠጡ እንደመሆናቸው እኔ ነኝ መዳኘት ብሎ የመሪነት ሚናውን አልተወጣም። ይሁንና የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማደራደር ከጀመሩ ወዲህ ጥሩ የሚባሉ እምርታዎች አይተናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ መጀመሪያ ላይ ሊቀመንበሩ ወደ ስልጣን እንዲመጡ የግብፅና የሱዳን ድጋፍ ስለነበራቸው በኢትዮጵያ በኩል ብዙ ስጋት ነበር ። በግሌም ሰውየው ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት በግልፅ ግንባታን ሲቃወሙ እንደነበር ስለማውቅ ከፍተኛ ስጋት ነበረኝ። ይሁንና ወደ ህብረቱ ሊቀመንበርነት ከመጡ በኋላ ጉዳዩን በአፅዕኖት ለመመልከት ሉኡካቸውን ይዘው ከጎበኙ በኋላ ነገሩ ገብቷቸዋል። ግብፅና ሱዳን የሚያነሱት ጉዳይ ተገቢ ያልሆነና ፍትሃዊ ያልሆነ መሆኑን አምነው ሀገራቱ እንዲቀራረቡና እንዲነጋገሩ ብዙ ጥረት አድርገዋል። በተለይም መጨረሻ ላይ በሀገራቸው ኪንሻሳ ላይ ያሳዩት አቋም ለእኔ ትልቅ ለውጥ ነው። የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ አለመሆኑን ቀጠናውና አህጉሪቱንም ጭምር የሚያስተሳስር መሆኑን ነው ያሰመሩበት። ይህም ለተጀመረው ነፃ የንግድ ቀጠና ስርዓት ምቹ መደላደል የሚፈጥር መሆኑን እንዲሁም ግድቡ የንግድ ስርዓቱ አካል መሆን እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት። ምክንያቱም ከግድቡ በሚመነጨው ሃይል ሃገራት የማደግ አቅም ይፈጥራል ብለው ስላመኑ ነው።
በተጨማሪም በአጀንዳ 2063 ከተቀመጡ የልማት ግቦች መካከል አንዱ የሃይል ማመንጫዎችን ማስፋፋት እንደመሆኑ የህዳሴ ግድብም ትልቅ አቅም እንዳለው ነው የተናገሩት። መጨረሻ ላይ ግብፆችም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸዋል። በህብረቱ ላይ እምነት እንደሌላቸው በፀጥታው ምክር ቤት ላይ ተናግሯል። ይህም የአህጉራዊ ድርጅቱን ክብር የሚያዋርድ ነው። በአጠቃላይ ህብረቱ ጉዳዮችን በፍጥነት የማስፈፀም ዘገምተኝነት ቢኖርበትም አሁን በተለይ ከግድቡ ጋር ተያይዞ ቀላል የማይባል ተፅእኖ እየፈጠረ ነው። ቁርጠኝነቱንም አሳይቷል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የራሷን አቋም ከማስረዳት አልፋ ለአፍሪካ ህብረት ግርማ ሞገስ መመለስ የሰራችው ስራ የገዘፈ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ግብፅና ሱዳን ከፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ እንደወጡ አሁንም የአለም ሀገራትን ትኩረት ለመሳብ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በኩል ሊሰራ የሚገባው የዲፕሎማሲ ስራ ምንድነው ይላሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– ትልቁ ስራ መሆን ያለበት ተቋም መገንባት ነው። እርግጥነው በተለይ የዲሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አሉ። ግን ደግሞ እነዚህ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። በተለይም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ብዙ ሊሰሩ የሚጋባቸው ስራዎች አሉ። አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ ዘመኑ የሚጠይቀውን የዲፕሎማሲ ስልት መጠቀም ያስፈልጋል። ከሀገራት ጋር ሊኖረን የሚገባው ግንኙነት በተጨባጭ ብሄራዊ ጥቅም ያስቀደመ እንዲሆን የሚያስችል የተቀናጀ ስራ መስራት ይገባዋል። ለዚያ ደግሞ የተደራጀ ተቋም ያስፈልገናል። የሀገር ውስጥ ጉዳይን ጠቅልሎ የሚይዘውን የሰላም ሚኒስቴርን ጨምረሽ፣ ከደህንነት፤ ከወታደራዊ ከትምህርት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየተመጋገበ መስራት የሚችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሊኖረን ይገባል። የውጭና የሀገር ውስጥ ጉዳዮቻችን ተነጣጥለው ሊታዩ አይገባም። መሰናሰል ወይም መያያዝ መቻል አለባቸው። በውጭ የምናደርገው እንቅስቃሴ ከውስጥ ፍላጎታችንና ውስጥ ካለው ነባራዊ አውድ ጋር መተሳሳር አለበት። ለዚህ ደግሞ በጋራ የመስራት ባህል ያስፈልጋል። የተናጠል ሩጫ መቆም አለበት። እየተመጋገበ የሚሄድ ስራ መስራት አለበት። ከዚያ የተቀዳ ፖሊሲ ያስፈልገናል። በውጭ ያሉን ዲፕሎማቶች ህግ አውጪዎች በጠቅላላ እውቀትን እና በመነጋገር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ መስራት የሚችሉና የሀገራቸውን ፖሊሲና መፅዓዊ እቅዶችና ስትራቴጂክ ፍላጎቶች የተረዱ ሰዎች መሆን አለባቸው። ምክንያቱም ከሌላው አለም ጋር የሚያገናኙን ድልድዮች በመሆናቸው ነው። ያንን የሚመጥን አደረጃጀት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። እስከዛሬ ድረስ ስንከተል የነበረው የፖለቲካ አካሄድ መፈተሽ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ መርህ መከተሉ እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅሞች ከፍ ማድረግ የሚያስችሉ እይታዎች ሊታከሉበት ይገባል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– የህዳሴ ግድቡን ጉዳይ ኢትዮጵያ አሁን ካጋጠማት የውሥጥ የፖለቲካ ችግር ጋር በማያያዝ አለም አቀፍ ጫና ማዕቀብ እንዲጣልባት ግብፅ የማትምሰው ጉድጓድ እንደሌላት አይተናል። በዚህ ረገድ ምን አይነት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለው ያምናሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– ለዚህም ቢሆን መፍትሔው ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ነው። ግንኙነታችንን በደንብ አይቶ ለዚያ በሚሆን መልኩ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ቀድሞ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ ብሎ አስቦ የሚንቀሳቀስ ለምላሾች የተዘጋጀ ተቋም መገንባት የግድ ይላል። አለበለዚያ ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ የምትነሺ ከሆነ አስቀድመን እንዳልነው እሳት የማጥፋት ዘመቻ ነው የሚሆነው። አሁን ያለው የትግራይ ችግር ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው ብዬ ነው የማስበው። በውስጥ መልስ መስጠት የሚችልበት ሁኔታ በመፍጠር የውጭ ጣልቃ ገብነቱን ማስቆም ይገባል። ይህም ከመነጋገር ጀምሮ ጠንካራ የሆነ ፍሬያማ ስራ መስራት ይገባናል። ይህንን ማድረጋችን ደግሞ ነገም እንደዚህ አይነት ችግሮች እንዳይነሱ ይረዳናል። በጥቅሉ ተቋማት ግንባታ ላይ በደንብ መስራት መቻል አለብን። የውጭ ተፅዕኖ እያጋለጠን ካሉ ጉዳዮች መካከል በዋነኝነት ድህነታችን ነው። በእርዳታ ስም የሚመጡ ሃይሎች ብዙ ጊዜ ቅድመ ሁኔታዎች አላቸው። ሁለተኛ እርዳታ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው፤ ሀገራት የራሳቸውን ፖሊሲዎችና ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም ሌሎች ሀገራትን ለማስገደድ የሚጠቀሙበት መሳሪያ ነው።
ስለዚህ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች በእኛም ሀገር ላይ ተንፀባርቀዋል። በተለይ ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጠና ስትራቴጂካዊ የሆነና ሊቆጣጠሩት የሚፈልጉት ከፍተኛ የፖለቲካ መስመር ነው። ከዚህ ሁኔታ ለመውጣት ለብቻ የሚገፋ አይደለም። አጋር ያስፈልጋል። ከሁሉ በላይ ግን የሀገር ውስጥ ህብረት ለእርዳታና ድጋፍ የሚዳርገንን ድህነት መውጣት ያስፈልገናል። ከዚሁ ጎን ለጎን ግን በጋራ ጥቅም የምንጋራባቸውን ሃገራት አጥንቶ ከእነሱ ጋር ስትራቴጂክ የሆነ ግንኙነት መፍጠር አለብን። ይህም በአጭር ጊዜ መልስ የሚሰጡ አይደሉም። መሰረት ያለው ስራ ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ተቋም መገንባትና የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ያስፈልጋል። የትምህርት ፖሊሲዎቻችንን መፈተሽም ይገባናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠያቂነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተከፈተ የትምርት ክፍል ቢኖርም ሰው በማጣቱና ትኩረት ያልተሰጠው በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ተዘግቷል። ስለዚህ እንደዚህ አይነት የተጀመሩ ስራዎችን ማስቀጠልና ማጠናከር ይገባናል። ይህንን ማድረግ ካልቻልንና ሁልጊዜ እርዳታ ተቀባዮች እየሆንን በቀጠልን ቁጥር የውጭ ተፅዕኖ እየበረከተና ሁልጊዜ የራሱን ጥቅም ማስከበር የማይችል መንግስትና ሀገር ይፈጠራል። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በምንችለው አቅም ተረባርበን የሃገራችንን ችግር በመነጋገር በውይይት መፍታት አለብን። የዚህ ዘመን ትውልዶች እንደመሆናችን መጠን መጥፎ ታሪክ ጥለን እንዳናልፍ መጠንቀቅ ይገባናል የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ።
ረ/ ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2013