ህወሓት ህጻናትን ከእናቶቻቸው እየነጠቀና ከቤታቸው ጎትቶ እያወጣ ወደ ጦር ሜዳ እየላከ ነው።በዚህም የተነሳ የጦርነቱ ቅርጽ እና ባህሪ ተቀይሮ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በመዋጋት ፈንታ እነዚህን ህጻናት ከሞት የማስጣል ግዴታ ውስጥ ገብቷል።ህጻናቱ በተለይም በአደንዛዥ እጽ እንዲነፍዙ ተደርገው ምን እያደረጉ እንደሆነም ሆነ የት እንዳሉ በማያውቁበት ሁኔታ ውስጥ በመሆናቸው እንኳን እነሱ ላይ ለመተኮስ ጠንከር ብሎ ለመቆጣት እንኳን አስቸጋሪ ነው።በሌላ መልኩ ህጻናቱን ለውትድርና በገፍ እየላኩ ያሉት እነ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው እንደ ደህና ሙያ ነውራቸውን እያወጁት ነው።ሰብአዊነት ፤እፍረት እና ይሉኝታ ከጁንታው መሪዎች መዝገበ ቃላት ውስጥ የሌሉ በመሆናቸው በአይን አውጣነታቸው ማንም ባይደነቅም እንኳ የሰዎቹ ነገር ግን ሲታሰብ ማስገረሙ አይቀርም።
የሆነ ሆኖ ዋናው አስደናቂ ነገር የህወሓት እፍረት አልባ ግፈኝነት ሳይሆን የሞራል መለኪያ በእጃችን ነው፤ ሰብአዊ መብትን ማክበር እና ማስከበር ግዴታችን ነው፤ የህጻናት ጉዳይ እንቅልፍ ይነሳናል የሚሉት የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎች እና ዓለምአቀፍ ተቋማት ዝምታ ነው።ይህ አስገራሚ እና አስነዋሪ ዝምታ ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አንስቶ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ያስገረመ ነበር።
እስኪ ከተቋማቱ እንጀምር።እነዚህ ተቋማት እስከዛሬ በትግራይ ክልል በተፈጠሩ ክስተቶች ላይ ስንት መግለጫ አውጥተዋል ብንል መልሱ ስፍር ቁጥር የለውም የሚል ነው።መግለጫዎቹን ለማውጣትስ ምን ያህል ጊዜ ፈጅቶባቸዋል ብንል የምናገኘው መልስ ከአንድ ቀን ያነሰ የሚል ነው፡አንዳንድ ጊዜም በቀን ሁለት ጊዜ መግለጫ ሲያወጡ ቆይተዋል፡የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፤ የአውሮፓ ህብረት ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ቢሮዎች እና ሌሎች ኤጀንሲዎች በትግራይ ተከሰተ ስላሉት ረሀብ ፤ የንጹሀን ሞት ፤ አስገድዶ መድፈር ፤ የእርዳታ መንገድ መስተጓጎል ወዘተ…ቀን በቀን ሪፖርት እና መግለጫ ሲያወጡ ከርመዋል።አብዛኞቹ መግለጫ የሚያወጡባቸው ጉዳዮች መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሀቅን ያላገናዘቡ እና የአንድ ወገን ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ናቸው።ብዙዎቹ መግለጫዎች አለቅጥ በተጋነኑ ጥቃቅን እውነቶች እና ሀሰተኛ ድምዳሜዎች የተሞሉ ሲሆን የሆነ አይነት አላማን ለማሳካት ያቀዱ ነበሩ።የኢትዮጵያ መንግሥትም በተደጋጋሚ እነዚህ ተቋማት የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ፖለቲካዊ አላማ ያላቸው እንደሆነ ሲያሳስብ ከርሟል።እነዚህ የኢትዮጵያ ጉዳይን እንደ ግል ጉዳያቸው አስመስለው የያዙ ተቋማት ታዲያ አሸባሪው ህወሓት የሚፈጽማቸውን ነውረኛ ተግባራት በማንቆለጳጰስ ላይ ይገኛሉ። ለአቅመ ጦርነት ቀርቶ ለአቅመ አዳም እና አቅም ሄዋን ያልደረሱ ህጻናት በጦር ሜዳ መሳሪያ ታጥቀው ሲታዩ እስካሁን መግለጫ ሲጽፉበት የከረሙበት ብእር ቀለሙ ያለቀ ይመስል ዝምታን መርጠዋል።የአሜሪካ መንግሥት ፤ የአውሮፓ ህብረት ፤ ብሪታንያ ፤ አምነስቲ ኢንተርናሽና ፤ ተመድ እና ሌሎችም እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ አንድም ያሉት ነገር የለም።ምናልባትም ከህጻናቱ ጦርሜዳ ላይ መገኘት ይልቅ የዚህ ፎቶ ሾልኮ መውጣት ሳያናድዳቸው አልቀረም።ወይም ይህን ያህል ጊዜ የወሰዱት እንዲህ አይነቱን ነውር በምን አይነት መልኩ ምክንያታዊ ማድረግ እንደሚችሉ እየተመካከሩ ሊሆን ይችላል።ሁኔታው ግን ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ሌሎች አካላት እነዚህ ተቋማት ገለልተኝነት እና የሞራል ከፍታ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ የሚያሰፋ ነው።
ሚዲያዎቹስ? ሚዲያዎቹ ከተቋማቱ በተሻለ በድፍረት የህጻናቱን ውትድርና ማሞካሸት ይዘዋል። ህጻናቱ መሳሪያ አንግበው የሚታዩበትን ፎቶ የለጠፈው ኒውዮርክ ታይምስ ህጻናቱን “ተነሳሽነት ያላቸው ወጣት ምልምሎች ” በማለት ሲያሞካሸው አሶሺየትድ ፕሬስ በበኩሉ አንዲት ለውትድርና የተሰለፈች የ16 ዓመት አፍላ ለምን ወደጦር ሜዳ ልትገባ እንደፈለገች እንድታብራራ በመጠየቅ የውትድርናቸውን ምክንያታዊነት ለማስረዳት ሞክሯል። ዘገባውን የሰራው ጋዜጠኛ መቀሌ የሚገኝ ቢሆንም ህጻናቱን ለጦርነት የሚመዘግቡትን የጁንታው መሪዎች ተግባራችሁ አግባብ ነው? ወይ ዓለም አቀፍ ህግንስ አይጻረርም ወይ? ብሎ አልጠየቀም።አሶሺየትድ ፕሬስ በዘገባው ውስጥ ግን ሳያውቅ እውነቱንም አፍርጦታል። ጋዜጠኛው የጠየቃት አፍላ እሷ የተመዘገበችው ጓደኞቿ ስለተመዘገቡ እንደሆነ የተናገች ሲሆን ይህ አንድም የገባችበትን ጦርነት አላማ እንደማታውቅ እና የአቻ ግፊት ተጽእኖ እንዳሳደረባት በሌላ መልኩ የሷን አይነት ብዙ አፍላ ወጣቶች እና ህጻናት ወደጦርነቱ እንደገቡ የሚያሳይ ነው።”I actually wanted to go (fight) at the beginning but I was told I was too young. but because I saw my comrades come,I came here to fight along them /በእርግጥ ሲጀመር ነበር ልዋጋ የመጣሁት ነገር ግን ልጅ ነሽ ብለው መለሱኝ።ግን አሁን ጓደኞቼ ሲመጡ ስላየሁ ከነሱ ጋር አብሬ ልዋጋ መጥቻለሁ” ብላለች።ልጅቷ ለቃለመጠይቅ የተገኘችበት ቦታ ራሱ ለውትድርና ምዝገባ የሚካሄድበት እና መሳሪያ የሚታደልበት ቦታ መሆኑ እንዲሁም ከ8 ወር በፊት ልጅ ነሽ ተብላ የተመለሰች አፍላ አሁን ከነጓደኞቿ እንድትመዘገብ መደረጉ አንድም የህወሓት አቅም ክፉኛ መመናመኑ በሌላ መልኩም ጁንታው ጨቅላ ህጻናትንና አረጋውያንን ጭምር እያሰለፈ አሁን የመጨረሻውን የሞት ትግል ለማድረግ መቁረጡን ያመለክታል።
ስለ ፎቶው እውነተኝነት ፎቶውን ካነሳው ጋዜጠኛ አረጋግጫለሁ ያለው ቢቢሲ አማርኛ በበኩሉ በዚህ ዙሪያ ህወሓትን ለማነጋገር አልደፈረም።ለሌላ ጉዳይ ሲሆን የህወሓት ሰዎችን ምሽጋቸው ድረስ ሄደው አልያም በሳተላይት ስልክ ደውለው የሚያገኙት የውጭ ሚዲያዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ህወሓቶችን ማግኘት አልቻልንም ማለታቸው አስቂኝ ነው።
እውነቱን ለመናገር ዓለምአቀፍ ተቋማትም ሆኑ ሚዲያዎቻቸው ዝም ማለታቸውም ያልተጠበቀ አይደለም። ምክንያቱም ይህ ለእነሱ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ስለማይጠቅም ነበር።የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባም ቢሆን በኋላ ራሱ ላይ ባርቆ አዋረደው እንጂ አላማው የጁንታውን “ጀግንነት” ማወጅ ነበር።ያም ሆነ ይህ ነገሩ ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም።ከዚህ ቀደምም እነጌታቸው ረዳ በህይወት መኖራቸውንም ለማስመስከር በህዝብ መሀል እየተንጎራደዱ የሚታዩበትን ፎቶ ይዘው ሲወጡ ይሄ ነገር በጦርነት ቀጠና ንጹሀንን ለጦር ከለላ መጠቀም ነው አግባብ አይደለም ሲባል እነሱ ግን እንደ ህዝብ ፍቅር መገለጫ እንዲታይላቸው ለማድረግ ሞክረዋል።የእስከዛሬው ጩኸትም ሆነ የሰሞኑ ዝምታ የሚያሳየን አንድ ነገር ቢኖር ግን ከጁንታው ጀርባ የተሰለፈ ሌላ አደገኛ ሀይል እንዳለ ነው።ይህ ሀይል ሁሌ እንደሚደሰኩረው በእውነት የሰብአዊ መብት መርህ ካለው ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅሙ ሲል መርሁን ወደጎን ማለቱ ነገ ዋጋ ያስከፍለዋል።ቀድሞውንም መርህ ከሌለው ደግሞ ይህ ወቅት ትክክለኛ ማንነቱን በተቋማቱ እና በሚዲያዎቹ ዝምታ ውስጥ ገልጧልና እናመሰግነዋለን።ምክንያቱም ከአሁን በኋላ ከነዚህ ተቋማት እና ሚዲያዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት እንድናጤነው እድል ሰጥቶናልና ነው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2013