የቅመማ ቅመም ማህበር አምራቾችንና እሴት ጨምረው አዘጋጅተው(አቀነባብረው)ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አባላትን ይዞ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣አባላቱ ቅመማቅመምና መአዛማ ምርቶችን በማምረት ከግል ተጠቃሚነት ባለፈ ለዜጎቹ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሪም በማስገኘት በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ አስተዋጽኦ በማድረግ ሚናቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የማህበሩ የልማት እንቅስቃሴ እንደ ጅምሩ ባለመሆኑ ሥራው ተቀዛቅዟል። ምክንያቶቹ ደግሞ ሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው አለመረጋጋት አንዱ ሲሆን፣በዓለምአቀፍ የተከሰተው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ሌላው መንስኤ ነው። ምክንያቶቹ አባላቱ ተገናኝተው በእንቅስቃሴያቸው ላይ ለመምከር እንዳይችሉ ከማድረጉ በተጨማሪ ተጽዕኖውን መቋቋም ያልቻሉ አባላት ከልማቱ ሥራ እንዲወጡ አድርጓቸዋል።ተጽዕኖዎችን መነሻ በማረግ አሁን ያሉበትን ሁኔታና ስለቀጣይ የማህበሩ እንቅስቃሴ ከማህበሩ ተወካይ አቶ ጌታቸው ማሞ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አቶ ጌታቸው እንዳስረዱት ቅመማቅመም ምርት በሥፋት የሚከናወነው ቴፒ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ የማቀነባበሩ ሥራም የሚከናወነው በተለይም የዕርድ ቅመም የዕርዱን ሽፋን በማንሳት ነው።የዕርድ ምርት ለመካከለኛው ምሥራቅና ኤዥያ ገበያ ተፈላጊ በመሆኑ በስፋት ይቀርባል።ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ገበያው እንደጅምሩ አይደለም።ምርቱ በሚከናወንበት ቦታ የተፈጠረው የፀጥታ ችግርና አለመረጋጋት በሰው ጉልበት የሚሰራውን የልማት ሥራ ሠራተኞችን ከቦታ ወደ ቦታ አንቀሳቅሶ ለማሰራት ባለመቻሉ አምራቹ የማምረት አቅሙን መጠቀም አላስቻለውም።አንዳንዶችም ልማቱን ትተው ለመውጣት ተገደዋል።የፀጥታ ችግሩ በክልል፣ በአካባቢ ማህበረሰብና የሀገር ሽማግሌዎች፣በመንግሥትም ጭምር መፍታት ሳይቻል እስካሁን ቆይቷል።
ለልማቱ ተጨማሪ ተግዳሮት የሆነው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ደግሞ በማቀነባበሩ ተግባር ላይ ተጽዕኖ በማሳደር የዘርፉን እንቅስቃሴ ጎድቶታል።ምርቱን በመላክ ላይ የተሰማራው ባለሀብት ኮቪድን ለመከላከል የሚያስችሉ መርሆዎችን በመተግበር ሥራውን ለመሥራት የማቀነባበሪያው ቦታ ጠባብ መሆን እንደቀድሞ ሰፊ ቁጥር ባለው የሰው ኃይል ለመንቀሳቀስ አላስቻለውም።ኮቪድ ቀደም ሲል ምርቶቹን በተለያየ መንገድ ለገበያ በማስተዋወቅ ሰፊ የገበያ ዕድል ለማግኘት ይደረግ የነበረውን ጥረት አስተጓጉሏል።
አቶ ጌታቸው ‹‹ናቲ ኮፊ ኤንድ ስፓይስ›› በሚል ስያሜ የሚጠራ ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት አላቸው። ድርጅታቸው በማምረት፣ በማቀነባበርና ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ጭምር እየሰራ ይገኛል።ከእርሳቸው የሥራ ተሞክሮ በመነሳት እንደገለጹት፤የልማት ሥራውን በሚያከናውኑበት ቴፒ አካባቢ ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እንኳን አዲስ ምርት ለማምረት ቀድሞ የተመረተውን ከእርሻ ማሳቸው ላይ ለመሰብሰብ አልቻሉም።ምርት በሚደርስበት ወቅት እስከ ሦስት መቶ የሰው ኃይል ይሰማራ ነበር።ይሄን ማድረግ አልተቻለም።በአጠቃላይ ይህ ሁኔታ እያስከተለ ባለው ችግር የምርት መቀነስ እስከ 90 በመቶ እየደረሰ ይገኛል።የምርቱ መቀነስና ከኮቪድ ጋር ተያይዞ በወጭ ንግዱ ላይም በተመሳሳይ እያሳደረ ባለው ተጽዕኖ በገበያው እስከ 30 በመቶ የመቀነስ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።መረጃው በጥናት ተደግፎ ቢቀርብ ደግሞ ጉዳቱ ከዚህም በላይ ሊሆን ስለሚችል በጥናት የተደገፈ ቢሆን ይመረጣል።ጥናቱ ያለውን ክፍተት ከመለየቱ በተጨማሪ ማን ምን ያስፈልገዋል ለሚለውና ድጋፍና ክትትል ለማድረግም ይጠቅማል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ በተለያዩ ጫናዎች ማህበሩ ከአባላቱ ጋር መገናኘት አለመቻሉ እንዲዳከም መንገድ ከፍቷል።አባላቱ ላለመገናኘታቸው ኮቪድ አንዱ ምክንያት ቢሆንም የገበያው መቀዛቀዝም አባላቱን አላነሳሳቸውም።ማህበሩ አባላቱን ጠርቶ ለመወያየት አቅዷል።በግንኙነቱ ወቅት አንድ ሀሳብ ላይ ለመድረስ ይቻላል የሚል ተስፋ በመኖሩ ያኔ የሚታይ ይሆናል።
የማምረትና ምርቱንም ወደ ውጭ የመላክ ሂደቱ በተለያየ ችግር ውስጥ እያለፈ ቢሆንም እንቅስቃሴው ሙሉ ለሙሉ አልቆመም።በምርት እንቅስቃሴው ላይ ያሉትም ቢሆኑ ተስፋ መቁረጥ አልፈለጉም።ችግሮች ይፈታሉ በሚል በሚችሉት ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ምንም እንኳን አቶ ጌታቸው በአሀዝ አስደግፈው ሊነግሩኝ ባይችሉም በመጠኑም ቢሆን እያመረቱ ለውጭ ገበያ የማቅረቡ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሆነ ነው የገለጹት።ለአብነትም የእርሳቸውን የድርጅት እንቅስቃሴ እንደገለጹት ችግር ከመፈጠሩ በፊት በዓመት እስከ ስድስት መቶ ሜትሪክ ቶን ድረስ ቅመማቅመም ለውጭ ገበያ ያቀርቡ ነበር።በአሁኑ ጊዜ ወደ አንድ መቶ ሜትሪክ ቶን ዝቅ ብሏል።ለወጭ ንግዱ መቀነስ ትልቁን ድርሻ የያዘው ምርቱ በሚመረትበት ቦታ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ነው።ምርቱ ቢኖር የወጭ ንግዱ ያን ያህል ስጋት አይሆንም ነበር።
አቶ ጌታቸው ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት በአጠቃላይ የነበረውን ሂደት እንዳስታወሱት የዓለምአቀፉን ገበያ በማየት አዳዲስ አምራቾች ዘርፉን በመቀላቀል ምርቱ እየጨመረ፣ገበያውም እያደገ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ነበር።የአጭር ጊዜና ዓመታዊ ምርቶች በመኖራቸው አበረታች ሁኔታ ነበር።አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት በተሻለ ለመሥራት ገና በሀሳብ ደረጃ ላይ ቢሆንም በነበረው ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።አቶ ጌታቸው ዘርፉን ላጋጠመው ችግር በግላቸው ዘላቂ መፍትሄ ብለው ያስቀመጡት አምራቹ እንደጅምሩ ተጠቃሚ ሳይሆን ጫናውን ተቋቁሞ ከዘርፍ ላለመውጣት ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።አሁን ከአቅሙ በላይ እየሆነ ስለሆነ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የዘርፉን ህልውና ለማስቀጠል ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።
ለምለም ምንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013