
መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ የኑሮ ውድነትን እና የዋጋ ንረት ጫናን ለመቀነስ የተለያዩ ርምጃዎች እየወሰደ ይገኛል፡፡ ከትግበራዎቹ መካከል በሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መውሰድ አንዱ ተግባር ነው፡፡
የምርት አቅርቦት እንዲጨምር እና የሰንበት ገበያ ማዕከላት እንዲስፋፉ እና ዘመናዊና ተደራሽ የግብይት ሥርዓት እንዲዘረጋ ማድረግም በቀዳሚነት ከሚወሰዱ ተግባራት መካከል መጥቀስ ይቻላል፡፡
በተለይም አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ የቅዳሜና እሁድ የግብይት ማዕከላትን በወጣው የደረጃ መስፈርት መሠረት የማስፋፋት ተግባርን የበለጠ ማጠናከር መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የሚመደብ ነው፡፡
ለሕጋዊ ነጋዴዎችና ለሸማቹ ኅብረተሰብ የተመቸ የንግድ ምሕዳርና የተረጋጋ የገበያ ሥርዓት ስር እንዲሰድ ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሠራ ያለው ሥራ በበጎነት ይታያል፡፡
ይሁን እንጂ ተግባሩ ገና በጅምር ላይ ያለ እንደመሆኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች የታየው መልካም ጅምር ሊስፋፋ የሚገባ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
በዚህ ዓምድ ስር ለምናነሳው ርዕስ መነሻ የሆነን ሰሞኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር “በጥራት ወደ ተሳለጠ የንግድ ሥርዓት” በሚል መሪ ሃሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያካሄደውን ጉባኤ መሠረት ያደረገው በገበያ ማዕከላት የተካሄደው ጉብኝት ነው፡፡
ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከንግዱ መዋቅር አመራር እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቡታጅራ ከተማ የሚገኙ የገበያ ማዕከላትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ‹‹ከሰንበት እስከ ሰንበት›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው የገበያ ማዕከላት ለሌሎች አካባቢዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው።
የገበያ ማዕከላቱ ሳምንቱን ሙሉ አምራችና ሸማችን በቀጥታ የሚያገናኙ መሆናቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ላሉን አንድ ሺህ 213 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችና ለሌሎች አካባቢዎችም መልካም ተሞክሮ ተደርገው የሚታዩ መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡
ገበያዎቹ ትኩስ ምርቶችን ከማቅረብ ባለፈ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ነዋሪዎች ዓይነተኛ መፍትሔ ለመሆን መቻላቸውን በጉብኝታቸው ማረጋገጥ እንደቻሉም ነው ካሣሁን (ዶ/ር) የሚጠቁሙት፡፡
ገበያዎቹ ትኩስ ምርቶችን በየዕለቱ ከማቅረብ ባለፈ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውና በየዕለቱ እንደ አቅማቸው ለሚጠቀሙ ነዋሪዎች ዓይነተኛ መፍትሔ መሆን መቻላቸውን በአካል ተገኝተው እንደተመለከቱ ይመሰክራሉ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 134 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የተመቻቹ መሆኑን፤ በቡታጅራ ከተማ ሦስት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መመቻቸታቸውንና ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ ከሰንበት እስከ ሰንበት ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን በጉብኝቱ መረዳት ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንደሚናገሩት፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከሌሎች ክልሎች በተለየ መንገድ የሰንበት ገበያን ‹‹ከሰንበት እስከ ሰንበት›› በሚል በርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
እነዚህ ገበያዎች ከሰንበት እስከ ሰንበት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ላይ አምራቹና ሸማቹ ማኅበረሰብ በቀጥታ ግብይት እንዲፈጽሙ ያስቻሉ ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለዕለት ጉርሳቸው እንዲሸፍኑ በሳምንት አንድ ጊዜ መግዛት ስለማይችሉ ይህንን በማገናዘብ ዛሬ የሚያስፈልጋቸውን ዛሬ እንዲሸምቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታሳቢ የተደረገ መሆኑን ነው፡፡
ይህንኑ ተከትሎም በክልሉ 134 ከሰንበት እስከ ሰንበት ገበያዎች ማቋቋም እና ወደ ሥራ ማስገባት እንደተቻለም አቶ ዳንኤል ይናገራሉ፡፡
አምራች እና ሸማቹ አካባቢ ያለውን ያልተገባ ሕገወጥ የደላላ ጣልቃ ገብነትን ጭምር ማስቀረት የተቻለበት ተግባር መሆን ችሏል፡፡ ለአቅመ ደካሞች ደግሞ በተለይ የዕለት ጉርሳቸውን በዕለት ሠርተው ለሚሸፍኑ አካላት ተጠቃሚ እንዲሆኑበት ታሳቢ ተደርጎ የተሠራ ነው፡፡ በግብይቱም (ያላደረ) ትኩስ ምርት የሚቀርብበት ነው፡፡
ያለፉት ስድስት ወራት ከሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ተያይዞም የማጠናከር ሥራ በትኩረት የተሠራበት ነው፡፡ በክልሉ የተለያዩ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቢኖሩም በተደራጀ እና በተጠናከረ መልኩ ለኅብረተሰቡም አገልግሎት በሚሰጥ ደረጃ በክልሉ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር ተቋቁሟል፡፡
የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ለከተማው ማኅበረሰብ የመንግሥት ሠራተኞች ጭምር ታሳቢ በተደረገ መልኩ የተሠሩ መሆናቸውንም ነው አቶ ዳንኤል የሚጠቁሙት፡፡
እንደአቶ ዳንኤል ማብራሪያ፤ ከሰንበት እስከ ሰንበት ገበያን በክልሉ ባልደረሱ አካባቢዎች ላይ ማስፋፋት እንደሚገባ ታሳቢ ተደርጓል፡፡የሰንበት ገበያ የአንድ ወቅት ተግባር ብቻ እንዳይሆን ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
‹‹ከሰንበት እስከ ሰንበት›› ተብለው የሚሠሩ ሥራዎች የሆነ ወቅት ላይ ብልጭ ብለው እንዳይጠፉ እና ኅብረተሰቡን ባማከለ መልኩ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ኢኒሼቲቩን ወስዶ ዘንድሮ በስድስት ከተሞች ዘመናዊ ‹‹ከሰንበት እስከ ሰንበት›› ገበያዎችን ግንባታ በስድስት ዞኖች በዋና ከተሞቻቸው ላይ ይጀመራሉ። ቀጣይነቱን ማረጋገጥ በሚቻልበት መንገድ መመራት እንዳለበት መተማመን አለን፡፡
ገበያዎቹ የሚስፋፉባቸው ስድስቱ ከተሞች ቡታጅራ፣ ወራቤ፣ ሆሳዕና፣ አላባ ቁሊቶ፣ ወልቂጤ እና ዱራሜ ከተሞች ናቸው፡፡
ግንባታዎቹ አምራቹ በቀጥታ የሚገባበት ብቻ ሳይሆን፤ አምራቹ ወይም ባለፋብሪካዎች ገብተው ቀጥታ ከሸማች ጋር ግንኙነት ሊፈጥሩ የሚችሉበት የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት በሀገር አቀፍ በወጣው የሰንበት ገበያ ስታንዳርድ በክልሉ መመራት ያለበትን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ወደሥራ ተገብቷል፡፡
በስድስቱ ከተሞች ላይ ከሰንበት እስከ ሰንበት ገበያዎችን ግንባታ ለማከናወን የዲዛይን ሥራው ተጠናቅቋል፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የጨረታ ሂደቱ አልቆ ወደ ግንባታ ሽግግር የሚደረግ ይሆናል።
ትግበራው የከተማው ነዋሪዎች ከመደበኛ ዋጋ በዝቅተኛ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል፤ በመሐል ያለውን ክፍተት ሊሞላ በሚችል መልኩ እንዲተገበር ታስቦ የተከናወኑ መሆናቸውን አቶ ዳንኤል ይናገራሉ፡፡
ከሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ተያይዞም፤ በክልሉ ውጤታማ የሆኑ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አሉ፡፡ ቡታጅራ የሚገኘው ‹‹አገልግል›› የኅብረት ሥራ ማኅበር አንዱ ነው፡፡
ማኅበሩ በሆሳዕና እና በወራቤ ከተሞች የጀመራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ማኅበራቱ በመጀመሪያ ባሉባቸው ከተሞች ቅርንጫፎች እንዲያስፋፉ ተደርጓል፡፡ የቡታጅራ አገልግል የኅብረት ሥራ ማኅበር አሁን በቡታጅራ ሦስት ቅርንጫፎች ከፍቷል። በቀጣይም በሌሎቹ የክልሉ ከተሞች የቅርንጫፎቹን ቁጥር እንደሚያስፋፋ ይጠበቃል፡፡
በተለየ መልኩ ከሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር የታሰበው ከውጭ ምርት ማስገባት የሚችሉበትን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ማኅበራቱ ከአዲስ አበባ ከተማ ከመርካቶ ገበያ አጓጉዘው ከመሸጥ ይልቅ ማኅበራቱ የግብይት ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት ቀጥታ ከውጭ እያስገቡ ለኅብረተሰቡ ሊያደርሱ የሚችሉበትን ሥርዓት ይገነባል፡፡ በዚህም ተግባር የውጭ ምንዛሪ እንዳይቸገሩ ወደ ውጭ ምርት የሚልኩበትን የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት የሸማች ማኅበራቱ አቅማቸውን የማደራጀት ሥራ ይሠራል፡፡
በክልሉ ከንግድ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በመሠረታዊነት የትኩረት አቅጣጫ ተብሎ የተለዩ ዋና ዋና ተግባራት አሉ የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ ከትኩረት አቅጣጫዎቹ መካከል በተለይ የኦን ላይን አገልግሎት አሰጣጥን በማሳደግ የንግድ ሥርዓቱን ከማዘመን ጋር ተያይዞ ያለው ተግባር በወሳኝነት የሚታይ ነው፡፡
በክልሉ በሚገኙ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ኅብረተሰቡ ቀልጣፋ እና በቀላሉ አገልግሎት ማግኘት የሚችልበትን በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሠራር ሥርዓት ተደራሽ ማድረግ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡ በቀበሌ፣ በወረዳ እና ክፍለ ከተሞች ጭምር ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ በክልሉ ባለፈው ዓመት 56 ሺ ነጋዴዎች በኦንላይን የንግድ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት ያገኙ ሲሆን፤ ዘንድሮ አፈጻጸሙን በማሳደግ ከ70 ሺህ በላይ ነጋዴዎች በኦንላይን የታገዘ የንግድ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት እንዲያገኙ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት አኳያ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ እንደነበር የሚያነሱት አቶ ዳንኤል፤ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት የኅብረተሰቡን ኑሮ እንዳይጎዳ፣ ባልተፈለገ እና ባልተገባ ሁኔታ የኑሮ ውድነቱ የሚከብደው የኅብረተሰብ ክፍል በክልሉ እንዳይሰፋ ለማድረግ ሁለት አንኳር ነጥቦችን በመለየት ተሠርቷል።
አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ሕግን ከማስከበር ወይም ሕገወጥነትን ከመቆጣጠር አኳያ የተሠራው ሥራ ነው፡፡ ከ75 ሺህ በላይ የሚጠጉ ነጋዴዎች በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የተገኙት ርምጃ ተወስዷል፡፡
አለፍ ሲልም ችግራቸው ከፍ እያለ የቀጠለ 151 ነጋዴዎች በእስራት ጭምር እንዲቀጡ የተደረገበት ሂደት መኖሩንም ያመለክታሉ፡፡ የተቀጡት ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ የተደረገበት ሂደት በንግድ ሥርዓቱ ሕግን ከማስከበርና ሕገወጥነትን በመከላከል ረገድ የተከናወነ ነው፡፡
ከነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት ጋር ተያይዞ በሀገር አቀፍም ሆነ በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ ጉዳዮችን ለማጥራት ጥረት ተደርጓል፡፡
በተለይ ሕገ ወጥነት እና ኮንትሮባንድን ለመከላከል ጥረት ተደርጓል፡፡ ከኮንትሮባንድ ንግድ ጋር በተያያዘ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ66ሺ ሊትር በላይ ቤንዚን በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተይዟል፡፡ ወደ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ተሸጦ ለመንግሥት ገቢ መደረጉንም ነው የሚጠቁሙት። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወደ 13ሺ የሚጠጉ ነጋዴዎችን የማረም ሥራ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉንም ያመለክታሉ፡፡
የኑሮ ውድነትን ከመከላከል አኳያ መሠረታዊ የሆነው ጉዳይ እንደሀገር የሰንበት ገበያዎችን የማስፋፋት ሥራ በትኩረት ሲተገበር ቆይቷል የሚሉት አቶ ዳንኤል፡፡ በንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመከታተል እና በመቆጣጠር ረገድ የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት ሊኖር እንደሚገባም ነው የሚናገሩት፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ክልሉ የተመሠረተው ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ነው፡፡ በሰባት ክላስተር የተደራጀ እና ከሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚገኝበት ክልል መሆኑንም ጠቁመዋል። ከሰባቱ ክላስተሮች መካከል ቡታጅራ የኢኮኖሚ ክላስተርና የኢንዱስትሪ ከተማ ሆና ተለይታለች፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሰላምን በማስፈን የኢኮኖሚ ሽግግር እና ግንባታ እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የተሠራው ሥራ ውጤት ተመዝግቦበታል፡፡
ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ የለውጡ መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በመታገዝ የመላውን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡
በመንግሥት መዋቅርና በባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት አመርቂ ውጤት ከተመዘገበባቸው ሴክተሮች አንዱ የንግዱ ዘርፍ ነው፡፡ የንግዱ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት የሚያበረክተውን ወሳኝ ድርሻ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በከፍተኛ የአመራር ቁርጠኝነት ትግል እየተደረገ ነው። የንግዱ ዘርፍ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር የዘርፉን አበርክቶ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው ይላሉ። በሕገወጥ ንግድ ላይ በተደረገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ከ108 ሺ በላይ በሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ ርምጃ በመውሰድ ገበያው እንዲረጋጋ ተደርጓል ብለዋል፡፡
እንደ ካሣሁን (ዶ/ር) ገለጻ፤ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ስድስት ወራት ሰው ሠራሽ የምርቶች እና የሸቀጦች እጥረት በመፍጠር የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ሕገ ወጥ የንግድ ተግባራትን ሲፈፅሙ በተገኙ 108 ሺህ 011 የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡ ኢትዮጵያ ለንግድ ሥራ ያላትን አመቺነት በማሻሻል ለንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ እና ተወዳዳሪ እንድትሆን ማድረግ የተልዕኮው አካል ነው፡፡ በዚህም ተግባራዊ በተደረገው የኦን ላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መሠረት ባለፉት ስድስት ወራት ሁለት ሚሊዮን 50 ሺ አገልግሎቶችን በኦንላይን ተሰጥቷል። ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ48 በመቶ ብልጫ አለው።
የንግድ ዘርፍ ስብራቶች የሆኑ የግብይት መሠረተ ልማት፣ የምርትና አገልግሎት ጥራት ማስጠበቅ፣ የኮንትሮባንድ እና ሕገ ወጥ ንግድ ሕገ ወጥ ኬላዎችና በነዳጅ አቅርቦትና ግብይት የጋራ ርብርብ ይሻሉ፡፡ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው የሚገኙ የንግድ መዋቅር ተቀናጅተው በትኩረት መሥራት አለባቸው፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም