
ኢትዮጵያ በርካታ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁነቶች እያስተናገደች መሆኗ ይታወቃል። ይህ መስተንግዶዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ መጥቷል። በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከ80 በላይ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ማስተናገዷን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ ብቃቱ ያላቸው ግዙፍ ማዕከላትና ባለ ኮከብ ሆቴሎችን ተገንብተው ወደ ሥራ ማስገባታቸው ይህን ሁነት የማስተናገድ አቅሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲመጣ አስችለዋል። ለእዚህም የዓድዋ ድል መታሰቢያ እንዲሁም የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ወደ ሥራ በገባ በጥቂት ጊዜያቱ በርካታ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን አስተናግዷል፡፡
አዲሱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልም እንዲሁ ገና ተመርቆ ወደ ሥራ በገባ ማግሥት ወደ አስር የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ ጥያቄ እየቀረበለት ይገኛል።
ማዕከሉን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት፤ ማዕከሉን ኢትዮጵያ የስብሰባ፣ የኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን ዘርፍን (MICE) ለማጠናከር ለምታደርገው ጥረት ተጨማሪ አቅም ሆኗል። ዓለም አቀፍ ደረጃን እንደጠበቀ ተቋምነቱ የንግድ ቱሪዝምን በማሳደግና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በመሳብ ኢትዮጵያን የስብሰባዎች ቀዳሚ መዳረሻ እንድትሆንም ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ተመርቆ ለጎብኚዎች ክፍት ከሆነ ጀምሮ ለተከታታይ አስር ቀናት የዘለቀ አውደ ርዕይ ተካሂዶበታል። በኢግዚቢሽኑ ላይም አምራቾችና አቅራቢዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል። አውደ ርዕዩ በዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ማዕከል መካሄዱ ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ አምራቾችና አቅራቢዎች የኢትዮጵያን ምርቶች ለዓለም ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው አምራቶችና አቅራቢዎች ተናግረዋል ፡፡
በአውደ ርዕዩ ምርቶታቸውንና አገልግሎቶቻቸውን ሲያስተዋውቁ ከነበሩ ድርጅቶች መካከል አንዱ አዳማ ቆርቆሮ ወይም ኤኤም ጂ ሆልዲንግ ኮፊ ኤክስፖርት የተሰኘው ድርጅት ነው።
አዳማ ቆርቆሮ ወይም ኤኤም ጂ ሆልዲንግ ስድስት እህትማማቾች ኩባንያዎች ያሉት ሲሆን፣ እነሱም አዳማ ሪል ስቴት፣ አፍሪካ ጋዝ ስቴሽን፣ አዳማ አፍሪ ስካል፣ አዳማ ስቴልና ኮፊ ኤክስፖርት የተሰኘ ናቸው። ድርጅቱ የኢትዮጵያን ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ባለመው ኢግዚቢሽን ላይ አዲስ ምርትም ይዞ ቀርቧል።
በኢግዚቢሽኑ ላይ የድርጅቱን ምርቶች ስታስተዋውቅ ያገኘናት ወጣት ሩት ይርጋለም የድርጅቱ ብራንድ አስተዋዋቂ ናት። እሷ እንደምትለው፤ ድርጅቱ ቡና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል። የተቆላ ቡና አዘጋጅቶ ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ በስፋት እንዳልተለመደ ገልጻ፣ ይህ ቡና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ጸዱ ቡና ቆልቶ እያቀረበ ይገኛል፡፡
ለሀገር ውስጥ ገበያ አምስት ኪሎ፣ አንድ ኪሎ፣ ግማሽ ኪሎ እያለ እስከ ሩብ ኪሎ ድረስ እያቀረበ ነው። ለውጭ ገበያ ደግሞ ጥሬ ቡና ወደተለያዩ ሀገራት ኤክስፖርት ያደርጋል። የውጭ የገበያ መድረሻዎቹም በኤዥያ፣ አውሮፓና ዓረብ ዓለም የሚገኙ ሀገሮች ናቸው።
ድርጅቱ የሐረር፣ የጉጂ፣ ሲዳማ፣ ሊሙ፣ ነቀምት፣ ጅማ ይርጋጨፌና የመሳሰሉት አካባቢዎችን ቡና በማስመጣት ነው ለገበያ የሚያቀርበው። ለዚህም ቡና ከሚያመርቱ አርሶ አደሮች ጋር እየሠራ መሆኑን አስታውቃለች።
ቡና የተለያዩ ደረጃዎች እንዳሉት ጠቅሳ፣ ‹‹ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለው የቡና ምርት ምንም የሚጣል ያለው፤ ሁሉም አገልግሎት ላይ ይውላል›› የምትለው ሩት፤ ለአብነት ስትጠቅሰም የቡናው ቅጠል ወይም ቁጢ፤ ለሻይ፣ ሀብስከስ የተሰኘ መጠጥ መሥሪያ እንደሚያገለግል ተናግራለች። ጀንፈል ወይም ቡናው ከተፈለፈለ በኋላ የሚቀረው ገለባ ደግሞ ካስካራ የተሰኘ መጠጥ እንደሚሰራበት ገልጻለች።
የቡና አዘገጃጀት ከመጀመሪያ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ባለው ሂደት ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ በአውደ ርዕዩ እንዲቀርብ መድረጉን ትገልጻለች። የአቆላል ሂደቱም እንዲሁ የተለያየ በመሆኑ እንደየአቆላሉ የቡናው የተለያየ ጣዕም ስለሚኖር ያንን ኅብረተሰቡ አውቆ ግንዛቤ ወሰዶ ቡናን በሥርዓቱ ቆልቶ እንዲጠቀም ለማድረግ ያለመ ዝግጅት ይዞ መቅረቡን አስታውቃለች።
እሷ እንዳብራራችው፤ ድርጅቱ ቡና ማቅረብ ከጀመረ ሦስትና አራት ዓመታትን አስቆጥሯል፤ ወደዚህ ሥራ ከገባ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ኤክስፖርቱን ከሚመሩት ዋና ላኪዎች ተርታ ተሰላፊ መሆን ችሏል። ቡና እያመረቱ ለድርጅቱ ከሚያቀርቡ ብዙ አቅራቢዎች ጋር አብሮ ይሠራል፡፡
ሩት እንዳብራራችው፤ ድርጅቱ ቡና የሚያቀርበው በደንበኞች ፍላጎት ነው። ዋጋውም ቢሆን በገበያ ላይ ካለው ጋር ሲታይ ተመጣጣኝ የሚባል ነው። በዚህ አውደ ርዕይ አንድ ኪሎ ቡና 760 ብር ሸጧል። የቡና ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረበት በዚህ ወቅት ይህ ዋጋ በጣም ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን ጠቁማለች።
ቡና ኤክስፖርት ሲደረግም እንዲሁ እሴት ከመጨመር ባሻገር የሚጠይቁ መስፈርቶች እንዳሉ አመልክታ፣ በመስፈርቶቹ መሠረት ደረጃውን ጠብቆ ኤክስፖርት እንደሚደረግም ታመላክታለች። ድርጅቱ በገላንና አዳማ ከተማ ባሉት ማምረቻዎቹ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩንም ጠቁማለች።
አውደ ርዕዩ ድርጅቱንና ምርቶቹን እንዲሁም አዲስ የቡና ምርትን ለማስተዋወቅ ጠቅሞናል የምትለው ሩት፤ በቡና ላይ መሥራት የሚፈልጉ ድርጅቶችና የቡና አቅርቦት ከሚፈልጉ ካፌዎች ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር አስችሎናል በማለትም አብራርታለች።
ኢግዚቢሽኑ በዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱ ብዙ አጋሮችን ለመገናኘትና አብሮ ለመሥራት የሚቻልበት ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር ዓለም አቀፍ የኢግዚቢሽን ፍለጋ ሌላ ሀገር መሄድ ሳያስፈልገን ወጪን በመቀነስ እዚሁ ሀገራችንን ሆነን ምርታችንን ለዓለም አቀፍ ደንበኞች ጭምር ማሳየት የቻልንበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል፤ እንደዚህ ዓይነት አውደ ርዕይ ይበል ይቀጥል የሚያሰኝ ነው›› ስትልም አብራርታለች።
ሌላኛው የአውደ ርዕዩ ተሳታፊ ፍሪል ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት ነው። ፍሪል ኢትዮጵያ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ኦሞራቲ በተሰኘ አካባቢ በ10ሺ ሄክታር መሬት ላይ በግብርና ልማት ተሰማርቷል። ፓፓያ፣ ሀባብ፣ ሙዝ፣ መንግቢን( ሞሾ)፣ ጥጥ ዝንጅብል የመሳሰሉትን ያመርታል፡፡
የድርጅቱ የማርኬቲንግ ባለሙያ ሊዲያ ከበደ እንደምትለው፤ ድርጅቱ አሁን በዋናኝነት ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን ቦታ ላይ ሙዝ ያመርታል፤፤ ከሙዝ ምርቱ 80 በመቶ ያህሉን ኤክስፖርት የሚያደርግ ሲሆን፤ 20 በመቶ ያህሉን ለሀገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል። ከሶስት ሺህ 500 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ዜጎች በድርጅቱ ይሠራሉ።
የገበያ መዳረሻው በዋነኝነት ሶማሊላንድ ሲሆን፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ሳውድ አረቢያና ዱባይ ምርቶቹን መላክ እንደሚጀመር ትገልጻለች። ድርጅቱ ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችል ዘር ከእስራኤል እያስመጣ እንደሚያለማም ተናግራለች። ሙዝ በማምረት ረገድ በኢትዮጵያ ካሉ አምራቾች ለየት የሚያደርገው ዓመቱን በሙሉ ሙዝ ማምረት በመቻሉ መሆኑንም አስታውቃለች።
ድርጅቱ ሙዙን የሚያለማው የኦሞ ወንዝን በመጠቀም መሆኑን አስታውቃለች። የሙዝ ልማት በተለምዶ ሙቀትና እይታ እንደሚፈልግ ጠቅሳ፣ ጥሩ የምግብ ይዘት ያለው ለጤናም የሚጠቅም ሙዝ እንደሚያመርት አመልክታለች። ሙዙ ከፍተኛ ምርት እንደሚሰጥ ገልጻ።
ልማቱም በጥንቃቄ እንደሚካሄድና ለገበያ የሚቀርበውም ብዙ ሂደቶችን አልፎና ታሽጎ መሆኑን ጠቅሳለች። ይህም ሙዙን ገበያ ላይ ካለው ሙዝ ለየት እንዲል እንዳደረገው አስታውቃ፣ ገዥ ሀገራት የኢትዮጵያን ሙዝ በጣም እንደሚወዱትና ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጻለች።
ድርጅቱ በሀገር ውስጥ ገበያም ሆነ በውጭ ገበያ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሟላት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሳ፣ ለሀገር ውስጥ ገበያ በአዲስ አበባ፣ በደሴ፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ በመሳሰሉት ከተሞች ሙዝ እያቀረበ ይገኛል ስትልም ጠቁማለች፡፡
እሷ እንዳለችው፤ ድርጅቱ ቀደም ሲል ጥጥ እየመረተ ሌሎች ይሰጥ ነበር። አሁን ግን ቦታው ላይ ያሉ ሥራውን የሚያውቁ ባለሙያዎች ስላሉት እሴት በመጨመር ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል የጥጥ ማዳመጫ ፋብሪካ ገንብቶ አጠናቋል። በቀጣይም ጥጥ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ ደረጃ ያለውን ሂደት በአንድ ቦታ እንዲርስ በማድረግ እሴት የተጨመረበት ምርት ለውጭ ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቅቋል።
የዝንጅብል እና የመሳሰሉት ምርቶችም እንዲሁ ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚደርሱ እንደመሆኑ እሴት እየተጨመረባቸው ለገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውንም ጠቁማለች።
ይህ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ያካተታቸው ብዙ አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ የሁነት ማቅረቢያ ቦታ እንዲሆን እንደሚያደርጉት ተናግራለች። ‹‹እኛም ምርቶቻችንን በዚህ ታላቅ ማዕከል ማስተዋወቅ መቻላችን በራሱ ትልቅ እድል ፈጥሮልናል ብላለች።
እሷ እንዳብራራችው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫ እንደመሆኗ ይህ ማዕከል ይመጥናል። በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎች ሊጎበኙት የሚችሉ መሆኑ ተደራሽነት ያሰፋል። እንደ አምራች ደግሞ ብዙ ገበያዎች ለማግኘት እና ከተለያዩ አካላት ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ አስችሎናል ትላለች።
አውደ ርዕዩ ድርጅቱን ብዙ ሰዎች እንዲያውቁት አስችሏል፤ ከብዙዎች ጋርም ግንኙነት መፍጠር የቻለበት ሆኗል፤ የሚሠራ አካልን የሚያበረታታና ተነሳሽነት የሚፈጥር ነው ብላለች፡፡
ሌላኛው የአውደ ርዕዩ ተሳታፊ ፋብሪካው ከተመሠረተ 78 ዓመታትን ያስቆጠረ ላሜ ዴሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው። የድርጅቱ ምርቶች ፓስቸራይዝድ የሆነ ወተት፣ እርጎ፣ ክሬምና ቅቤ( የገበታና የምግብ) ናቸው። ለበርገር፣ ለፒዛ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቺዞችንም ያመርታል፡፡
አይስክሬም በስምንት ዓይነት ጣዕምና በአራት ዓይነት መጠን ያመርታል። እነዚህ ምርቶች በድርጅቱ መሸጫ ሱቆች፣ በኩዊንስ ሱፐር ማርኬቶች፣ በፍሬንድ ሽፕ፣ በአባድር ሱፐር ማርኬት እና በተለያዩ ሱፐር ማርኬቶች ላይ ይገኛሉ፡፡
የላሜ ዴሪ ወይም ሾላ ወተት ፋብሪካ የገበያ ልማት ክፍል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ጎቾ እንደሚሉት፤ ድርጅቱ አሁን ኬዶ በተሰኘ አዲስ ምርት የሕፃናት ወተት በ150 ሚሊ ሊትር በማምረት ለገበያ አቅርቧል። አይብ በተለይ በበዓላት አካባቢ በብዛት ያመርታል፤ ምርቶቹንም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እንዲውሉ ያደርጋል፡፡
ድርጅቱ ፓስቸራይዝድ ወተት የማምረት አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን አቶ ሳሙኤል ጠቅሰው፣ አዲስ ባቋቋመው ፋብሪካ በየቀኑ 20ሺህ 040 ሊትር እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል። ፓስቸራይዝድ ወተት ለማምረት የሚያስፈልገውን ጥሬ ወተት ከአማራና ከኦሮሚያ ክልል ይሰበሰባል ያሉት ኃላፊው፣ በተለይ ከባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሰላሌ፣ ጎርፎ እና ጫንጮ፣ ሆለታ፣ ሰበታ፣ ሰንዳፋ፣ ደብረ ብረሃን ከቆቃ ሀዋሳ፣ ይርጋለም፣ አሰላ፣ ከቢሾፍቱና ከሌሎችም አካባቢዎች ይሰበስባል። ይህን ጥሬ ወተት ወደ ፋብሪካ በማስገባት ፓስቸራይዝድ አድርጎ እርጎና ቺዞችን እንደሚያምርት አመልክተዋል። በአጠቃላይ ጥሬ ወተቱን በላብራቶሪ በመለየት ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል እንደሚያደርግ ይገልጻሉ። ሌሎች ከውጭ የሚያስመጣቸው ግብዓቶች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ድርጅቱ በምርቶቹ ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ አላደረገም ነበር የሚሉት ባለሙያው፤ በቅርቡ ግን የተወሰነ ጭማሪ መደረጉን ገልጸዋል። ለእዚህ ዋናው ምክንያት ጥሬ ወተቱን ማግኘት ባለመቻሉና አቅራቢዎች ዋጋ እንዲጨመር ጥያቄ በማቅረባቸው እንደሆነ አመላክተዋል።
አሁንም ቢሆን ድርጅቱ የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ባገናዘበና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ምርቶቹን እንደሚቀርብ ጠቅሰው፤ ችግሩ ግን ድርጅቱ በሚያከፋፍልበት ዋጋ ታች ያለውን ማኅበረሰብ መድረስ እንዳልቻለ አስታውቀዋል። ድርጅቱ በወኪል አከፋፋዮቹ በኩል የተወሰነውን ምርት ተደራሽ ቢያደርግም፣ በአከፋፋዮች ሥር ያሉ ኤጀንቶች ከዚያ ሱቆች እያለ የሚሄድ የገበያ ስንስለት ያለው በመሆኑ የድርጅቱ ምርት መሸጫ ዋጋ ኅብረተሰቡ ጋ ሲደርስ ከፍተኛ እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡
ድርጅቱ ፓስቸራይዝድ ወተት በፕላስቲክ የታሸገ ወተት በ45 ብር፣ በሃይላንድ የተዘጋጀውን ደግሞ በ130 ብር እንደሚሸጥ ገልጸው፤ ይህ ምርቱ ኅብረተሰቡ ዘንድ ሲደርስ ዋጋ እንደየቦታው የተለያየ ሆኖ የሚደርሰበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዳሉ። ምርቱን በቀጥታ ለተጠቃሚው በማድረስ ተደራሽነቱን ለማስፋት አዳዲስ ሱቆች ለመክፈት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁለት ሱቆች በቅርቡ ሥራ እንደሚጀመሩ አመላክተዋል። ሱቆቹ እየሰፉ ተደራሽነቱ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ኅብረተሰቡ ምርቶቻችንን በቀጥታ እየገዝ መጠቀም እንደሚችል አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ድርጅቱ በአውደ ርዕዩ ላይ ምርቶቹን ይዞ መቅረቡ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ያደርገዋል፤ አብረውት ከሚሠሩ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ለመገናኘት አስችሎታል። አውደ ርዕዩ በብዙ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች መጎብኘቱ ምርቶቹን ለማስተዋወቅ እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ ለማከፋፈል ከሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር አስችሎታል። እንደ አይስክሬም ያሉ ምርቶቻንን የማያወቁ፣ ከውጭ የሚመጣ የሚመስላቸው ሰዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ምርቱን ለማስተዋወቅ በሀገር አቅም ብዙ መሥራት እንደሚቻል ለማሳየት አስችሎናል።
በተለይ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን መገንባት ለአምራቹ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ ያመላክታሉ። በጣም ብዙ ሰዎች እየጎበኙት መሆናቸውን ተናግረው፣ ይህም በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ የመሆን እድልን እንደሚያሰፋ አስታውቀዋል። በአሁኑ አውደ ርዕይ የተሳተፉት ጥቂት ድርጅቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ ብዙ ድርጅቶች እንዲሳተፉና ብዙ ጎብኚዎች እንዲጎበኙ ሊደረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም