
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው ቡና ከዚህም የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ በየዓመቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። ለዚህ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከልም ሀገሪቱ በዘርፉ ያደረገችው ሪፎርም በዋናነት ይጠቀሳል። ሪፎርሙ በተለይ በቡናው ግብይት ላይ የነበረውን ስር የሰደደ ችግር በመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይገለጻል።
ሀገሪቱ ቀደም ሲል ወደ ውጪ የምትልከው በአብዛኛው ኮሜርሻል ቡና ነበር፤ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ የሚችለው ስፔሻሊቲ ቡና መሆኑን በመገንዘብና በዚህም ላይ ሰፊ ሥራ በመሥራት በአሁኑ ወቅት ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ቡና ከፍተኛውን እጅ የያዘው ስፔሻሊቲ ቡና እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።
የቡና ጉዳይ ሲነሳ ሁሌም አብሮት የሚነሳው እሴት የተጨመረበት ቡና ጉዳይ ነው። እሴት የተጨመረበት ቡና በስፋት ለውጭ ገበያ የማቅረብ አስፈላጊነት በተለያዩ ትላልቅ መድረኮች ላይ ይጠቀሳል። መንግሥት ከቡና የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ ለሚያስችለው ለእሴት ጭመራ ትኩረት እንዲሰጥ ሁሌም ያስገነዝባል።
የተቆላ ቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ምኒልክ ሀብቱ፣ የቲፒካ ስፔሻሊቲ ቡና ላኪ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ናቸው። የተቆላ ቡና ለውጭ ገበያ መላክ ላይ ተሠማርተው ይሠራሉ፤ በዘርፉ ስልጠናም ይሰጣሉ። እሴት የተጨመረበት ቡና ከቀደመው አኳያ ሲታይ ለውጥ እንዳለው መንግሥት ከሰጠው ትኩረት አኳያ ሲታይ ግን ብዙ ርቀት እንዳልሄደ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ምኒልክ በቡና ላይ እሴት መጨመር ማለት የሰው ኃይል ወይም ጉልበት፣ ማሽነሪ ፣ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቡናውን ወደሚጠጣበት ደረጃ ማድረስ ነው ይላሉ። ቡና ከእዚያም አልፎ የሚዘጋጅበት ሁኔታም እንዳለም ይገልጻሉ። አሁን ተቆልቶና ተፈጭቶ ሱፐር ማርኬት ላይ ከቀረበውም በላይ በቡና ላይ እሴት ሊጨመርበት እንደሚችል በመጠቆም፤ በዚህ ዘመን በካፕሱልና በመሳሰሉት አዳዲስ መንገዶች ቡና እንደሚዘጋጅ ገልጸው፤ ይህ አይነቱ እሴት ጭመራም በሀገር ውስጥም ተጀምሯል ይላሉ።
በእሴት ጭመራ ላይ ያለውን የሀገሮች ተሞክሮ አስመልክተው ሲያብራሩ እንዳሉትም፤ ጀርመን ቡና ላይ እሴት ጨምራ እንደ ገና ለውጭ ገበያ በማቅረብ በአንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ተቆልቶ የተፈጨውን ብቻ ሳይሆን ጥሬውን ራሱን ከሌሎች ሀገሮች ገዝታ ለውጭ ገበያ በማቅረብም እንዲሁ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ኢትዮጵያ በዚህ በኩል ገና ጅምር ላይ ናት። ቡናን በዚህ መልኩ ማዘጋጀት ከጀመረች 80 ዓመት ይሆናታል። በሰፊው ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመረችው ግን ካልተሳሳትኩ በ2009 ዓ.ም ነው፤ ሰባትና ስምንት ዓመታት ቢሆን ነው ይላሉ። ከእዚያ በፊት በተወሰነ መልክ ነበር የሚላካው። ኢትዮጵያ አሁን ከምትልከው አጠቃላይ ቡና ውስጥ እሴት የተጨመረበት ቡና አንድ በመቶም አልደረሰም ሲሉም አቶ ምኒልክ አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የኢትዮጵያ የተቆላ ቡና በትናንሽም ቢሆን ወደ ሁሉም ሀገሮች ይላካል፤ አሜሪካና ካናዳ ይጠቀሳሉ፤ ወደ ቡና አብቃይ ሀገር ቡና አይላክም፤ ይህ የተቆላ ቡናን ስለማይጨምር የተቆላ ቡና ወደ ብራዚል ይላካል።
የኢትዮጵያ እሴት የተጨመረበት ቡና በጀርመን ፣ ሆላንድ፣ ፈረንሳይ እንግሊዝ፣ ኮሪያ ይሸጣል። በዱባይ በከፍተኛ ደረጃ ለገበያ ይቀርባል። ቡና በመጠጣት አዳጊ በመባል በሚታወቁት እንደ ቻይና ባሉት ሀገሮች በደንብ ይላካል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቻይናውያን ወደ ሀገራቸው ሲሄዱ የሚወስዱት ትልቁ ስጦታ ቡና ሆኗል።
አቶ ምኒልክ እሴት ሲጨመር የሥራ እድልም እንደሚፈጠር አስታውቀው፣ በተለይ ለወጣቶችና ሴቶች ከፍተኛ የሥራ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ሴቶች ጠንቃቃ ስለሆኑ በየትኛውም ዓለም ጥራት ላይ ብዙ ጊዜ ያስፈልጋሉ። ተበጥሮ እንደሚላከው አረንጓዴ ቡና የጉልበት ሠራተኛ ብቻ አይደለም የሚያስፈልገው። የሰለጠነ የሰው ኃይልን ይፈልጋል፡፡
በዚህ ዘመን ‹‹ሲንግል ኦሪጅን›› ቡናዎች በዓለም በጣም እየተዋወቁ መምጣታቸውንም አመልክተው፤ እንደ ዱሮው ቡና ተብሎ ብቻ የሚጠጣበት ዘመን ላይ አይደለንም፤ ቡና አሁን አምስተኛ ትውልድ ላይ ደርሷል ሲሉ ያብራራሉ።
ያ ማለት የመጨረሻውን ደረጃ ስንመለከት አንድ ቡና ጠጪ ቡናው የበቀለበትን ቦታ፣ የሚለማበትን ከፍታ/ ኢሊቬሽን/ ፣ አፈሩን፣ ታሪኩን አውቆ የሚጠጣበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ሲሉ ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ቡና ላይ እሴት በሚጨምሩ የውጭ ሀገሮች ኩባንያዎች በኩል ቡና እንደ ቅመም እንደሚታይ ተናግረው፣ በዚህ ዘመን ግን የብሌንድ / እሴት መጨመር/ ጉዳይ ብቻ እንደማይታይ አመላክተዋል።
በሌላው የዓለም ክፍል ደግሞ በተመረተበት ሀገር የተቆላ ቡና /ሮስት አት ኦሪጅን/ ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዳለውም ጠቅሰው፤ እኛ በዚህ በኩል እድለኞች ነን ሲሉም አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ይሄም ሁለት ጥቅሞች አሉት። አንደኛ አርሶ አደሩን በሚገባ ይጠቅማል። ‹‹እኔ ቡናውን ሃያ ዶላር ብሸጠው ቡናውን ከአርሶ አደሩ በአስር ዶላር ልገዛው እችላለሁ። አሁን ግን አርሶ አደሩ አራት ወይም አምስት ዶላር ነው የሚሸጠው። ቢያንስ 150 በመቶ ጭማሪ እከፍለዋለሁ›› ሲሉም አብራርተዋል።
እዚህ ደረጃ ላይ ገና አልደረስንም፡፡ነገ ከነገ ወዲያ ግን በእሴት ጨማሪው ላይ በደንብ መሥራት ከተቻለ አርሶ አደሩን በደንብ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ይላሉ።
በተመረተበት ሀገር የተቆላ ቡና ሲባል ደግሞ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እየጨመረ እንደሚመጣ ጠቁመዋል። ‹‹ተጠቃሚም በቡናው ላይ እምነት ያሳድራል፤ ከዚያ በኋላ ቡናው ብሌንድ ስለማይደረግ መቶ በመቶ የኢትዮጵያ ቡና ነው ይላል። ይሄ ራሱ አንድ እድል ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
እሴት ለተጨመረበት ቡና በሀገር ውስጥ ያለው ገበያ በጣም እያደገ መምጣቱን አቶ ምኒልክ አስታውቀዋል። በየቲክ ቶኩ ስለቡና ስልጠና፣ የኮፊ ሾፓች/ ቡና መሸጫዎች/ በስፋት እናያለን። ይሄ ለዓመታት ሲፈለግ ቆይቶ ዛሬ መምጣት የጀመረ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ቡና በውጭ ሀገር ለማስተዋወቅ አቅማችን ውስን ስለሆነ በጣም ይከብዳል ያሉት አቶ ምኒልክ፤ ሁለተኛ ሥራህን መልመድ ያለብህ ሀገር ቤት ነው። በሜዳህ በደንብ ተለማምደህ ነው ወደ ውጪ መውጣት ያለብህ ሲሉ አብራርተዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያን በጣም ብዙ ቱሪስቶች ይጎበኟታል፤ ከዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ መቀመጫ ናት፤ ለእነዚህ ሁሉ ጥራት ያለው ቡና ማቅረብ ሲጀመር በተዘዋዋሪ የሀገሪቱ እሴት የተጨመረበት ቡና ተዋወቀ ፣ ፕሮሞሽን ተሠራ ማለት ነው።
ዛሬ በየቦታው ዘመናዊ ኮፊ ሾፖች ይታያሉ፤ ጥራት ያለው ቡና ወደ ገበያ ማቅረብ ተጀምሯል፤ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚፈቀደው ለውጭ ገበያ የሚቀርበው አይደለም፤ ለሀገር ውስጥ ገበያ ተብሎ የተለየው ነው። ያንኑ ቡና በጥራት ለቅመው ብዙ ወጪ አውጥተው የሚሠሩ ኮፊ ሾፓች እየከፈቱ ናቸው፤ ይህም በተዘዋዋሪ ፕሮሞሽን ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው መነቃነቅ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፤ በውጭ ሀገሮችም እንዲሁ አንዳንድ ኮፊ ሾፖች እየተከፈቱ መሆናቸውን ተናግረዋል። መካከለኛው ምሥራቅ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውሮፓ ላይ ኢትዮጵያውያንም ኮፊ ሾፖችን እየከፈቱ ናቸው፤ ይህ ሲሆን እሴት የተጨመረበት ቡና ገበያው እየሰፋ ይመጣል ሲሉም አስታውቀዋል።
እነ ኮሎምቢያ ዛሬ በዓለም በጣም ታዋቂ የሆኑት በሀገራቸው ብቻ ሳይሆን በመላ ዓለም ወደ 126 ይሁን 200 አካባቢ ኮፊ ሾፖች ከፍተው በማስተዋወቃቸው ነው። ቡናችንን ግዙን እያሉ ብቻ አይደለም ለእዚህ የበቁት፤ ኮፊ ሾፖች ከፍተው ቡናችንን ጠጡ ብለውም ነው። ይህን ያህል ሠርተው ነው ዛሬ ቡናን በትልቅ ዋጋ ዓለም ላይ ለመሸጥ የበቁት።
ብራዚል በዓለም ላይ ትልቋ ቡና አቅራቢ ሀገር ናት፤ አምራችም ላኪም በመሆን በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የኢትዮጵያን አስር እጥፍ ቡና ለዓለም ገበያ ታቀርባለች። በእዚያው ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ከዓለም ቁጥር አንድ ቡና ጠጪ ሀገርም ናት። ስለዚህ ኢትዮጵያ በመጠጣትም በመላክም እድሉ አላት።
ኮሎምቢያም በዓለም ብዙ ኮፊ ሾፖችን በመክፈት ትታወቃለች። የሀገራቸውን የቡና ማህበር ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫ ሆላንድ ላይ አድርገው ፕሮሞሽንን ይሠራሉ። ቬትናም ወደ ውጪ ከምትልከው ቡና አምስት በመቶ አካባቢ እሴት የተጨመረበት ነው። ኢንስታንት ቡና የሚባሉትን አይነቶች በማምረትም በብዛት ትልካለች።
በኢትዮጵያ በእሴት ጭመራ በኩል አንዳንድ ለውጦች ቢኖሩም በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈለገውን ያህል እየተሠራበት አለመሆኑን አቶ ምኒልክ አስገንዝበዋል። መንግሥትም ለእሴት ጭመራ ትኩረት እንዲሰጥ ሁሌም እንደሚያስገነዝብ አመልክተው፤ መሬት ላይ ያለው እውነታ ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷል በሚያሰኝ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
እሴት ጭመራውን በሚፈለገው ልክ ማሳደግ ያልተቻለባቸውን ምክንያቶች ሲያብራሩ፤ ‹‹እኔ እንደሚገባኝ ሁለት ተግዳሮቶች አሉ፤ አንደኛው ዓለም አቀፍ ሁለተኛው ደግም የሀገር ውስጥ ተግዳሮት ናቸው›› ሲሉም አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ አንዱ ዓለም አቀፉ ተግዳሮት ገዥ ሀገሮች እሴት የተጨመረበትን ቡና ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸው ነው፤ ይህ የሆነው ደግሞ ትልቁን ጥቅማቸውን የሚያገኙት ጥሬ ምርት ከሚልኩ ሀገሮች በመሆኑ ነው።
ላኪዎች የተቆላ ቡና ወደ ውጪ ሲልኩ በከፍተኛ ደረጃ መጠቀም ይችላሉ። አንድ ኪሎ አረንጓዴ ጥሬ ቡና በጣም ተወደደ ተብሎ 10 ዶላር ቢያወጣ፣ አንድ ኪሎ የተቆላ ቡና ግን በትንሹ 30 እና 40 ዶላር ሊያስገኝ ይችላል፤ ስለዚህ በመሀል ያለውን 300 ወይም 200 በመቶ እጅ ሀገራቸው ላይ ማግኘት ሲችሉ እድሉን ለእኛ ሊሰጡን አይችሉም። እንደ ኢትዮጵያ አይነት ሀገር ሁልጊዜም ጥሬ እቃ አቅራቢ እንዲሆን ይፈልጋሉ፤ እነሱ ዋጋ ሰጪ ናቸው፤ ሁሌም እጅህን ይጠመዝዛሉ።
‹‹እኛም እሴት የተጨመረበት ቡና ለመላክ በደንብ ዝግጁ አይደለንም ሲሉም አቶ ምኒልክ የሀገር ውስጥ ተግዳሮቶችን ይጠቅሳሉ። ፖሊሲው እሴት የተጨመረበት ቡና እንዲላክ ይደግፋል፤ ትግበራ ላይ ግን እንደሚባለው አይደለም ብለዋል። የማምረቻ ቦታ በሰፊው አይሰጥም፤ ወደእዚያ ለሚገቡ ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ደረጃ እንደሚባለው የብድር አገልግሎቶች አይመቻችም ብለዋል።
አንዳንድ ማነቆ የሆኑ ሕጎችም እንዳሉም ጠቁመዋል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘህ በሀገር ደረጃ ችግር ሊገጥምህ አይገባም ሲሉም ተናግረው፤ እሴት ከተጨመረበት ቡና አኳያ ያለው የኢትዮጵያ የምግብና የመጠጥ የብቃት መመሪያ ለኢትዮጵያ የሚሆን አይደለም ብለዋል። ‹‹በዚሀ ላይ ስንከራከርበት ኖረናል፤ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ለአረንጓዴው ቡና ፈቃድ እንደሚሰጠው ሁሉ እሴት ለተጨመረበትም ፈቃድ መስጠት ያለበት ይሄው ተቋም መሆን እንዳለበት ያመለክታሉ።
አንዳንዴ ገበያው ላይ የሌሉ መስፈርቶች ትጠየቃለህ ሲሉ አስታውቀው፤ ብዙ እድሉ ገጥሞኝ ትላልቅ ቡና የሚቆሉ ኩባንያዎችን ጎብኝቻለሁ፤ እኛ ሀገር ላይ እንደሚጠየቀው አይነት መስፈርት በሌሎች ሀገሮች አላየሁም ይላሉ።
ሁለተኛ ዘርፉ ላይ ባለነው ሰዎች ዘንድም ችግር አለ ሲሉ አመልክተዋል። ገበያው በትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መያዙንና ይህን ሰብሮ ለመግባት እንደሚከብድም ጠቅሰዋል።
በቡና ቆልቶ ላኪዎች ማህበር በኩል ቀደም ሲል በተከናወኑ ሥራዎች ነው አሁን ላለንበት ደረጃም የበቃነው ብለዋል። ፊት የተቆላ ቡና ወደ ውጭ ይልኩ የነበሩት ስድስትና ሰባት ሰዎች አይሞሉም ነበር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ አሀዝ 40 እና 50 ተቋማት አካባቢ ደርሷል፤ ይህ ደግሞ የመጣው ማጋነን ካልሆነብኝ እኛ ባደረግነውም ጥረት ነው ብለዋል።
ቡና ከገበሬ መግዛት የሚቻልበት ሁኔታ የተፈጠረው በማህበሩ ጥረት መሆኑን ጠቅሰዋል። ዘርፉ ከምንም አይቆጠርም ነበር ሲሉ ገልጸው፤ አሁን በትንሹ ከአምስትና አስር ሚሊዮን ዶላር በላይ ማስገኘት እየቻለ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለእሴት ጭመራው የተሰጠው ትኩረት እውነት እንነጋገር ከተባለ ብዙም መሬት አልወረደም ሲሉ ገልጸው፤ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን እሴት ጭመራን ያበረታታል፤ ይሁንና በዳይሬክተር ደረጃ እሴት የተጨመረበት የቡናን ጉዳይ የሚከታተል ክፍል የለውም፤ እዚያ ላይ የተጠናከረ ሥራ አላይም፤ ክፍተት ያለ ይመስለኛል ሲሉ አቶ ምኒልክ ገልጸዋል።
እሴት ጭምራ ላይ የሚሠራ ባለሙያ በመቅጠር ሥራውን የሚከታተልና የሚመራ አካል በማቋቋም መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በዚህም ያሉትን ክፍተቶች ማስተካከል ይቻላል ብዬ አስባለሁ፤ ተቋሙ እሴት ጭመራ ላይ ጠንከር ብሎ መሥራት ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
አቶ ምኒልክ፤ ዘርፉ ላይ ያለው ባለሀብትም በዚያው ልክ መጓዝ እንዳለበት አስታውቀዋል። ‹‹ቢዝነሱ ላይ ያለነው አካላት ዝግጁነት ምን ያህል ነው የሚለውም መታየት አለበት ›› ብለዋል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም